Print this page
Sunday, 03 March 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ዶ/ር ደብረፅዮን “ከህደት ተፈፀሞብናል” ይላሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(15 votes)


   ወደ ትግራይ ክልል ያመራሁት ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዩን ገ/ሚካኤል ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ነበር፡፡ ጉዞዬን በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አድርጌ ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ ላይ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ገባሁ፡፡ ከአየር ማረፈያው ጀምሮ ሆቴሌ ድረስ እንዲሁም በመቀሌ ቆይታዬ ሁሉ የትራንሰፖርት አገልግሎት የሰጡኝ ባለታክሲና ባለባጃጅ ፍፁም ትሁትና አንግዳ አክባሪ ናቸው፡፡ ያለ ክፍያ እንግድነቴን አክብረው
አስተናግደውኛል፡፡ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ቢሮ በቀጠሮዬ ሰዓት ደረስኩ፡፡ በር ላይ የነበሩት ጥበቃዎች የተቀበሉኝ በአክብሮት ነው፡፡ ቋንቋቸውን
አለመቻሌ የፈጠረብኝ ችግር አልነበረም፡፡ አስተርጓሚ ተመድቦልኝ ወደ ቢሮአቸው ተላኩ፡፡ ቢሮአቸው ስደርስ ዶ/ር ደብረፅዮን ከአሜሪካ ከጀርመን፣ ከኖርዌይና ከእስራኤል አምባሳደሮች ጋር ዉይይት ላይ ነበሩ፡፡ ተራዬ እስኪደርስ ግማሽ ሰዓት ያህል ጠብቄ ገባሁ፡፡ዶ/ር ደብረፅዮን ከወንበራቸው ተነሰተው
በአክብሮት ተቀበሉኝ፡፡ ለጥያቄዎቼ ሁሉ ምላሸ ለመስጠት ፍቃደኝነታቸውንም ገለፁልኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሰጡን ምላሾች የመጀመሪያው ክፍል እነሆ፡-

የትግራይ ክልል ዋንኛ ችግር ምንድነው?
የክልሉ  ችግር ብዙ ነው፡፡ በስፋት በአገር ደረጃም ሆነ በክልላችን ችግሮች አሉ፡፡ አንዱ ችግር ድህነት ነው፤ ብዙ ተሰርቷል ነገር ግን መነሻችን በጣም ዝቅ ያለ ድህነት ውስጥ በመሆኑ ገና ብዙ ይቀራል፡፡ ብዙ ርቀት ሄደናል፤ ግን አሁንም የተሸከምነው ድህነት በጣም ትልቅ ነው፤ ስለዚህ ትልቁ ፈታኝ ስራችን ህብረተሰቡን ከድህነት ማውጣት ነው፡፡
ሌላው ችግር የመልካም አስተዳደር ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት ሲኖር ድህነቱ እንዲባባስ ነው የሚያደርገው፤ ምክንያቱም አስተዳደሩ በጎ የአገልግሎት አሰጣጥ ከሌለው የህዝቡ ችግር እየተባባሰ ይመጣል፡፡
ሌላው ልማት የምንለው ጉዳይ ነው፡፡ በልማት ላይ መመለስ ያለባቸው፣ በግብርና ላይ መስራት የሚገባን፣በኢንዱስትሪው፣ በመሰረተ ልማት ላይ… ብዙ ዝርዝሮች ነው ያሉን፡፡ በየቦታው ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል ግን የሚጎሉ ስላሉ ከፍተኛ ግምገማ አድርገናል፡፡ ግምገማው ላይ ህዝብም እንዲሳተፍበት ተደርጓል፡፡ ይህንን ካደረግን በኋላ ወደ ስራ ነው የገባነው፡፡ አንዳንዶቹ  ወዲያው የሚመለሱ ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ጥናት የሚጠይቁ ናቸው፡፡
ዘንድሮ በ2011 ግምገማ ባደረግነው እንደ መርህ ያስቀመጥነው፣ “ብዙ መስራት ትንሽ መወያየት” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ውይይት፣ ብዙ ግምገማ አድርገናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ንግግር ሳይሆን ብዙ ስራ የሚሰራበት ነው። ይሄ አመት የስራ ነው፡፡
