Sunday, 24 February 2019 00:00

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያፀና ውል ሊፈራረሙ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


ከ20 ዓመታት በኋላ ዳግም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ በወደብ አጠቃቀም፣ የጋራ የንግድ ቀጠና በመመስረትና በሌሎች ዘላቂ ግንኙነቶቻቸው ላይ የመጨረሻውን ስምምነት ሊፈራረሙ መሆኑን በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ አገራት መሪዎች በዝርዝር የሃገራቱ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርጉ መሰንበታቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ የሁለቱን ሃገራት የንግድና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ተቋማዊ የሚያደርግ ስምምነት በቅርቡ ይፈራረማሉ ብለዋል፡፡ ስምምነቱ ከሚያካትታቸው ጉዳዮች መካከልም የወደብ አጠቃቀም፣ የግብር (ቀረጥ) ጉዳይ፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ የትራንስፖርት (የአየር፣ የየብስ፣ የውሃ) ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡ በሁለቱ ሃገራት የጋራ ድንበሮች ላይ ስለሚኖር የንግድ እና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴም ሃገራቱ ቋሚ ስምምነት ይፈራረማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የስምምነቱ ረቂቅ ለሁለቱም መንግስታት ቀርቦ በየራሳቸው እየተወያዩበት መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ደግሞ አንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይህን  የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት የሚያፀና ውል ይፈራረማሉ ተብሏል፡፡
ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ትግበራውን የሚከታተል ከሁለቱ ሃገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚካተቱበት የጋራ ኮሚሽን እንደሟቋቋም ታውቋል፡፡
የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት የመሪዎቹ በጎ ፍቃድ እንጂ በስምምነት የፀና አይደለም በሚል በርካቶች ስጋት አዘል ትችት ሲሰነዝሩ የቆዩ ሲሆን ይህ ዘላቂ ስምምነት ይህን ስጋት ያስወግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

Read 6600 times