Sunday, 24 February 2019 00:00

“ዶላር ማሸሽ” - ፋይዳ ቢስ የወረደ አባባል!

Written by  ዮሃነስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


“ዶላር ማሸሽ” እየተባለ፣ በዩኤን እና በአፍሪካ ህብረት ዘንድ የሚናፈሰው ወሬና ዜና፣ ትርጉሙ ከምር ምን ማለት ይሆን? የሆኑ ሰዎች፣ የኢትዮጵያንና የሌሎች አገራትን ዶላር ዘርፈው ይወስዳሉ ማለት ነው? ከኢትዮጵያ በዓመት፣ 2.6 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጭ አገራት “ሸሸ” ተብሎ ሲነገር፣ “ኧረ፣ ጉድ.... አገር ተወረረ” ያስብላል።
በዩኤን እና በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት የሚራገበውና IFG የተሰኘ ድርጅት የሚያሰራጨው ሪፖርት፣... በአስር ዓመታት ውስጥ፣ ከኢትዮጵያ በድብቅ የወጣው ገንዘብ (illicit financial flow)፣ 26 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገልፃል።
ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት፣... በዓመት በአማካይ 67 ቢሊዮን ዶላር በድብቅ እንደሚወጣ በመጥቀስ፣ የአስር ዓመታት ግምቶች ድምር፣ 670 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ሪፖርቱ ያወሳል።
ይሄ ሁሉ “ጉደኛ መረጃ” በሪፖርት ታውጆ፣ በመግለጫና በዲስኩር ከተናፈሰ በኋላ፣ እጅጉን በመገረም ሪፖርቱን በደንብ ለማንበብ ስትሞክሩ ግን፣ ነገሩ ሁሉ “የነፈሰበት” ይሆንባችኋል። ዩኤን እና የአፍሪካ ሕብረት፣ መልሰው መላልሰው እንደ አዲስ መረጃ፣ አሟሙቀው ቢያስተጋቡት ሪፖርት፣... ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረና መረጃን በማዛባት ላይ ተማምኖ የተዘጋጀ ሪፖርት ነው። “ጉደኛ መረጃ የያዘ ሪፖርት” ሳይሆን፣ “ጉደኛ ሪፖርት” ቢባል ይሻላል። የሪፖርት አዘጋጆቹ ደግሞ፣ “ሃላፊነት የጎደላቸው ቀሽሞች ናቸው” ቢባሉ አይበዛባቸውም።
ከመነሻው፣ የሪፖርቱ አዘገጃጀት ከጅምሩ ዘረክራካ ነው። ርዕስ ሆኖ የተመረጠው “illicit financial flow” የሚለው አገላለፅ፣ በትክክል ምን ማለት እንደሆነ ወይም ምንን እንደሚያመለክት አጥርቶ ማስረዳትም ሆነ መጠኑን ለክቶ ማሳየት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ራሱ ድርጅቱ ይናገራል። እንዲያውም፣ “NO EASY TASK: Quantifying Illicit Financial Flows” በሚል ርዕስ በሰነድ አዘጋጅቶ አቅርቧል - IFG።
በመንግስታዊ መስሪያ ቤቶችና በአለማቀፍ ተቋማት ዘንድ በሕጋዊ መንገድ ያልተመዘገበ የገንዘብ ወጪ እና የገንዘብ ገቢ በሙሉ፣ “illicit financial flow” ተብሎ እንደሚፈረጅ ድርጅቱ ይገልጽና፣... ወደ አገር የሚገባ ሳይሆን ከአገር የሚወጣውን ገንዘብ ብቻ ነው የምንቆጥረው ይላል። ግን ደግሞ፣ ወደ አገር የሚገባ ዶላር፣ አንዳንዴ “illicit financial flow” ተብሎ እንደሚቆጠር በመናገር፣ ነገርን ያወሳስባል - ድርጅቱ። ገለጥ አድርጎ ጉዱን ለማየት፣... እስቲ አንድ ምሳሌ እንጥቀስ።
ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የተሸጠ የቡና፣ የከብት ወይም የጫት ምርት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ለማወቅ ያስቸግራል። በአብዛኛው የድንበር አካባቢ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች “በኮንትሮባንድ” ነው የሚገበያዩት። እናም በመንግስታዊ በዓለማቀፍ ተቋማት አይመዘገብም።
የተወሰነ ያህል ግብይት ደግሞ፣ በባንኮች በኩል ይካሄዳል። ምን ያህል ምርት በምን ያህል ዶላር እንደተሸጠ፣ በኢትዮጵያ በኩል ሊመዘገብ ይችላል ማለት ነው። አምና፣ ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የ230 ሚሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ሽያጭ እንደተከናወነ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል ተመዝግቧል። ነገር ግን፣ IFG ይሄን ሽያጭ እንደ ሕጋዊ ይቆጠረዋል ማለት አይደለም። በሶማሊያ በኩል፣ የ230 ሚሊዮን ዶላር ምርት ከኢትዮጵያ እንደተገዛና እንደገባ እንደተፈፀመ የሚመዘግብ የመንግስት ተቋም ባለመኖሩ ሳይመዘገብ ከቀረ፣ ነገሩ እንደሕገወጥ ይቆጠራል።
 በኢትዮጵያ በኩል፣ 230 ሚሊዮን ዶላር፣ “ሕገወጥ ወይም ድብቅ የገንዘብ ዝውውር” ተካሂዷል ተብሎ ይፈረጃል። በIFG ሪፖርት ውስጥ ጉደኛ መረጃ ተብሎ ይደመራል፤ ይደሰኮርበታል።
ይህም ብቻ አይደለም። በሰው በሰው ከዳያስፖራ የሚመጣ ዶላርም፣ “ድብቅ”፣ “ሕገወጥ” የገንዘብ ዝውውር ነው ተብሎ ይመደባል። ከዳያስፖራ በመጣው ዶላር፣ በድንበር በኩል ከሶማሊያ አልያም ከጂቡቲ፣ ከሱዳን ወይም ከኬንያ እየተገዙ የተለያዩ ቁሳቁሶች ሲመጡም፣ “ዶላር ማሸሽ” ተብሎ ሪፖርት ይቀርብበታል።
ምን ማለት እንደሆኑ አስቡት። በባንክ በኩል ሳይሆን፣ በሰው በሰው ከዳያስፖራ የሚመጣው ዶላር ባለፉት አስር ዓመታት ጨምሯል - ከ400 ሚሊዮን ዶላር ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላርና ከዚያ በላይ። ታዲይ በዓመት ውስጥ፣ በሰው በሰው የሚመጣው ሁለት ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁ ቤት ውስጥ በፎቶ ፍሬም እንደጌጥ የሚንጠለጠል አይደለም። እንደአመጣጡ፣ በባንክ በኩል ሳይሆን በሰው በሰው እየተመነዘረ ለምን ተግባር ይውላል? ሌላ ምን ተግባር አለው?
በድንበር በኩል፣ ሞባይልና ቴሌሊቪዥን የመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን፣ አልባሳትና ሌሎች በርካታ ምርቶችን “በኮንትሮባንድ” ግብይት ለማስመጣት ያገለግላል። ታዲያ፣ ይህንን ይህንን በግልፅ ከመናገር ይልቅ፣ በደፈናው “ዶላር ሸሸ” እያለ በሚጮህ ሪፖርት፣ አገርን ብቻ ሳይሆን አህጉርን መቀወጥ ተገቢ ነው? ሃላፊነት የጎደለው ቀሽምነትስ አይደለም?

