Wednesday, 06 March 2019 10:08

አዲሱ ፓርቲ፤ ይመጣልናል ወይስ ይመጣብናል?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና በጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸው፣ ከአምስቱ ክልሎች ማለትም ከጋምቤላ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከሶማሊያ፣ ከአፋርና ከሐረሪ ከመጡ ሰዎች ጋር በጽ/ቤታቸው ሰሞኑን ተወያይተዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ የመጡበት ብሔር ቢኖርም የመጡት የብሔር ውክልናን ለማጋነን ስላልሆነ፣ የየብሔራቸው ተወካይ አድርጌ ላያቸው አልፈለግሁም፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበሩ በመጪው ጊዜ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶች የሚለው አጠራርም አሠራርም እንደሚቀር፣ ኢሕአዴግ ፈርሶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፉበት ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ እንደሚደራጅ፣ ለዚሁም ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጠዋል፡፡ የእነሱም ለስብሰባ መቀመጥ ለአዲሱ ፓርቲ ምሥረታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ የኢሕአዴግን ሞት ለምንመኝ ለእኔና ለእኔ ቢጤዎች፤ ትልቅ የምሥራች መሆኑን የምገልጠው በድርብ መስመር ነው፡፡ የኢሕአዴግ መፍረስና በአዲስ ፓርቲ መተካት እፎይ የሚያሰኝ እርምጃ የሚሆነው፣ አዲሱ ፓርቲ ከኢሕአዴግ ተውሳክ የፀዳ ከሆነ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ተውሳክ ምንድነው የሚለውን እመለስበታለሁ፡፡ ከዚያ በፊት እንደ እኔ ለውጥ ለሚፈልጉት ሁሉ አንድ ነገር ላስገንዝብ፡፡
መዲናችንን አዲስ አበባን እንደ ሞዴል እንውሰድ። አዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ልደታ፣ ጉለሌ፣ የካ፣ ቦሌ ወዘተ የሚባሉ ክፍለ ከተሞች አሏት፡፡ የየካ ኗሪ ሕዝብ የቦሌን፣ የየካው የላፍቶን ኗሪ አይተካም፡፡ ቢቆጠር ቢመዘገብ፣ የሚቆጠረውና የሚመዘገበው በዚያው በሚኖርበት በቦሌ፣ በየካ፣ በልደታ ወዘተ ነው፡፡ አዲሱ ፓርቲም ሲደራጅ አባል የሚያደርጋቸው ሰዎች፣ ፓርቲው የሚደራጅበት አካባቢ ሰዎች መሆናቸው ግድ ነው፡፡ ወላይታ ላይ የወላይታ ተወላጆች ቢበዙ ኃጢያት ሊሆን አይችልም፡፡ የከፋ ኃጢያት የሚሆነው እዚያ አካባቢ የሚኖር ትግሬ፣ ጉራጌ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ወዘተ አባል እንዳይሆን ሲገፋና በፓርቲው የሥልጣን ድልድል ውስጥ  ወደ ዳር ሲገፋ፣ እሱ የተሻለ ብቃት ኖሮት፣ በአካባቢ ስሜት ምክንያት ከጨዋታ ውጪ ሲደረግ ነው፡፡ ስለዚህም የፓርቲው አደራጆች አስቀድመው ሊዘጋጁበት የሚገባው መጪውን ፓርቲ እስከ አሁን ስናያቸው ከኖርነው የቤተሰብና የጓደኛ ሰብስቢነት የፀዳ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ይህ በቤተ ሕወሓት ሲጠና፣ በሌሎችም ዘንድ ያለ ተወሳክ በመሆኑ ወደ አዲሱ ፓርቲ እንዳይዛመት በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ደርግ የጀመረው ኢሕአዴግ የወረሰው ልማድ አለ፡፡ ኢሕአፓና ሌሎች ተቃዋሚዎች፤ ደርግን ፋሽሽስትና አምባገነን ብለው በመፈረጃቸው፣ ከደርግ ጐን መሰለፍ የሚያስፈራ ነበር፡፡ “ባንዳ” የሚል ቅፅል ስምም ያሰጥ ነበር፡፡ ስለዚህም በፈቃደኝነት አባል የሚሆን ያጣው ደርግ፤ በሁለት እጁ ካሮት እና ዱላ ይዞ ብቅ አለ፡፡ በፊት ሰደድ በኋላ የኢሠፓ አባል መሆን መጀመሪያ በቀይ ሽብር ከመመታት ያድናል፤ ቀጥሎ ሥልጣንና ሹመት ያስገኛል፡፡ ሥልጣኑም ሹመቱ ቢቀር ቢያንስ በሥራ ላይ ለመቆየት የእለት እንጀራ ለመብላት ያገለግላል፡፡
በዘመነ ኢሕአዴግ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ እንኳን በመንግሥቱ መ/ቤት፣ በአምራችና በጥቃቅን ተደራጅቶ እራስን ለመጥቀም፣ ባዶ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ የሚጠብቀው ምርጫ፤ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የአንዱ አባል ወይም ደጋፊ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ይህ በክልል ፓርቲዎችም ዘንድ የታወቀና የተለመደ የተዘወተረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን አለማድረግ ሁሉንም ነገር ያሳጣል፡፡  የሚመጣው አዲስ ፓርቲ መነገጃ ላለመሆኑ ሕዝብ ማረጋገጫ ይፈልጋል፡፡ እኔም እፈልጋለሁ፡፡
እዚህ ላይ ወዳጅ ብዙአየሁ ወንድሙ በአንድ ወቅት ያሰፈረው ሃሳብ ትዝ አለኝ፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም መንፈሱ እንዲህ የሚል ነው፡፡
“ኢሕአዴግ ኪራይ ሰብሳቢነትን እቃወማለሁ ይላል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አባላት አባል የሚሆኑት ሹመት ለማግኘት፣ እድገታቸውን ለመጠበቅ፣ የታክስና የግብር ቅናሽ ለማግኘት፣ ጨረታ አሸንፎ ለመጠቀም ወዘተ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ ክራይ ሰብሳቢነት አለ?”
