Print this page
Sunday, 03 March 2019 00:00

ሦስቱ ተስፋዎች…ሦስት ፈተናዎች ሆነዋል!!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)


• ከተሞች፣ የእድገት ተስፋዎች ናቸው፡፡
• ኢንዱስትሪ አልባ ሲሆኑ ግን፣ ተቀጣጣይ ጭድና ማገዶ ናቸው (ለአመፅና ለትርምሰ የተመቹ)፡፡
• የፖለቲካ ምርጫ ጥሩ ተስፋ ሊሆን ይቻላል
• ህግ አክባሪነት የጎደለውና በዘር መቧደን የገነነበት ምርጫ ግን፣ እልፍ አእላፍ እሳቶችን ለመለኮስ ሰበብ ይሆናል፡፡
• የመገናኛ አውታሮች? ኢንተርኔትና እነፌስቡክ “አምኘሊፋየር” ናቸው። ያጉኙትን ነገር ያሰተጋባሉ፣ ያራግባሉ።
የተለኮሰ እሳት፣ ጭድና ማገዶ ሲያገኙ እያራገቡ ያቀጣጥሉታል፡፡


የከተሞች መስፋፋት፣ እና የተመራቂዎች ብዛት፣  ለወትሮው የእድገት ምልክቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የእድገት ተስፋዎችም ናቸው፡፡
አሁን ግን ፈተና ሆነዋል፡፡ ፍራንሲስ ፋክያማ እንደሚሉት፣ ኢንዱስትሪ አልባ ከተሞች ከተበራከቱና ከተስፋፍ የዜጎች ኑሮንና የአገር ህልውን ያናጋሉ፡፡ ሸቀጥ የሚፈበርኩ ኢንዱስትሪዎች ካላደጉ፣ ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ ፋብሪካዎች ካልተበራከቱ፣ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ በሸቀጥ ንግድና ችርቻሮ ላይ ብቻ ይራኮታል። ይባስ ብሎም የመንግስት ሰራተኛ እየበዛና፣ ቢሮክራሲው እየተንዛዛ፣ ከፋይዳቢስነትም አልፎ የምርታማ ዜጐችን ስራ የሚያደናቅፍ፣ በዜጐች ስራ የተገናኘችውንም ምርት የሚሻማ ከባድ ሸክም እየሆነ ይሄዳል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የመንግስት ተደጓሚም ይበራከታል፡፡ በተለይ በድሃ አገራት ውስጥ፣   በኢንዱስትሪና በፋብሪካ እጦት ሳቢያ፤ የወጣቶች ስራ አጥነትና የመንግስት ድጎማ ሲታከልበት፣ የአገሬው ኢኮኖሚ እየተመናመነ ያሄዳል፡፡  በሌላ አነጋገር፤  ከፋብሪካ ጋር የማይተዋወቁ  ኢንዱስትሪ አልባ ከተሞች እና  ስራአጥ ወጣት ተመራቂዎች  እየተበራከቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ አገሬው አደጋ ይጠብቀዋል፡፡ ለወትሮ፣ የእድገት ተስፋን የሚያበስሩ ተናፋቂ  ድምፆችና ደማቅ የብርሃን ጭላንጭሎች ቢሆኑም፣ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራትግን አስፈሪ የአደጋ ድምፆች ናቸው - ኢንዱስትሪ አልባ ከተሞችና ስራአጥ ወጣት ተመራቂዎች፡፡ የማስጠንቀቂያና የማንቂያ ደውሎች ናቸው! “የታለ ኢንዱስትሪው?” እያሉ የሚያጥጡ አጣዳፊ ቀይ የአደጋ መብራቶች ናቸው፡፡
