Sunday, 03 March 2019 00:00

መወለድ ኩራት? ኩራት አይደለም፤ አይሆንም!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)


ከመወለድ በኋላ፣ በስራ የሚቀዳጁት ስኬትና የግል ብቃት ነው ኩራት!

“የሉሲ ጉዞ”፣ ሸክሙ ትልቅ ነው፤ የሰላምና የፍቅር መልእክትን ሰንቋል፡፡ ቢጨንቀን ነው። የጨነቀው ብዙ ነገር ያደርጋል፡፡ ሉሲን ከሞት ለማስነሳት ይሞክራል፡፡ በእውን ዮሚሊዩን ዓመታትን ተሻግራ፣ “ሕይወት አዳሽ” እንድትሆንልን፤ ቢያንስ ቢያንስ የማገገሚያ ተስፋ እንድትሰጠን፣ አልያም ጊዜያዊ የህመም ማስታገሻ ፋታ እንድታስገኝልን ላይ ታች የምንሯሯጠው፣ ቢጨንቀን ነው፡፡ አገር ምድሩ፣ በጭፍን አስተሳሰብ ሲሳከር፣ ሰው ቢጨነቅ አይበ ዛበትም፡፡ በተብረከረከ ኢኮኖሚና በተናጋ ኑሮ ላይ፣ ኢንቨስትመንትን የማስተጓጎልና የማውደድ፣ ትራንስፓርትን የመዝጋት የመዝረፍ አጥፊ ዘመቻ ሲቀጣጣል…… በዘር እንድንቧደን የሚቀሰቅሱ ክፉዎች እየገነኑ “በነፃነት ”በአገሬውን ሲያምሱ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጦር ሰራዊት ካልተሰማራ በቀር መረጋጋት የከበደው አገር  ሲሆንብን፣ ያሳስባል፡፡
በህልውና ለመቆየትና ከፍፁም ጥፋት ለመዳን የሚረዳ ከሆነ፣ ሉሲን ከሞት ለመመለስ  እስከ መመኘት ያደርሳል፡፡ በአንዳች ተዓምር የአገር አንድነት እንዲያገግም ብቻ ሳይሆን፣ ሰላምና ፍቅርም  እንዲበርከትልን የምታግዘን ከሆነ፣ ሉሊን ከሞት እንድትመለስልን ብንመኝ  ይፈረድብናል?
በጭፍን እምነት መናቆርን፣ በጭፍን ስሜት መራኮትን፣ በዘረኝነት መጠፋፋትን እየሰበኩ እሳት የሚጭሩና የሚያራግቡ  ምግባረ ብልሹ ጋጠወጦችና የለየላቸው የክፋት አበጋዞች የገነኑቦት ዘመን ላይ ነን፡፡ በይሁንታ ወይም በዝምታ ከመመልከት ይልቅ፣ ሳይረፍድብን  አስቀድመን መከላከል ነበር የሚሻለን፡፡ ነገር ግን፣ አስቀድሞ መጠንቀቅና ጥፋትን መከላከል፣  እሳቱን ቶሎ ማብረድ፣ የተሳሳተውን ማስተካከልና የተጣመመውን መንገድ በጊዜ ማቃናት እየተቻለ፣ በተቃራኒው የጥፋት ጅምር ተለኩሶ ከዳር ዳር እስኪዳረስ በይሁንታ ወይም በዝምታ መጠበቅ የተላመደ አገር ሆነ፡፡
ጥቂቶቹ የክፋት አወራዎችና ጭፍራዎች፣ በየቦታው እየገነኑ፣ አሳፋሪ አስፀያፊያና ዘግናኝ የጥፋት ዘመቻ ለኩሰውና አራግበው፣ ወደ ውድመትና ወደ እልቂት ሲያወርዱን ነው የምንደነግጠው፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው?