በአጠቃላይ በሁለት መንገድ ነው ያየነው፡፡ አንዱ ዲሞክራሲ ያልነው ነው፤ ሌላኛው ደግሞ ትራንስፎርሜሽን ነው፡፡  በትግራይ በሁለቱም ዘርፍ ለውጥ እናመጣለን፡፡ ለዚህ የሚጠቅሙ ሃሳቦች ደግሞ መጥተዋል፡፡ ከልማቱ አንዱ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ አምና ከሰላሙ ጀምሮ ትግራይ ላይ ብዙ ችግር አልነበረም። በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ግን ችግሮች ሰፊ እንደሆኑ ተገምግሟል፡፡ ጥናት ጀመርን ማለት ወደ ስራ መግባት ጀመርን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ  መሻሻል የሚገባቸውን እየነካን ነው፤ ሰላም መሆኑ ግን አምናም ሰላም ነበር፡፡ በእኛ ክልል የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በሰላም ነው የሚማሩት:: ግጭት የለም፡፡ ቤተሰብም የሚቸገርበት ሁኔታ የለም። አስተሳሰቡ የተስተካከለ አስተዳደር ካለ እንደዚህ ነው የሚሆነው፡፡  እዚህ ህወሓት ነው የሚያስተዳድረው፤ ግን የተስተካከለ አስተሳሰብ ስላለው ከየትም ብሔር ይምጣ በአግባቡ ነው የሚያስተናግደው፡፡ ፓርቲው የተስተካከለ አመለካከት ስላለው፣ ህብረተሰቡም የተስተካከለ አስተሳሰብ አለው፡፡ ከሁሉም ክልል ቢመጣ ይስተናግዳል የትግራይ ልጆች የትም ቦታ ሲቸገሩ፣ ሲባረሩ እናውቃለን፡፡ ከጐረቤት ክልሎች ጀምሮ ለችግሮች ምላሽ አይሰጡም። እዛ ስህተት ስለተፈፀመ እዚህም እንደገና ሌላ ስህተት ሊፈፀም አይችልም፡፡
እዚህ ክልል አይደለም ኢትዮጵያዊ፣ የውጪ ሀገር ዜጋም በሰላም ይንቀሳቀሳል። ከአማራ ክልል የትግራይ ተወላጆች ተባረሩ ተብሎ የአማራ ተወላጆችን ማባረር ታሪካችን፣ ፖለቲካችን፣ አስተሳሰባችን አይፈቅድም። ህዝቡን ማስተማር፣ እንደዚህ አይደረግም ብሎ ማውገዝ፣ መጠየቅ ያለባቸውም በህግ ነው መጠየቅ ያለባቸው፡፡ ዛሬ ባይጠየቁ በሂደት እንደሚጠየቁ ማሳየት ነው እኛ የምንፈልገው፡፡
በተደጋጋሚ ተከበናል ትላላችሁ በማነው የተከበባችሁት?
ተከበናል ማለት በሌላ አማርኛ በአራቱም አቅጣጫ ጫናዎች አሉ ማለት ነው፡፡ ዋናው የፖለቲካ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው፤ ትግራይ ላይ የሚያነጣጥር ዘመቻ ሰፊ ነው፡፡ በፌደራልም፣ በሁሉም ክልል በተለያየ አቅጣጫ ይታያል፡፡ ይሄ ደግሞ በየአደባባዩ በየሚዲያው የሚነገር ነው፡፡
በአገራችን ብዙ ግምገማዎችን አከናውነናል የችግሮች ምንጭ ያልነው የሁሉንም ድርጅቶች አመራር ነው፡፡ ችግሩ የጋራ ነው ብለናል፡፡ በቅርብ ጊዜ የምንሠማው ግን የሁሉም ችግር ምንጭ ህወሓት ነው የሚል ነው፡፡
ከዛም አልፎ ትግራይ ነው ወደሚል ሄደ፡፡ ይሄ ከተገመገመው ውጪ ነው፡፡ ጥፋቱ የአንድ ፓርቲ ብቻ ተደርጎ፣ እኛ ንፁህ ነን የሚል ንግግር በአደባባይ ነው የሰማነው፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን “27 አመታት የጨለማ ዘመን” የሚል ሳይቀር ነው የሰማነው፡፡ 27 አመት አገራችን በጨለማ ውስጥ አልነበረችም፤ ታይቶ በማይታወቅ የእድገት ለውጥ ከዛም አልፎ አለምም የመሰከረው ፈጣን እድገት አስመዝግባለች፡፡ ሚሊዮኖች ከድህነት እየወጡ እየተቀየሩ፣ ለሌላ ደሀ ሀገራትም አብነት ነው እየተባለ ሲገለጽ ነበር፡
እኛ እራሱ በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና…በሁሉም ምን ለውጥ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ይቺ ሀገር ከተማዋ እንዴት እየተሻሻለ እንደመጣ፣ ባለሀብቱ ምን ያህል እየጨመረ እንደሄደ … በግልፅ ይታያል። አጠቃላይ ነው ለውጡ፡፡ ገጠሩም ከተማም በለውጥ ነው፡፡ ይህቺ አገር በለውጥ ነው የምሁራን ሀገር የሆነችው፡፡ ስንት ዩኒቨርስቲ እንደነበር እናውቃለን፡፡ አንድ ሁለት የሚባል እንጂ 40 እና 50 ዩኒቨርስቲ አልነበረም፡፡ ይሄ ነው የጨለማ ዘመን የተባለው፡፡ ስለዚህ በአመራሩ ላይ ችግር አለ ማለት ነው፡፡
