Print this page
Sunday, 24 February 2019 00:00

‘የባንኳ ዲምፕል

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)


እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ቡና ይዛችሁ ተቀምጣችኋል፡፡ የሆነ የምታውቁት ወይም ራሱን “ጓደኛው ነኝ፣” ብሎ የሚያስብ ሰው አጠገባችሁ መጥቶ ይቀመጣል፡፡ አቀማመጡ እኮ ሰልክ ደውላችሁ “አንተ ሰውዬ፣ እየጠበኩህ አይደል እንዴ!” ብላችሁ የተቆጣችሁት ነው የሚመስለው። “ስማ፣ በጣም ነው እኮ የጠፋኸው…” ምናምን አይነት ነገር ይላል፡፡ (ከሁለት ቀን በፊት መንገድ ላይ ያገኛችሁት ሰው ነው እንዲህ የሚለው! የናፍቆት ሰላምታ እያቀረበላችሁ ሳይሆን ቀጥሎ ለሚመጣው ‘እያለሳለሳችሁ ነው፡፡) መቅደም ይሻላል!
“ሻይ ቡና ነገር ያዛ!” ትላላችሁ፡፡
ያመነታል፣ እንደ መንጠራራትም ይላል፡፡ “እ… ልጠጣ ብለህ ነው! አሁን እኮ ነው ማኪያቶ የጠጣሁት…”
“ግዴለም…ማኪያቶ ቢደገምም አያሰክርም፡፡ የሆነ ነገር ያዝ…” ትላላችሁ፡፡ አንደኛ ስህተት፣ ግዴለም የሚለው ቃል፡፡ ልክ “እኔ የመከሰስ መብትህን ካላነሳሁ በስተቀር የፈለግኸውን ብታደርግ ማንም ጫፍህን አይነካህም፣” አይነት… ‘ግሪን ካርድ’ እንደመስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው ስህተት፣ “የሆነ ነገር ያዝ፣” የሚለው፡፡ ይህኛው ፈረንጅ ‘ፋታል ሚስቴክ’ የሚለው አይነት እንደሆነ ‘የሆነ ነገር ሲያዝ’ ታውቁታላችሁ፡፡
ያጨበጭባል… “አስተናጋጅ… .እዚሀ አንድ ቢራ ታመጪልኝ…” (ምን! ቢራ! “ኸረ የሚያበር ነገር ያብርርህ!” ልትሉት ታስቡና ቀኑ ‘የጾም ቀን’ መሆኑ ትዝ ሲላችሁ ትተዉታላችሁ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… “በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ፣” ለፖለቲካ ብቻ ትመስላችሁ ነበር።)
“ስማ…ደግሞ ቀዝቃዛ… ያላበው አድርግልኝ፡፡”