አገር ቁልቁል ሲወርድ፣ በአንድ ትንፋሽ ተንሸራትቶ፣ በአንድ ዥውታ ተወርውሮ አይከሰከስም፡፡ ከዓመት ዓመት፣ ከወር ወር ሸርተት ዘጭ፣ እንደገና ሸርተት አረፍ፤ እያለ ነው ከወለል በታች ቁልቁል የሚጓዘው፡፡ የራሱን ጉድጓድ እየቆፈረ ጭምር ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ አንጦሮጦስ የሚወርደው።  በየጊዜው ሸርተት እያለ ቁልቁል በወረደ ቁጥር፤ ከቀድሞ የከፋ አዲስ ጥፋት እየተፈጠረ እንደናገጣለን፡፡ አብዛኛው ሰው በድንጋጤ  “ቆጠብ፣ ሰከን እንበል፣  ኸረ ከጥፋት እንመለስ” ይላል፡፡ ነገር ግን  ከሰበብና ከማመከኛ ጋር እዚህም እዚያም ጥፋት ሲደጋገም አሳፋሪው ጥፋት፣ አሳፋሪነቱም አስደንጋጭነቱም ይደበዝዛል፤ ይለመዳል፡፡
ከከተማ ከተማ ከክልል ክልል በየእለቱ  እየተመላለሱ የሚሰሩና የሚነግዱ ሰዎች የእለት ተእለት ምልልሳቸውን በየሳልስቱ ያደርጉታል - በስጋት፡፡
እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ የሚሰሩ ድርጅቶች 3 ሰዓት ላይ መዝጋት ይጀምራሉ፡፡ በቶሎ ቤት ደርሶ ለመግባት መቻኮልም፣  ኖርማል ይሆናል። የመኪና መንገድ ለግማሽ ሰዓት ዘግቶ ጉዞ ማስተጓጐልም እንዲሁ ይለመዳል፡፡ እንዲያውም፤ “የህዝብ ጥያቄ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የለውጥ ፍላጐት” የሚሉ ሰበቦችና ማመካኛዎችን እየደረደሩ ጥፋትን የማቆንጀት ፈሊጥ ይበራከታል።
ብዙም ሳይቆይ፣ ቁልቁል እንደገና እንወርድና ለበርካታ ሰዓታት መንገድ መዝጋት ይጀመራል። ይሄም ግን፣ ከድንጋጤና ከማመከኛ በኋላ በየቦታው ይለመዳል፡፡ ጎን ለጎን፣ የአብዛኛው ሰው የስነምግባር መርህም፣ በየደረጃው እየተሰበረ እየተሸረሸረ ይመጣል፡፡ ቀኑን ሙሉ መንገድ መዝጋት ብቻ ሳይሆን፣ የመንገደኞችን ንብረት መዝረፍና መኪና መስበር ይለመዳል። ከዚያስ መኪና ማቃጠልና ሰው መግደልም…ያጨመርበታል፡፡
ዘረኝነትም እንደዚያው ነው፡፡ እያዋዙና በዘወርዋራ ዘረኝነትን የሚሰብኩ ናቸው ጀማሪዎቹ ፡፡ ዘረኝነትን የማዋዛት ሰብከታቸው፣ እንደብልጣብልነት ብቻ ሳይሆን እንደ ጥበብ እንዲቆጠርላቸው የሚፈልጉ ናቸው ጅምር ላይ የሚበራከቱት፡፡ በእርግጥ፣ ብልጥነታቸው ለትንሽ ጊዜ ነው፡፡ “ከመምህሩ ደቀመዝምሩ” ይባል የለ! አስቀያሚውን ዘረኝነት ማዋዛት በሚችሉ   ወግ አዋቂዎች ምትክ፤ ከማዋዛት ይልቅ ወዳፈጠጠ ዘረኝነት፣ ከወገኛነት ይልቅ ወደ መዋጋት ያዘነበሉ የዘረኝነት አጋፋሪዎች ይፈጠራሉ፡፡  ከጊዜ ወደ ጊዜ የባሰባቸው ዘረኞች እየተፈለፈሉ በሩቁ ከመተነኳኮስ አልፈው፣ እየተቧደኑ ወደ መበሻሸቅ፣ ከመሰዳደብ ተሻግረው በጅምላ  ወደ መወነጃጀል ያመራሉ፡፡ ከዚያማ የዛቻና ጥቃት ቅስቀሳ ላይ እንደ ረሃብተኛ አውሬ የሚረባረብ የዘረኝነት አስተባባሪ እየበዛ ይመጣል፡፡
ምናለፋችሁ ቁልቁል መውረድ…በአንድ ዥውታ አይደለም፡፡ ሸርተት ቆምእያለ፣ እንደገና እየወደቀ እያረፈ ነው አገር መቀመቅ የሚወርደው። አንዱን አሳፋሪ ጥፋት እየተላመደ ወደባሰ የከፋ ጥፋት እየተሸጋገረ ቁልቁል ይሰጥማል፡፡  እንዲህ ጥፋትን እየተላመድን የመጨረሻው ቋፍ ላይ ከመድረሳችን በፊት፣ አስቀድመን የውርደትን ጉዞ ለማስቆምና ለማቃናት፣ ከጥፋት ለመዳንና ከእንጦሮጦስ ለመውጣት ብንጥር ጥሩ ነበር። ገና ድሮ ከጅምሩ መባነን ብንችልና የመዳን ዘመቻ ብንጀምር ያሻለን ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሌም ነገሮች ጦዘው ጦዘው፣ ከስረው ከሳስረው፣ ወርደው ተራክሰው ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆኑ፤  ከመጨረሻው ፍፃሜ ጋር እስክንፋጠጥ ድረስ፣  የመዳን ዘመቻ ብዙም አይታይም፡፡
ቢሆንም ግን፣…. በመጨረሻዋ ሰዓት፣ ፍፁም ላለመንኮታኮትና ላለመጥፋት፣ የመዳን ዘመቻ የሚጀምሩ፣ ለመፍጨርጨርም የሚሞክሩ መኖራቸው፣ አንድ ቁም ነገር ነው። ያስመሰግነቸዋል።- (ሉሲን ከሞት የማስነሳት ዘመቻም ቢሆን፡፡) በእርግጥ የሉሲ ጉዞ አዘጋጆች ምኞት፣ “ለሉሲ ህይወት እንድንዘራባት ሳይሆን ህይወት እንድትዘራብን” ይመስላል፡፡  ከመተራመስ ይልቅ የአገር ህልውና (አንድነት) እንዲፀናልን፣ በዘር ከመቧደንና  ከጅምላ ጥላቻ ይልቅ  ሰላምና ፍቅር እንዲበረክትልን ነው - የዘመቻው ምኞት። ይሄ ያስመሰግናል፡፡ ከአስከፊ በሽታና ከጥፋት የመዳን ምኞት በመያዝ የሚደረግ ጥረት መልካም ጅምር ነውና፡፡
ነገር ግን፤ ይህንን መልካም  ምኞት የሚበርዙ እና ጥረታቸውንም የሚያሰናክሉ ሁለት ችግሮችን ልጠቁማቸው፡፡
በጥያቄ ልጀምር፡፡ እንዴት ነው፣ “የሉሲ ጉዞ”፣ ከዘረኝነት፣ ከትርምስና ከእልቂት ለመዳን ይረዳል ብለው ያሰቡት? (ከ3 ሚሊዮን ዓመት በፊት በህይወት የነበሩት እነ ሉሲ፣ ሲወልዱ ሲዋለዱ፣ ከሚሊዮኖች ትውልድ በኋላ፣ ሰው የሰው ልጅ መከሰቱን ለማወቅ የረዳ፣ ትልቅ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤት ነው- የሉሲ ቅሪት፡፡) እና የሉሲ ቅሪትን ወይም በቅሪቱ አምሳያ የተቀረፀውን ቅርስ ይዞ መዞር እንዴት ብሎ ከዘረኝነት በሽታ የሚያድን፣ የአገር ህልውናንና አንድነትን የሚያፀና፣ የሰላምና የፍቅር በረከት ይሆንልናል?