የተመዘገበውን እድገት ሁሉ አጥፍቶ፣ የጨለማው ዋናው ተጠያቂ ደግሞ አንድ ፓርቲና አንድ አካባቢ ከዛም አልፎ ወደ ህዝብ ሄዶ የተለየ ተጠቃሚ ተብሎ የተፈረጀበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ሁኔታው ከመንገድ የወጣ ነው። ለዚህ ነው ተከበናል የተባለው፡፡ የሰብአዊ መብትም ጥሰት ከተባለ አንድ አካባቢ ነው፣ የኢኮኖሚ ሙሰኝነትም ከተባለ፣ ዝርፊያ ከተባለ አንድ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ ይሄ በጣም የተወላገደ አመለካከት፣ ለጥፋት የሚዳርግ አስተሳሰብ ነው፡፡
ህዝብ ለህዝብ የሚያጫርስ፣ ወደ ሌላ ጥፋት ሊያመሩ የሚችል ነው፡፡ አሁንም እሱ ቀንሶ ሊሆን ይችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ግን ግፊቱ አለ፡፡ “እኛ ንፁሃን ነን፤ እመኑን ተቀበሉን፤ ሰይጣኖቹ ሌሎች ናቸው” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የተፎከሩ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የስልጣን ፍላጐትን ነው የሚያሳየው፡፡
አሁን እኮ ትግራይ ወይም ህወሓት አይደለም፤ ሁላችንም ነን ተጠያቂ የሚል የለም እኮ፡፡
“አራታችን የድርጅት መሪዎች እንደተወያየነው የሚል የለም፤ ለዚህ ነው ክህደት ተፈፅሞብናል የምንለው ፡፡         
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ ተዋሃደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ይለወጣል ብለዋል፡፡ ይሄ ደግሞ አሁን በአገሪቱ የሚታየውን የዘረኝነት ችግር ለመፍታትና አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል የሚሉ ወገኖች አሉ እርስዎ ምን ይላሉ?
ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣቱ ጉዳይ ቀደም ሲል የነበረ አስተሳሰብ ነው፡፡ እናጥናው ተብሎ ሲንከባለል የቆየ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ባደረግናቸው ስብሰባዎችም፣ ይሄ ነገር ለአንድነታችን ይጠቅማል በሚል ተነስቶ ነበር። ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ጥቅም አለው፡፡ ይሄ ማለት ግን የብሔር ብሔረሰብ አደረጃጀት ይጠፋል ማለት አይደለም፡፡ ኢህአዴግም ቢፈልግ ሊያጠፋው አይችልም፡፡ ፌደራል ስርአቱ፣ በብሔር ብሔረሰብ ደረጃ የሚታዩ ህብረተሰቦች እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ነው፡፡ እራሱን ለማስተዳደር የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል፡፡
ህብረተሰቡ በራሱ ቋንቋ፣ የራሱ አካባቢ፣ የራሱ ታሪክና ባህል ያለው ስለሆነ ልናጠፋው አንችልም፡፡ በዚያ ላይ የክልል ፓርቲ ሊኖር ይችላል፡፡
አንድ አገራዊ ፓርቲ መሆን ግን ዘረኝነት ሊያስቀር አይችልም፡፡ እዚህ አገር ላይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኮ በብሔር ላይ ያተኮረ ያን ያህል ግጭት አልነበረም፡፡
ግጭቶች ዜሮ ነበሩ ባንልም አሁን የምናየው ዓይነት መረን የለቀቁ፣ ግጭቶች አልነበሩም፡፡ ባለፉት 27 አመታት ይህን ያህል ትልቅ የሚባል ችግር አልነበረም፤ እሱን መመርመር ነው የሚያስፈልገው - እንዴት ያለ ችግር መዝለቅ እንደቻልን መጠናት አለበት፡፡
