Sunday, 24 February 2019 00:00

ሰመጉ መንግስት በለገጣፎ ቤት ላፈረሰባቸው ተመጣጣኝ ካሣ እንዲሰጥ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

“የዜጎች መኖሪያ ቤት መፍረሱ፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው” - ተመድ
“መንግስት ዜግነታችንን የካደ ግፍ ፈጽሞብናል” - ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች

በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ለገጣፎ ከተማ፣ የዜጐች መኖሪያ ቤት መፍረሱ በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ጉዳዩን በትኩረት እንደሚመረምር አስታውቋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ ቤት ምጣኔ ሃላፊዋ ሲሊያና ፈራህ እንደገለፁት፤ በለገጣፎ 12ሺህ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቤት አልባ አድርጐ፣ ለእንግልት ይዳርጋል፤ ይህም ግልጽ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል፡፡
ስለ ቤቶቹ መፍረስ መረጃው ለተቋማቸው መድረሱን ያረጋገጡት ፈራህ፤ በቀጣይ ጉዳዩ በልዩ መርማሪዎች ተመርምሮ፣ በዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወገኖች እንዲጋለጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የዜጐችን መኖሪያ ቤት በዚህ መልኩ ማፍረስ በተባበሩት መንግስታት፣ ሀገራት ቃል ኪዳን የገቡለትን የማንኛውም ዜጋ፣ መጠለያ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በእጅጉ የሚፃረር ነው ብለዋል - ሃላፊዋ፡፡
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ በለገጣፎ ዜጐች መጠለያ አልባ መደረጋቸውን በጽኑ አውግዞ፣ ቤት ለፈረሰባቸው ወገኖች፣ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ተመጣጣኝ ካሣ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ እንዲሁም እየተካሄደ ያለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስና ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡
ሠመጉ በመግለጫው የዜጐችን መኖሪያ ቤት በ7 ቀን ማስጠንቀቂያ ብቻ በሃይል ማፍረስና ማፈናቀል በአለማቀፍ ደረጃ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያስጠይቅ ተግባር ነው ብሏል፡፡ የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር የወሰደውን የሃይል እርምጃ ይበልጥ አስከፊ የሚያደርገው ያለ ማስጠንቀቂያ፣ ያለ ምንም አማራጭ የመኖሪያ ስፍራም ሆነ ጊዜያዊ መጠለያ ዝግጅት መሆኑ ነው ያለው መግለጫው፤ ለተፈናቀሉ ዜጐችም የሰብአዊ እርዳታ እየተደረገላቸው አለመሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ ያደርገዋል ብሏል፡፡
ሰመጉ በስፍራው ተገኝቶ ቤት የፈረሰባቸውን አካላት መጎብኘቱን ጠቁሞ፣ በርካቶቹ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ላይ እምነት በመጣል፣ በተለያየ ጊዜ በገዙት ቦታ ላይ ቤት በመስራት እንዲሁም አካባቢውን በማልማት፣ ከተማዋን አሁን ላለችበት የእድገት ደረጃ ማብቃታቸውን አመልክቷል፡፡ በእነዚህ አመታትም፣ በአካባቢው የመንግስት ሃላፊዎች ዕውቅና፣ ነዋሪዎች የመብራትና የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውም ተረጋግጧል ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር፣ ከነዋሪዎች ጋር በቂ ምክክር ሳያደርግና ሊመጣ የሚችለው ሠብአዊ ቀውስ ላይ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይኖረው፣ ቤቶቹን በማፍረስ ህፃናት፣ ሴቶችንና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ሜዳ ለይ እንዲወድቁ አድርጓል ሲል ወቅሷል - ሠመጉ፡፡ በዚህም የዜጐች ለኑሮ አመቺ በሆነ አካባቢ የመኖር፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃና ምግብ የማግኘት፣ እንዲሁም የአካል ደህንነት መብትና ሌሎች ተያያዥ ሰብአዊ መብቶች ተጥሰዋል ብሏል - ተቋሙ ባወጣው መግለጫ፡፡  
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ በህገ ወጥ መሬት ወረራና በህገ ወጥ የቤት ግንባታ ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ እየተወሰደ ያለውም ከተሞች ስርአት ባለውና አለማቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንዲያድጉ ለማድረግ በማለም ነው ብሏል - የክልሉ መንግስት፡፡ በዚህም ከከተማ ፕላን ጋር የማይጣጣሙ ማንኛውም ቤቶች ይፈርሳሉ ያለው የክልሉ መንግስት፤ በቅርቡም በአዳማ፣ በሻሸመኔና በመቱ ከተሞች ተመሳሳይ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁሟል፡፡  
በለገጣፎ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጐች በበኩላቸው፤ ቤቶቹን የከተማ አስተዳደሩ ህጋዊነታቸውን ተቀብሎ መንገድ፣ መብራትና ውሃ ማስገባቱን እንዲሁም የቤት ቁጥር በመስጠት ግብር ሲቀበላቸው እንደነበር በመጥቀስ፤ አሁን ግን “በ7 ቀን ከቤት ልቀቁ” ማስጠንቀቂያ ብቻ ቤታቸውን በማፍረስ፣ “መንግስት ዜግነታችንን የካደ ግፍ ፈጽሞብናል” ሲሉ አማረዋል፡፡
ቤቶቹ ህጋዊ እንዳልሆኑና ከአንድ አመት በፊት ለባለቤቶቹ እንደተነገራቸው የጠቆመው ክልሉ፤ ቤቶቹና የማፍረሱ ተግባር በድንገት ያልተካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በለገጣፎ ከተማ ባሳለፍነው ሣምንት ብቻ 3ሺህ ያህል ቤቶች በቡልዶዘር የፈረሱ ሲሆን በድምሩ 12ሺህ ቤቶች በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደፈረሱ የከተማዋ ከንቲባ ሃቢባ ሲራጅ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ40 ሺህ በላይ ዜጐች ቤታቸው በመፍረሱ መጠለያ አልባ ሲሆኑ፣ ዘመድ ያለው ከዘመዱ ሌሎችም በየአካባቢው የፕላስቲክ መጠለያ ወጥረው እየኖሩ መሆኑን አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የተፈናቀሉ ዜጐች አስታውቀዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ቤት ያፈረሰባቸው ከ40 ሺህ በላይ ዜጐች ቀጣይ ዋስትና ምንድን ነው ለሚለው እስካሁን ምላሽ አልተሰጠም፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች ከ10 አመት በፊት የተገነቡ ናቸው የሚሉት ነዋሪዎች፤ ቤታቸው በዚህ ወቅት መፍረሱ ልጆቻቸው ከትምህርት እንዲስተጓጐሉና ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እንደሚዳርጋቸውም ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡  

Read 7215 times