“ሕጋዊና ሕገወጥ”
ቡና፣ ወርቅ፣ እንስሳት፣…የሚያመርቱ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ ምርታቸውን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ወደ ውጭ አገራት ይሸጣሉ። በዶላር ወይም በሌላ የውጭ አገር ገንዘብ (ማለትም በውጭ ምንዛሬ) ግብይት ይካሄዳሉ። ነገር ግን፣ በውጭ ምንዛሬ የሚከናወኑ ግብይቶች በሙሉ፣ መንገዳቸው አንድ አይነት አይደለም። በባንክ በኩል እና ያለ ባንክ የሚካሄዱ ግብይቶች፣ ይለያያሉ። “ሕጋዊ” እና “ኮንትሮባንድ” ግብይቶች፣ መንገዳቸው ለየቅል ነዋ። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እናንሳ።
ለምን አምራቾች ከሕጋዊው መንገድ ውጭ በኮንትሮባንድ መገበያየትን  ያዘወትራሉ? መፍትሄውን ለማየት፣ ሁለቱን የግብይት መንገዶች እናነፃፅራቸው።
አንደኛው መንገድ፣ መንግስት የሚቆጣጠረው የባንክ መንገድ ነው። ቡና፣ ወርቅ፣ እንስሳት ወይም ሌላ ምርት ወደ ውጭ የሚሸጡ ኢትዮጵያውያን፣ ሽያጫቸው በዶላር ቢሆንም፣ ዶላሩ እጃቸው ውስጥ አይገባም። መንግስት ደላሩን ይቀበልና፣ ራሱ መንግስት በሚተምነው የምንዛሬ ዋጋ፣ በብር መንዝሮ ይሰጣቸዋል።
ማለትም፣ ያመረታችሁትን ቡና ወይም ወርቅ፣ በ1 ሚሊዮን ዶላር ብትሸጡ መንግስት ዶላሩን ወስዶ፣ ራሱ በሚተምነው ዋጋ መንዝሮ ስንት ብር ይሰጣችኋል? በስንት ተመን እንደሚመነዝርና ስንት አስቀርቶ ስንት እንደሚሰጣችሁ፣ በእርግጠኛነት ለማወቅ ያስቸግራል። የመንግስት ውሳኔና ባህርይ በተለዋወጠ ቁጥር፤ ነገሩ ይለዋወጣል። ድንገት ሃሳቡን ቀይሮ አዲስ ውሳኔም ያመጣል።
በአንድ ቀን ልዩነት፣ የብዙ ሚሊዮን ብር ልዩነት ሊፈጥርባችሁ ወይም ሊፈጥርላችሁ ይችላል - መንግስት።
አምና፣ በ2010 ዓም፣ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ፣ 1 ሚሊዮን ዶላር መንግስት ሲወስድባችሁ፤ 23 ሚሊዮን ብር ነበር የሚሰጣችሁ።
በማግስቱስ? ጥቅምት 2010 ዓ.ም መባቻ ላይስ? መንግስት፣ የምንዛሬ ተመኑን ለመለወጥ መሰነ።
1 ሚሊዮን ዶላር መንግስት ሲወስድባችሁ፣ 27 ሚሊዮን ብር መንዝሮ መስጠት ጀመረ።
ትርጉሙን ሰፋ አድርጎ ማየት ይሻላል። በ2009 ዓ.ም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ የተለያዩ ምርቶችን፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ፣ ወደ ውጭ ሸጠው ከሚያመጡት ዶላር ውስጥ፣ መንግስት 2 ቢሊዮን ዶላር ወስዶ፣ በ22.50 ብር የምንዛሬ ተመን፣ 45 ቢሊዮን ብር ሰጣቸው።
በ2010 ግን፣ የምንዛሬ ተመኑን ለመለወጥ የወሰነው መንግስት፣ 2 ቢሊዮን ዶላር እየወሰደ፣ በ27.50 ብር ምንዛሬ፣ 55 ቢሊዮን ብር ሰጣቸው ማለት ነው።
ልዩነቱ ቀላል አይደለም። 10 ቢሊዮን ብር ነው። ይሄ የመንግስት መንገድ ነው - እነ ዩኤን እና የአፍሪካ ሕብረት የሚደግፉት መንገድም ነው። የተመዘገበ፣ ሕጋዊ ባለኬላ የግብይት መንገድ።
ነገር ግን፣ ሕጋዊው መንገድ ፍትሃዊ መንገድ አልሆነም። በ2009 ዓ.ም፣ መንግስት 10 ቢሊዮን ብር አስቀርቶባችሁ ነበር ማለት ነውና። “በግልጽ ያልታወጀ ቀረጥ” ብለን ልንጠራው እንችላለን።