በአገሪቱ ላይ በአንድነት ተዋህደው የቆዩ ሌሎች ፓርቲዎች የሉም፡፡ ከእነሱ ልምድ እንቅሰም እንዳይባል ኢህአዴግ ነው የነበረው። እሱም አንድ ውህድ ፓርቲ ሳይሆንም በሠላም ሲሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ዋናው የአመራር አስተሳሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የአመራር አስተሳሰብ ሲበላሽ ነው ዘር የሚባለው ነገር የሚመጣው። አንድ ፓርቲ ቢሆንም የዘር አስተሳሰቡ አይቀርም፡፡
አሁንም መጀመሪያ የአስተዳደር አስተሳሰብ ሳይቀየር ወደ አንድ መምጣት አይጠቅምም። ነገር ግን በተስተካከለ አስተሳሰብ መመራት ከተቻለ፣ አንድ መሆኑ የበለጠ ያጠናክራል እንጂ አይጐዳም፡፡ የተዛባ ከሆነ ግን ያው እንደ “ኢሰፓ” ነው የሚሆነው፡፡ እሱ ደግሞ መልሶ ወደ ውጊያና ጭፍጨፋ ነው የሚያስገባው። አስተሳሰብ ሲስተካከል ሠላም ይመጣል፡፡ ሠላም ሲኖር ልማትና እድገት ይኖራል፡፡
ከኤርትራ ጋር በድንበር በኩል የተጀመረው የንግድ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?  
እንቅስቃሴዎቹን ክፍት ስላደረግናቸው፣ ሰዎች በራሳቸው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ከግብርናና ከእንስሳት ጋር የተያያዙ ግብይቶች አሉ፡፡ በአብዛኛው የግብርና ውጤቶች … ከአትክልት ጀምሮ እንዲሁም የፋብሪካ ውጤቶችም (እዚህም ትግራይ የተመረተ ሊሆን ይችላል) ኤርትራውያን በራሳቸው ቀጥታ ገዝተው የሚሄዱበት፣ እዚህ ያለው ኢትዮጵያዊም ሄዶ እቃውን ሸጦ፣ ገዝቶ የሚመለስበት ሁኔታ አለ፡፡
ሆኖም እንደ መንግስት ስርአት አላስያዝነውም፤ ሰው እራሱ ነው የሚገበያየው። እነሱም ናቅፋ አላቸው፤ እኛም ብር አለን፡፡ በራሳቸው ነው የሚገበያዩት፡፡ በባንክ የሚባል ነገር የለም፡፡ በሌሎች አገሮች አዋሳኝ ላይ በተወሰነ ደረጃ በብር ግብይት ይካሄዳል፡፡ ይሄ በየትኛውም ጐረቤት አገራት የተለመደ የተፈቀደ ነው፡፡ እዚህም ገና ነው እንጂ መፈቀዱ አይቀርም። ግን ይሄ ሰው ወደ ውስጥ ገብቶ የሚገበያየው ገና ነው፤ የምንጨርሳቸው የጉምሩክ፣ የኢምግሬሽን ጉዳዮች አሉ፡፡ እንቅስቃሴው የተጀመረው ይሄ በሌለበት ስለሆነ ገና ዝርዝር ውይይት ያስፈልገዋል፡፡ መሀል ላይ ደግሞ መንገዱ ስለተዘጋ፣ ተጀምሮ የነበረው የንግድ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ የመኪኖች እንቅስቃሴ በሁመራ በኩል ካልሆነ፣ በሌሎች በኩል የለም፤ ስለዚህ እንደ መጀመሪያው አይነት ግብይት አይታይም፤ ነገር ግን ሰው በራሱ መሸከም የሚችለው ነገር አለ፤ በእንስሳም ጭኖ ሊሄድ ይችላል፡፡ እሱን አልዘጋነውም፡፡
ለረጅም አመታት በጦርነት ምክንያት የህዝቦች መለያየት ስለነበር፣ ህዝብ ለህዝብ እንዲገናኝ ለማድረግ ታስቦ ክፍት የሆነው በህዝቡ መካከል መራራቅም ብቻ ሳይሆን ጥላቻም ስላለ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የወደብ ጉዳይ፣ የመላክና የማስገባት፣ የውጪ ምንዛሬ ጉዳይ ላይ ስርዓት ለማስያዝ እየሰራን ነው፡፡ በፊት ተጀምረው የቀሩ ብዙ የቤት ስራዎች አሉ፡፡  ዘለን የንግድ ስራዎች ላይ አንገባም፤ በነፃ ማስጀመሩ ይጠቅመናል፡፡  በርግጥ የኢኮኖሚ ጉዳት አለው፤ ኮንትሮባንድን እንደ መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ግን ለፖለቲካውና ጥሩ መንፈስ ለመፍጠር፣ ግንኙነትን ለማሻሻል ይበጃል በሚል ነው ክፍት የተደረገው፡፡ አሁን ሁለቱም መንግስታት እየተደራደሩ ነው ያሉት፤ ስርዓቱን አስይዞ መንገዶችን ለመክፈት እስካሁን ያለው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡
በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ክልላችሁ  እየገቡ ነው ተብሏል፡፡ ጥሪ አቅርባችሁ ነው ወይስ?
