Sunday, 24 February 2019 00:00

የኢሳት ጋዜጠኞች ምን ይላሉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(15 votes)


ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት፣ በርካታ ዜጎች በተለይም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች በመንግስት ላይ በሚሰነዝሩት የሰላ ትችትና ተቃውሞ የተነሳ በሽብርተኝነት እየተፈረጁና እየተከሰሱ፣ ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባልም አገራቸውና ወገናቸው እየናፈቃቸው፣ በስደት አገር እያሉ ለህልፈት በቅተዋል፡፡ የማታ ማታ ህዝብ ባደረገው እልህ አስጨራሽ ትግልና አመጽ፣ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ በተገኘው ለውጥና ነጻነት፣ ብዙዎች ለአገራቸው መሬት በቅተዋል፤ከቤተሰቦቻቸውና ከወገኖቻቸው ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ሰሞኑን በመንግስት በአሸባሪነት ከተፈረጁ ደርጅቶች አንዱ በነበረው ኢሳት የቴሌቪዥን ጣቢያ
የሚሰሩ ጋዜጠኞችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች “የኢሳትን ቀን” ለማክበር አገር ቤት መግባታቸው ይታወቃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ አበበ ገላውና ደረጀ ሀብተወልድ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ጋዜጠኞቹ ባለፉት ዓመታት የሚያውቋትን ኢትዮጵያንና የአሁኗን በስፋት ያነጻጽራሉ፡፡ እነሆ፡-



“ኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ መጥቷል”    ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና

ከስንት ጊዜ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለስከው?
ከሌሎቹ ጓደኞቼ አንፃር ሲታይ፣ የእኔ አጭር ጊዜ ነው፤ ከስምንት አመት በኋላ ነው የተመለስኩት፡፡
አዲስ አበባን እንዴት አገኘሃት?
እርግጥ ከመጣን ዛሬ አራተኛ ቀናችን ነው (ሰኞ ነው ቃለ ምልልሱ የተደረገው)፡፡ ብዙ ተዘዋውሬ ያየሁት ነገር የለም፡፡ የሚታዩ የተለወጡ ነገሮች አሉ። ህዝቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮው ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተረድቻለለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ ከተማ ውስጥ ያሉ ህንፃዎች እኔም እያለሁ እየተገነቡ ነበር፡፡ አሁን የምንገኝበት (ቦሌ) አካባቢ የተጀመሩ ህንፃዎች አሁን አልቀዋል፡፡ ትልቁ ነገር ይሄ አይደለም፡፡ ነፃነት ሲኖር ነው፣ ሁሉም ነገር ትርጉም የሚኖረው። ያም ብቻ ሳይሆን ምናልባት አጠቃላይ ሂደቶችን ለማይገመግም ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ ላለፉት 27 ዓመታት ለኢትዮጵያ የሚሰራ፣ ኢትዮጵያዊ መንግስት ቢኖር ኖሮ፣ ተዓምር ሊታይበት የሚችል ነገር ነበር፡፡ በዚህ አልታደልንም፡፡ እንግዲህ በእርዳታም በብድርም፣ እስከ ዛሬ ከ100 ሚሊዮን  ብር በላይ ነው ወደ አገር የገባው፡፡ የተሰራው ደግሞ ቢመዘን፣ የብሩን ሩብ አያህልም፡፡ በአንፃሩ ስንዘረፍ ነው የኖርነው። አንዳንድ ሰው ህንፃ ምናምን ይላል። ያንን ገንዘብ ስራ ላይ አውለነው ቢሆን ኖሮ፣ ተዓምር የማየት እድል ነበረን፤ አልሆነም፡፡  ከምንም በላይ አሁን ነፃነት መምጣቱ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊም ሆነ በፖለቲካው ትርጉም ያለው ለውጥ ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡
ለውጡን እንዴት ትገልጸለህ ? አብዮታዊ ነው ወይስ ጥገናዊ ለውጥ?
ይሄ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡ ለትርጓሜም የሚያስቸግር ነው የጠየቅሽኝ፤ ከውስጥ የመጣ ጥገናዊ ይመስላል ፤ነገር ግን እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች ስንመለከት ስር ነቀል ነው ያስብላል፡፡ በአጠቃላይ በጥገናና በስር ነቀል ለውጥ መካከል ያለ ሂደት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮች ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ በፍጥነት ነው የሄዱትና የተቀየሩት፡፡ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ምንም ማድረግ የማይቻልባት አገር ነበረች፡፡ አሁን ምንም ነገር ማድረግ የሚቻልበት እየሆነች ነው፡፡ በኦባማ አስተዳደር ጊዜ ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የነበረች ሚሚ አለማየሁ የምትባል ኢትዮጵያዊት፣ በጃንዋሪ ወር ላይ አፍሪካን ማጋዚን ላይ የፃፈችው ነገር ነበር፤ አርዕስቱ ምን ይላል መሰለሽ፤ “ሁሉም ነገር የሚቻልባት ኢትዮጵያ” የዛሬ ስምንት አመት ከኢትዮጵያ ስወጣ፣ ሁሉም ነገር የማይቻልበት ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በዚህ ስምንት አመት ውስጥ ነገሮች የባሰ ድቅድቅ ጨለማ ሆነው፣ ጓደኞቻችን ቤተሰቦቻችን፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዱዓለም አራጌ ምንም ባላጠፉት፣ እድሜ ልክ እና 18 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል፤ነገሮች እየከፉ የመጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ ዛሬ ከዚያ አስከፊ ሁኔታ በዚህ በአጭር ጊዜ በዘጠኝ በ10 ወር ውስጥ ወጠተን የምናየው ነገር አብዮት ነው፤ ስር ነቀል ነው ብሎ ለመተርጐም ያስቸግራል፡፡ ማናችንም ባልገመትነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ መጥቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢሳት በተደጋጋሚ ጃም መደረጉን ስትገልፁ ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ ተቋሙ በገንዘብ አቅም የጠነከረ አይደለም፤ በቂ የሰው ሀይልም አልነበራችሁም፡፡ ፈተናውን  እንዴት ተቋቋማችሁት?
ኢሳት ያለፈበት ፈተና ምናልባት እዛ ውስጥ ለነበርነው ብቻ ሳይሆን ለትውልዱም ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ኢሳት የተመታው ስራ በጀመረ በሶስት ወሩ ነው። በሶስት ወሩ ከአየር ላይ መውረድ እንደሚችል ታወቀ። እንዳልሽው ኢሳት በትንሽ አቅም፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ መሰረት አድርጐ፣ በብድርም በእርዳታም እየተደገፈ፣ ጡንቻ ከያዘ መንግስት ጋር ግብግብ መግጠም በጣም ከባድ ነው፡፡ ተስፋ አለመቁረጥ ያቆየው ተቋም ነው፡፡ ወደ መፍትሔው ነው ያመራነው፡፡ ምን ብናደርግ ነው ኢሳትን ማስቀጠል የምንችለው፤ ወደ ሚለው ነው ያተኮርነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢሳት የሚባለው ይሄ ከፊት ለፊት የሚታየው ጋዜጠኛው ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ዓለማት በአውሮፓም በአሜሪካም ትልልቅ ቦታ ላይ የሚሰሩ፣ ከኋላ ሆነው የአርበኝነት ስራ ይሰሩ የነበሩ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ በትርፍ ጊዜያቸው ሁሉ ያግዙን ነበር፡፡ ምንድነው የሆነው፣ ኢሳት ሲመታ አረብሳት ከሳተላይቱ ላይ እንዲወርድ ነው ያደረገው፡፡ ኢሳት ሲመታ ሌሎች በተመሳሳይ መስመር ላይ የሚተላለፉ ቴሌቪዥኖች ስለታወኩ፣ ለእነዛ ደህንነት ሲባል ነው ያወረዱት፡፡ ምንድነው መፍትሔው ብለው የእኛ ሰዎች ሲያጠኑ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያለበት ሳተላይት ላይ ብንወጣ፣ የእነሱ እንዳይታወክ ሲሉ ይተውናል የሚል አማራጭ ያዝንና ተመልሰን አረብሳት ላይ ወጣን፡፡ በመንግስት በኩል ኢሳት ከሚታይ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ይቋረጥ የሚል አቋም ላይ ደርሰው፣ ኢሳትም ኢቲቪም አብረው ተመቱና አብረን ወረድን፡፡ ያው እነሱ ግን መንግስት ስለሆኑ፣ ብርም አላቸው፤ ድርድርም ታክሎበት እነሱ መመለስ ቻሉ፡፡
ከዚያ የኢሳት ሰዎች፣ ባለሙያዎቹ፣ ሌላ በቀላሉ የማይመቱ ሳተላይቶችን ፍለጋ ገቡ፡፡ የታይላንድ የሆነ “ታይኮ” የሚባል የሳተለይት ኩባንያ ነበር፤ ወደዛ ጉዞ ተደረገ፤ በዛ በኩል የገጠመን ፈተና ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሚዲያ ተቋማት የሚጠቀሙበት አረብሳት እና ናይልሳት ስለነበረ ታይኮ ሙሉ ለሙሉ አቅጣጫው ወደ ሌላ የዞረ ነው። ይህን ክፍተት ለመሙላት የግድ ተጨማሪ አቅም ያለው ሰው መሆን አለበት፡፡ አንድ ሰው ሁለት የዲሽ ሰሀን መጠቀም ሊኖርበት ሆነ፡፡ ያንን ማድረግ የቻሉ ሰዎች፤ ኢሳትን ሲያዩ ቆይተዋል፡፡ መንግስት ኢሳትን ማውረድ አልቻለም፤ በኋላ በተገኙ መረጃዎች እንደተረዳነው፤ ከቻይና መንግስት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ቻይና የታይላንድ መንግስት ላይ ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጫና፣ ኢሳት ከታይኮ ላይ እንዲወርድ ተደረገ፡፡ በዚህ መልክ ካልተሳሳትኩ፣ ለ27 ጊዜ ወይም ከ25 ጊዜ በላይ እንዲህ አይነት ድብብቆሽ ሲያካሄዱ ነው የቆዩት፡፡
መንግስት ጡንቻ አለው፤ ገንዘብ አለው፡፡ ከዚህ ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የማድረግ ሀይል አለው። ይህንን ሁሉ ጫና፣ ፈተናና ተግዳሮት አልፈን፣ ታግለን፣ በነፃነት አገራችን መግባት መቻል ከኢሳት ባሻገር በአንድ ነገር ላይ ተስፋ አለመቁረጥ፣ እጅ አለመስጠት፣ ለውጤት እንደሚያበቃ የሚያስተምር ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት በዚህም አላቆሙም፤ ከጀርመን ኩባንያ ጋር በፈፀሙት ውል ብዙ ሚሊዮን  ዶላር ከፍለው በኢሳት ጋዜጠኞች ላይ “ፊን ፊሸር” የሚባል የስለላ ሶፍትዌር አሰራጭተው ነበር፤ “ሲዜን ላብ” የሚባል ኩባንያ ደረሰበት፡፡ ያ ጉዳይ ትልቅ የመነጋገሪያ ዜና ሆኖ፣ ዋሽንግተን ፖስት  ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችንና “ሲዝን ላብ” የተባለውን ኩባንያ አነጋግሮ፣ በፊት ለፊት ገፁ ይዞት ወጥቶ ነበር፡፡ የውጭ አገር መንግስት፣ አሜሪካ ግዛት ውስጥ ስለላ እያካሄደ ስለመሆኑ ነው ዘገባው። ይህ ሁሉ ታልፎ ነው እንግዲህ እዚህ የተደረሰው። ቀደም ብዬ እንዳልኩሽ፣ ያለ ነፃነት ህይወት ትርጉም አልባ ነው፡፡ ህይወት ትርጉም እንዲኖረው ታግለናል፤ ብዙዎች ህይወት ገብረዋል፣ አካላቸው ጐድሏል። በወጣቶቹ መስዋዕትነት በተለይም ደግሞ ከውስጥ የወጡት ሀይሎች፣ ያንን ቅርስ ሰጥተው፣ የፖለቲካ አቅጣጫ አስይዘውት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋታቸው፣ ኢትዮጵያ ከመቃብር ውስጥ ወጥታለች፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤በጋዜጠኝነት ሙያህ  ስምህን  ደጋግመው  በአድናቆት አንስተዋል። ምን ዓይነት ስሜት አደረብህ?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንድ የአገር መሪ፣ በመጥፎም ሆነ በበጐ ስም ሲያነሳ ቀላል አይደለም፡፡ አንደኛ መኖሬ ይታወቃል ወይ ነው፤ አለሁ ማለት ነው፤ በመጥፎም ተነሳሁ፤ በበጐም፡፡ ከዚያ አልፎ ደግሞ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በመልካም መነሳት ስሜትን ከፍ ያደርጋል፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር ዐቢይ አገር መሪ ብቻ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ በማውጣት በኩል፣ በተጫወቱት ሚና፣ ትልቅ የአገር ባለውለታ ናቸው ብዬ ነው የማምነው። ባለፉት 8 እና 9 ወር ያየነውን፣ አገር ለሚገመግም ሰው፣ ህልም የሚመስሉ ነገሮችን እውን ባደረጉ መሪ መሞገስ ለእኔ ኩራት ነው፡፡ አሁን ይልቅ ችግሬን ልንገርሽ፡፡ ኢህአዴግ የሚለው ስም ሲነሳ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ጨለማ፣ ጭካኔ፣ ዝርፊያ፣ ዘረኝነት፣ አፈናና የመዓት ክፉ ነገሮች ሁሉ ቁንጮ ስለሆነ፣ ዶ/ር ዐቢይን ኢህአዴግ ብዬ ለመጥራት አቅም አጣለሁ፤ ይከብደኛል፡፡ እርግጥ እርሳቸው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ናቸው፤ በኢህአዴግ ውስጥ የቆዩ ናቸው፤ ግን ኢህአዴግ ናቸው ብሎ ለመጥራት ችግር ፈጥሮብኛል፡፡
እስከ ዛሬ ይሰራበት የነበረውንስ ይቀይር ይሆን?
ስለ ለውጡ ካነሳሽ አይቀር፣ ሰው እየተሳሳተ ያለውንና በግሌም የሚቀርብልኝን ነገር ልንገርሽ፤ “አንተ ዶ/ር ዐቢይን ትደግፋቸዋለህ፤ የቀደመውን መንግስት ግን አጥብቀህ ትቃወማለህ” ይሉኛል፡፡ እኔ የምቃወመው እኮ መንግስት ስለሆኑ አይደለም። እኔም፣ እኔን መሰሎችም፣ ራሱ ኢሳትም ቢሆን፣ ሌላውም ነፃው ፕሬስ የሚቃወመው ስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ ኢትዮጵያዊ መንግስት አይደለም በሚል ነው፡፡ የአፈና፣ የጭቆናና የዘረኛ መንግስት ነው፡፡ ጥያቄያችንና ተቃውሟችን ዘረኛ ካልሆኑ፣ አፈና ካላካሄዱ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ካልሆኑ ለምንድነው የምቃወማቸው? አሰራራቸው ትክክል ካልሆነ፣ ይሄ አካሄድ ትክክል አይደለም በሚል እንጽፋለን፣ አስተያየት እንሰጣለን፡፡ ከዛ ውጭ ግን እኔ ለ27 ዓመት ስጮህለት የነበረውን፣ የማምንበትን እንዲሆን የምመኘውን፣ የአገር መሪው ሲተረጉመው፣ እውን ሲሆን እያየሁ እንዴት እቃወማለሁ፡፡
ለመቃወም ካልተፈጠርክ በስተቀር?
ለመቃወም አይደለም የተፈጠርኩት፤ ሚዲያውም የተቋቋመው ለመቃወም አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ይህን ግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛ፤ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነገር በጣም አደገኛ  ነው፡፡ ነፃነት ከጨለማ ውስጥ ሲወጣ ያልተጠበቀ ነገር ታይቷል፡፡ ከ40 ዓመት በላይ አገራቸውን ያላዩ ሰዎች፣ አገራቸው ገብተዋል፡፡ ዛሬ ያለ ከልካይ አገራቸው ገብተው የሚወጡበት፣ ከፈለጉም እዚሁ ኑሮ መስርተው፣ መኖር የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሁሉም ተቃዋሚ ገብቷል፤ ኢሳትን ጨምሮ ሁሉም ሚዲያ ገብቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይህን ነፃነት ለመቀልበስ፣ የቀደመውን የጭቆናና የአፈና አገዛዝ ለመመለስ ደፋ ቀና የሚሉ አካላት አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትንንሽ የሆኑ አገርና ዘውድ የሚመኙ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚያ በሁለት ጫፍና ጫፍ የሚሳሳቡ ወገኖች፣ መልሰው ወደ ቀውስና መከራ ነው የሚከትቱን፡፡ ስለዚህ ይሄ መንግስት ተረጋግቶ፣ በደንብ መሰረት ይዞ፣ እንዲቆም መደገፍ ማለት ኢትዮጵያን መደገፍ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይህ መንግስት መሰረት ይዞ ኢትዮጵያ በትክክለኛ ሀዲዷ ላይ እንድትቀጥል፣ ይህን መንግስት ከመደገፍ ውጪ ያለው አማራጭ አይታየኝም፡፡
ከመንግስት በቀጣይ ምን ይጠበቃል?
ተቋማትን ማደራጀትና መገንባት አለበት፡፡ እነ አውሮፓና አሜሪካ ላይ ባንደርስ እንኳ እንደነ ኬኒያ ያሉ ጐረቤቶቻችን የደረሱበት እንድንደርስ መደረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚል፣ አገሩን የሚወድ፣ ልጆቹ እኛ ባለፍንበት ሰቆቃ እንዳያልፉ የሚመኝ ሁሉ፣ ለውጡን መደገፍና ማጠናከር አለበት፡፡ በግሌም ይህን አደርጋለሁ፤ እንደ ሚዲያም ይህንን እናደርጋለን፡፡
በስምንት አመት የኢሳት ቆይታህ፣ በቤተሰቦችህ ላይ የደረሰ እንግልት እስራት ወይም ሌላ ችግር ነበር? አሁንስ በሰላም አገኘሃቸው?
አጋጣሚ ሆኖ ሁሉንም ቤተሰቦቼን በሰላም ነው ያገኘኋቸው፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ ቤተሰቦቼን በነበረው ሁኔታ ወዲያውኑ ማየት ባልችልም ደህና አግኝቻቸዋለሁ፡፡ አባቴ ኤርፖርት ድረስ መጥቶ ነበር፡፡ እናቴም ሆቴል መጥታ አግኝታኛለች፡፡ ከዚያም በኋደኞቼ በአብሮ አደጐቼ፣ ተወልጄ ባደግኩበት በሽሮሜዳ፣ በከፍተኛ ዝግጅት፣ የሚገርም አቀባበል አድርገውልኛል፡፡ ሁሉንም በአንድ መድረክ አግኝቼ ሰላምታ አቅርቤ አመስግኛለሁ፡፡ ይሄ ለእኔ ትልቅ ደስታና ክብር ነው። በአጭር ጊዜ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም፡፡ እርግጥ ትግሉ ተስፋን የሰነቀ እንጂ የምድረበዳ ጩኸት አይደለም፡፡ ስለዚህ ለውጥ ይመጣል ብዬ ባምንም፣ በዚህ ፍጥነት አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ጨቋኝ መንግስት መውደቁ እንደማይቀር እርግጠኛ ነበርኩ። እንደውም መውደቁ አይቀርም፣ እንዳይወድቅብን አል ነበር፡፡

==================


“ቆራጥና ለነፃነት የቆመ መሪ አግኝተናል”     ጋዜጠኛ አበበ ገላው


ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ አገር ቤት መመለስህ መምን ስሜት ፈጠረብህ?
እውነት ነው አንድ ሰው ከ20 ዓመት በላይ ከአገሩ፣ ከወገኑ፣ ከቤተሰቡና ከጓደኞቹ ሲለይ የሚፈጥረው ስሜት ይታወቃል፡፡ እኛ ተሰደን ብቻ ሳይሆን በግዞት የኖርነው፡፡ ለምን ካልሽኝ፣ ከአገር የወጣነው አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ነው፡፡ ከአገሬ ውጭም ስኖር ተመልሼ የምመጣበት ሁኔታ አልነበረም። እኔ ከአገሬ ከወጣሁ ጀምሮ ሥርዓቱ በህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና ስቃወም ነው የቆሁት፡፡ በዛም ምክንያት በሀሰት ክስ አሸባሪዎች ብለውን፣ የሀሰት ዶሴ ይዘው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ፣ የ15 ዓመት እስራት ተፈርዶብኝ ነበር፡፡ እስከዚህ ድረስ ነው ስርዓቱ እኛን ለማሳደድና ለማባረር ሲሰራ የነበረው። አሁን ላይ ያሁሉ አልፎ የኢትዮጵያ ህዝብ በነፃነት መተንፈስ ጀምሮና የተሰበረ አንገቱን ቀና አድርጎ ለማየት በመብቃቴ፣ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። እኔ ስመኝ የነበረው ይሄን ነው፡፡ ነፃነት ሳይመጣ አገሬ ብመለስ ትርጉም የለውም፡፡ ነፃ የሆነ ህዝብና አገር በሌለበት፣ ወደ አገር መመለስ ምንም ጣዕም፣ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ስለዚህ እስከዛሬ አለመመለሴ አልቆጨኝም፡፡ ነገር ግን የቆጨኝ ያጠፋነው ጊዜ ነው፡፡ እንኳን አንድ አገርና ህዝብ፣ እንስሳትም ነፃነታቸው ተከብሮ መኖር አለባቸው፡፡ በሰለጠነው ዓለም እንኳን የሰው የእንስሳትም ነፃነት ይከበራል፡፡ የእኛ ህዝብ ማንነቱ ተገፎ፣ ስብዕናው ተደፍሮ፣ ከእንስሳት በታች ነበር የሚኖረው፡፡ በየእስር ቤቱ ጥፍሩ እየተነቀለ፣ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመበት፣ ብልቱ እየተኮላሸ ነው የኖረው፡፡ ይህን የሚያደርገው ደግሞ መንግስት ነው፡፡ መንግስት አገርን ማስተዳደርና ወደ ልማት መምራት እንጂ ዜጎችን እያፈኑ እያሰሩ፣በየወህኒ ቤቱ ማሰቃየት የመንግስት ስራም ኃላፊነትም አይደለም። ስለሆነም ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ መንግስት አልነበራትም ብዬ በድፍረት እናገራለሁ፡፡ አገሪቱ ላይ የነበረው አንድ የተራ ወንበዴ ስብስብ ነበር፡፡ ሥራውም የአንድ ተራ ወንበዴ ተግባር ነበር፡፡
በዚህ በ27 ዓመት ወንበዴው ቡድን የኢትዮጵያን ወርቃማ ጊዜ አባክኖ፣ ወንድማማቾችን በዘርና በጎሳ እየከፋፈለ እርስ በርሳቸው እንዲባሉ እንዲናከሱ በማድረግ፣ ሥልጣኑን ለማራዘምና ለዘረፋ ተጠቅሞበታል፡፡ አገርም ህዝብም ተዘርፈዋል፡፡ ይህቺ አገር አጥንቷ እስኪቀር በህውሃትና በእነሱ ጋሻ ጃግሬዎች ተግጣለች፡፡ ይሄ ሲሆን እኛ በሩቅ ሆነን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም ታግለናል፡፡ በተለይ ኢሳትን ካቋቋምን ጀምሮ፣ በዛ ጨለማ ዘመን ብርሃን ሆነን ዘልቀናል፡፡ ይሄ ያኮራኛል፤ ስለዚህ ዛሬ የታገልንለት ዓላማ ተሳክቶ፣ በነፃነትና በኩራት፣ ወደ አገሬ ስመለስ፣ የተሰማኝ ደስታ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ህዝብም አንፃራዊ ሰላም አግኝቶ በማየቴና የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት ብዙ ተስፋ ፈንጣቂ ነገሮችን እያሳየ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቆራጥና ለነፃነት የቆመ መሪ አግኝተናል፡፡ በዚህም ኩራት ይሰማኛል፡፡ በአጠቃላይ፣ እግዚአብሔር፣ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ትልቅ ሥራ የሰራበት ጊዜ ነው። ወደፊት ህዝቡ ተመልሶ ወደ ጭቆና እንዳይገባ፣ የተገኘውን ነፃነት የመጠበቅ ኃላፊነት የሁላችንም ነው፡፡ እዚህ መጥቼ ይህንን ሁሉ ማየት መቻሌ ጠቅለል ሳደርገው፣ የአምላክ ገፀ በረከት ነው እላለሁ፡፡
እንዴት ነበር  ከአገር የወጣኸው?
ከአገር ቤት ከመውጣቴም በፊት ሲፈፀሙ የነበሩ በደሎችን ስቃወም ነበር፡፡ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ፣ 42 ያህል ምሁራን፣ ፕሮፌሰሮች ዶክተሮች ተባረሩ፡፡ የሜዲካል ትምህርት ቤቱን ያቋቋሙትን ፕሮፌሰር አስራትን አባሮ ዩኒቨርሲቲ ማለት አይገባኝም ለእኔ፡፡ እነ ፕሮፌሰር መስፍን፣ እነ ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ እነ ዶ/ር ምንዳርአለው /አሁን በቅርቡ በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ሲሰጡ በአድናቆት ልቤን ሞልተውታል/ እነዚህን የመሳሰሉ ትልልቅ የአገር ዋልታዎች ተባረሩ፡፡ ያኔ እኔ  ይህንን በመቃወምም የተማሪዎች መሪ ነበርኩኝ፡፡ በዛ ምክንያት ታስሬም ነበር፡፡ ያኔ እዚህም አገር ኖርኩ ተሰደድኩም፣ ይህንን ሥርዓት መታገል አለብኝ ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ይህ የሆነው በእኛ አቆጣጠር በ1985 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ ለሁለት ወራት ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታ ታስሬ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የኤርትራ ህዝበ ውሳኔ ትክክል አይደለም ብለን ተቃውመን ሁሉ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ብዙ ነገሮች የተወሰዱት፡፡ ከዚያም በብሔራቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ፕሮፌሰሮች እየተመረጡ ተባረሩ፡፡ ይሄ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ይህን ያደረጉት ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ አቶ መለስ፣ ሁሉም እንደሚያውቀው፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ ውሳኔዎች የወሰኑ ሰው ናቸው፡፡
እስኪ ዋና ዋና የምትላቸውን ንገረኝ?
አንደኛ፣ ዋናውና አስከፊው፤ እነዚህን ምሁራን ማባረራቸው ነው፡፡ ለምን ካልሽኝ፣ አገር ያለ ምሁር ዋጋ የላትም፤ አንድ አገር የተማረ ዜጋ ከሌላት አታድግም፤ እነዚህ ምሁራን ሲባረሩ በስርዓቱ ላይ ተስፋ ቆረጥኩ፤ መታገልም ጀመርኩኝ፡፡
አንዳንዶች፤የኢህአዴግን “የምሁራን ማባረር”፣ ከደርግ “60ዎቹን መግደል” ጋር ያወዳድሩታል፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
መወዳደርም አለበት፡፡ እንዳልኩሽ አንድ ትልቅ የትምህርት ተቋም፣ የሀሳብ ነፃነትን የማያከብር ከሆነ፣ መጀመሪያም ዩኒቨርሲቲ ሊባል አይችልም፡፡ የህሊናና አካዳሚክ ነፃነት ለአንድ ዩኒቨርሲቲ ወሳኝ ቁም ነገሮች ናቸው፡፡ ይሄንን ጥሶ መምህራንን እየመረጠ ማባረሩ፣ ከደርግ የጄነራሎች ግድያ አይተናነስም። ሰዎቹን አልገደላቸውም እንጂ የዩኒቨርሲቲውን አላማና ግብ ገድሏል፡፡ ወደ አወጣጤ ስንመለስ፣ ከመውጣቴ በፊት በጋዜጠኝነት ከእነ እስክንድር ነጋ ጋርም ሰርቻለሁ፡፡ ያኔ እስክንድር “ሀበሻ” የተባለ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ይሰራ ነበር፤ ለተወሰነ ጊዜ አብሬው ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ ኢትዮጵያን ሄራልድ ላይም ሰርቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ሄራልድ መስራቴ አይን ገላጭ ነበር፡፡ ይበልጥ ሥርዓቱን እንዳውቀው አድርጎኛል፡፡ ሥርዓቱ ከፋፋይ፣ ጨቋኝና በአድልኦ የተሞላ መሆኑን በግልፅ ያሳየኝ ኢትዮጵያን ሄራልድ መስራቴ ነው፡፡ ለትምህርት ወደ አሜሪካን አገር ልወጣ ስል እንቅፋት ፈጠሩብኝ፡፡ በኋላ የሮይተርስ የሚዲያ አውታር የስልጠና ዕድል ሰጥቶኝ ለንደን ሄድኩኝ፡፡ ለንደን እንደሄድኩኝ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቅኩኝ፡፡ ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የምመጣበት ዕድል አልነበረኝም፡፡ እኔም ደግሞ በአገሬ ነፃ ሆኜ መስራትና መኖር የምችልበት ሁኔታ ከሌለ መመለሴ ትርጉም ስለሌለው፣ በዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ተሰደድኩ፡፡ ለዘጠኝ ዓመት ለንደን ቆይቻለሁ። በቆይታዬ “Addis Voice.com” የተሰኘ ታዋቂ ድረ-ገፅ ከፍቼ ለ10 ዓመት ሰርቼበታለሁ፡፡ ይህን ድረ-ገፅ ኢሳት ሲቋቋም ትኩረቴን ወደ ኢሳት በማድረጌ ነው የተውኩት፡፡ በአጠቃላይ እንደ አክቲቪስት ብዙ ሰርቻለሁ፡፡
ለውጡን እንዴት ትገልጸዋለህ? የለውጡ ፈተናዎች ምንድን ናቸው ብለሀ ታስባለህ?
ለውጡ አብዮታዊ ለውጥ ነው፤ ስር ነቀል ለውጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ የተከለውንና ያሳደገውን መጥፎ ነገር ሁሉ የነቀለ ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚባለው በዓለም ላይ የሌለና እርስ በእርሱ በሚጋጭ ርዕዮተ አለም ነው ሲደናበር የኖረው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ርዕዮተ ዓለም፣ በዓለም ላይ የለም፡፡ አብዮትና ዴሞከራሲ ሁለቱ የሚቃረኑ እንጂ አብረው የሚሄዱ አስተሳሰቦች አይደሉም፡፡ ዴሞክራሲ በሂደት የሚያድግ ነው፡፡ አብዮት በስር ነቀል ለውጥ የሚመጣና ብዙ ነገሮችን የሚቀይር ነው፡፡ አንደኛ ኢህአዴግ አብዮታዊ ሆኖ አያውቅም፤ አብዮታዊነት ህዝብ መርገጥና መጨቆን ነው ካልተባለ በስተቀር፡፡ ዴሞክራሲንም አያውቁትም፤ ዴሞክራሲ ማለት በህዝብ ፍላጎት መኖር ማለት ነው፡፡ ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ተደርጎ አያውቅም፤ምርጫ አክብረው አያውቁም። የተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ የይስሙላ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ኢህአዴጎች ጨቋኝ፣ በዝባዥ፣ ዘራፊ እንጂ አብዮታዊም ዴሞክራሲያዊም አልነበሩም። ቃሉንም ትርጓሜውንም በአግባቡ አያውቁትም፡፡ የሽፍታ ሥርዓትና ስብስብ ነበር፡፡ የራሳቸውን ህገ መንግስት እንኳን የሚያከብሩ ነበሩ፡፡
አሁን የስርዓቱ ቁንጮ የነበሩት እነ አቶ በረከት ስምኦን መታሰራቸውና በህግ ተጠያቂ መሆናቸው በራሱ ለውጡን ትልቅ ያደርገዋል። ለውጡን ምን ፈተና ይገጥመዋል ላልሽው፣ አንድ ለውጥ ሁልጊዜ ሲመጣ ጥቅማቸው የሚነካባቸውና የቀደመው ስርዓት ተጠቃሚ የነበሩ፣ የቀድሞውን ስርዓት ለማስቀጠልና ለውጡን ለማኮላሸት መፍጨርጨራቸው አይቀርም፡፡ በመላ አገሪቱ መረጋጋት እንዳይፈጠርና ለመቀልበስ እንዲያመቻቸው እዚህም እዛም እሳት የመለኮስ ስራውን ተያይዘውታል፡፡ ገንዘብ በየቦታው እየበተኑ፣ አንዱን በሌላው ላይ በማነሳሳት አለመረጋጋት በመፍጠር ላይ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የወቅቱ የለውጡ ፈተና ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ ከተመራ በቶሎ ይከሽፋል እንጂ ለውጡ አይቀለበስም፡፡ ህወሐት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከእነሱ ጋር የጥቅም ተጋሪ የነበሩትን ሁሉ እያነሳሱ፣ ሁከት በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ ይህን በማድረግ ለውጡን ለመቀልበስና አዲሱ የአገር መሪ መምራት እንዳልቻለ ለማስመሰል ይሞክራሉ፤ አይሳካም፡፡ በየቦታው ሰው እየሞተ፣ አካል እየጎደለና ንብረት እየወደመ መሆኑ አሳዛኝ ቢሆንም ለውጡ አይቀለበስም፡፡ ለምን ከተባለ፣ ህዝቡ ከልቡ የተቀበለው ለውጥ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የህወሓት የበላይነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡
የኦዴፓ የበላይነት (በተራው) እንዳይመጣ ብለው የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
እንዲህ ዓይነት ነገር የሚመጣ ከሆነ መታገል ነው፡፡ ነገር ግን ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ዶ/ር ዐቢይና የስራ አጋሮቻቸው፣ ሁሉም ዜጋ እኩል እንዲከበርና ኢትዮጵያ የሁሉም አገር እንድትሆን ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ ሁኔታዎችና ድርጊቶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው፡፡
በቀጣይ የኢሳት እቅድ ምንድን ነው?