“ፋብሪካዎችና ምርታማ የስራ እድሎች የታሉ?” እያሉ የሚጮሁ የድረሱልኝ ጥሪዎች ናቸው፡፡
ከተማ ያለ ኢንዱስትሪ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ተመራቂዎች ያለ ፋብሪካ፤ጨርሶ አያዛልቅም፡፡ በሚሊዮኖች ለሚቆጠር የከተማ ነዋሪና ለወጣት ተመራቂ፣ “ፈጣን የኢንዱስትሪ እድገትና እልፍ አእላፍ ፋብሪካዎች የታሉ? … አስተማማኝ መኖሪያ ቤትና የስራ ቦታስ የታለ?”… መሬት የመንግስት ሆኖ፣ ዘረኝነትም ገንኖ፣ በመንጋ “ይሄ ቦታ የኛ ነው”፣…. “ያኛው መሬት የኛ ነው” የሚል የብሽሽቅና የመጠፋፋት  ዘመቻ  በዝቶ፣  እንዴት መኖሪያ ቤትንና የስራ ቦታን በስርዓት መገንባት ይቻላል? እንዴትስ ቀልጣፋ የከተማ   ትራንስፖርት፣ ከቶ የማይቋረጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ሃይል ሊኖር ይችላል?  ያኛውም፣ ያኛውም የመንግስት ሆኖ እንዴት አይቋረጥ?
ኧረ ችግሩ ከዚያም በላይ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሮች፣ “ራዕይና እቅድ ብለው” የያዙት ነገር ያስፈራል፡፡ ጨርሶ፣ የአደጋ ደወሉን የሰሙ አይመስሉም፣ ለመስማት አለመፈለግም ነው እንጂ፡፡
“ከፋብሪካ የፀዳ ከተማ መፍጠር” ነው ራዕያቸው፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የቀውስ እና የትርምስ እጣ ፊንታ የተቆረጠላቸው ከተሞች እየበዙ የሚሄዱበት አገር ሆነናል፡፡
“ሁሉም ነገር ፀረ ኢንዱስትሪና ፀረ ፋብሪካ ሆኖ፤ ነገር ሁሉ ጠመመብን” ያስብላል፡፡ ከተማ ጋር አብሮ ማደግ የሚገባው ኢንዱስትሪ እና ፋብሪካ፣… ስነስርዓት የተላበሰ አኗኗርን ይጠይቃል። ህግና ስርዓት የሰፈነበት፣ የንብረት ባለቤትነት በአስተማማኝ የተከበረበት የነፃ ገበያ ስርዓትን ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡
በሁሉም አቅጣጫ ሲታይ፣ “ኢንዱስትሪ አልባ ከተሞች፣ የጭድ እና የማገዶ መናኸሪያ ናቸው” ማለት ይቻላል፡፡ የአገራችን ከተሞች፣ ተቀጣጣይ የተባለ ነገር ሁሉ እየሰበሰቡ የሚያከማቹ  አስፈሪ የአደጋ ቦታዎች እንዲሆኑ አድርገናቸዋል፡፡
እሳት የሚለኮስበት  ወይም ድንገተኛ መብረቅ የሚወድቅበት አጋጣሚን ነው የሚጠብቁት፡፡
ደግሞም እንደሰማነው፣ ድንጋይና ድንጋይ የሚፋጭበት አጋጣሚ የበዛበት አገር ሆነናል።   ከሁለት ሰዎች አምባጓሮ ላይ እሳት እየጫረ፣ በዘረኝነት እየቃኘ፣ አገሬውን እንደጭድ ለማቀጣጠል፣ ነዋሪውን እንደማገዶ ለማንደድ የሚዘምት እሳት ለኳሽ ደግሞ በርከቷል - በዘር እየተቧነ ወይም በሃይማኖት ተከታይነት እንደ መንጋ እየተንጋጋ ለመዝመት ይቀስቀሳል፡፡ በዚህ መሃል የፖርቲካ ምርጫ ይመጣል፡፡
የፖለቲካ ምርጫ - ከነተስፋው እና ከነአደጋው!!