በየትኛውም ክልል ያለ ኢንቨስተር መምጣትና ኢንቨስት ማድረግ ይችላል፡፡ እየመጡም ነው… ከውጪ ሳይቀር፡፡ እንደተባለው ለክልሉ ተወላጆች ጥሪ ቀርቦ ሳይሆን ከዚህ ቀደም እንዳይሠሩ የተደረጉ ወይም የተባረሩ የመጡበት ሁኔታ አለ፡፡፣
አንዳንድ ደግሞ ከኤርትራ ጋር በተፈጠረ ሠላም፣ በተለይ አስመጪና ላኪዎች፣ የወደብ አገልግሎት በቅርበት ለማግኘትና ወጪያቸውን ለመቀነስ ይመጣሉ፡፡ ግን የትግራይ ተወላጅ ብቻ አይደሉም፡፡ ይሄ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሠራ ሳይሆን አምናም የነበረ ነው፡፡ አሁን ወደ ትግበራ እየገቡ ነው፡፡
በማምረቻ ዘርፍ ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ኢንቨስተሮች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 222 የሚሆኑት ወደ ስራ እየገቡ ነው፡፡ እነዚህ ከ22 ሺህ በላይ ሠራተኞች የሚቀጥሩ፣ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ያላቸው ሲሆኑ አንድ ላይ ነው የሠጠናቸው፤ ግን ከአምና ጀምሮ የፕሮጀክት ፕሮፖዛላቸውን ያቀረቡ ናቸው፡፡
ከአንድ ሺዎቹ ውስጥ ቶሎ ወደ ስራ ሊገቡ የሚችሉና በኢኮኖሚውም ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ናቸው፡፡ አሁን የተመረጡት ኢንቨስተሮች በአዲስ አበባም ሆነ ሌላ ክልል በቢዝነስ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ይሄ በአንድ ከተማ ነው፤ ሌሎች ከተሞችም በዚህ ደረጃም ባይሆን አለ፡፡
ኢንቨስተር ሲመጣ የመሬት ካሳ እንዴት ይሁን? የሚለውን እናያለን ግን እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ አልሚውም ሊከፍል ይችላል። በካሳ ምክንያት የኢንቨስተር ፍሰቱ መወሰን የለበትም ባዮች ነን፡፡ ከካሳ ጋር በተያያዘና በሌሎች ምክንያቶች ኢንቨስትመንት ማደናቀፍ ቀርቷል፡፡ ከዚህ በላይ አናስተናግድም የሚለው ተቀይሯል። ስለዚህ  ነው ትልቅ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያለው፡፡
በፌደራል ደረጃ ያሉ ችግሮች ቀንሰዋል ወይስ ተባብሰዋል?
ችግሮቹን ለመፍታት ጥረቶቹ አሉ፤ እሱ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የፖለቲካ አየሩን ስናየው፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች (አገር ውስጥ የነበሩና ከውጭ የገቡ) የተሻለ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይሄ ለውጥ ነው፡፡ አንዳንድ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውና በዲሞክራሲ ምርጫ ለመሳተፍ ማሰባቸው - መፍቀዳቸው ለውጥ ነው፡፡ ለቀጣይ ስራችንም የሚጠቅም ነው፡፡
በከፍተኛ ደረጃ የታሠሩም እንዲፈቱ ብለን በወሰነው መሰረት ተፈተዋል፡፡ ይሄም ነፃ የመሆን ስሜት ፈጥሯል፡፡ ይሄንን በመልካም ጐን ነው የምንወስደው፡፡
በአገር ደረጃ አንድ ለውጥ ያየነው ከኤርትራ ጋር እርቅ መፈጠሩ ነው፡፡ የኤርትራ ጉዳይ በአገር ደረጃ ነው የተፈታው፡፡ በቀጥታ ጠ/ሚ ዐቢይ መፍታታቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ በግልፅ የሚታይ ለውጥ አለ ለማለት አንችልም፡፡ ኢኮኖሚው እየተቀዛቀዘ ነው ያለው። ኢንቨስትመንቶች እየጨመሩ አይደሉም፡፡
የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ምክንያቱ ምንድነው?
