Print this page
Sunday, 24 February 2019 00:00

አውሮፓዊቷ የኢትዮጵያውያን ወዳጅ - አናጐሜዝ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


“አቶ በረከት የታሰሩት በፖለቲካ አመለካከታቸው ቢሆን እጠይቃቸው ነበር”
በአውሮፓ ህብረት ላይ ቅሬታ እንደነበራቸው ተናግረዋል


የ64 ዓመት እድሜ ባለፀጋዋ ፖርቹጋላዊትና የአውሮፓ ፓርላማ አባል፤ አና ጐሜዝ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለየ ቦታ የሚሰጣቸው ትልቅ ዲፕሎማት ናቸው፡፡ በ1997 በኢትዮጵያ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ፣ የህዝብ ድምፅ መዘረፉንና ምርጫው መጭበርበሩን ለዓለም ህብረተሰብ በተደጋጋሚ በማጋለጥ፣ የህዝቡ ድምጽና የትግል አጋር በመሆናቸው ነበር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ገብተው የተቀመጡት፡፡ በተለያየ አጋጣሚም ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድና ዲሞክራሲ እንዲጠናከር ወትውተዋል።
በተለይ በ97ቱ ምርጫ በገዢው ፓርቲ ጥርስ ውስጥ የገቡት ማዳም አና ጐሜዝ፤ ባሉበት ሆነው ኢትዮጵያውያን ከጭቆና አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ድምጽ ሲያሰሙና ሲታገሉ የቆዩ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር በኢትዮጵያ ሆቴል በስፋት ተወያይተዋል፣ እርሳቸው ለምርጫው በመጡ ጊዜ የተወለዱና ለአና ጐሜዝ ክብር ሲባል በስማቸው የተሰየሙ ሶስት ታዳጊ ሴት ልጆችን አግኝተዋል፣ በ97 ምርጫ በደረሰባቸው ጥቃት አካል ጉዳተኛ የሆኑ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ፣ ጧሪ ልጃቸውን የተነጠቁ ሰዎች ጋር ተገናኝተው፣ ሀዘናቸውን ገልፀዋል፡፡ ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ባለፈው እሁድ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ ለእርሳቸው ክብር በኢትዮጵያ ሆቴል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ንግግር አድርገዋል “በ97 እና በ2002 የነበረው ያ ሁሉ ግፍና መከራ አብቅቶ፣ እዚህ ከእናንተ ጋር ተገኝቼ የነፃነት አየር እየተነፈስኩ ነው፡፡ ይህ ለእኔ በጣም አስደሳች ነው፡፡ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መጥተው ልዩነት በመፍጠራቸው ነው፣ ህዝቡም የነፃነት አየር መተንፈስ የጀመረው ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ህዝብ በአሸናፊነት ይወጣዋል” ብለው እንደሚያምኑ አና ጐሜዝ ገልፀዋል፡፡
በ1997 ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁ ጊዜ የብሄር ግጭት ምልክቶች ይታዩ ነበር” ያሉት  ዲፕሎማቷ፤ “ችግሩ ስልጣን ላይ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ህዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲመቻቸው የፈጠሩት ችግር ነው”
“ይህ አይነት አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም አለ፤ የራስን ብሔር ከሌላው ይበልጣል የሚል አስተሳሰብ በጠቅላላ ፀረ - ሰላም ነው” ብለዋል፡፡
“ሊዝብን ሰው ነኝ፣ ፖርቹጋላዊት ነኝ፣ ከዚያም አውሮፓዊት ነኝ፣ ሲቀጥል የአለም ዜጋ ነኝ፡፡ እንደዚህ ነው የማስበው፤ በመሆኑም “America first” በሚለው የትራምፕ አባባል እንኳን አልስማማም” ሲሉ እምነታቸውን አንፀባርቀዋል - ጐሜዝ፡፡
“ሁላችንም አንድ አይነት ብንሆን ሁሉ ነገር አሰልቺ ይሆናል፤ ልዩነት ውበት መሆኑን አምነን ተደጋግፈን መኖር አለብን” ያሉት አውሮፓዊቷ የኢትዮጵያ ወዳጅ፤ እሳቸውም በአገራቸው ለ20 ዓመታት ያህል በአምባገነን መሪ አገዛዝ ሥር መኖራቸውንና ሁሉም በትግል እንደተቀየረ አስታውሰዋል፡፡
