Print this page
Sunday, 03 March 2019 00:00

ክብረት የአድዋ ዕለት

Written by  ታምራት ደሳለኝ (የሜ)
Rate this item
(6 votes)

ክብረት ይባላል ባለታሪኩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዕድሜው አርባዎቹን አጋምሷል፡፡ ከአዲሳባ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ የዞን ከተማ ውስጥ ነዋሪ ነው፡፡ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት አንድ እግሩን ያጣ ወታደር ነው፡፡ መኖሪያው ከወላጆቹ በወረሰው ቤት ለብቻው ሲሆን ወጣ ብሎ  ከልብስ መሸጫ ሱቆች አጠገብ፣ በልብስ ስፌት መኪናው እየሰራ ይተዳደራል፡፡
ክብረት ልዩ ባህሪው፣  ስለ ሃገር ፍቅር ያለው ከፍተኛ ስሜትና አገሩን በተመለከተ ተከራክሮም ሆነ አውርቶ የማይጠግብ መሆኑ ነው፡፡ አያቱ፤ የአንድ ታዋቂ አርበኛ፣ ተወዳጅና የቅርብ ወታደር ሆነው፣ ፋሺስት ኢጣሊያን፣ በአምስት አመቱ የሽምቅ ውጊያ አርፎ እንዳይቀመጥ፣ የራሳቸውን ድርሻ የተወጡ ጀግና ናቸው፡፡ የልጅ ልጃቸው ክብረት፣ በአያቱ ታሪክ ይኮራል፤ መኩራት ብቻም ሳይሆን አንዳንዴም ሲምል፣ “ግራዝማች ደለሳ ጎቤ ይሙት!” እያለ ነው፡፡
በመኖሪያ ቤቱ ግርግዳ ላይ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ አጼዎችና ታላላቅ ጀግኖች ምስል አይጠፋም፤ ብቻ ክብረት ታምሩ የዛሬ ታሪክ የሌለው የሚለውን ትውልድ ነቃፊና ሃገራቸውን ከጠላት ወረራ ያስጣሉ አያት ቅድመ አያቶች አፍቃሪ ነው። ዛሬ ደግሞ የአድዋ ድል የተፈጸመበት 120ኛ ዓመት ታስቦ የሚውልበት ቀን ነው። ክብረት ማለዳ ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ፊቱ ጭፍግግ እንዳለ ነበር፤ ሰውነቱ ተጫጭኖታል። ይሄን ሶስት ቀናት ሌሊቱን ሲያቃዠው ነው የሰነበተው፤ ጭልጥ አድርጎ የሚወስድ እንቅልፍ ናፍቆታል። ሶስቱንም ቀናት የሚታየው ህልም ደግሞ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ጭልጥ ባለ በረሃማ ሜዳ ላይ ብቻውን ሆኖ፣ ከኋላ በርካታ ጦረኛ ሰራዊት ያባርረዋል፤ ዞሮ ሲመለከት አቤት መብዛታቸው! አቤት አስፈሪ ያመረረ ፊታቸው! አመጣጣቸው! ወደ ኋላ የሚሉ እንዳልሆነ ያስታውቃል፤ ደም የጠማቸው ናቸው፡፡ እሱ ከፊት ይሮጣል፤ ነፍሱን አያውቅም፤ እነሱም ያለ ርህራሄ ይከተሉታል፤ ይሮጣል፤ ይሮጣል…፤ በዚህ መሃል ከፊት ለፊቱ ከመቶ ሜትር ርቀት አካባቢ ከተቆፈረ የጉድጓድ ምሽግ፣ በርካታ ወታደሮች  ወደ እሱ አቅጣጫ እየመጡ ተመለከተ፤ ልብሳቸው አንድ አይነት ነው፡፡ ልክ በረሃማውን አፈር የሚመስል ቡላ ዳለቻ ቀለም ያለው፤ ጨነቀው። ወደ ኋላ ዞሮ ሲመለከት፣ እነኛ ቁጥራቸው ለመገመት የሚያዳግት ፊታቸው እልህና ሞት ሞት የሸተታቸው የሚመስሉት ሰራዊት አባላት ደርሰውበታል፡፡ ከፊቱ ደግሞ ከምሽጋቸው የወጡት ወታደሮች የጥይት ሩምታ ማዝነብ ጀምረዋል፡፡ የሚያደርገው ሲጠፋው፤ ወደ መሬት ተደፋና አሸዋማ ምድሩ ውስጥ አይኑን ጨፍኖ ጭንቅላቱን ያዘና እሪታውን አቀለጠው፡፡ ከተደፋበት መሬት ውስጥ ግን በቀይ ቀለም፣ በጉልህ የተጻፈ፣ 23 ቁጥር ይታየዋል። መደቡ ጥቁር ሆኖ እንደ ፍም እሳት መልክ ያለው፣ 23 ቁጥር!  ይሄንን ሲመለከት እንደ መረጋጋት ተሰምቶት፣ ቁጥሩን ለመንካት እጁን ቢሰድድ ግን ሊነካው አልቻለም፤ በዚህ ጊዜ እኩለ ሌሊት መሆኑን ከእንቅልፉ ነቅቶ ይረዳል። ሰውነቱ በሙሉ በላብ ተጠምቋል፤ እያማተበ ይተኛና፣ ትንሽ ቆይቶ፣ ተመልሶ እንቅልፍ ይወስደዋል፡፡
አሁን ደግሞ በኮረብታማና ጢሻማ መልክዓ ምድር ላይ ብቻውን እየሮጠ ነው፡፡ ከኋላ የሚከተሉት ወታደሮች እያለሙ፣ ጭንቅላቱን ሊነድሉት ይተኩሳሉ፡፡ እሱ ጢሻዎቹን  ይዘላል፤ በኮረብታ መሬቶች ይሽሎኮሎካል፤ ነፍሱን አያውቀውም፤ ይሮጣል፤ ይሮጣል… የተተኮሱት ጥይቶች፣ በአናቱ በኩል በግራና በቀኝ ትከሻዎች እየተወናጨፉ ሲያልፉ ይሰማዋል፤ እሱ ግን ነፍሱ እስከሚጠፋ ይሮጣል፡፡ በዚህ መሃል ግን ከትልቅ ኮረብታ ግርጌ ሲደርስ፣ ከኮረብታው አናት ላይ ግዙፍ ቋጥኝ፣ ማን እንደላከው ሳያውቅ፣ እየተንደረደረ ሊጨፈልቀው፣ ግልብጥ ብሎ ይመጣል፤ ለጥቂት ወደ ጎን በመፈናጠር  ያመልጠዋል፤ወዲያው ሌላ ቋጥኝ እየተንደረደረ፣ ተንዶ ይመጣል፤ ያመልጠዋል፤ ሌሎችም እንደ ናዳ እየተከታተሉ ወደርሱ ሲንደረደሩ፣ ከአቅሙ በላይ ሆኖበት፣ አናቱን እንደያዘ፣ ወደ መሬት ተደፍቶ፣ ኡኡ ብሎ ይጮሃል፤ ከዛም 23 ቁጥሩ፣ በመሬቱ ውስጥ ደምቆ ይታየዋል፤ ከእንቅልፉ ባንኖ ይነቃል። ያማትባል፤ ተመልሶ ለመተኛት ረዥም ጊዜ ይወስድበታል፡፡ 23 ቁጥሩ ግን ትርጉሙ ግራ አጋብቶታል። በሁለቱም ህልሞቹ፣ ከመሬቱ ውስጥ ያየው በደማቅ ቀይ ቀለም ጎልቶ የተጻፈው 23 ቁጥር ከነቃም በኋላ ቁልጭ ብሎ ይታየዋል፤ ውብ ሁለትና ሶስት ቁጥሮች ጎን ለጎን ሆነው፡፡
ይሄ እንግዲህ ክብረት ላለፉት ሶስት ቀናት የታየው፣፣ ህልምና የቃዠበት ትርኢት ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ህልም ነው በሚል ችላ ብሎት፣ ህልም ፈቺ አፈላልጎ ባይጠይቅም፣ 23 ቁጥሩ ግን ከዛሬ የአድዋ ዕለት የካቲት 23 ጋር መግጠሙ የሆነ የተለየ ነገር፣ ይኖረው እንደሆነ ተጠራጠረ። የተለየ ከእለቱ ጋር የተያያዘ ነገር ቢኖረው እንኳን፣ አባቶቻችን ደማቅ ታሪክ የሰሩበት  የድል ቀን እንደመሆኑ፣ ለክፉ ሳይሆን የበጎ እድል ማሳያ ሊሆን እንደሚችል አሰበ፡፡ በልቡም ዛሬ የተለየ ነገር እንደሚገጥመው ይሰማዋል። ነገር ግን ወደ ውጪ ለመውጣት አልፈለገም፡፡
ጸሀይቱ በማለዳ የእንቁላል አስኳል መስላ ከአድማሱ ብቅ ብላለች፡፡ ቀጭን ብርሃኗን በየቤቱ ማድረስ ጀምራለች። የአድዋ መታሰቢያ ክብረ በዓል እንደመሆኑ፣ በብሄራዊ ደረጃ ማንኛውም የመንግስት ቢሮዎች፣ ት/ቤቶችና ተቋማት እንዲሁም አብዛኛው የዕለት ተዕለት የአዘቦት ስራዎች የሚቆሙበት፣ ዕረፍት ቀን ነው፡፡ በዕለቱ የማለዳዋ ጸሀይ የምትረጨው ብርሃን፣ በውስጡ ከክፍለ ዘመን በፊት፣ አድዋ ተራራ ላይ ያየችውን ገድል፣ ለኢትዮጵያውያን፣ በሹክታ የሚያስታውስ ነገር ያዘለች ትሆናለች፡፡ ዕለቱን ከልቡ ለሚያስብ፣ በዚች ቀን የሚነፍሰው አየር እንኳን ከወትሮ ለየት ያለ፣ በድሉ ምክንያት የተገኘውን ነጻነት አጉልቶ የሚያራግብ ይመስላል፡፡ ነዋሪው ስለታ ሪኩ በአይን እማኝነት የሚያውቀው ባይሆንና እንደ መንፈሳዊ በዓላት፣ በየቤቱ የሚያዘጋጀው የተለየ ነገር ባይኖርምመ፣ በልቡ ግን ሁሉም ስለ አድዋ ድሉ ማሰቡ አይቀርም፡፡ ከማያባራው የህይወት ውጣ ውረድ፣ ለአፍታ ረገብ ብሎ፣  የአያቶቹን ገድል ወደ ኋላ ተጉዞ በአይነ ህሊናው ይታየዋል፡፡ በአጠቃላይ እለቱዋ በትንሹም ቢሆን፣ ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዜጋ፣ የአንድነትና የጥቁርነት፣ ውስጣዊ ስሜትን፣ ከልብ ትጭራለች፡፡
ክብረት ቤቱን ሲያስተካክልና በሚዲያ የሚተላለፉ የአድዋ ድልን የሚዘክሩ ልዩ ልዩ ሰገንታዎችን (ፕሮግራሞችን) ሲከታተል ቆይቶ ወደ በረንዳው ብቅ አለ። ሰውነቱ ከመጫጫን ስሜቱ በተጨማሪ ጎሮሮው ውሃ ለረዥም ጊዜያት እንዳጣ መሬት፣ ከንፈሩ ላንቃው ድረስ ድርቅ ብሏል፤ የሚያርስ እርጥበት ነገር እንደሚያስፈልገው ይሰማዋል፡፡ ልውጣ አልውጣ በሚል ከራሱ ጋር ሲሟገት ቆይቶ፣ እኩለ ቀን ደረሰ፡፡ የተጫጨነ ሰውነቱንና የደረቀ ጎሮሮውን በቆንጆ ጠላ ቢያሟሸው፣ በርግጠኝነት እንደሚሻለው አውቆታል። እናም ከሰዓት በኋላ ወደ ደንበኛው ደብሪቱ ጠላ ቤት ለመሄድ ተነሳ፡፡
ሰማዩ ጥርት ብሎ ጸሀይም ሃይልዋን  ሞቅ አድርጋ፣ ምድር ላይ መስደድ ጀምራለች፡፡ በከተማዋ ውስጥ በብዛት ጠላ ቤቶች የሚገኙበት ሰፈር አለ፤ በየበራፉ እንጨት ቆሞ፣ በአናቱ ላይ አሮጌ ጣሳ እንደ ባርኔጣ ከተደፋበት፣ ከፊቱ ያለው ግቢ፣ ጠላ ቤት መሆኑን ማሳያ ምልክት ነው፤ እናም በዚህ ሰፈር ይሄን መሰል ምልክቶች በብዛት ይታያሉ፤ ከቤቶች መካከልም የክብረት ደንበኛ የሆነችው ደብሪቱ ጠላ መሸጫ፣ አንዱ ነው፡፡
ክብረት በክራንቹ በዝግታ፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች እየተጓዘ ነው፡፡ ለሃገሩ ፍቅር አንድ እግሩን መስዋዕት አድርጎ መስጠቱ የሚያንስ እንጂ የሚቆጨው እንዳልሆነ በኩራት ያወራል፡፡ ብዙ ነቃሾቹ ግን ትርጉም በሌለው የድንበር ጠብ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ሆኖ መቅረቱ በውስጡ እያበገነው፣ እሱ ግን ከማንኛውም ሙሉ አካል ካለው ሰው በላይና፣ ልዩ መሆኑን ለማሳወቅ፣ ለይስሙላ ለሃገር ፍቅር የከፈልኩት እያለ ወሬ ይነዛል ይሉታል፡፡ ይሄ ወሬ ለክብረት፣ ባለው አቅምና ጊዜ፣ ስለ ሃገር ፍቅር የበለጠ እንዲያስብና እንዲያወራ አድርጎታል። ዛሬም ታዲያ በአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን፣ ሳያንገራግር፣ እንደ ዘመን መለወጫና መንፈሳዊ በዓላት፣ ስራውን ትቶ፣ በዓሉን በማሰብ ለማሳለፍ ወስኗል፤
ወደ ደብሪቱ ጠላ ቤት ለመድረስ ሲቃረብ፣ ከአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አጥር ታኮ፣ ባለ ሜዳ ላይ፣ የሰፈሩ ልጆች፣ ኳስ እየተጫወቱ፣ አጋጠሙት፤ ቀርቦ ተጠጋቸውና፤
“ልጆች፤ የዛሬ ቀን የድል በዓል ምን ይባላል?” ሲል ጠየቃቸው
“አድዋ አደዋ” ሲሉ መለሱ፤ የሁለትና ሶስት ልጆች ድምጽ ተከታትሎ እየተሰማ፡፡
“ለምን በዓል ሆነ? የሚነግረኝ ልጅ አለ? ወይም ዛሬ ት/ቤት ለምን ተዘጋ?” ብሎ አስከትሎ ጠየቃቸው። በዚህ ጊዜ ልጆቹ እርስ በርስ መተያየት ጀመሩ፡፡ ለጥያቄው መልስ የሚሰጠው ልጅ ግን አላገኘም። ስለ ክብረ በዓሉ ምክንያት በትንሹ ሊያስረዳቸው ሞከረ፡፡ ሆኖም ግን ልጆቹ ጫወታው ላይ ትኩረት አድርገው ስለነበር፣ በስርዓቱ አላዳመጡትም። እንደተገረመና ያዘነ ሰው፣ ራሱን ከቀኝ ወደ ግራ እየነቀነቀ፣ ወደ ጠላ ቤቱ ደጃፍ ተቃረበ፡፡
“በወደፊቱ ትውልድና ባለፈው አኩሪ ታሪክ መካከል ያለው የግንኙነት ገመድ እየላላ ነው፤ ምንም አልተሰራበትም “ ሲል እያሰበ ነበር፡፡
የደብሪቱ ጠላ ቤት ግቢ፣ ለአጥር ተብሎ ዙሪያውን ከተከለለው ቋሚ እንጨት ይልቅ እሱን አጅቦ የከበበው የሰንሰል ቅጠል ወርሶት፣ የሰንሰል አጥር መስሏል፡፡ ከመዛጉ የተነሳ መልኩ ወደ ቡኒነት የሚያደላው የውጪው ግቢ በር፣ እንደ ወትሮው ወለል ተደርጎ እንደተከፈተ ነው። ክብረት የጠላ ምልክቱን ገና ሲያየው ምራቁን በጉጉት እየዋጠ፣ በመንገዱና በግቢው በር መካከል ያለ ቦይ ላይ ለመሸጋገሪያ የተረበረበውን እንጨት በጥንቃቄ አልፎ፣ ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡
የጠጪው ወሬ ተደማምሮ የፈጠረው ጉምጉምታ ድምጽ፣ ገና ከበራፍ ሳይደርሱ ይሰማል፡፡ በሳጠራ የተከለለውን በረንዳ  አልፎ ወደ ቤት ሲገባ፣ በቡድን የሚያወጋው ጠጪ በወሬው ተመስጦ፣ ነገሬ ብሎ የተመለከተው አልነበረም፡፡ ከቤቱ በራፍ ትይዩ ውስጥ ላይ ሁለት ጠጪዎች ብቻ ከተቀመጡበት አግዳሚ ወንበር ላይ አረፍ ለማለት ሲጠጋ ብድግ ብለው ተቀበሉት፡፡ የፈረስ ጋሪ ነጂው ሰንበቴና የወፍጮ ቤት እህል አስፈጪው አሰግድ ነበሩ። ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ አጠገባቸው ቦታ ይዞ ከመቀመጡ የአንድ ነጭ ሼፍ ምስል ያለበት ጣሳ ሙሉ ጠላ፣ የወ/ሮ ደብሪቱ አገልጋይ አምጥታ፣ ፊት ለፊቱ ካለ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠችለት፡፡ ቀስ በቀስም ከቤቱ ድባብ ጋር ተዋሀደ፡፡
የቤቱ ጣሪያ ኮርኒስ የሚባል ነገር ስለሌለው ወደ ላይ ከፍታው ሩቅ ነው፤ ለጣሪያው ደጋፊ የሆኑት ወፋፍራም ማገሮች በአግድመትና በሰያፍ እንደ ደም ስር መስለው፣ በጣሪያው ውስጠኛ ክፍል ተቀጣጥለው ይታያሉ፡፡ ቆርቆሮውም አጠናዎቹም በጪስ ጠቁረው፣ ተመሳሳይ ጥቁር ቀለም ይዘዋል፡፡ ግርግዳው ላይ አልፎ አልፎ ክብ ወንፊት ቅርጽ የያዘ ሸረሪት ድር፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ የተበጣጠሰ ድር ሆኖ፣ በየአጠናዎቹና ግርግዳው ላይ ተንጠልጥሏል። በሙቅ ማጣበቂያነት ከግርግዳ ጋር በአራቱም ማዕዘን የተለጠፈው የውጪ ሀገር ጋዜጣ ብቻ የቆየ አይመስልም፡፡ የቤቱ ወለል የበረንዳውን ጨምሮ በከብት እበት በደንብ የተወለወለ ሆኖ፣ አልፎ አልፎ፣ ጅባ ጣል ጣል ተደርጎበታል፡፡ ከቀርከሃ መቀመጫዎች በተጨማሪ በቤቱ አንደኛው ረድፍ፣ ጨርቅ የለበሰ መድብ እንደ አግዳሚ ወንበር ያገለግላል፡፡  
ከአራቱ የቤት ጥጎች ወደ ጓዳ በሚወስደው በር  አጠገብ ዳንቴል በለበሰ የሳጠራ ጠረጴዛ ላይ ከሙሉነቱ ትንሽ የቀለጠ ሻማ በርቷል፡፡ ከሻማው ኋላ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ነጭ ፈረስ ላይ እንዳለ መሬት ላይ ወድቆ የሚታይ አስፈሪ ፍጡርን በጦሩ ሲወጋው የሚያሳየው ስዕል በትልቁ ከግርግዳው ተደግፎ ይታያል፡፡ ወ/ሮ ደብሪቱም አንዴ ወደ ሳሎኑ ብቅ ብላ፣ አንዴ ወደ ጓዳ ገባ እያለች፣ ከተስተናጋጆቿ አልራቀችም፡፡ የዶሮ አይን የመሰለ ጠላ እንደምትጠምቅ የሚያሞግሷት ደንበኞቿ፣ ዛሬም በጉሮሮዋቸው እያንቆረቆሩት፣ መንፈሳቸው ሞቅ ሲል፣ ቤቱንም በስሜታቸው ሞቅ ያደርጉት ይዘዋል፡፡
ክብረት አንድ ጣሳ ጠላ ጨርሶ ጥሙ መለስ ካለለት በኋላ፣ ከሰንበቴና አሰግድ ጋር ጨዋታቸው ሞቅ እያለ መጥቷል፡፡ ወጋቸው በአብዛኛው በማህበራዊ ኑሯቸው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በመሃል ሰንበቴ ውጪ መንገድ ጥግ ያቆመውን ጋሪ ወጣ ገባ እያለ ይመለከታል፡፡ ለፈረሱ በአነስተኛ ከረጢት የያዘለትን ፍሩሽካ እንዲበላ ልጓሙን ፈትቶ አቁሞታል፤ ሲያናፋና ሲያፋሽግ በመሃል ድምጹ ይሰማል፡፡
ሰንበቴ  ወፍራም ጃኬት ፣ሁለት ሱሪ መደራረብና ሰፋፊ ጫማዎች ማድረግ ልማዱ ነው፡፡ ከእጁም አለንጋ አይጠፋም፡፡ ሰፊ የሰሌን ባርኔጣውን እንዳደረገ ነው ጠላ ቤት የገባው፡፡ ሰፌድ የሚያክል የእጅ መዳፍ ነው ያለው። በዚህ ሰውነቱ የሆነ ነገር ላይ ቢቆም፣ ረገጠው ሳይሆን ጨፈለቀው ማለት ነው የሚሻለው፡፡ አሰግድ በበኩሉ፤ በደቃቃ ሰውነቱ ላይ የተጣጠፈ ኮት፣ የተጣጠፈ ሱሪ፣ የተጣጠፈ ኮፊያ፤ ጫማው እንኳን በግራ የተሰፋበትና በቀኝ የተሰፋበት ክሩም ሶሉም የተለያየ የሆነ አለባበስ መልበስ ያዘወትራል፡፡ በባህሪም ቢሆን ተመሳሳይ ገጽታ ነው ያለው፡፡ ዛሬ በምላሱ ያወራውን ነገ ከራሱ የሚቃረን ሌላ ነገር ያወራል፡፡ እንደተጣጠፉት ልብሶቹ፣ ሃሳቡም የተጣጠፈ እንጂ ወጥ አይደለም፡፡ የራስ ጸጉሩ ደግሞ ሁልጊዜም አመዳም እንደሆነ ነው፤ በስራው ላይ ወፍጮ ቤት እህል ሲያስፈጭም ሆነ ከስራ ውጪ ወይም ጸጉሩን ቢታጠብ እንኳን የራስ ጸጉሩ አመዳም ከመሆን አይመለስም፡፡
“አንተ የትም ተወለድ መቼም ተወለድ፣ እግዚያብሄር እህል አስፈጪ ወይም የዱቄት ጎረቤት ብቻ እንድትሆን ነው የፈጠረህ” እያሉ ይቀልዱበታል። አንዳንዶቹ “ሽሮ ራስ”ብለው ይጠሩታል፡፡
እንግዲህ ሶስቱ በፈጠሩት ቡድን ውስጥ እንደሚሰራው አቡጀዲ፣ ወሬ መቅደድና መስፋት የሚችለው ራሱንም የተሻለ መረጃ እንዳለው የሚያምነው ክብረት፤ የወሬያቸው ጆከር ሆኖ መቀመጫዋን ሞቅ አደረገው፡፡ ሰንበቴ በወፍራሙ ጠላውን እየተጋተ፣ በመሃልም የሃብታም የሚመስል ወፍራም ሳቅ እየሳቀ፣ አሰግድ ደግሞ በታጣፊ ባህሪው፣ ከክብረት የባጥ የቆጥ ወሬ ጋር አብሮ እየተጣጠፈ ሲያወጉ ቆዩ፡፡
ክብረት ያወራል፡፡
“ፈጣሪ በአባቶቻችን ላይ አድሮ ይሄን ጻዲቅ ጸበል የሆነውን ጠላ፣ ያለ ፎርሙላ ቀምመው እንዲጠምቁ አደረገ፡፡ ደብሬ ደግሞ አሳምራ እንደ መላዕክት ለኛ አደረሰችን፤ አቤት ጠላ ባይኖር ምን ይውጠን ነበር!?” ሰንበቴ እየተመለከተው ሌላ የሚጨምረውን ወሬ ይጠብቃል  አሰግድ
 “መጠጥ በአሁን ጊዜ ሞልቷል፣እንደውም ጠላ ቦታዋን እየተነጠቀችና ክብሯን እያጣች ነው፡፡”
“ኧረ ባክህ¡  ፈረንጅ በፋብሪካ በርሜል ብቅልን በውሃ ለቅልቆ ትላንት ያመጣውን ሁሉ መጠጥ አልለውም በበኩሌ፤ ግራዝማች ይሙት! ርኩስ ጠበል ነው፤ ይሄ እኮ የጥንት የጠዋቱ፣ ምግብ የሚሆን አንጀት አርስ የእጅ ስራ ነው፡፡” ቺርስ እንደሚል ሰው፣ ጣሳውን ከፍ አድርጎ  እያሳየ ቀጠለና፤
“እኛ የራሳችንን ማክበር አቅቶን የሌላውን እናያለን እንጂ ብናውቅ ኖሮ ጠላ ማለት ሰውነት የሚገነባ መድሃኒትም ጭምር የሆነ የአዋቂ ሽሮፕ ነው፡፡” ሰንበቴ በዚህ ጊዜ እግሩን ከፍ አድርጎ ሳቀ፡፡
አሰግድ በበኩሉ፤
“እውነትህን ነው፣ አይ አንተ ሰውዬ…” እያለ፣ ራሱን በመገረም፣ በሚመስል ፈገግ አለ፡፡
በዚህ ሁኔታ ለሶስት ወግ እየቀያየሩ ከቆዩ በኋላ፣ ጓደኛቸው ድንበሩ ከጆሮው ጋር በክር የታሰረ ወፍራም መነጽሩን እንዳደረገ ከች ብሎ ተቀላቀላቸው፡፡ ክብረትና ድንበሩ በስራ ምክንያት ይተዋወቃሉ፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም ወቅት አብረው ዘምተዋል፡፡ በጦርነት ላይ ሳሉ በአንድ ብርጌድ ቆይተው ባልታወቀ ምክንያት ተለያይተው፣ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ሀገር ሲመለሱ ነበር የተገናኙት፤ ጦርነቱን በድል ተወጥቼ ከሰራዊቱ በፈቃዴ ለቀቅኩ እያለ ቢያወራም፣ ክብረት ግን አያምነውም። አሽሙር መናገርና ሰዎችን መፎገር ይችልበታል። ልብስ ተኳሽ እንደመሆኑ ደግሞ አሮጌም ይሁን አዲስ፣ የለበሳቸው ልብሶች ሁሌም የተተኮሱ ናቸው፤ ለአለባበሱ በጣም ጠንቃቃ ነው፡፡ ሸሚዙ ከኮሌታ እስከ እጅጌው ድረስ ቀጥ ብሎ የሚወርድ ቅርጽ፣ ሱሪውም ከወገቡ እስከ ቁርጭምጭሚቱ በካውያ የተተኮሰው ጨርቅ ላይ ቀጥ ብሎ የሚወርድ ቅርጽ በለበሳቸው አልባሳት ላይ መታየቱ አይቀርም፡፡
“እሺ እንኳን አደረሳችሁ” አላቸው፤ በቀጭን ድምጹ፣ በቆሪጥ ክብረትን እየተመለከተ፤ በሽሙጥ መልክ ነበር፡፡ ሰንበቴና አሰግድ እርስ በርስ ሲተያዩ
“እንኳን አብሮ አደረሰን”ብሎ መለሰ ክብረት ምላሹ በቁምነገር እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ጎርናና ድምጹና ሰፊ ፊቱ እንደ ሽንብራ ከተቆጣጠረው ጥቃቅን ጸጉሩ ጋር ሲተያዩ ተቃራኒ ናቸው፡፡
ድንበሩ እንደተቀመጠ በመርቲ ጣሳ የመጣለትን ጠላ በአንድ ጊዜ ግጥም አድርጎ አጋመሰው፡፡ወዲያውም ጣሳውን አስቀምጦ የራሱን ወሬ አስከተለ
“ዛሬ ስራ ምንም ሊቀናኝ አልቻለም ቢሮ ዝግ ስለሆነ ባለው ረፍት ቀን ተጠቅሞ ሰዉ ልብሱን ሊያስተኩስ ይመጣል ብዬ ተስፋ ባደርግም የባሰ ቀን ሆነብኝ፤ ቡሽቲ ቀን!”አለ የመጨረሻዋን ቃል ጠበቅ አድርጎ
“እንዴ መጀመሪያም አኮ አንተ እለቱን አክብረህ ወደ ስራም መሄድ አልነበረብህም፤ ዛሬ አድዋ ነው፤ ታላቅ ቀን ነው” ክብረት ነበር፡፡
“እኔ ባክህ አድዋ ይሁን ምንም ቢዝነሴን  ማጧጧፍ ነው የምፈልገው ደርሶ አፌን የሚያሟሽልኝ ካሽ ነው ወሳኙ ነገር ካሽ” አለ በጣቶቹ የገንዘብ አቆጣጠር ስልትን በምልክት እያሳየ
“አ….ይ ተሳስተሃል  አድዋ በገንዘብ የሚገመት አይደለም፡፡ እለቱን እኛ ብቻ ሳንሆን ጥቁር ህዝቦች በሙሉ ሊያስቡት የሚገባ ቀን እኮ ነው፤የድል ቀን ነው፡፡ ከዛሬ 120 ዓመታት በፊት ከነሱ በኋላ ለምንመጣው የልጅ ልጆቻቸው ነጻነት ደማቸውን የሰጡ በሺ የሚቆጠሩ አያቶቻችንን መካድ ማለት ነው፤ ስለነሱ ሳናስብ ብንውል ያፈሰሱት ደም፣ የወደቁበት መሬትና ያዩት ስቃይ የተመለከተ ዱር ተራራው ይቺ የረገጥናት ምድር ራሳቸው ይታዘቡናል፡፡”ክብረት ድንበሩን ለማሳመን ተጨማሪ ዓረፍተ ነገሮችን አስከትሎ ተናገረ፡፡ ድንበሩ ግን ችላ በማለት
“ታሪክ ምግብ አይሆንም ባክህ፤ ትላንት ዛሬ አይደለም ሲባል አልሰማህም? የምበላው፣ የምጠጣው፣ የምተነፍሰውና በህይወት ያለሁት በዛሬው አየር ነው አለቀ፡፡ ይሄ የማይካድ ሀቅ ነው፤ ስለዚህም ያለፈውን ታሪክ እንደተበላ ምግብ ከድኖ ዞር ማድረግ ነው የሚገባው”አለና ተጨማሪ ጠላውን አስቀዳ፡፡
በቤቱ በርና መስኮት በኩል የምትገባው የጸሃይ ብርሃን ውጪ ላይ ጠንከር ማለቷ ያስታውቃል። በመስኮት በኩል በጠራው ሰማይ የሚወርደው የከረረ ሙቀት የሰንሰሎቹን ቅጠል ሳይመሽ አጠውልጎ የሚያደርቃቸው ነው የሚመስለው፡፡ ከቤቱ ውስጥም በሙቀቱ  ኮታቸውን የሚያወልቁና ኮፊያቸውን ጉልበታቸው ላይ ጣል የሚያደርጉ ደንበኞች መታየት ጀምረዋል፡፡ከጥግ ላይ የሚበራው ሻማ ወደ ግማሽ አካባቢ ሊቀልጥ ሆዱ ጋር ተቃርቧል።
“እሺ ሽሮ ራስ አንተስ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ስለተከሰተ ሁኔታ እያሰላሰልን የዛሬው ህይወታችንን ስላለፈው እያሰብን መዘናጋት ይኖርብናል ትላለህ” ሲል ድንበሩ መነጽሩን እየነካካ ጠየቀው አሰግድን፤ አሰግድ ክብረትን ገረፍ አድርጎ ካየው በኋላ
“እሱማ አያስፈልግም፤ ያለፈው አንዴ አልፏል፤ ምንም የሚጨበጥ ነገር የለህማ፤ ታሪክን እንደ ጥሬ ፈጭተህ አትመገበው ወይ ደግሞ ዛሬ ያለብህን የሆነ ቀዳዳ አትደፍንበትም እንደዛ ነው እንግዲህ ሃሳቤ”
“እንዴ አድዋንማ እንደማንኛውም የታሪክ ክንዋኔ አታስቡት፤ አድዋ እኮ ትንግርት ነው፤ በሰው ልጆች ታሪክ ተፈጽሞ የማያውቅ ወደፊትም ሊፈጸም የማይችል  ብቸኛ የታሪክ ባለቤቶች ያደረገን ድል ነው፡፡ ጸሃይ በምስራቅ አትጠልቅም፤ ጥቁርም ነጭን አያሸንፍም ሲባል የነበረው፣ የኛ ጀግና አባቶቻችን ግን ይህን እንደተፈጥሯዊ ህግ ይታይ የነበረውን እምነት ቀይረው ጥቁር ማለት ከሰው በታች ሳይሆን ሰው መሆኑንና ሰው መሆን ደግሞ ክብር መሆኑ የታየበት  ድል ነው፡፡ ፈጣሪ አምላክ በአንድ ወቅት ጸሃይን እንዳቆመ መጽሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፤ አድዋም ከዚያ ጋር የሚነጻጸር ታሪክ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ተዓምሩ ደግሞ የተገለጸው በደም ነው፤ በጀግንነት ነው፤ በመስዋትነት ነው። የዛሬው ዘመናዊነት ደግሞ የታሪኩን ታላቅነት ሊጋርደን አይገባም…..”
ክብረት በዚህ ሁኔታ ክርክሩን አግሎት አላቆም ሲለው ድንበሩ በመሃከል ገብቶ
“ክብሩ በናትህ ዝም ብለህ አትድከም፤ ታሪክ በታሪክነቱ ትንሽነትና ትልቅነት እናስተናግደው አልወጣኝም…ማንኛውም የተፈጸመ ታሪክ በራሱ የጊዜ ሂደት ውስጥ በራሱ ምክንያት ተፈጽሟል፡፡እኛ ደግሞ የዛሬ ታሪክ ሂደት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ማወቁ ይጠቅመናል እንጂ በዛሬው ኑሯችን ላይ ምንም አይነት ተጽኖ ሊያሳድርብን አይገባም ነው የምልህ፡፡”
“አልገባኝም”አለ ክብረት የተቀመጠበት አግዳሚ ወንበር ላይ እጆቹን አጣጥፎ ወደ ኋላ ከግርግዳው ጋር እየተደገፈ
“ግልጽ ላርግልህ አይደል?ቀናት ይሄዳሉ፤ ቀናት ይመጣሉ የካቲት 23ም ይመጣል ይሄዳል፤ ድሮም ዛሬም ፤ ስለዚህም በቀናት መካከል ምንም ልዩነት በሌለበት ሁኔታ የዛሬ 120 ኣመታት ይህቺ ቀን ታሪክ ተፈጽሞባታልና እኔም በባዶ ሜዳ ስራዬን ፈትቼ ቁጭብዬ የማከብርበት ምክንያት አይገባኝም፤ ስለአድዋ ለማሰብ የፈለገ በማንኛውም ቀን ስለ አድዋ የተዘፈኑ ሙዚቃዎችን ከፍቶ ማዳመጥ ወይም መጽሃፎችን ማንበብ ይችላል አለቀ፡፡”ቀጠለናም
“አይደለም እንዴ” ወደ አሰግድና ሰንበቴ እያፈራረቀ በማየት ጠየቃቸው፡፡ አሰግድ ራሱን በአዎንታ ሲነቀንቅ ሰንበቴ
“አድዋ ቀን እንደ መስቀልና ፋሲካ አመትበኣል አይደለም፤ የሚታረድም የሚጋገርም ነገር ስለሌለው አይደምቅም፤ ታዲያ ስራ ማቆም ለምን ያስፈልጋል እየሰሩ ማሰብ ነው፤ ስራ ካልተሰራ ደግሞ በልቶ ማደር የለም፤ ጤናም የለም፡፡” ጠላ መጠጫውን ወደ አፉ እያስጠጋ
ክብረት በዚህ ጊዜ በብስጭት ፊቱን አላበው የባሰ ጥቁረቱ ጨምሮ ላቡ ሲታከልበት ቆዳው ጤዛ ያዘለ ምጣድ መሰለ፡፡
“ትገርማላችሁ!ስንት የማይረቡ ዕለታት ብሄራዊ በዓላት እየተባሉ መንግስት በተቀያየረ ቁጥር ስራ ዘግተው  ባንዲራ እየሰቀሉ ህዝብን ሰልፍ በሰልፍ ያደርጉት የለም እንዴ፤ ስንትስ ሃይማኖታዊ በዓላት ሳይገባንና ሳይመለከተን ስራ ፈተን እንውል የለም አንዴ፣ አረ በየሃገሩ ሂዱ የትኛውም የዓለም ሃገር የነጻነት ቀን የሚለውና የሚያከብረው በዓል አለው፤ የኛን ግን ከብዙዎቹ ልዩ የሚያደርገው የድል ቀን መሆኑ ነው፡፡ ይህም ቀን ያለጥርጥር አድዋ ነው፡፡ መንግስት በተቀያየረ ቁጥር ሊሽረው የማይችለው ቀን፤ ምን ሆናቹሃል? አድዋ ሲባል ደግሞ በአድዋ ላይ ለአንድ ቀን ስለተደረገው ጦርነት ብቻ ማሰብ አይደለም፣ አድዋ ማለት ለረዥሙ የኢትዮጵያ ከዛም አልፎ ጥቁሮች ለነጻነት ብለው በተለያዩ ሃገራት ጦርሜዳዎች በተለያዩ ጊዜያት ስላደረጉት ትግልና ስለከፈሉት መስዋትነት በመጨረሻም በድልና በነጻነት ስለማጠቃለላቸው የሚወክል ጥቅል፣ ነገርግን በውስጡ ዝርዝር ክስተቶችን ያቀፈ ነው፡፡ አድዋን ስናስብ ዶጋሊ ላይ ስለወደቁት ሃገር ወዳድ ታማኝ ዜጎችም እያሰብን ነው፤ አድዋን ስናስብበ በማጂ ማጂ አመጽ፣ በጋና አሻንቲዎችና በደቡብ አፍሪካም ዙሉዎች በሌሎች አለማት ስለጥቁርች ነጻነት የወደቁትን ሁሉ እያሰብን ነው”  ክብረት እንደ ስሜታዊነቱ በመካከል ጣልቃ ገብቶ ለማስቆም የሞከረ አልነበረም፤ ከልባቸው ስለማዳመጣቸው ግን ፍንጭ የለም፡፡እሱ ግን ቀጠለ
“ድንቄም ስራ ወዳድ መሆን¡ ዛሬነው እንዴ የስራ ፍቅር የሚታያችሁ? 365 ቀናት ሙሉ ስራን በመናቅና በመሰላቸት ሲያለምጥ የኖረ ሁላ ዛሬ ገና ስራ ፈታሁ፤ ወይ የሃበሻ ስራ! እነኛ ምንም አይነት ዘመናዊ ቴከኖሎጂ ሌላው ቢቀር እንኳን መኪና አይተው የማያውቁ ሳይንሳዊ ትምህርት የሚባለው ጫፋቸው ያልደረሰ ከተፈጥሮ ጋር ብቻ የተዋደዱ አያት ቅድመ አያቶቻችን ስንት ነገር ያስተምሩናል፤ እኛ ግን የማስተዋል ልቦና አጥተናል፡፡መንገድ በማይታወቅበት በጫካና በጢሻ እያቆራረጡ ረዥም ርቀት ለወራት መጓዝ በራሱ አስደናቂ ነው፡፡ ኩታቸውን ጣል አድርገው፣ እንደዛሬው ማሽን ያልነካ ጸጉራቸውን አጎፍረው ወይም ጨርቅ በአናታቸው ጠምጥመው ባህላዊ የጦር መሳሪያቸውን እንደያዙ በልባቸው ላደረችው የአንዲት ሃገር ፍቅር ተማርከው ሞገስ ባለው የባላገር አረማመድ ሲተሙ ማየት ምን ያህል ወኔ እንደነበራቸው ማሰብ ይቻላል፡፡ ታዲያ እኛ የሶስትና የአራት ጊዜ ትውልዶች አንድ ቀን እንኳን መታሰቢያ አድርገንለት ብናስበው ምን ክፋት አለው፤ ልደታችን ቀን እንደምናስበው በዓመት አንድ ቀንም ነጻነታችንን ለተጎናጸፍንበት ዕለት የድል ሻማ ብናበራ ምንድነው ስህተቱ?”
”የነድንበሩ ጸጥታ ሃሳቡን እንደተቀበሉና እንዳሸነፋቸው በመገመት ክብረት ንግግሩን ገታ አድረጎ ወደ ጠላው ዞረ፡፡
ቤቱ ቡድን ሰርተው በሚጫወቱ ጠጪዎች ከመከፋፈሉም በላይ እያንዳንዱ ቡድን የራሱ መገለጫ ያለው ይመስላል፡፡ በአንዱ ጎራ የቀን ጉልበት ሰራተኞችና ወዛደሮች ክብ ሰርተዋል። በዚህ ቡድን ብዙዎቹ ከገጠር የቀን ስራ ፍለጋ ወደ ከተማይቱ ፈልሰው የመጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ ሰፊውን የገጠር መሬት በገዛ እጅ እየለቀቁ የማይያዝ የከተማ ህይወትን ለመጨበጥ የሚጥሩ ወጣቶች ሃገራችን በየቦታው እየበረከቱላት ነው፡፡ በሌላኛው ጎራ ደግሞ የተለያዩ ቢሮዎችና ተቋማት ጥበቃ ሰራተኞች የሚበዙበት ነው፡፡ጠና ጠና ያሉ ሆነው ሲያወሩም ወከባና አንዱ ሃሳቡን ሳይጨርስ በላዩ ላይ የሚደረቡ አይደሉም፡፡ ከመግቢያው በረንዳ ላይም ሌላ ቡድን ያለ ሲሆን በመተራረብና በቧልት የመነጨ ሳቅ ውስጥ ድረስ የሚሰማበት ነው፡፡
ድንበሩ ለክብረት ዝርዝር ወሬ ሊሰጠው የሚችለውን መልስ ሲያብሰለስል ነበር፣ እናም በክርክሩ መሸነፉን አሜን ብሎ አልተቀበለም፡፡
“በግልጽ እንነጋገር ከተባለ በዛ ዘመን የነበሩ ዘማቾች ለጌቶቻቸው ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ሲሉ እንጂ ስለሚዋጉበት ጦርነት አላማና ምክንያት ገብቷቸው አይደለም፡፡ጀግንነት ማለት ተመራምሮ በመፍጠር የሃገር ፍቅርን መግለጽ የማያበረታታ በጦረኝነትና ዘራፍ በማለት  ብቻ መሆኑን በሚሰብክ ማህበረሰብ ውስጥ በመሆናቸው  ጠላት መጣብህ ሲባል ለውጊያ የሚሮጥ ጭፍን ጀግንነት የመጣ እንጂ ምክንያታዊ አልነበሩም፡፡ እንደውም አውነት እናውጣውና ስንት ዘመናት ባህሩዋ ተከብሮ የኖረችው ሃገር ዛሬ ላይ ተከፍላ ባህር አልባ እንድትሆን የአድዋ ጦርነት መንስኤና የድሉ ጎዶሎነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡” ብሎ ተጨማሪ ቃላትን ሊቀጥል ሲል ቤቱ ትኩረቱ ሁሉ ወደ ደብሪቱ የድንገቴ ጩኸት ተስቦ ሁኔታው ተቀየረ፡፡
ከግርግዳው ጥግ ባለ ቅርጫት ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠው ሻማ ሳይታወቅ አልቆ ከአጠገቡ ያለውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕልን ማያያዝ ጀምሯል። ባለጠላ ቤቷ ደብሪቱና ሰራተኛዋ እየተጯጯሁ  ተረባርበው አጠፉት፡፡እሳቱበቶሎ ባይነቃበት ኖሮ የተቀመጠበት ባለሳጠራ ጠረጴዛን ጨምሮ ስዕሉን በቀላሉ ያወድመው ነበር፡፡የሻማው እሳት ሲጠፋ ጪሱ በቤቱ ያለ ታዳሚ አፍንጫ ላይ ደረሰ፤ የሆነ ከአገልግሎት ውጪ  የሆነ እቃ ሲቃጠል የሚፈጥረው ሽታ አይነት ፈጠረ፡፡ግማሹ ጠጪ ደብሪቱን ግዴለሽነት ገሰጻት፤ የተወሰነው አተረፍን በሚል ማመስገን አንዳንዱ ተሯሩጦ ስዕሉ ጋር ደረሰ፤ ቀሪው ደግሞ ዞር ብሎ ከማየት ውጪ ምን አልመሰለውም። ከነዚህ መካከል ክብረት አንዱ ነበር፤ አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረ ቆጥሮ ድንበሩንሳያስጨርስ ወደ ወሬው ተመለሰ፡፡
“ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ በየዓመቱ የሚያስበውን ብሄራዊ የክብር ቀንን እንዲህ በአንድ ጨርቅ ተኳሽ ሰው በአንዲት ዓረፍ ነገር ሲንቋሽሸ መስማት በጣም ያሳዝናል።” ድንበሩ  በዚህ ጊዜ አይኑ ፈጠጠ መነጽሩ ውስጥ ሲታይ ብሌኑ በነጭ ሰሌዳ ላይ የተቀመጠች ጥቁር ነቁጥ ትመስላለች፡፡ ክብረት እንደ ቀልድ የጀመሩት ክርክር ስሜታዊ አድርጎት ምን ይመጣል የሚል ሃሳብ በአይምሮ አልመጣም፡፡
“ሰበብ መፍጠር ነው እንጂ የአድዋ ጦርነት ከባህር በር ማጣት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ንጉሱ ብዙ የጣሊያን ምርኮኞችን ከያዙ በኋላ በሰብዓዊ ስሜት በምህረት ለቀዋቸዋል፤ ይሄ ማለት እነሱን መጨረስ አቅቷቸው አይደለም፤ ዋናው ጦርነት ሜዳ ላይ ተጋጥመው ክንዳቸውን አሳይተውታል፡፡ ጣሊያኖቹም ቢሆን መሸነፋቸውን አውቀውታል፤ የባህረ መላሽ ጉዳይም ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ተሸንፎ በእጅ የገባን ምርኮኛ ጨርሶ መግደል ሽንፈትና ፈሪነት ማሳያ ጭምር ነው፡፡ ገባህ” ብሎ ወሬውን ለአፍታ ገታ አድርጎ ቀጠለ
“እኔ የምለው ግን የአድዋ ቀንን ማክበር በራሱ ያንን አንድነትና እንደ ንብ መንጋ የመሰማራትን ሚስጥር ምንድነው ብለን ለይተን ዛሬ ላይም ለማምጣት እንድንመራመር ያደርጋል፡፡ ከየአቅጣጫው የሃገሪቱ ክፍል ተሰባስበው ለአንዲት ሀገር በአንድ ኣላማ የተነሱ ከ70,000ሺ በላይ ዜጎች መሬታቸውን እንደ ፍልፈል ደፍሮ የሚቆፍር የሰለጠነ ተብዬ ጠላት ለማባረር ሆ ብለው ሲወጡ በኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳ ነው፡፡በአለማችን ታሪክ በርካታ የጦርነትም የሁን የስደት ጉዞዎች ቢደረጉም ለአድዋ ጦርነት ይህን ያህል ህዝብ በጋራ ሲዘምት ግን ምናልባትም በአፍሪካ ደረጃ ታላቁ ዘመቻ ነው፡፡ ከሰማይ በብዙ ርቀቶች በሳተላይት ወይም ከጨረቃ ላይ ሊታይ የሚችል የህዝብ እንቅስቃሴ ነው የተደረገው። ወደፊትም ቢሆን ሴት - ወንድ፣ ወጣት - ሽማግሌ፣ ጌታ- ሎሌ፣ ባላገር - ባለሃብት፣ ደገኛ - ቆለኛ፣ መሳፍንት  - ገበሬ፣ ሸዌ፣ ሀረርጌ፣ ሲዳሞ ወዘተ ሳይለይ በየመንገዱ እየታደረ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በእግር ተፈረስ በቆራጥ ልብ መጓዝ መጪው ትውልድም ቢሆን የማይፈጽመው ታሪክ ነው፡፡”
ቀሪው የጠላ ደንበኛ ትኩረቱ ወደ ክብረት ተስቧል፡፡ተጨማሪ ሃተታዎችን እጆቹን እያወናጨፈ ማንኛውም ሰው የሚያውቀውን ወሬም እንደ እንግዳ ነገር እየጨማመረ ለፈለፈ፡፡ ተነስቶ መፎከር ብቻ ነበር የቀረው፡፡ ባለጋሪው ሰንበቴ እነ ክብረት እንደዋዛ ያነሱት ጉዳይ አታካሮው እየከረረ መምጣቱ አስጨንቆት ነበር፡፡ ለሱ ግን ጉዳዩ ይሄን ያህል ማከራከሩ ገርሞታል፡፡ ሲቁነጠነጥና  ወጣ ገባ ሲል ቆይቶ የቀረውን ጠላ በአንድ ትንፋሽ ገልብጦት ሰፊ ባርኔጣውንና አለንጋውን አንስቶ ተሰናብቷቸው እያዘገመ ወደ ጋሪው ተመለሰ፡፡ አሰግድ በበኩሉ የደነዘዘ ይመስላል፤ ክርክሩ ይሁን ወይም ጠላው በመሃል አመዳም ጸጉሩን ይደባብሳል፡፡ የተጣጠፈ ሱሪው ስር መዳፉን እየሰደደ ይፎክታል፡፡ ላብም ጀምሮታል፡፡ በሶስቱ መካከል ለተወሰነ ጊዜ ዝምታ ሰፈነ፤ጸሃይቱ ከራርነቷን ረገብ ማድረግ ጀምራለች፡፡
ሶስቱም አይናቸው ቡዝዝ ማለቱና መሰላቸታቸው ያስታወቃል፡፡ ክብረትና ድንበሩ ግን እርስ በርሳቸው እየተጠባበቁ አንዱ ከጀመረ ሌላኛውም ምላሽ ለመስጠት እያብሰለሰሉ መሆናቸው ያስታውቃል፡፡ በመጨረሻ ድንበሩ
“ለማንኛውም በሰላም ያውለን፤ የታሪክ አባቶችን ጠላ ላይ በከንቱ ከማንሳት ይጠብቀን” ብሎ ዝም አለ፡፡
“ምን ማለትህ ነው?” ጠየቀ ክብረት
“የአድዋን ታሪክ የሰራው ትውልድ ሁሌም መታወስና መከበር አለበት አላልክም”
“አዎ”
“ዛሬን ለምን አትመለከትም ታዲያ ቀድሞ አያቶቻችን ሊወራቸው የመጣውን ነጭ ደም ተፋሰው አባረው መለሱት ዛሬ ግን በተቃራኒው እንደምናየው ወጣቶቻችን እነሱ ጋር ለመሄድ ደማቸውን ያፈሳሉ፤ በአካል ሲመጡብን መልሰን አባረርናቸው እንጂ በማይጨበጠው ባህልም በደንብ ሰርጸው ገብተዋል ከመከላከል ይልቅ እንደውም እሰይ ብለን እየተቀበልናቸው ነው፤ ይሄ ደግሞ ሽንፈት ነው ሁል ጊዜም ስለ ድላችን ብቻ ማጋነን ስንፍና ነው። ዛሬ ስራ ፈተን አድዋ እያልን የምንቀመጥበት ጊዜ አይደለም፤ የሩጫ ዘመን ላይ ነን፡፡ ይህን ማወቅ አለብህ፤ ስለዚህም ስላለፈው ታሪክ ከማውራት ውጪ መማር እንኳን ያልቻልነው የዛሬው ልፍስፍስ ትውልዶች  እኛንም ጨምሮ ያውም በጠላ ጠጪ ስራ ፈቶች ጉዳዬ ብለን መከራከር ክብራቸውን ዝቅ ማድረግ ነው፤ ጨርሻለሁ” ብሎ ፊቱን አዞረ፤ ክብረት ነገሩ ገባው እሱንም ለመንካት ያወራውን ሁሉ ዋጋ ለማሳጣት መሆኑ ገብቶታል፡፡
“ወደድክም ጠላህም አድዋ ሀገራዊ በዓል ሆኖ ተከብሯል” በህልሙ ቁልጭ ብሎ አሁንም ድረስ የሚታወሰው በደማቅ ቀይ ቀለም የተጻፈው 23 ቁጥር እንደ ዲምላይት ቦግ ብልጭ እያለ ከዚያም ቆራጦቹ ሰራዊቶች አይኑ ላይ ተፈራርቀው ታዩት፤ በዚህ ጊዜ ድምጹን የበለጠ ከፍ አድርጎ
“የካትቲ 23 ከሁሉም ቀናት የተለየች ናት፤ ትላንትም ደምቃለች፤ ወደፊትም የካቲት 23 ሌላ 120 ኣመታት ለዘላለሙም ማንም አይነካትም” ድንበሩ መነጽሩን እንደማይክሮስኮፕ ተጠቅሞ ከጠላ ውስጥ ደቃቃ ነፍሳትን የሚፈልግ ይመስል ጣሳው ውስጥ አጮልቆ ሲመለከት ቆየና ቀና ብሎ
“አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅህ ክብረት”
“እሺ ምንድነው” ቀጥል በሚል አስተያየት
“ዛሬ እስቲ በዓሉን ስታከብር ጀግኖቹ በአየር ተንሳፈው እንደ መለዕክት ታዩህ? ለኢጣሊያ ጠላት የተተኮሰው መድፍ የተመዘዘው ጎራዴ ድምጽ ተሰማህ? የጥይተ ባሩዱ ሸተተህ ወይስ የነሱን ቆራጥ የጀግንነት ልብ በመንፈስ ላኩልህ እስቲ ዛሬ አንተ ራስህ ምን የተለየ ነገር ፈጠርክ ወይም ተሰማህ? መልስህ መልስ የለም ነው አውቀዋለሁ”
በዚህ ጊዜ ክብረት ጠላውን በላይ በላዩ ደጋግሞ ጠጣ፡፡ የድንበሩ ደረቅና ለዛ የሌላቸውን ጥያቄዎችንም ጭምር ግጥም አድርጎ እንደጠጣቸው ተሰማው፡፡ ክርክሩ ወደ ጭቅጭቅና አላስፈላጊ ሰጣገባ መድረሱ ስለሆነ ከመናደዱም በላይ የድንበሩን ፊት ላለማየት ሂሳቡን ከፍሎ ፈንጠር ብሎ ወጣ፡፡
የድንበሩን የሚነዛነዙ ሃሳቦችን በአይምሮው እያሰላሰለ በመጣበት መንገድ ወደ ቤቱ ጉዞ ጀመረ። ከሌሎች ቀናት በተለየ ሁኔታ የስካር ስሜቱ አይሎበታል፤ ወትሮ ጠላ ቢጠጣም አምሮቱን ለመወጣትና ጉሮሮውን ለማራስ እንጂ ከዛ በላይ ብዙ አይገፋበትም ነበር፡፡ አከታትሎ የገለበጠው ጠላ ፊኛውን ስለወጠረው ከአንድ መንገድ ጥግ ካለ ቱቦ ሊደፋው ዳር ይዞ ማውረድ ጀመረ፡፡ አንዳች ሸክም እንደወረደለት ቀለል ያለ ስሜት በመላ ሰውነቱ ተሰማው፡፡ የተዘጋ መውረጃ ሲከፈት በነጻነት ፈሳሹ ሲወርድ እንደሚፈጥረው መረጋጋት በፊኛ ቱቦው ርጋታ ሰፈነ፡፡ ባለበት ቀና ብሎ ከቤቶች ጣሪያ በላይ የሰፈሩ ት/ቤት ሰቅሎት ያልወረደ ባንዲራ ሲውለበለብ አስተዋለ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ አላማ እንደ ባህር ሞገድ በግርማ ሞገስ አየሩ ላይ ይውረገረጋል፡፡
የነጻነታችን መለያ፣ የአንድነታችን ማሳያ ምልክት፣ የማንነታችን ልብስ፣ የቃልኪዳን ቀለማችን፣ ከፍ ባለችበት ሁሉ ከፍ የምንል ዝቅ ብላ በተውለበለበችበት ሁሉ አንገታችንን የምደፋበት፣ በተቀደደችበት በተናቀችበትና በተረገጠችበት ጊዜ ደማችን የሚፈላላት ስሜታችን የሚቀደድላት፣ ስጋችንን የምንሰዋላት- አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ፤ በተገኘችበት ሁሉም ቦታ በመንፈስ በውስጧ አኛም መኖራችንን የምትነግርልን ይህቺ ባንዲራ - እሷን አክብረው ያስከበሯት ታማኝ  ጀግኖች እንዴት ይዘለፋሉ? እንዴት መታወስ የለባቸውም  ይባላል?
ክብረት ሰንደቅ አላማ እየተሰቀለ የህዝብ መዝሙር ሲዘመር እንዳለው ስርዓት ለብቻው ቀጥ ብሎ ለደቂቃዎች ከቆመ በኋላ አንዳች የመደፈር መንፈስ ወረረው፤ እንደ ቆሰለ አውሬ አይነት ቱግ ብሎ ወኔው ተቀሰቀሰ፤ ጀግንነት ነሸጠው፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ደብሪቱ ጠላ ቤት በፍጥነት ተመለሰ፤ አድርጎት የማያውቀውን፤
ድንበሩን ነበር የሚፈልገው፤ ድንበሩን፤ ያ ወኔ ቢስ! ምቀኛ የሃገር ጠላት! በጠላ ቤቱ ውስጥ ግን አልነበረም። ከመመለሱ በፊት ለጥቂት ወጥቷል። እንደ አኳኋኑ ቢያገኘው ከመሳድብም አልፎ መደባደቡ የሚቀር አልነበረም፡፡ ስለድንበሩ ፈሪነት፣ የሃገር ከሃዲ ስለመሆኑ፣ በጀግና አያቶቻችን ከመኩራት ይልቅ የሚያፍር ስሜት የለሽ ሰው መሆኑን ወዘተ ከራሱ ጋር እያነጻጸረ ድምጹ ከፍ አድርጎ ለሚያዳምጠው ደንበኛ ሁሉ ለፈለፈ፡፡ አንዳንዱ ታዳሚ ይባስበት ብለው ወይም የምራቸው አይታወቅም ብቻ ድንበሩ በጦርነት ወቅት ሸሽቶ ወደ ሃገሩ መምጣቱን እንጂ እንደሚያወራው ከድሉ በኋላ በሰራዊት ቅነሳ እንዳልተመለሰ በሚስጥር አስመስለው ሹክ አሉት፡፡አሰግድ ሽሮ ራሱ ደግሞ ከሌሎቸ አዛውንቶች ሰማሁ ብሎ አያትየውን በደንብ እንደሚያውቋቸውና የሚወራውም የጣሊያን ባንