Sunday, 03 March 2019 00:00

በተሻሻለው የፀረ ሽብር ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተካሄደ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)


- “በመንግስት ላ ይ ተ ፅዕኖ ለማሳደር የ ሚደረግ አ ድማ አ ሸባሪነት አ ይደለም…”
- “የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ፤ ተጠርጣሪዎችን መያዝ አይችልም”


ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ለማሻሻልና ለማስተካከል የሚችል አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀረበ፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ ምሁራን የህግ ባለሙያዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እየመከሩበት ነው፡፡
ከትናንት በስቲያ ውይይት የተደረገበት ይኸው ረቂቅ አዋጅ፣ የቀድሞው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ይዞት የነበረውንና 38 አንቀፆችን ያካተተውን ህግ በማሻሻልና አንዳንድ ተጨማሪ አንቀፆችን በመጨመር፤ አዋጁን 54 አንቀፆች ያሉት እንዲሆን አድርጓል፡፡
የቀድሞው አዋጅ እንደሚያመለክተው፤ የሽብር ድርጊት ማለት በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ፣ በተፈጥሮ ሀብቶችና በአገር ቅርስ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ሲሆን ይህም ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ሊደርስ በሚችል ቅጣት ያስቀጣል፡፡ በሽብር ድርጊት ውስጥ በመተባበር፣ ማቀድ፣ ማሴርና ወንጀሉ ሲፈፀም ዝም ብሎ ማየት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ቅጣት ያስቀጣል፡፡
ይህንን ህግ አዲሱ ረቅቅ አዋጅ ያሻሻለው ሲሆን በዚሁ መሰረትም የሽብርተኝነት ወንጀል ሲፈፅም የተገኘ ሰው ከ10 ዓመት እስከ 15 ዓመት ሊደርስ በሚችል የእስራት ቅጣት ይቀጣል ይላል፡፡ የሽብር ወንጀሉ የተፈፀመው ህጋዊ ሰውነት ባለው ተቋምና በመንግስት ከሆነና ድርጊቱ የተፈፀመው ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ ከሆነ ቅጣቱ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክና እስከ ሞት ሊደርስ የሚችል ቅጣት እንደሆነ ረቂቅ አዋጁ ላይ ተመልክቷል፡፡
በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚደረግ አድማ እንደሽብር ድርጊት እንደማይቆጠርና በዚህ ሳቢያም የሚጣል ምንም አይነት ቅጣት እንደማይኖር ረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
የሽብር ድርጊትን ለመፈፀም መዛት ማስፈራራት፣ ማቀድ፣ ማሴርና ሽብርተኝነትን ማበረታታት ቀደም ባለው የፀረ ሽብር አዋጁ ላይ እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፤ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከአራት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ በሚችል የእስር ቅጣት የሚያስቀጣ እንዲሆን ተደርጎ ተሻሽሏል፡፡
በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተገለፀው ድርጅቶችን ወይም ተቋማትን አሸባሪ ብሎ ለመሰየም የሚያስችል ሂደት በግልፅ የተቀመጠ ሲሆን በዚህ ሂደት መሰረትም፤ ድርጅቱ የፈፀማቸው የሽብር ወንጀል ድርጊቶች ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቦ፤ ምርመራ ተደርጎበት ሁኔታው ከተረጋገጠ በኋላ ጉዳዩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብና የሽብር ወንጀል ፈፅሟል የተባለው ድርጅት የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል ዕድል ይሰጠዋል፡፡
ድርጅቱ ቀርቦ መከላከልና የቀረበበትን ክስ ውድቅ ማድረግ ካልቻለ አሸባሪ ተብሎ ይሰየማል - ይላል ረቂቅ አዋጁ፡፡
በአዲሱ የፀረ ሽብር ረቂቅ አዋጅ ላይ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ሰዎችንና ተቋማትን የመመርመር ሂደት ነው፡፡
በዚህ መሰረትም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ፣ የሽብርተኝነት ወንጀልን መረጃ ለማግኘት ሲባል የተጠርጣሪዎችን የስልክ፣ የፋክስ፣ የኢሜይልና ሌሎች የኢንተርኔት ግንኙነቶችን ጠልፎ መስማት እንዲሁም ሰራተኞቹ ሰርገው እንዲገቡ በማድረግ ምርመራ ማድረግ ይችላል የሚለውን የቀድሞ ህግ ለማሻሻል የቀረበው አንቀፅ፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ያለፍርድ ቤት ፈቃድ ይህንን መፈፀም እንደማይችልና ፍርድ ቤቱ ለተወሰኑ የጊዜ ገደቦች ያህል የምርመራ ፍቃድ እንዲሰጠው ይደነግጋል፡፡
በአዲሱ የፀረ ሽብር ረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በፀረ ሽብር ህጉ ውስጥ ያለውን ኃላፊነት የሚያስቀር አንቀፅም ተካትቷል፡፡ በቀድሞው የፀረ ሽብር አዋጁ ላይ እንደተመለከተው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደሚችል የሚደነግግ ሲሆን አዲሱ የፀረ ሽብር ረቂቅ አዋጅ ግን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደማይችልና የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች የሚያዙት በፖሊሲና በሌሎች የፀጥታ አካላት ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ምሁራን፣ የህግ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በስፋት የተወያዩበት ሲሆን ረቂቁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ተገጿል፡፡



Read 5540 times