(እስከ መጨረሻው ጠብታ ላብህን ያድርቅለህ! አሀ… የፈለገ ‘የጾም ቀን’ ይሁና! እርግማን ጥሩ ባይሆንም ‘አስጋዳጅ ሁኔታዎች’ ሲፈጠሩ ምን ይደረግ፡፡ በማን ‘ዋሌት’ ነው እንዲህ የሚመጻደቀው!) እናማ… የታሪኩ መጨረሻ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፣ ገና መጀመሩ ነው፡፡ ያላያችኋት ጸሀይ ሾልካ ገብታ ቢራውን ‘ታትንነው፣’ ሰውየው በመንፈስ ይጨልጠው ብቻ ቀና ስትሉ ብርጭቆው ባዶ ነው፡፡ ከመቼው ተጠጣና! ለነገሩ ኪሱ እንደሁ የሌላ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሆነ ነገር ‘የሌላው’ እስከሆነ ድረስ ጉዳያችንም አይደል። የእኛ አጥር እስካልተነቀነቀ ድረስ የሌላው ግምብ ቢደረማመስ.. አለ አይደል… “ሶ ሁዋት!” ነው፡፡
እንደገና ያጨበጭብላችኋል… “እዚህ ትደግመኝ… የቅድሙ በደንብ አልቀዘቀዘም…ያላበውን መርጠህ አምጣልኝ፡፡ (አልቀዘቀዘም!  አልቀዘቀዘም! እናንተ አንጀታችሁ ‘ቀዝቅዞ’ የአርክቲክ በረዶ ሊሆን ደርሷል፣ አጅሬ “አልቀዘቀዘም!” ይመጻደቃል፡፡)
ታዲያላችሁ… እንዲህ አይነት የኪስ ድንኩዋን ሰባሪ የዋዛ አይምሰላችሁ፡፡ ጨዋታውን ለቢራ ግብዣ እንዲሆን አመቻችቶ ነው የሚያመጣው። ታዲያላችሁ… በየሚኒባሱ የሚወራውን “ይህ ሳሪ የሚሉት ሰውዬ ቼልሲን የቀበሌ ሠላሳ ሦስት የጤና ቡድን አስመሰለው እኮ!” ብሎ ነገር የለም፡፡ “ስማ…አጅሬዎች ድምጻቸውን አጥፍተው ሠሩልን አይደል!” አይነት ‘የሴራ ፖለቲካ’ የለ!
“ስማ…ያቺ የባንኳ ልጅ ትዝ ትልሃሀለች…”
“የባንኳ…” የሚለውን ቃል ስትሰሙ የሆነ ነገር ይነዝራችኋል፡፡ አጅሬም አንደሚነዝራችሁ ያውቃላ!
“ያቺ ዲምፕሏ ልጅ…”
ዲምፕሏ! አሁን ቻርጅድ ሆናችሁ፡፡ የሆነ አምስት ሺህ ቮልት ምናምን የሆነ የ‘ኮረንቲ’ ገመድ ከጭንቅላታችሁ ጋር ያገናኙባችሁ ነው የሚመስለው፡፡ “ያላበው ቢራ” የሚለው ለአናንተ ‘ዌፐን ኦፍ ማስ ዲስተረክሽን’ ነው፡፡
“እሷን ልጅ አገኘኋት እንዳትለኝ…”
ሰውየው ገጽታ ላይ የሚታየው ብርሀን ድፍን አዲስ አበባን ‘ፏ’ ያደርጋት ነበር፡፡ ስትራቴጂ ሲሠራስ!
“አገኘኋት ብቻ…አንተ ግን ምን አይነት ሰው ነህ?”
‘ምን አይነት ሰው ነህ’ ማለት ምን ማለት ነው! “ሰውየዋ በሁለት ቢራ ጦሽ አለች እንዴ!”
“ለምንድነው የማትደውልላት! ምን አድርጌው ነው የማይደውልልኝ ስትለኝ ምን እንደምላት ግራ ገባኝ፡፡!”