ድንጋይና ድንጋይ በየቦታው የሚፋጭበት ትልቁ አጋጣሚ  ከፊታችን ነው -የምርጫ ጊዜ፡፡
አዎ፣ የፖለቲካ ምርጫ የሚካሄድባቸው አገራት፤ ለወትሮ የሰላምና የመከባበር ባለፀጐች ነበሩ፡፡
ነፃነት ወዳድነትና ሕግ አክባሪነት የበዛላቸው፤ ህግና ስርዓት የበረከተላቸው ጭምር ነበሩ፡፡ አዎ፤ የፖለቲካ ምርጫ፣ የስልጣኔ ውጤት  ብቻ ሳይሆን የስልጣኔ ተስፋም ነበር፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት ግን፣ አስፈሪ የአደጋ መፈልፈያ አጋጣሚ ሆኖባቸዋል፡፡ በሚፋጩ ድንጋዮች  የሚለኮስ እሳት እንደ አሸዋ የሚበዛበት ወቅት ነው፣ የምርጫ ወቅት፡፡ የተለኮሰው እሳት ይዛመታል፡፡ ኢንዱስትሪ አልባ ከተሞች ውስጥ፣ ተቀጣጣይ ጭድ እና ማገዶ ሞልቷልና፡፡
ነፃነት ወዳድነትና ሕግ አክባሪነት በሌለበት አገር የሚካሄድ ስልጣኔ አልባ የፖለቲካ ምርጫ፣ ነፃነትንና ህግን ያላጣመረ የምርጫ ድግስና ታዳሚ፣ ችግር ይጠብቃቸዋል፡፡ በአፍሪካ አገራት በተደጋጋሚ እንደምናየው፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ ህግ አስከባሪ ሃላፊዎችን ለመምረጥ የሚካሄድ፣ የጥበቃ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚደረግ ምርጫ አይደለም - የአፍሪካ አገራት ምርጫ፡፡ አሰፈሪነታቸውም እዚህ ላይ ነው። በእርግጥም፣ ህግ አከከባራን ለመምረጥ ሳይሆን እንዳሻው ህግን የሚሽር ገዢ ለመሾም የፖለቲካ ምርጫ የሚያካሄድ አገር መከራ ይበዛበታል፡፡ የሰው ህይወትና ንብረት ላይ እንዳሰኘው ማዘዝ የሚችል ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ለመሾም ድምጽ የሚሰጥ መራጭ የበረከተበት አገር፣ አደጋ ይገጥመዋል፡፡  
የጥበቃ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚካሄድ ምርጫ እና፤ ቤት ንብረታችሁ ላይ እንዳሻው የሚወስን አዛዥ ናዛዥ ለመሾም ወራሽ ለመሰየም የሚካሄድ ምርጫ፣ ልዩነታቸው ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ አስቡት፡፡
 የጥበቃ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚደረግ ምርጫ ብዙም አያጣላም፡፡
አዛዥ፣ ናዛዥ እና ወራሽ ለመሾሞ የሚካሄድ ምርጫ ግን እስከማጋደል ይደርሳል፡፡
ምን ይሄ ብቻ! በአንድ በኩል፣ እያንዳንዱ መራጭ በየግሉ ድምጽ የሚሰጥበት የፓለቲካ ምርጫ ማካሄድ፣ በሌላ በኩል  በዘር እንደመንጋ የመቧደን ፖለቲካ መያዝ፣… አብረው ሊሄዱ አይችሉም፡፡ በአንድ በኩል፣ አሁን ባለው ህግና ስርዓት አማካኝነት  ዳኝነትን እቀበላለሁ ብሎ የፖለቲካ ምርጫ ውስጥ መግባት፤ በሌላ በኩል፤ “ምርጫው ተጭበረበረ፤ ዳኝነቱም ከንቱ ነው” ብሎ ለመቀስቀስ መዘጋጀትስ እንዴት አብረው ይሄዳሉ?”
እንግዲህ መልከቱ፡፡
ጭድና ማገዶ ተሟልቷል፡፡ ኢንዱስትሪ አልባ ከተሞች ናቸው የአገራችን ከተሞች፡፡
በየቦታው ድንጋይ እና ድንጋይ እየተጋጩ፣ እልፍአ እላፍ እሳቶችን ለመጫር፣ ሺ አጋጣሚና ሺ መድረኮችም ይፈጠራሉ፡፡ ምክንያቱም፣ የህግ ዳኝነት የማይከበርበት የፖለቲካ ምርጫ ከፊታችን አለ፡፡  የምርጫ ድምጽ በግል  መስጠት  እና በዘር የሚያቧድን የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ሲዋሃዱ፣ ለአገር ጤና አይበጁምና፡፡ በፍጭት እሳት የመጫር ሰበቦች  ያበራከታል፡፡
ምን ቀረ?
በየቦታው የሚለኮሰውን እሳት የሚያቀጣጥል ማራገቢያ?
ማራገቢያ፣ እንደዛሬ በዝቶ፣ እንደዛሬ ተትረፍርፎ አያውቅም፡፡ የሚያራግብም ሞልቷል፡፡ ከጥንታዊ ማራገቢያ ዘዴዎች፣ ከሽኩሽኩታና ከኡኡታ፣ ከጨጫታና ከሆታ  በተጨማሪ፣ የጋዜጣና የመጽሐፍ ህትመት፣ እንዲሁም ከነባሮቹ የቲቪና የሬዲዮ ማሰራጫ አንቴናዎች በተጨማሪ፤ ዛሬ፣ ሰማይ ምድሩ ሁሉ አንቴና በአንቴና ሆኗል፡፡
የሳተላይት ቴሌቪዥን ማሰራጫና መቀበያ ዲሽ፣ ተበራክቷል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን፤ ኮምፒዩተርና ሞባይል፣ ኢንተርኔትና እነፌስቡክ ተደማምረው፣ ነገሩን ሁሉ ቀያይረውታል፡፡ በሚሊዮን ካሜራና በሚሊዮን ማይክራፎን ምስልና ድምፅ እየቀረፀ፣ በሚሊዮን ኪቦርድ እና በሚሊዮን ተችስክሪን እየፃፈ ቀን ከሌት ማሰራጨት እና መቀበል የሚችል ብዙ ሚሊዮን አንቴና የተትረፈረፈበት አገር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አገር፡፡
“የመናገርና የመስማት ነፃነት” ለብቻው ትልቅ የስልጣኔ ግስጋሴ ቢሆን ኖሮ፣ ከዛሬ ጋር የሚስተካከል “ነፃነት” በየትኛውም ዘመን ታይቶ አይታወቅም። እንዲያውም የነፃነት ልኬት የሚታወቀው፣ በተናጋሪና በአንቴና ብዛት ቢሆን ኖሮ፤ ዛሬ ዛሬ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ውስጥ ያለው “ነፃነት”፣ ከ15 ዓመታት በፊት በእነ አሜሪካ እና በነእንግሊዝ እንኳ ያልነበረ እጅጉን “የሰፋ ነፃነት” እንደሆነ በተመሰከረለት ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡
ከሚሊዮኖቹ አንቴናያች  ውስጥ፣ የተወሰኑት ብቻ ናቸው በቀውጢ ሰዓት ገዝፈው የሚታዩት- እሳት የሚያራግቡት አንቴናዎች ናቸው አገር ምድሩን ለማቀጣጠል ድምፃቸው ሰልቶ ጮሆ የሚስተጋባው።
እውነታው ይሄ ከሆነ፣ ከወዲሁ መጠንቀቅ፣ አደጋውን ለመቀነስና፣ ለዘላቄታውም ለማስተካከል መጣር አለብን፡፡  











Read 1480 times