Wednesday, 27 February 2019 13:04

ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ሴቶችን ለልብ ህመም ሊያጋልጥ ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ በዕድሜ የገፉ ሴቶችን ለልብ ህመም ሊያጋልጥ እንደሚችል በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ የተሰራ አንድ ጥናት ማመልከቱን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ከ63 እስከ 97 አመት የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 5 ሺህ ሴቶች ላይ የሰሩትን ጥናት መሰረት አድርገው ባወጡት ሪፖርት፤ ለተራዘመ ጊዜ ቁጭ የሚሉ ሴቶች ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአንድ ቀን ውስጥ በመቀመጥ የሚያሳልፉትን ጊዜ በአንድ ሰዓት መቀነስ የቻሉ ሴቶች፣ ለልብ ህመም የመጋለጥ ዕድላቸውን በ26 በመቶ መቀነስ እንደሚችሉም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ለረጅም ጊዜ ያለምንም እረፍት የሚቀመጡ ሴቶች፣ መየመሃሉ ከመቀመጫቸው እየተነሱ ለተመሳሳይ ጊዜ ከሚቀመጡ ሴቶች ጋር ሲነጻጸር ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው በ52 በመቶ ከፍ እንደሚል ማረጋገጣቸውንም ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ለተራዘመ ጊዜ መቀመጥ የደም ዝውውርን እንደሚቀንስና በደም ስሮች ግድግዳዎች ላይ የሚገኙ  ህዋሶችን እንደሚጎዳ የጠቆሙት አጥኚዎቹ፣ በአንድ ቀን ውስጥ ለ11 ሰኣታት ያህል የሚቀመጡ ሴቶች፣ የስኳር በሽታንና የደም ግፊትን ጨምሮ ለተለያዩ ህመሞች የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

Read 5894 times