አዎ፤ “የሉሲ ጉዞ” አንድ የትኩረት  መድረክ፣ አንድ በጎ አጋጣሚ ሊሆንልን ይችላል፡፡ የአገር ህልውና እጅግ ውድ ነገር መሆኑን የምናገናዝብበት አጋጣሚና የምንማማርበት መድረክ ለመፍጠር ነውና ማሰባቸውም፣ ያስመሰግቸዋል፡፡
የአገር ህልውና እየተሸሸረና እየነተበ ካለቀለት፤ ሌላው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው - ከስደት በስተቀር፡፡
አገርን የማሻሻል ማንኛውም ጥረትና ለውጥ፣ ትርጉም የሚኖረው፣ አገር በህልውና ከፀና ብቻ ነውና፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት፣ የዘረኝነትን ወራዳነት በመገንዘብ፣ “ዘረኝነትን እንፀየፍ” ብለን ቃል ኪዳን የምንገባበት አጋጣሚ፣ እንዲሁም ለሰላምና ለፍቅር የሚበጅ ትክክለኛ ሃሳብን  የምናስተጋባበት መድረክ የማዘጋጀት ሙከራ፣ መልካም ጥረት ነው።
በዚህ መሃል፤ በሌላ ተናጋሪ፣ በዚያው መድረክ፣ “ሊሲ ኩራታችን ናት፣ ሁላችንም የሉሲ የልጅ ልጆች ነን፤ ዘራችን አንድ ነው” የሚል ሃሳብ ሲስተጋባ ደግሞ ይታያችሁ፡፡  በዚህም በዚያም ብለን ከዘረኝነት በሽታ ለመዳንና ከጥፋት አደጋ ለመትረፍ፣ ማንኛውንም ድንጋይ ለመፈንቀል መሞከር፣ ስህተት ቢሆንም እንኳ፣ ክፋት ላይሆን ይችላል፡፡ ከዘረኝነት በሽታ ለመዳን፣ “ዘራችን አንድ ነው” ብሎ መናገር፣ አጋዥ መፍትሔ ይመሰለንም ይሆናል፡፡  ግን፣ ተሳስተናል። “ዘራችን አንድ ካልሆነ፣  ከዘረኝነት የማምለጥ ተስፋ የለንም” እንደማለት ይሆናል፡፡ የዘር ሐረግ ተቆጥሮና ተዘርዝሮ ከአንድ ግንድ እና ስር መምጣቱ ካልተረጋገጠ፣ “በዘር እየተቧደኑ አገር ከሚያፈርሱና ከሚያተራምሱ አጥፊዎች መዳን አንችልም” ማለት ነው? የትውልድ ሃረጉና ዘሩ ምንም ሆነ ምን፣ እያንዳንዱን ሰው፣ በግል ብቃቱ፣ በግል ተግባሩ፣ በግል ባህርይው የመመዘን የቅንነትና የፍትህ መርህ አይደም እንዴ ከአስፀያፊው ዘረኝነት የሚያድነን? ሁነኛውና አስተማማኙ የዘረኝነት ማርከሻ፣ የግል ማንነትን ማክበር ነው፡፡
አእምሮ የግል ነው፤ አካል የግል ነው፤ ብቃት የግል ነው። በአጠቃለይ ሰው በተፈጥሮው የግል ነው- ህይወትም ሞትም፡፡  ለሁለት ተቆርጦ ብዙ ትንንሽ ሰው አይወጣውም። ሁለት ሦስት ሰዎችን አቧድኖ በመጨፍለቅ አንዳች ቅልቅ ፍጡር እንዲወጣቸው ማስብስ? ይሄ ከእውነታ ጋር የተጣላ ጭፍን   አስተሳሰብ ነው - ዘረኝነት ማለት ፡፡  
