Sunday, 03 March 2019 00:00

“ኦዴፓ” - የተከበበው ነብር!

Written by 
Rate this item
(3 votes)


የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ኢ.ላኔ፤ “መንግሥትና ሕዝብ ከሚነጣጠሉባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሳይቆም ሲቀር፣ ህዝቡ መንግሥት ስለ እኔ ጉዳይ ደንታ የለውም ብሎ ሲያስብ ነው” ይላሉ፡፡
መንግሥትን ህዝብ የሚከተለው፣ የሚያጅበውና ከጐኑ የሚቆመው፣ ለኔ ጥቅም የቆመ፣ ደህንነቴን የሚጠብቅና እኔን አሳታፊ ያደርጋል ብሎ ካሰበ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ በቸልተኝነት ቆሞ ያያል፤ አደጋ የተጋረጠበት መስሎ ከታየው፣ ያንን አደጋ ለማስወገድ፣ አደጋ ፈጣሪው መንግሥት የሚወድቅበትን መንገድ ያሰላስላል፡፡ መንግሥት ወዳጁ ካልሆነና በጠላት ዐይን ካየው፣ የጠላቱን ጠላት ለመወዳጀት ቀዳዳና ዕድል እስከ መፈለግ ይደርሳል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ መንግሥታት ሁሉ ህዝብን ከጐናቸው ያሰለፉ ሳይሆን በጐናቸው ጠመንጃና ሽጉጥ የታጠቁ ስለነበሩ፣ መጨረሻቸው በክብር አልተደመደመም፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ የመንግሥት ቁንጮ የነበረው የወያኔ ቡድን፣ ሥልጣኑን እንደ ቀልድ የተነጠቀው፣ ለሕዝብ ዕድል ባለመስጠቱና ለሌሎች ሃሳቦች ጆሮውን ደፍኖ፣ የራሱን ዘፈን በመስማቱ ነው፡፡ “ያለ እኔ ጀግናና ብልህ የለም” ብሎ በማሰቡ፣ ዛሬ ያ ሁሉ ትዕቢት አልፎ የተነፈሰ ፊኛ ሆኗል፡፡ ታዲያ ይህ ጉዳይ ያለ ጦርነትና ዕልቂት እንዲህ ይሆናል ብሎ ማሰብ ለልቡና በእጅጉ የራቀ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር በወያኔ የሚመራው መንግሥት፣ ስግብግብነቱን ትቶ ለጋራ ጥቅማችን ቢሰራ ኖሮ፣ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ የተመቻቸ አጋጣሚና ዕድል ነበረው፡፡
አሁን በወያኔ ቁንጮነት ቦታ የተተካው “ኦዴፓ” የተባለው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ለዚህ ለውጥ ግንባር ቀደም መሪ ሆኖ፣ አፈትልኮ ሲወጣ፣ በሟቹ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው የሚመራው የ”ኦዴፓ” (አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ቡድንም አብሮት ነበር፡፡ ይሁንና የአማራው ፓርቲ በብዙ የሕወሓት ሰዎች ተጠፍንጐ ስለነበር፣ በቀላሉ ጠርቶ መውጣት አልቻለም፡፡ ስለዚህም ቀደም ሲል በኦነግ ሰበብ ሲታሠርና ሲገደል የነበረውን የኦሮሞ ወጣት በማደራጀት፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ትግሉን አጧጡፎ ከሄደ በኋላ፣ በሁለቱ ትልልቅ ብሔሮች መካከል በተፈጠረው አንድነት፤ አሮጌውን የጭቆና ቀንበር ሰብረው መውጣት ችለዋል፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ ግንባር ቀደም መሪው የያኔው ኦህዴድ፣ ያሁኑ ኦዴፓ - ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በተለይ በሁለቱ ትንታግ መሪዎች፣ ሁሉን አቀፍ ሃሳብና ንግግር፣ ከዳር እስከ ዳር ህዝቡን ነቅንቆ ከጐኑ ማሳለፍ ችሏል፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ፣ የትኛውንም መሪ ከተቀበለበት ፍቅርና አድናቆት በተለየ ሁኔታ፣ በጊዜው የለውጡን ሃሳብ ይዘው አደባባይ የታዩትን አቶ ለማ መገርሳን በታላቅ ጭብጨባና ሆታ አጀባቸው፡፡ ህዝቡ የራሱን ብሔር ትቶ እንደ ብሔራቸው ሆነ፡፡ ሀገራችንን ወደ ቀድሞ ክብር የሚመልሱ፣ ህልም ያላቸው፣ ምናልባትም ከመለኮት የተላኩ ሰዎች መጡልን ብሎ አጨበጨበ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የምንደነቅበት የአቶ አዲሱ አረጋ ድፍረት የተሞላና በጥበብ ያጌጠ ንግግር፣ የወያኔ ሥልጣን ሳይላላ፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ ሲነበነብ ተዓምር ተባለ፡፡ በርግጥም የኢትዮጵያ ህዝብ ንግሥት እንዳገኘ ንብ፤ ወደ አንድ አቅጣጫ ተመመ፡፡ ሁላችንም ያለንን ይዘን ከኦዴፓ ጐን ተሠለፍን፡፡ የደስታ እንባ ጉንጮቻችንን አጠባቸው፡፡ ሳቃችን ከከንፈሮቻችን እንደ አዲስ ተወለዱ፤ የተስፋ እሸቶች ታቅፈን፣ ዳር እስከ ዳር እልልል አልን፡፡ በብሔር ቁርኝነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ደም ተቀላቀልን ብለን በመሪዎቻችን ኮራን፡፡
በተለይ በየአደባባዩ ላይ ያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮችና ሃሳቦች በእጅጉ ቀልብ ሳቢ እንጂ ከፋፋይና አግላይ ስላልነበሩ፣ አንድም ሰው ስለ ብሔር አላሰበም፡፡
ስለዚህም መሠለኝ … ገጣሚ መንገሻ ክንፉ፤ “እምባም ይናገራል” በሚል መጽሐፉ ውስጥ በአንዱ ግጥም እንዲህ ያለው፡-
ነቢዩ ቢወለድ ከትግራይ ኦሮሞ
ከጉራጌ አማራ አለዚያም ከጋሞ
በጭንቃችን ጊዜ ከኛ ጋር ታድሞ
ስናለቅስ አልቅሶ፤ ስንታመም ታሞ
በይቅር ባይነት ከፈታው ህልማችን
ዘመን ካሻገረው ካደሰው ተስፋችን
በሰላም በፍቅር በአንድ ከደመረን
በአረንጊዴ ቢጫ በቀይ ካሰመረን፡፡
እኛ ከግብሩ እንጂ ከዘሩ ምን አለን፡፡
አሥር ወራት ያህል ያስቆጠረው በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት፤ በህዝቡ ውስጥ ያሳደረው እምነትና ፍቅር ቀላል አልነበረም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከታታይ የወሰዷቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች፣ የለውጡን ተዓማኒነት ከፍ አድርጎታል፡፡ ለውጡም የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ እንዲሠማን በማድረጋቸው፣ ሁላችንም ለውጡን ለማገዝ የምንችለውን ሁሉ ያደረግን ይመስለኛል፡፡ ይህ ሲሆን የለውጡ መሪዎች፣ የተሳሳቱትና ዋጋ የከፈልንበት ነገር አልነበረም ብለን አንክድም፡፡ በተለይ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ፓርቲዎችን አቀባበል አስመልክቶና