Sunday, 03 March 2019 00:00

በኢህአዴግ የሚፈጠረው ውህድ ፓርቲ በተቃዋሚዎች ዕይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


በአንድ ውህድ ፓርቲ መሰባሰቡ የዘር ክፍፍልን አዳክሞ ኢትዮጵያዊነትን ያለመልማል - ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
- የአገሪቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የፓርቲ አደረጃጀት ሳይሆን ሀቀኛ ፓርቲ መኖሩ ነው - ፕ/ር መረራ ጉዲና

ኢህዴግ አንድ ሁሉን አቀፍ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት ማቀዱ የሃገሪቱን የፓርቲ ፖለቲካ ወደፊት የሚያራምድ፣ የሃሳብ ፖለቲካ እንዲጎለብት የሚያደርግ ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡
በዘር ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር ሆኖ ላለፉት 27 ዓመታት ሃገሪቱን የመራው ኢህአዴግ በሚከተለው የፓርቲ አደረጃጀት ምክንያት የሃገሪቱ የፖለቲካ መንገድ ጎጠኝነትና የባለተራነት፣ የገዥ እና የተገዥነት አካሄድ ውስጥ መቆየቱን የጠቆሙት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በሩ ክፍት የሆነ ፓርቲ መመስረቱ የአግላይ አካሄድን ያስቀራል ብለዋል።
ኢህአዴግ አንድ ሃገር አቀፍ ሁሉን ያካተተ ፓርቲ ለመመስረት መንቀሳቀሱ ተገቢ አቅጣጫ ነው የሚሉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እስካሁንም ኢህአዴግ የብሄር ጉያ ውስጥ ተወሽቆ አርአያነት ያለው ተግባር ሳያሳይ ለ27 ዓመት መቆየቱ አግባብ አልነበረም” ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ አንድ መሆን ሳይችል ሃገሪቱን ለሚከተለው የፖለቲካ ድርጅት አካሄድ የተነሳ የተከፋፈለ ነው የሚል እምነት ያላቸው ፕ/ር በየነ በተለይ አዲሱ ውህድ ፓርቲ ግለሰቦችን እንደዜጋ የሚያሳትፍ ከሆነ ስርአተ መንግስቱንም የማቃናት አቅም ሊኖረው ይችላል የሚል ግምት አላቸው፡፡
ኢህአዴግ ሁሉን አቀፍ ፓርቲ መመስረቱ ተቃዋሚዎችን ያዳክማል የሚል ግምት እንደሌላቸው የሚገልፁ ፕ/ር በየነ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያሳድረው ምንም ተፅዕኖ የለም፤ ሌላውም ራሱን እንዲያጠናክር የበለጠ ያበረታታዋል ይላሉ፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት በጎሳ ተነሳሽነት እና ስልጣንን በብሄር ኮታ በሚያደላድል ፓርቲ ሃገሪቱ መመራቷ ብዙ የፖለቲካ ዋጋ አስከፍሏታል የሚሉት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በበኩላቸው በኢህዴግ ስልተ ፖለቲካ የተነሳ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመኖር ዋስትና ያጡበት ሃገር በከፋፍለህ ግዛ ሴራ የተሸበበችበት ጊዜ ነበር ይላሉ፡፡
አሁን በለውጥ ሃይሉ ቀማሪነት አዲስ ሁሉን አቀፍ ውህድ ፓርቲ ወደ መመስረት መገባቱ የከፋፍለህ ግዛ የኢህአዴግን የቀደመ አካሄድ የማስቀረት አቅም ይኖረዋል የሚሉት ዶ/ር በዛብህ የኢትዮያዊነትና የአንድነት ጉዳይም እየዳበረ እንዲሄድ ትልቅ መሰረት ሊጥል ይችላል የሚል ምልከታ አላቸው፡፡
በአንድ ውህድ ፖርቲ መሰባሰቡ ዘር ክፍፍልን አዳክሞ ኢትዮጵያዊነትን ያበለፅጋል ያሉት ዶ/ር በዛህብ ይህ አካሄድ ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም አርአያነት የሚኖረው ነው ብለዋል፡፡
በአሁን ወቅት ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ዋነኛ የሃገሪቱ ፓርቲዎች ወደ ውህደት እና ግንባር ስብስብ መሄዳቸው እውነተኛ የጠሩ፣ የነጠሩ አማራጭ ሃሳቦችን ለህዝብ ለማቅረብ ጠቃሚ ነው የሚል ምልከታ ያላቸው የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ በበኩላቸው በተለይ ኢህአዴግ ወደ ውህደት ማምራቱ የዘር ፖለቲካን ለመሻገር በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ በዘር ከመቧደን ወጥቶ ወደ ሃሳብ ብቻ አራማጅ ፓርቲነት መቀየሩ የሃገሪቱን የ27 ዓመት የፖለቲካ ድርጅቶች አጠቃላይ አሰላለፍ የሚቀይር ነው የሚል እምነት ያላቸው አቶ የሸዋስ አዲስ የሚፈጠረው ፓርቲ ምናልባትም ያልታሰቡ ሽግሽጎችና ሊፈጥር ይችላል ይላሉ፡፡
ከተቃዋሚ ወደ ኢህአዴግ ከኢህአዴግ ወደ ተቃዋሚ የሚሸጋሸጉና የሚሸጋገሩ ኃይሎች እንደሚኖሩ የሚያስረዱት አቶ የሸዋስ በዚህ መንገድ እስከቀጣይ ምርጫ ሶስት ወይም አራት ጠንካራ ሁሉን አቀፍ ኃይሎች መፈጠራቸው አይቀርም ባይ ናቸው፡፡ ከላይ ከተሰጡት አስተያየቶች የተለየ አቋም ያራመዱት ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የሃገሪቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የአንድ ውህድ ጠንካራ ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የብሔራዊ መግባባት የሃቀኛ ፌደራሊዝም እና ሃቀኛ ዲሞክራሲ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 50 ዓመታት አስቸጋሪ ሆኖ የቆየው የፖለቲካ ድርጅቶች የቅርፅና አደረጃጀት ጉዳይ አይደለም ያሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ደርግ ኢሰፓን መስርቶ የፈየደው ነገር የለም ሲሉም የውህድ ፓርቲ ጉዳይ ብዙም ቦታ ባይሰጠው እንደሚመርጡ ያስረዳሉ፡፡
ለሃገሪቱ የሚፈይደው ዋናው የፓርቲ አደረጃጀት ቅርፅ ሳይሆን ሃቀኛ ዲሞክራሲን ፌደራሊሊምንና ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጣ ሃሳብ ያለው ፓርቲ መኖር ነው የሚል ፅኑ አቋም እንዳላቸው የሚያስረዱት ፕ/ር መረራ ኢህአዴግ አንድ ውህድ ፓርቲ ሆነ የ11 ፓርቲዎች ግንባር ሆነ ዋናው ሃቀኛ መሆኑ ነው ይላሉ፡፡
የሃገሪቱ ችግር የፓርቲ ቅርፅ ሳይሆን ምን ዓይነት የፖለቲካ ስርአት እንፍጠር የሚለው ጉዳይ መሆኑንም ፕ/ር መረራ ያሰምሩበታል፡፡
ኢህአዴግ ሊፈጥር ያቀደው ሁሉን አቀፍ ውህድ ፓርቲ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ተቃዋሚዎች ካሻቸው የሚሳተፉበት መሆኑን የገለፀው ኢህአዴግ የሚመሰርተው ፓርቲ የኢህአዴግ መሰረታዊ ባህሪ የሆነውን የብሔር፣ ቋንቋ እና ማንነት የማይስት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡


Read 5823 times