ከዚህ ቀደም የነበረው የኢሕአዴግና የአጋር ድርጅቶች የአባላት ምልመላ፣ በፓርቲው ፕሮግራም የማመንና ለፕሮግራሙ ተፈፃሚነት የመቆም ሳይሆን አባል በመሆን የመጠቀም ነው፡፡ ይህ ተለውጦ የአዲሱ ፓርቲ አባላት የአላማ ሰዎች ይሆኑ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ያለ ጥርጥር ታጥቦ ጭቃ መሆን ይከተላል፡፡
በሀገራችን የዲሞክራሲ ደብዛ የጠፋው ሁሉም ቦታ በፓርቲ ሰዎች በመወረሩና ነፃ የሙያ ማህበራት ባለመኖራቸው ነው፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት መሪዎች ወደውም ተገደውም የድርጅቶች አባል ይሆናሉ፡፡ የድርጅት አጀንዳ አስፈፃሚም በመሆን እንዲቆሙ ይገደዳሉ፡፡ ደርግ ይህን ያደርግ ነበር፤ ኢሕአዴግና አጋሮቹ ይህንን ሲያደርጉ ኖረዋል። መጪው ፓርቲም እንዲህ ያደርግ ዘንድ የሚቀፈድ ከሆነ ለውጡ ምን ላይ ነው? ብሎ አምርሮ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
የመንግሥትና የፓርቲ አለመለያየት፣ በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኙ የመንግሥት ንብረት ያለ ገደብ መገልገል፤ ኢሕአዴግ ከደርግ የወረሰውና ዛሬም ድረስ እየሠራበት ያለው መንገድ ነው፡፡ አዲሱ ፓርቲ ከዚህ ወንጀል የፀዳ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ እዚህ ላይ አዲሱ ፓርቲ ሊያስብበት የሚገባው፣ እሱ በአገሪቱ ካሉ ፓርቲዎች በላይ ይሆን ዘንድ የተለየ መብት የሚሰጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሕግ የለም፡፡ እራሱን የተለየ ተጠቃሚ የሚያደርገውን የኢሕአዴግን አሠራር  ማረም አለበት፡፡
ይህ ፓርቲው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሚያደርገውን የተለየ ተጠቃሚነት ከማስቀረት መጀመር አለበት፡፡ የእሱን ሙሉ መግለጫ የሚያነቡ የመንግሥት የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሌሎችንም መግለጫ ሙሉውን ማንበብ አለባቸው። አዲሱ ፓርቲ ደቦውን እየገመደለ ለራሱ የሚያደርግ ከሆነ ባይፈጠር፣ ከተፈጠረም ቢጨነግፍ ሺህ ጊዜ ደስ ይለኛል፡፡
ይህ ብዙዎቻችን ስንሰማው የኖርነውና የታዘብነውም ነው፡፡ የፓርቲ አባል መሆን አላማን ለማስፈፀም ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ለመሥራት ያልተገደበ መብት ያጐናጽፋል፡፡
 የመንግሥት ንብረት ያባክኑ፣ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ የተጠቀሙ ወደ ፍ/ቤት ሳይሆን በፓርቲ ግምገማ ከነበሩበት ቢሮ ወደ ሌላኛው ወደማይታወቁበት ይዛወራሉ፡፡ ፋይላቸው ይጠፋል ወይም ደግሞ ቅጣታቸው ከዶሮ ላባ የቀለለ ይሆንላቸዋል፡፡
ተመሳሳይ ጥፋት የፈፀሙ ግለሰቦች፣ እንደ አውሬ ታድነው ወደ እስር ቤት ሲወረወሩ፣ የፓርቲ አባል የሆኑት ከነወንጀላቸው በአደባባይ ሲንጐማለሉ ይውላሉ፡፡ የሚቋቋመው አዲስ ፓርቲ ይህን ለማስቀጠል የሚመጣ ከሆነ ይቅርብን፡፡
ያሉንና የነበሩን ፓርቲዎች፣ ሰውን በፋብሪካ የተመረቱ ቁስ አድርገው የሚያስቡ፣ የአባሎቻቸውን የሃሳብ ነፃነት የማያውቁና የማያከብሩ ናቸው፡፡ መጪው ፓርቲ እንዲህ የሚሆን ከሆነ፣ ኢህአዴግ ምን በደለ ሊያሰኝ ይችላል፡፡ እኔ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ አዲሱ ፓርቲ ይመጣልናል ወይስ ይመጣብናል?  







Read 4840 times