መንግስት እና ዩኤን፣ ይሄኛውን የቁጥጥርና የኬላ መንገድ የሚወዱት ለምንድነው? ዶላሩ ወደ አምራች ዜጎች እጅ ሳይሆን ወደ መንግስት እጅ እንዲገባ፣ በምንዛሬ ተመን አማካኝነትም ሩብ ያህሉን አጉድሎ መንግስት ከዜጎች እንዲወስድና፣ “አገርን” እና “ህዝብን” በሚጠቅም ጉዳይ ላይ እንዲያውል መደረግ አለበት ባይ ናቸው።
በሚሊዮን የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን፣ ምርታቸውን በዓለም የገበያ እንደማንኛውም ግብይት፣ በገበያ ዋጋ በዶላር ሲሸጡ፣ ዶላሩንም በአገር የገበያ ዋጋ መንዝረው፤ መንግስት ምንም ሳይወስድባቸው፣...  በስራ ያገኙት ምርት፣ ከምርታቸው ያገኙት ውጤት፣ በአጠቃላይ በገዛ ጥረታቸው ያፈሩት ሃብት ሳይጓደል እጃቸው ውስጥ ቢገባ፣ ለሚበጃቸው አላማም ቢያውሉት፣.... ስራቸውን ለማስፋፋትም ሆነ ኑሯቸውን ለማደራጀት፣ ለቁጠባም ሆነ ለአስቤዛ፣ ለቋሚ ንብረትም ሆነ ለእለት ተእለት ወጪ፣ መኪናና ሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመክፈት አልያም፣ መኪናና አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ ከውጭ ለማስመጣት ቢጠቀሙበት፣ የአገር ዶላር እንደሸሸና እንደተዘረፈ ነው የሚቆጠረው።
ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ፣ በገበያ ዋጋ መገበያየትን… እንደ “ኪሳራ” ይቆጥሩታል - እነ IFG፣ እነ ዩኤን እና የአፍሪካ ሕብረት።
ኢትዮጵያውያን በድንበር በኩል፣ 1000 ግራም ወርቅ፣ 100 በግና ከብት፣ 100 ኩንታል ቡና በዶላር ቢሸጡ፣… ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህንን ዶላር በገበያ ዋጋ ውስጥ ገዝተው፣ በድንበር በኩል፣ 100 ሞባይል ስልኮች፣ 100 ካርቶን ዘይት፣ 100 ጀነሪተር ገዝተው ወደ አገር አስገብተው ቢሸጡስ?
ይሄም “ዶላር ማሸሽ” ተብሎ ይፈረጃል።
ዶላሩ በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ ቢገባና… 100 ካርቶን ዘይት ለመግዛት በተንዛዛ ቢሮክራሲ ለወራት ዘግይቶ እጥረት ቢፈጠር ግን፣... ችግር የለም - ሕጋዊ ነው። በዶላሩ አማካኝነት በፀሐይ ሃይል የሚሰራ የትራፊክ መብራት እንዲተከል ተደርጐ ስድስት ወር ሳይሞላው ተበላሽቶ ቢባክን፣... መቶ በባትሪ የሚሰራ ብስክሌቶችን መንግስት ገዝቶ ሦስት ወር ሳይሞላቸው ከአገልግሎት ውጪ ቢሆኑስ? ይሄም “ብክነት” አይደለም። ዶላር “ማሸሽ” ተብሎም አይፈረጅም - “ልማት” ነው። “ሕጋዊ የገንዘብ ዝውውር” ተብሎ ይወደሳል። በመንግስት ቁጥጥር ስር እስከተላለፈ ድረስ፣ “ችግር የለም”፣ “ለህዝብ ጥቅም”፣ “ለአገር ልማት” የዋለ ዶላር ተብሎ ይመዘገባል።
ምርታችሁን ሸጣችሁ ወይም ከዳያስፖራ ተልኮላችሁ ያገኛችሁትን ዶላር፣ መንግስት ሳይነካባችሁ በገበያ ዋጋ እየተመነዘረ፣ ከውጭ አገር ጠቃሚና ተፈላጊ ምርትን ለማስመጣት ብትጠቀሙበት፣ የገዛችሁት ዘይት ወይም የህፃናት ወተት፣ ሞባይልም ሆነ ላፕቶፕ፣ ሳይዘገይ በጊዜ ቢደርስ፣ ሳይበላሽ ቢያገለግል ግን፣.... “ዶላር ማሸሽ” ተብሎ ይመዘገባል።





Read 1311 times