ያልተጠናና በዘፈቀደ የተሠራ የሚመስለው ልቅ አካሄድ፤ እኛንና መንግሥትን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ምናልባትም ብዙ የለውጡ ደጋፊ የሚመስሉ ሰዎች፤ ለውጡን እንደ ሁለተኛ አማራጭ እንደቆጠሩት የሚያሳዩ ፍንጮችን አጢነናል፡፡ ይህንን ለማወቅ በማህበራዊ ሚዲያ የ“ቲም ለማ” ደጋፊዎች የሚመስሉ ሰዎች፣ አፈሙዛቸውን ወደ ለውጡ ደጋፊዎች አዙረው እንደነበር ልብ ማለት ብቻ ይበቃል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በሀገር ደረጃ ያመጣውን መሳከር ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ብቻ ልብ ብለን ስናየው፣ በለውጡ ሂደት መንግሥት ላይ አንዳች ቸልተኝነትና የበዛ ትዕግስት አይተናል፡፡ ለምን እንደሆን ባይገባኝም ፖለቲካ ባለፈበት ያላለፍነው እኛ የምንጠርጥረውን ነገር፤ መንግሥትን የሚመሩ ሰዎች ለዚያውም በሀገር ደህንነት ላይ ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው መሪዎቻችን ሲሳሳቱ እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ውስብስብ ሀገር ጣጣ፣ ልክ የለሽ ስለሆነ ሥራ በዝቶባቸው ይሆናል ብለን ስናልፍ ቆይተናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ “ኦዴፓ” ሸክሙ ብዙ፣ ጣጣው እልፍ ነው፡፡ ሲጀምር ኦዴፓ የለውጡ ተወርዋሪ አልፎ፣ ዛሬ ግን የተከበበ ነብር ነው፡፡ ግራና ቀኙ በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው፡፡
በተለይ ከሌሎቹ የኦሮሞ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ጋር ሲነፃፀር፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት በጥርጣሬ የተሞላ ነው፡፡ ፓርቲው ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የዛሬው በጡረታ የተሰናበተው የሕወሓት አክራሪ ቡድን ተለጣፊና መሣሪያ ስለነበር፣ በሕዝቡ ዘንድ የዛሬ የለውጥ ፊቱ ብቻ ሳይሆን የትናንት የግፍ ጠባሳው ይነበባል፡፡ “ዛሬ ተለውጠናል” ቢሉም፣ ትናንት ካድሬዎቹ ያደረሱበትን እሥራት፣ ግድያና እንግልት እያሰበ ህዝቡ ልቡን አልሰጣቸውም፡፡ አብዛኛውን የቀድሞ ካድሬዎቹን ነቅሎ ያባረረው የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን፤ ዛሬም በተለይ ወደ ታቹ ብዙ አሰስ ገሠሥ እንዳለው፣ ወደ ገጠር ወጣ ያለ ሰው ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡
ኦዴፓን፤ የቀድሞ ጠባሳው ያመጣበት ጣጣ ያለመታመን ብቻ አይደለም፡፡ በሀገራዊ አመራር ላይ መቀመጡ ወዲያና ወዲህ እንዲሳቀልና ባተሌ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተለይ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለሚኖረው ውድድር ለመዘጋጀት፣ በእጁ ላይ ከወደቀው የሰማንያ ብሔር ብሔረሰቦች ዕድልና አደራ ጋር ሥራውን አከብዶታል፡፡
እውነት ለመናገር የዶክተር ዐቢይ መንግሥት፤ ህዝባዊ ድጋፍ፣ ከኦሮሚያ ክልል ባለፈ መላው ኢትዮጵያን የሞላ ነበር፡፡ በተለይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ህዝቡን ሳይገምሰው በፊት! ታዲያ - በዚህ መከበብ ምክንያት ትናንት ለውጡን በእጁ በማስገባት በወኔ ይወረወር የነበረው ነብር (ኦዴፓ)፤ ዛሬ ብዥታ የገጠመው ይመስላል፡፡
ለዚህ ብዥታ ደግሞ ከላይ ከጠቀስኳቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ሌላው የቀደመውን ታሪኩን ስስነት ያዩ አክቲቪስቶችና ፓርቲዎች መሀል እየገቡ፣ ከህዝብ ጋር ያለውን ህብረት ሊነጥቁ መሞከራቸው ነው፡፡ በተለይ ቁጥራቸው የበዛ ሚዲያዎች ባሉበት ዘመን፣ የብሔር ግጭትን የሚፈጥሩ ንግግሮችንና የጥላቻ ታሪኮችን እየመዘዙ፣ ያጠበውን ልብ የሚያቆሽሹበት ስለበረከቱ ጉዞው እንቀፋት በዝቶበታል፡፡ አንዳንዴም ነገ ሊመርጠው የሚችለው የኦሮሞን ህዝብ ድጋፍ እንዳያጣ ሲል በሚወስዳቸው ወጣ ያሉ እርምጃዎች፣ የሌላውን ወገን አጋርነት እየተነጠቀ እንደሆነ እያየን ነው፡፡
ይህ ትግልና ፍልሚያ ደግሞ የአማራው ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሠረተ በኋላ ይበልጥ እያሰጋና እያስፈራ መጥቷል፡፡ ትግራይ መሽገው ፍላፃቸውን የሚልኩት ሰዎች፣ የሚሠሩት ሴራ እንዳለ ሆኖ “ለኦሮሞ ህዝብና ለእኛ ብቻ” የሚል ስግብግብ ቅዠት ያላቸው ሰዎች ቅብጠት ኦዴፓን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው፡፡
“ለውጡ የሁላችንም የትግል ውጤት ነው” የሚለውን የለማ መገርሳን ቡድን ሃሳብ ትተው፣ “እኛ ብቻ ነን” የሚል የተንሻፈፈና መረጃ የሌለው ወሬ የሚያወሩ ጽንፈኞች፣ ለውጡን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ወደለየለት ጥፋት እንደሚመሩ ባለማወቃቸው ተስፋችንን እያጨለሙና ታሪካችንን እያጠለሹ ነው። እነዚህ “የለውጡ ጌቶች” ነን የሚሉ ሠካራሞች፤ ለውጡ በብዙ ተግዳሮትና ፈተና እንደተከበበ እንኳ ማስተዋል የተሳናቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በብዙ ቢሊዮን ብሮች ኪሱ ያበጠውና ዛሬም የትግራይን ህዝብ በር ዘግቶ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ የጠላትነት መንፈስ እየጫረ፣ ለጦርነት የሚያዘጋጀው ቡድን ጠመንጃ ታጣቂ መሆኑን ማሰብ የዘነጉ ይመስላሉ፡፡
እንግዲህ - “ኦዴፓ” የተከበበ የመሠለኝ በነዚህና መሰል ጉዳዮች ነው፡፡ ከሁሉ ይልቅ ይህንን እንድቀበል ያደረገኝ የሰሞኑ የለገጣፎ ቤት የማፍረስ ጉዳይ ነው፡፡
የሕዝብ ጥቅምንና መብት እንተወውና ለራሱ ለመንግሥትስ ቢሆን ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው፣ ባላንጣዎችና ፈተናዎች እያሉበት የፀብና ሽንቁሮችን እድል መድፈን እንጂ ሌላ ቀዳዳ መክፈት ያስፈልገዋል? ደግሞስ በየጊዜው በገንዘብ እየተገዙ ሕዝብ መግደልና ማፈናቀል ሥራዬ ብለው የሚሠሩ ሰዎች እያሉ ሌላ በፍቃደኝነት ቦንብ የሚጥል ሠራዊት ማዘጋጀት ከአንድ ሀገር የሚመራ መንግሥት ይጠበቃል?