ኢሳት ከተቋቋመ ጀምሮ ለለውጥ የታገለ ሚዲያ መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ አሁንም አገሪቱ ተረጋግታ ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሄድ የበኩሉን አዎንታዊ አስተዋፅኦ የማድረግ እቅድ አለው፡፡ የበለጠ አቅሙንም ጉልበቱንም አጠናክሮ ስራውን ይቀጥላል፡፡ እኛ ሁላችንም ጋዜጠኞች ብቻ ሳንሆን የመብት ታጋዮችም ነን፡፡ ይሄ ጠቅሞናል አልጎዳንም፡፡ ኢሳት በአሁኑ ሰዓት የትግል ሚዲያ አይደለም፡፡ አስተዋፅኦውን ቢቀጥልም የቀድሞው አይነት ትግል ቆሟል፡፡ ነገር ግን በመንግስት በኩል የስልጣን መባለግ፣ አድልኦ እንዳይፈጸም፤ መብት እንዳይገፍ ሚዲያ ትልቅ ሚና የሚጫወት በመሆኑ፣ ያንን በማጋለጥ አሁን መቶ በመቶ ያልጠፋውን ሙስና ከመዋጋት ወደ ኋላ አንልም፡፡ ኢሳትም እንግዲህ አገሪቱንና ለውጡን በማገዝ ችግሮች እንዲስተካከሉ፣ ክፍተቶችን በማሳየት በኩል፣ የራሱን ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡

====================


“የኢሳትን በዓል አዲስ አበባ እናከብራለን ብዬ ነበር”   ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተወለድ


በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ነው አይደል ወደ አገርህ የመጣኸው?
ባለፈው መስከረም፣ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመጡበት ጊዜ፣ ሂደቱን ለመዘገብ ነበር የመጣሁት። በየሄዱበት ሁሉ አብሬ እየተጓዝኩ፣ አጠቃላይ ሂደቱን ዘግቤያለሁ፡፡ ያኔ ስመጣ ከ10 ዓመት በኋላ ነበርና የአገሬን መሬት የረገጥኩት፣ በተለይ ከአውሮፕላን ስወርድ፣ እግሬ ሁሉ ይንቀጠቀጥ ነበር። የእውነት ነው ወይስ ህልም? እያልኩ ነበር። የምሬን ነው የምልሽ፣ ወንድ ልጅ የሚያለቅሰው በውስጡ ነው የሚለው እኔ ላይ አልሰራም፤ እንባ አውጥቼ ነበር ያለቀስኩት፡፡ የትውልድ አካባቢዬ ኮምቦልቻም ሄጄ ቤተሰቤን አግኝቼ ነው የተመለስኩት፡፡ ያኔ የተሰማኝ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት ጓደኞቼ የተሰማቸው ነበር። አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ስመጣ ደግሞ የመግባትና የመውጣት ነፃነቴ እንደተከበረ እርግጠኛ የሚያደርግ የደስታ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ለምን ብትይ ታስረን ተሰደን፣ በውርደት ነበር የሄድነው። አሁን በክብርና በፍቅር ተመለስን፡፡ በፊት አንድ ቀን አገራችን እንገባለን ስንል፣ ቅዠታሞች እያሉ ሰዎች ይሳለቁብን ነበር፡፡ ግን ነገሮች ካሰብናቸው ፈጥነው ተቀይረው፣ ይሄው ለሃገራችን በቅተናል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
የዛሬ ዓመት የኢሳትን በዓል አዲስ አበባ እናከብራለን ብዬ ነበር ብለሃል፡፡ ምን ታይቶህ ነው?
በየዓመቱ የኢሳትን የምስረታ በዓል በተለያዩ አገሮች እናከብራለን፡፡ ስናከብር አንድ ቀን ኢሳት ኢትዮጵያ ይገባል እንል ነበር፤ ልክ እኛ አገራችን እንገባለን እንደምንለው ማለት ነው፡፡ በስዊዲን በለንደንና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከደጋፊዎችን ጋር እናከብራለን፡፡ ታዲያ የዛሬ ዓመት ስናከብር፣ “የዛሬ ዓመት ይህን በዓል አዲስ አበባ እናከብረዋለን” አልኩኝ፡፡ ምን ታይቶህ ነው ላልሺኝ፣ ተስፋ ብቻ ነበር፡፡ ያኔ ሁሉም ነገር ጨለማ ነበር፤ የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር እኮ በምድረ በዳም ያዘንባል፡፡ እናም የዛሬ ዓመት በድምቀት አዲስ አበባ እናከብራለን ስል በኢሳት ተላልፎ ስለነበር፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እኔን መቃወም ቋሚ ስራቸው የሆነ ልጆች ነበሩ፤ እነዚህ የህውሓት ልጆች “አንተ ቅዠታም ስትቃዥ ትቀራለህ” ብለው ፃፉብኝ፡፡ “እንዴት አስበኸው ነው እዚህ የምታከብረው?” ብለው የስድብ ናዳ አወረዱብኝ። ነገሩ ዓመት ሳይሞላው፣ አገራችንን ረገጥን፤ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡
አገር ቤት እያለህ አዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎችም ጋዜጦች ላይ ትሰራ እንደነበር ይታወቃል። እንዴት ነበር ከአገር የወጣኸው?