የአመራር ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊ መንግስት ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት የሚመዘንበት ኢኮኖሚውን እንዴት እየመራው ነው? የሚለው ነው፡፡ ኢኮኖሚው ውጤታማ፣ ፈጣን፣ ፍትሐዊም፣ ቀጣይም መሆን አለበት። ይሄም መሪ ያስፈልገዋል የግድ፡፡ በኢኮኖሚ አመራሩ ላይ ከተጐዳን ኢኮኖሚው፡፡
በራሱ አይሄዳም፡፡ ደጋግመን የምንናገረው ኒዮሊበራል የምንለው በዛ አይሄድም፤ የአደገ አገር በገበያ ይመራል - ኢኮኖሚውን ለማሻሻል። ያላደገ አገር ግን የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልገዋል፡፡ መፈትፈት ሳይሆን መምራት፡፡ ልማታዊ መንግስት እኮ የራሱ የልማት ድርጅቶች አሉት፡፡ ኢኮኖሚውን እያየ የማረጋጋት ስራ ይሠራል፡፡ ይሄ አሁን የለም። የነበረውም እየተዳከመ ነው፡፡ አዳዲስ ችግር መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
በፖለቲካው በዲሞክራሲው የምናያቸው ችግሮች ወደፊት የመሄድ ሲሆን ኢኮኖሚው ግን ወደ ኋላ እየሄደ ነው፡፡ በፊት ኢኮኖሚው ወደፊት ዲሞክራሲው ወደ ኋላ ነበር የቀረው። አሁን ግን ተገልብጧል፡፡ መቅደም ግን ያለበት ኢኮኖሚው ነው፤ ኢኮኖሚው ከሌላ ሃሳቡን መግለጽ አይችልም፡፡ ዲሞክራሲ አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፣ ነገር ግን በባዶ ሆድ ሰው ሊናገር አይችልም፡፡ እኛ ሁለቱንም ነው ማስኬድ አለብን፡፡
ልማታዊ መንግስት የምንላቸው አገሮች እኮ ኢኮኖሚውን ብቻ ይዞ መሄድ ነበር ልምዳቸው፤ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር የለም፡፡ እኛ ግን ያለ ዲሞክራሲ አንሄድም ነው ያልነው፤ ብዙ ህዝቦች ስለሆንን፡፡  አሁንም አደጋ ነው ሄዶ ሄዶ ይቆማል፡፡ በጉልበት የሚሠራ አይደለም ህብረተሰቡን ማሳመን ነው፡፡ ዲሞክራሲ ያስፈልገናል፤ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት፡፡
የኢኮኖሚ መውደቅ ችግር አንዱ አመራር ነው፡፡ ሌላው ሠላም ሲጠፋ ኢኮኖሚ ሊያድግ አይችልም፡፡ ኢኮኖሚው ጥሩ አመራር ቢያገኝ ሠላምስ? ለሠላሙም አመራር ያስፈልጋል፡፡ በሁከት ስንት ኢንቨስትመንት ተቃጥሏል እኮ። እነሱን እራሱ ወደ ስራ ለማስገባት ስንት ጊዜ ነው የሚያስፈልገው? መጨመር ነው እንጂ የሚገባን የያዝነውን ማጥፋት አይደለም፡፡ ብዙ ጠፍቷል፡፡ ይሄን እያየ አዲስ ኢንቨስተር ሊመጣ አይችልም፡፡ እስኪ ይረጋጋ ነው የሚለው ስለዚህ የነበረውን ፍጥነት የሚያቀዘቅዝ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሁን መፈናቀል ነው የበዛው፤ መፈናቀል መብዛት ማለት ኢንቨስትመንትም የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡
ይሄ ክልል እየተንቀሳቀሰ ነው ስንልም ችግሩ በአገር ደረጃ መስመር ካልያዝ መጐዳቱ አይቀርም፡፡ ይሄ የተሻለ ነው የምንለው በንጽጽር ነው እንጂ ተያይዞ ነው የሚወድቀው፡፡













Read 13950 times