“የኔ ብሔር ከሌላው ይበልጣል” የሚል አስቸጋሪና ያልተገባ ሃሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ መግነኑን ያሳሰቡት ዲፕሎማቷ ይህንን በካይ አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ ወዲያ መጣል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ አስመልክተው በሰጡት ምክር፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ መጥቷል፤ ለውጡን በአግባቡና በብልህነት መጠቀም ተገቢ ነው፤  ለውጡ ሥራ መፍጠርና የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት ካልቻለ ግን ሂደቱ የትም አይደርስም፡፡ አክራሪ ሃሳብ ያላቸው የወጣቱን ስሜት በማነሳሳት መጠቀሚያ እንዳያደርጓቸውና ለውጡ እንዳይደናቀፍ፤ ለወጣቱ በቂና አመርቂ የስራ ዕድል በመፍጠር ወጣቱን ከአክራሪዎች መንጠቅ አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በአገሪቱ ላይ ልዩነት ለመፍጠር የሚችሉበት ሰፊ አጋጣሚና ዕድል መፈጠሩን የተናገሩት አና ጎሜዝ፣ የተፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስና ለወጣቱ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ አገሪቱ ወደ ዘላቂ ልማትና ሰላም መሸጋገር ትችላለች ሲሉ መክረዋል፡፡
በፕሮግራሙ የታደሙ ኢትዮጵያውያን፤ ሲልቪየ ፓንክረስት በጣሊያን ወረራ ጊዜ የጣሊያንን ግፍና በኢትዮጵያዊያን ላይ ያደርስ የነበረውን ጥፋት በመፃፍ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማጋለጥ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ባለቤታቸውና ልጃቸውም ለኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ የሚቆረቆሩ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው እርሶም ከሲልቪያ ፓንክረስት ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ድምፅ የሆኑ የታገሉ በታሪክ ለዘላለም የምንዘክረዎት ባለውለታ ነዎት ብለዋቸዋል ማዳም አና ጐሜዝን፡፡ እሳቸውም “እኔ ምንም ባደርግ ከሲልቪያ ፓንክረስት ጋር በፍፁም አልወዳደርም፤ የእሳቸውን ያህል ለኢትዮጵያ ውለታ አድርጌያለሁ ብዬ አላምንም” በማለት የበዛ ትህትና አሳይተዋል፡፡ ቀጥለውም በ1997 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረግ የነበረውን ያልተገባ ነገር አይቼ ዝም ያላልኩት ለኢትዮጵያ ውለታ ለመዋል ሳይሆን ስለማምንበት ነው ያሉ ሲሆን በዛን ጊዜ አውሮፓ ህብረት ላይ ቅሬታ እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ የቅሬታቸው ምንጭም ህብረቱ በዛን ወቅት ይፈጠር የነበረውን ጥፋትና ስህተት እያየ እየተመለከተ ዝምታን መምረጡ በእሳቸው አስተሳሰብ የአውሮፓን እሴቶች መካድ ነው ብለዋል፡፡ ያኔ ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር የልማት ትስስር ፈጥረን እየሰራን ነው ይል የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ ልማት ሳይሆን ቢዝነስ ነበር ሲሉ ወቅሰው አሁን ላይ ዕድሜ ለዶ/ር ዐቢይ ያኔ ከእኛ ትክክል እነሱ ስህተተኞች መሆናቸውን ይገነዘባሉ ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡
ማዳም አና ጎሜዝ የ97 ምርጫን ተከትሎ በተነሳው ቀውስ የማይረሱትን ገጠመኝ ለታዳሚው እንዲህ አወጉ፡፡ “የማልረሳው ገጠመኝ ምን መሰላችሁ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄጄ ነበር ሆስፒታሉን ተጎጂዎች ሞልተውት የጤና ባለሙያዎቹ ህክምና የሚሰጡት እያለቀሱና ስሜታቸን መቆጣጠር እያቃታቸው ነበር “ኧረ እየጨፈጨፉን ነው ማለቃችን ነው” ሲሉኝ ቀጥታ በረከት ስምኦን ቢሮ ሄድኩኝ፡፡ በዛ ቢሮ ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ ሰዓት አሳልፌያለሁ፡፡ ምን እየሰራችሁ ነው ብዙ ሰው እየገደላችሁ ነው የምርጫ ድምፅ ሰርቃችሁ ነው ይሄን ሁሉ ሰው የምታስጨፈጭፉት ስለው “እኛ አይደለንም እናንተ አውሮፓ ህብረቶች ናችሁ ሰው የምታስጨፈጭፉት” አለኝ ይሄ በጣም ያዘንኩበት አጋጣሚ ነው”
ከአንዴም ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ በመጣሁ ጊዜ የሰበሰብኩት ብዙ መረጃ በእጄ ላይ ይገኛል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎች እንዲያግዙኝና ያ መረጃ ወደ መፅሐፍ ወይም ወደ አንድ ሌላ ዶክሜንት እንዲቀየር ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር እየተነጋገርን በመሆኑ የታሪክ ተመራማሪዎች እንድታግዙን እንጠይቃለን” በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበራችሁ ይባላል እውት ነው በሚል ከታዳሚ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ሳቃቸው ነበር የቀደማቸው፡፡