ያ - ብቻ አይደለም፣ ችግሮች በተፈጠሩ ጊዜ መግለጫ የሚሰጡ ሰዎች የንግግር ሥልጠናና ስልት ሊሰጣቸው አይገባም? ከአቶ አዲሱ አረጋ በቀር ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ የሚሰጡ የ”ኦዴፓ” አባላት ሁሉ የፓርቲውን አቋም መግለጥ የማይችሉና የጽንፈኞችን ድምፀት የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡ እንደኔ - እንደኔ በንግግር ጊዜ ከድምፀት ጀምሮ፣ የመንግሥትን ተቀባይነትና ድጋፍ የሚያጠናክሩ እንጂ በጥላቻ እሳት ላይ የሚጥሉ መሆን የለባቸውም፡፡
ይህ በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መንግሥት ለገጣፎ ላይ ስለፈፀመው ጥፋት ነገር ሺህ ነገር ስለተነገረ ደግሜ ማውራት አልፈልግም፤ ግን፣ የጊዜውን ሁኔታና ዐውድ ያልተከተለ፣ ጥበብ የጐደለውና ሀገርን በቀዳሚነት ከሚመራ ፓርቲ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ እንደ ኦቦ ለማ መገርሳ ካለ የሰለጠነ መሪ፤ ሊወጣ የሚገባው ጭካኔም አይመስለኝም፡፡ ምክንያታዊ ቢሆን እንኳ፤ የሚከወንበት መንገድና የሚሰጠው መግለጫ ይህን የመሰለ ቀሽምና ተዐማኒነት የጐደለው መሆን የለበትም፡፡ ስለ ኦሮሞ ገበሬ መሬት ያላግባብ መነጠቅን እንደ ሰበብ እንኳ ብናይ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጮህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ማለትም አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራዜና ሌሎችንም ይመለከተናል፡፡ እንደኔ እንደኔ የተፈናቀሉት የኦሮሞ አርሶ አደሮች ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ የምንጠቀምበት ሳይሆን፣ ዛሬም በቀጥታ የሚካሉበት መንገድ መፈጠር አለበት። የጥበቃ ሰራተኛ ሆነው የተጣትና ልጆቸውን ማስተማር የተሳናቸው ሰዎች ህይወታቸው መለወጥ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝብን ካስተባበርን ይህ ጉዳይ የማይሰማው ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡
ስለ ኦዴፓ ሳስብ አንድ አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ትዝ ይሉኛል፡፡ እኒህ ፕሬዚዳንት ዋይት ሀውስ ውስጥ ባሳለፉባቸው ዐመታት ሁሉ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ መቀበል ያቃታቸው፣ ወይም ህልም የመሰላቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ “ማስታወቂያ ሲያነብቡ፣ “ክቡር ፕሬዚዳንት” ሲባሉ ሌላ ሰው እና መሰላቸው ይደነግጡ እንደነበር ራሳቸው በአንደበታቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ኦዴፓም የዚህን ዓይነት ችግር ውስጥ ያለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሲነጋገርና ሲከራከር ወክልሉ ላይ ነው፡፡ እውነቱ ግን ያ አይደለም፡፡ የትናንቱ የሕወሓት ወንበር ዛሬ የ“ኦዴፓ” ነው፡፡ ልዩነቱ ሕወሓት በጦር ግንባር ታግሎ ወደ ሥልጣን መሪነት መጣ፡፡ ኦዴፓ ደግሞ በሰለጠነ መንገድ በፖለቲካ የበላይነት አግኝቶ በህወሓት እግር ተተካ። ስለዚህ ኦዴፓ ዛሬ የኢትዮጰየውያን መሪ ፓርቲም እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ፓርቲና መሪ ብቻ እንዳልሆነ ደጋግሞ ሊያስብ ይገባል፡፡
በብዙ ባላንጣዎች የተከበበው ይህ ነብር ራሱን መሬት ላይ አስቀምጦ ወደ ጐን ከማየት ይልቅ ዛፉ ላይ ወጥቶ ወደፊት ማየት አለበት፡፡ ህልሙ እውን የሚሆነው ይሄኔ ነውና!  
በተረፈ ሁላችንም አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ሳንል፣ በፍቅር በይቅርታና በመቀባል ሀገራችንን በጋራ ለመገንባት መነሳት ይኖርብናል፡፡   


Read 2006 times