በነገራችን ላይ አሁን ቃለ ምልልሱን እያደረግሁ ያለሁት በራሴ ጋዜጣ ላይ ነው፡፡ ይሄ ደስታዬን ጨምሮታል፡፡ አዲስ አድማስ በደንብ፣ ብዙ ካወቅኩባቸው ጋዜጦች አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው። እጅግ የምወደው ጋዜጣ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ስፅፍ የምጠቅሰው፣ ከግል ፕሬሶች የማልረሳው ነው፡፡ አሁን ደግሞ እናንተ ተተክታችኋል፤ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከአዲስ አድማስ ቀጥሎ ሀዳር  ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ነበርኩኝ፡፡ ከአዲስ አድማስ በፊት ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ያሳትመው የነበረው ዕለታዊ አዲስ ጋዜጣም ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ሃዳር ላይ ከጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ጋር በአጭር ጊዜ ብዙ ሥራዎችን ሰራን፤ ግን ከዳዊት ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ የሚገርምሽ ህዳር የሚወጣው ባልተለመደ መልኩ ሀሙስ ቀን ነበር፡፡ ከኤዲቶሪያል ጀምሮ አብዛኛውን ጽሑፍ የምጽፈው እኔ ነበርኩኝ፡፡ ጋዜጣው ኮፒው እየጨመረ፣ ተቀባይነቱ እየበዛ በመጣበት ሰዓት፣ ምርጫ 97 እየመጣ፣ ሁሉም ነገር በተፋፋመበት ሰዓት፣ ዳዊት ባልሆነ ነገር ምክንያት ፈጥሮ ተጋጨን፡፡
ከዚያስ?
ወደ ፒያሳ እየሄድኩ ነበር፤ አራት ኪሎ ጆሊ ባር ጋር ወረድኩኝ፡፡ ረቡዕ ቀን ነው፤ ጋዜጣችን የሚወጣው ሀሙስ ነበር፤ እናም የድሮው የሮዝ መጽሔት ባለቤት፣ አዲስ አድማስንም ሀዳርንም የሚያከፋፍለው እንዳልክ፣ አገኘኝ፡፡ “እንዴ ጋዜጣው የሚወጣው ነገ ነው፣ እዚህ ምን ትሰራለህ?” አለኝ። ለቀቅኩ አልኩት፡፡ “መቼ” ሲለኝ፤ አሁን፡፡ “ደረጀ፤ እኔ’ኮ አንተን እፈልግህ ነበር፤ አንድ ሰው ጋዜጣ ለማሳተም ይፈልጋል፤ ፈቃዱን እየገበረበት እጁ ላይ ነው” አለ፡፡ እና የጋዜጣ ፈቃድ አለው ነው የምትለኝ ስለው፣ አዎ አለ፡፡ ከዳዊት ጋር ስወጣ በወረቀት የተፃፈ አምስት ዜና ይዣለሁ፡፡ አንድ አርቲክልም ጽፌ ይዣለሁ፡፡ “አሁን ላገናኛችሁ” ሲለኝ፤ እባክህ ጥራው አልኩት፡፡ የነፃነት ጋዜጣ ባለቤት ዘካሪያስ ተጠርቶ መጣ፡፡  ጊዜው ለጋዜጣ ጥሩ ነበር፡፡ “ነፃነት የሚባል ጋዜጣ ለማሳተም ፈቃድ አለኝ፤ ግን ሙያተኛ ባለማግኘት ቆየሁ” አለኝ። የሚገርምሽ የጋዜጣ ሙያተኛ አይደለም እንጂ በቂ ቢሮ፣ ኮምፒዩተርና መሰል ነገሮችን አሟልቶ ቁጭ ብሏል። ከዚያ ነፃነትን ለመስራት በዛው ቀን ከሰዓት ቢሮ ገባን፡፡ አምስት ዜና ይዣለሁ፡፡ የዜና ገፅ ሞላ፤ አንድ አርቲክልም ነበረኝ ብዬሻለሁ፡፡ ከዛ ርዕሰ አንቀጽ ፃፍኩኝ፡፡ ዘካሪያስ “ደረጀ፤ ግዴለህም በዚህ ሳምንት አንችልም፤ በቀጣዩ ሳምንት በደንብ እንሰራለን” አለ። “አይ ለመጀመሪያ ጊዜ በ8 ገጽ ሰርተን እናውጣው” አልኩት፡፡ ለምን? የሚሞትብኝ ዜና እጄ ላይ አለ፡፡ የዛን ቀን ደግሞ 9.00 ሰዓት ላይ ቅንጅት መግለጫ ስለነበረው፣ ሁለት ልጆች ልኬ፣ እሱን ሪኮርድ አድርገው አመጡልኝ፡፡ ሰርቼ ጨረስኩኝና ሰባቱ ገፅ ሞልቶ፣ አንድ ገፅ ቀረን፡፡ ያኔ ገና የምርጫው ውጤት አልተገለፀም ነበር፡፡ የጀርባውን ገፅ፣ በትልልቅ ባለስልጣናት ፎቶ ሞላሁና፣” የዛሬ አምስት አመት ሰው ይበለን” ብዬ ዘጋሁት፡፡
እና “ነፃነት” ፣ “ህዳር” በሚወጣበት ቀን  ለአንባቢ ደረሰ ነው የምትለኝ?
እንዴታ! ከህዳር ጋር እኩል ወጣ፤ በመጀመሪያው እትም በስምንት ገፅ፣ በነጭና ጥቁር ቀለም ወጥታ፣ 40 ሺህ ኮፒ የተሸጠች ነፃነት ጋዜጣ ናት፡፡ በቀጣዩ ሳምንት ሁለት ጋዜጠኞች ጨመረልኝ፤ ባለ 16 ገፅ ባለ ቀለም ሆኖ ወጣ፡፡ በህይወቴ በጋዜጠኝነት ታሪኬ፣ የምገረምበት፣ የማስታውሰው ይሄ ነው፡፡ ነፃነት እስከ 130 ሺህ ኮፒ ታትማ የምትሸጥ ጋዜጣ ሆና ነበር፡፡ ሀዳር 35ሺ እና 40ሺህ ኮፒ ላይ ቆመ፡፡ እኔም አንድም ቀን ስራ ሳልፈታ ነው የጀመርኩት፡፡
የ97ቱን የምርጫ ቀውስ ተከትሎ ከታሰሩት ጋዜጠኞች  አንዱ ነበርክ፡፡ ከዚያ በይቅርታ ተፈታህ። ለምን ከሀገር ወጣህ?
እንዳልሺው ከምርጫ 97 በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል ታስረን፣ መጀመሪያ ሲሳይ አጌና፣ ሰርካለም ፋሲል፣ እኔ፣ እስክንድር ነጋ----በአጠቃላይ 8 ጋዜጠኞች፣ ከእነ ኢንጅነር ሃይሉ ሻውል ቀድመን በነፃ ተለቀቅን። ከወጣን በኋላ የተፈታነው ጋዜጠኞች መወያየት ጀመርን። እስክንድር እዚሁ ነው የምቀረው አለ፡፡ እንስራ ብለን ነበር፤ ፈቃድ እንደማይሰጥ ሲሳይና እስክንድር ቀድመው ሰሙ። የምንሰራባቸው ጋዜጦች ተዘግተዋል። እንደ ዜግነታችን፣በአገራችን ላይ ሰርተን መኖር አለብን። በሌላ በኩል፤ አቃቤ ህግም፣ “ይግባኝ እላለሁ” ማለትና ማስፈራራት ጀመረ፡፡ ደህንነቶች እየደወሉ፣ ማወክና ያልተገቡ ነገሮችን ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይሄ ሁሉ አላስጨነቀንም። ዋናው ሰርተን የመኖር መብታችንን ተነጠቅን፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ እና ፋሲል የኔዓለም (የአዲስ ዜና ጋዜጣ ባለቤት) ሆነን፣ እዚህ ሰርተን ካልኖርን፣ ሞራላችንም ከሚነካ ከዚህ አገር ወጥተን፣ ቴሌቪዥንም ይሁን ድረ-ገፅ ሚዲያ አቋቁመን ለምን አንሰራም። በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን አፈናና ጭቆናስ ለምን አናጋልጥም አልን፡፡ በወቅቱ ደግሞ በውስጣችን ቁጣም ነበር፡፡ ሲሳይና እስክንድር እዚሁ ለመስራት ይፈልጉ ስለነበር አንገራገሩ። እኔና ፋሲል ግን ተነስተን ኬንያ ገባን፤ 1998 ዓ.ም መጨረሻ ነው፡፡ በወቅቱ የእኛ ጉዳይ በተለያዩ ሚዲያዎች ተገልጾ ስለነበር፣ ቪኦኤም ጀርመን ድምጽም ቃለ ምልልስ አደረጉልን፡፡ ኬኒያ ያሉት የዩኤን ሰዎች በፍጥነት ተቀበሉን። በነገራችን ላይ እኛ ኬንያ ብዙ አልቆየንም፤ በሶስተኛው ወር ነው ሆላንድ የገባነው። አምስተርዳም በገባን በሁለት ዓመታችን ነው ኢሳት የተቋቋመው፡፡ እስክንድርና ሲሳይ የቀድሞዎቹ ቢዘጉም “አዲስ ፈቃድ ስጡን” እያሉ ይጠይቁ ነበር፡፡ መንግስት እንደለመደው  ለግማሾቹ እናት፣ ለሌሎቹ የአንጀራ እናት መሆኑን ተያያዘው፡፡
እስቲ ስለ ኢሳት ንገረኝ? እንዴት ጀመርክ? ተሞክሮህን-----?
ኢሳት ሲነሳ ፊት ለፊት ስለምንታይ እኛ ነን የምንመሰገነው፤ ነገር ግን ከጀርባ ሆነው ገንዘባቸውን ጉልበታቸውን ሙያቸውን የሰጡ፣ ብዙ አገር ወዳጆችም ውጤት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ፣ ኢሳት እዚህ የደረሰው ራስን ማመስገን አይሁንብኝ እንጂ በጋዜጠኞቹ ቁርጠኝነትና ተስፋ አለመቁረጥ ነው፡፡ ለዓላማ ነበር የምንሰራው፡፡ ለገንዘብ ቢሆን፤ ከታክሲ መንዳት ጀምሮ በርካታ የስራ አማራጭ አለ፡፡ እኛ ብር ከተገኘም ተገኘ፣ ካልተገኘም ለአላማ ብለን ኪሳችን ባዶ ሁሉ ሆኖ እንሰራ ነበር። ሚዲያው እንዳይቆም ሌትና ቀን እንጨነቅ ነበር፡፡ ግን አላማችንን ያሉ ከላይ የጠቀስኳቸው አገር ወዳዶች ይደግፉን ጀመር። ኢሳት አንድ ጊዜ ጃም ተደርጐ ሲመለስ እኮ ብዙ ገንዘብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሌላው ፈተና የመረጃ ምንጭ ነበር። በተለይ አሸባሪ ተብለን ከተፈረጅን በኋላ ብዙ ሰው በኢሳት ለመቅረብ ፈራ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሁሉ እስኪ እለፉን ማለት ጀመሩ። በዚህ አጋጣሚ አርቲስቶቻችን፣ በዛ በጨለማ ዘመን፣ ነፍሱን ይማርና አርቲስት ታምራት ደስታና ጐሳዬ ተስፋዬ ቃለ ምልልስ ሰጥተውናል፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍነው። እርግጥ በሰውም አይፈረድም፤”እኛ እዚህ ከእናንተ ጋር ከታየን ቤተሰቦቻችን አገር ቤት ይሰቃያሉ” ይላሉ፡፡ እውነት ነው፡፡
ብቻ ባልደረቦቼ፣ መሬት አንጥፈው ከመተኛት ጀምሮ በርካታ ነገሮችን ከፍለዋል፡፡ ከጀርባችን የነበሩት ለፍተው ደክመው በማምጣት፣ ትግሉን ተቀላቅለው፣ እዚህ ደርሰናል፡፡ ዛሬ ደግሞ በኢሳት ቀርቦ ቃለ ምልልስ መስጠት ሁሉም ይፈልጋል፡፡ ይሄ የሚያስደስተን ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ህልምህ ምንድን ነው?
እንግዲህ ለውጡን ያመጣው እግዚአብሔር ነው። ለምን ካልሽኝ፣ ለውጡ የመጣው ከውጭ ማለት ከድርጅቱ ውጭ ቢሆን፣ ሰዎችና በሁለት ተቃራኒ ወገኖች ቢሆኑ ብዙ ደም መፋሰስ፣ እልቂት ይፈጠር ነበር፡፡ ነገር ግን ከራሳቸው ሰዎች ሆኖ፣ የወጣቱ ትግልና መስዋዕትነት ተደምሮ በቀስታ አለፈ፡፡ የነፃነት አየር ተነፈስን፤ ውጭ ያለው አገሩን ረገጠ፤ የታሰረ ተፈታ፡፡ ከዚህ በኋላ ህልሜ፣ ለውጡ በፀና መሰረት ላይ ቆሞ፣ ቀጣይነት ያለው ነፃነት፣ በአገሬ ላይ ሰፍኖ ማየት ነው፡፡ ይህንን ለማየት የራስን አበርክቶ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በግሌ የሚጠበቅብኝን በማድረግ፣ ለውጡን እደግፋለሁ፡፡ ኢሳትም ይህንን ያደርጋል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 6039 times Last modified on Tuesday, 26 February 2019 15:38