በሰኔ ወር አካባቢ በ1997 መሆኑ ነው የቅንጅት አመራሮች በመንግስት ደህንነቶቸ መዋከብ ሲጀምሪ በየኤምባሲው መጠለልና መደበቅ ጀመሩ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ባለቤታቸው ደግሞ የወቅቱ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ወደነበሩት ቲምክላርክ ቤት ሄደው ተደበቁ፡፡
ይህንን ጉዳይ የመንግስት ደህንነቶች የደርሱበትና እነ አቶ በረከት ስምኦን ለቲም ክላርክ ደውለው እነ ዶ/ር ብርሃኑን በቤትህ ደብቀሃል በአስቸኳይ ከቤትህ የማታስወጣ ከሆነ በ24 ሰዓት ውስጥ ከአገር ትባረራለህ ብለው ቲም ክላርክን አስጠነቀቁ፡፡ ቲም ክላርክ ተጨንቆ ደውለው ያስጠነቀቁትን ደውሎ ከነገረኝ በኋላ አንቺ ያረፍሽው ሆቴል ነው ደፍረው ካንቺ ሆቴል አያስወጧቸውም እባክሽ በመኪና ልላካቸውና አንቺ ሆቴል ውስጥ ይደሩ ብሎ ጠየቀኝ።
እኔ ሸራተን ሆቴል ነበር ያረፍኩት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ሚስቱን የህብረቱ በመኪና ወደኔ ሆቴል አመጣቸው እኔም ክፍሌን ለእነሱ ለቅቄ እነሱን ባመጣው መኪና ወደቲም ክላርክና ባለቤቱ መኖሪያ ጄጄ አደርኩኝ፡፡
በዚህ ድራማ ውስጥ የጌታቸው አሰፋ፣ የበረከት ስምኦንም የመለስም እጅ ነበረበት፡፡ ኬጂቢም ነበረበት፡፡ ከዚያ ጁላይ 25 ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ነበረን፡፡
በረከት ሁለተኛውን ድራማ ሰራ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው መሃል ሰው አስቀምጦ “ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አንቺ ክፍል ውስጥ ምን ይሰራ ነበር አስባለኝ” እውነታው ይሄው ነው ብለው ታዳሚው በሳቅ እንዲያውካካ አድርገዋል፡፡
አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ እርሳቸውን ለማክበር በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ መገኘቱ እንዳስደሰተው ገልፆ፣ “ማዳም አና ጐሜዝ እባክዎ እባክዎ አንድ ውለታ ይዋሉልን አቶ በረከትን ባህርዳር ድረስ ሄደው እኛ ልክ ነበርን አንተ ተሳስተሃል የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ብሎሃል ይቅርታ ጠይቅ ቢሉት ምን ይመስልዎታል” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ዲፕሎማቷ በአጭሩ “አቶ በረከት የታሰሩት በፖለቲካ አቋማቸውና አመለካከታቸው ቢሆን ሄጄ እጠይቃቸው ነበር የታሠሩት ግን በሙስና ስለሆነ ሄጄ መጠየቅ አልችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በእለቱ በ97ቱ ግርግር አባቱን ያጣ እና እናቱንም በሀዘን የተነጠቀ የ14 ዓመት ልጅ ሌሎች አካላዊ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በፕሮግራሙ ተገኝተው አና ጐሜዝን ያመሰገኑም የጉዳት ሰለባ ሆነው ድጋፍ አለማግኘታቸውን የገለፁ ነበሩ። በተለይ እድሜያቸው ከ80 በላይ እንደሆነ የሚገመቱ አንድ እናት ልጄ ጧሪ ቀባሪዬ በጥይት ተመትቶ ወደቀብኝ ቀኑ ጨልሞብኛል ችግር ላይ ወድቄያለሁ በማለት እንባቸውን እያዘሩ ብሶታቸውን ገለፁ፡፡ ማዳም አና ጐሜዝ በበኩላቸው “በጣም አዝናለሁ ለእርሶ ክብር አለኝ ሀዘኑ ትልቅ ቢሆንም ተስፋም አለ፡፡ ወደፊት እንደ እርሶ የሚያለቅሱ እናቶች የማይኖሩባት ኢትዮጵያ ትኖራለች ሀዘንዎን እጋራለሁ” በማለት አጽናንተዋቸዋል፡፡
በእለቱ እሳቸው ኢትዮጵያን ሲረግጡና ከዛም አለፍ ሲል የተወለዱ አና አሸናፊ፣ አና ጐሜዝ አለማየሁ የተባሉ ታዳጊ ሴት ልጆች ከአና ጐሜዝ ጋር የመገናኘት ፎቶ የመነሳት እድል ገጥሟቸዋል። “በስሜ የሚጠሩ ቆንጆ ቆንጆ ልጆች በማግኘቴ ሰርፕራይዝ ሆኛለሁ አድራሻ ተለዋውጠን ግንኙነታችን ይቀጥላል ሲሉ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡
ታዳጊዎቹም ሲያድጉ እንደ አና ጐሜዝ የሰብአዊ ተሟጋችና የመብት ተቆርቋሪ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ ለማዳም አና ጐሜዝ ከሙገሳና ውዳሴ ባለፈ እጅግ በርካታ ስጦታዎች ተበርክተውላቸዋል።



Read 1167 times