መፍትሄው የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የዘወትርና የዘላለም እውነት ላይ የተመሰረተ፣ ነው የቅንነትና የፍትህ መርህ ነው መድትሄው፡፡ እያንዳንዱን ሰው በግል ተግባሩ የምንዳኝበት የፍትህ መርህ ነው ከዘረኝነት የሚያድነን፡፡ እያንዳንዱን ሰው በግል ብቃቱ የማድነቅ፣ በግል ተግባሩ የማመስገንን የመውደድና የማፍቀር ቀና የሃቅ መንገድ ነው፣ ከአሰቀያሚው የዘረኝት በሽታ የሚያነፃን፡፡ በዘር የማቧደን የጥላቻ ቅስቀሳን ለማስወገድና ከዘረኝነት አደጋ ለመዳን፤ “አንድ ዘር ነን” ብለን  ሁሉንም በአንድነት  ለማቧደን መሞከር ግን፤ ከአሰቀያሚው  የዘረኝነት ሜዳ የመውጣት ተስፋችንና ምኞታችንን ከመነሻው ይመከንብናል።
አንደኛ ነገር፤ በተግባር በሶማሊያና በሌሎች አገራት እንዲሁም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥም እንደምናየው፣ “አንድ ዘር ነን” በማለት ከዘረኝነትና ከጥፋት መዳን አይቻልም፡፡
ሁለተኛ ነገር፤ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት፣ የዘረኝነት ሜዳው በአንድ ጊዜ አይደለም የሚስፋፋው፡፡ በአንድ አፍታ አይደለም አገር እንጦሮጦስ የሚገባው፡፡ ቁልቁል ሸርተት አረፍ፣ ወረድ ቆም እያለ ነው እየተባባሰ ቁልቁል የሚወርው።
“የሊሲ ልጆች ነን፣ አንድ ዘር ነን” ብለን ሁሉንም በአንድነት ለማቧደን ስንሞክር፣ ያው “በዘር የመቧደን” ሜዳውን  በይሁንታ ተቀብለናል ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በየፊናቸው፣ በየስሜታቸው፤ በየክፋታቸውና በእልፍ አቅጣጫ፣ በዘር የሚያቧዳኑ  እልፍ የዘረኝነት አውራዎች፣ ሜዳውን ይቆጣጠሩታል፡፡ ያኔ፣ “በዘር መቧደን ያፀይፋል”  ብለን የመከላከል አቅም አይኖረንም፤ በምን አፋችንስ እንናገራለን?
እናም፣ የሉሲ ጉዞ እና  ከዘረኝነት ለመዳን የሚካሄዱ ሌሎች ዘመቻዎች ላይ በቅንነት የሚጣጣሩ ሰዎች፣ እንዲህ አይነት ስህተቶችን ካላስወገዱ፤ ምኞት ጥረታቸው ሁሉ መና ስለሚቀር፤ በደንብ ሊያስቡበት ይገባል፡፡
ሌላኛው ችግር፣ የሉሲ ጉዞና ተመሳሳይ ዝግጅቶችን የሚወጥኑ የመንግስት ተቋማት፤ የብዙ ሰው ትኩረት የሚስብ ደማቅ ዝግጅት እንዲሆንላቸው ከፈለጉ፤ ለዚያውም ያለ ተጨማሪ ወጪ፣ የተዋጣለት ዝግጅት እንዲሆንላቸው ከፈለጉ ፍቱን ዘዴውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡
መሰናዶውን ማሳመር ለሚችሉ የግል ኩባንያዎች በኮንትራት መስጠት ነው - ዘዴው፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከናወነው ትልቁ ዝግጅት፣ እንዲያ ባልፈዘዘ ነበር፡፡     






Read 1349 times