ምን!  ምን አድርጌው ነው የማይደውልለኝ አለች!… ምን አይነት ሰናይ ወሬ ነው እባካችሁ! ቢራዋ ከግማሽ ወርዳለች፡፡ በጣታችሁ እየጠቆማችሁ… “ቢራው አኮ ሞቆ ሊፈላ ነው!” ትሉታላችሁ። ተናግራችሁ ሳትጨርሱ ከንፈሮቹና ጠርሙሱ ከመቼው እንደተገናኙ ግራ ሁሉ ይገባችኋል፡፡ ማሽን ውስጥ ገብታ የደረቀች ነው የሚስመስላት፡፡ የባንኳን ዲምፕል ወሬ ጀምሮላችሁማ በቀላሉ መላቀቅ የለም።
“ስማ በቅዳሜ ምድር የምን ከብቅልና ከገብስ ጋር መዳረቅ ነው!” ታጨበጭባላችሁ... “ሰማሽ የእኔ አህት… እዚህ ሁለት ደብል ብላከ ሌብል…”
(የምር ግን… ፖለቲካ ወስጥም ‘የባንኳ ዲምፕል’ አይነት ‘ማኖ’ ማስነካት አለላችሁ፡፡ እናማ…መስማት ያለብን ይቀርና “መስማት የሚፈልጉት” ተብሎ የሚታሰበው ብቻ ይነገረናል፣ እኛም “ኢሮ!” እያልን እናጨበጭባለን፡፡ ሰውየው ወደ “ደብል ብላክ ሌብል” በምርኩዝ ዝላይ የተምዘገዘገው መስማት ስለሚፈልገው ስለ ‘ባንኳ ዲምፕል’ ስለተነገረው ነው! እናም… ‘የባንኳ ዲምፕል’ ስትራቴጂ ለፖለቲካችንም እየሠራ ይመስላል ለማለት ያህል ነው፡፡)
እናላችሁ… በ‘ባንኳ ዲምፕል’ ስትራቴጂ ከምንነጋገረው አብዛኛው ሄሚንግዌይ በህይወት ቢኖር ኖሮ ሊቀናበት የሚችልበት ፈጠራ ነው፡፡ (‘ውሸት’ ላለማለት ያህል የተደረገ…) ስለ ‘ውሸት’ ከጠቀስን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
“ስማ ሰው ልጠይቅ አንድ ሆስፒታል ሄጄ ነበር፡፡ ምነ አየሁ መሰለህ፣ ሰው ውሸት ሲያወራ የሚያውቅ መሳሪያ አየሁኝ፡፡”
“እና…ምን ይገርማል?”
“እንዴት አይገርምም፣ አንተም ውሸት የሚለየውን መሳሪያ አይተኸዋል ማለት ነው!”
ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው… “በጋብቻ የተሳሰርኩት ውሸት ከሚናገር መሳሪያ ጋር ነው፡፡”
ከወራት በፊት የሆኑ በእድሜ ገፋ ደደረጉ ሰዎች፣ የሆነች ካፌ በረንዳ ላይ አንድ ጓደኛቸውን ፊት ስለ መንሳት ሲነጋገሩ ነበር፡፡ እኚሁ ጓደኛቸው ራሳቸው ደውለው “እንገናኝ፣” ብለው ከተገናኙ በኋላ እስኪበቃቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሂሳቡን ጓደኞቻቸው ላይ ጭነው ይሄዳሉ፡፡ ነገርዬው ከልክ በላይ ተደጋግሞባቸው ነበር ‘ፊት ስለመንሳት’ ሲመካከሩ የነበረው፡፡
ስሙኝማ.. .ሀሳብ አለን…የጓደኝነት ‘አዋጪ ጥናት’ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡
“እንትናን ጓደኛ ለማድረግ ስላሰብኩ የአዋጪነት ሥራ እንድትሠሩልኝ ነው፡፡”
እንደውም በዚህ ጉዳይ ላይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ይምከርበት፡፡ አሀ… ማን ከማን ያንሳል! ዘንድሮ የማይቋቋም ኮሚቴ ወይ ኮሚቴ የሚመስል ነገር አለ እንዴ! ነገርዬው… “ሁልህም ተቀላቀል፣” አይነት እስከሆነ እንቀላቀላ!
ማመልከቻ ይገባል፣ ማመልከቻው ለእንትን ኮሚቴ ይመራል፡፡ እንትን ኮሚቴ ደግሞ ለእንትን ኮሚቴ ይመራዋል፡፡
“ጉዳዬ እንዴት ሆነልኝ?”
“የምን ጉዳይ?”
“የእንትኑ ጉዳይ፣ ማመልከቻ አስገብቼ ነበረ እኮ!”
“እሱን ወደ ኮሚቴ መርተነዋል፡፡”
ኮሚቴ አሪፍ ማምለጫ ነች፡፡ ቢሆንም…ቢሆንም ለ‘የባንኳ ዲምፕል’ ስትራቴጂ መፍትሄ ያስገኝልን ከሆነ ‘ኮሚቴውን’ እንሞክረዋ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2426 times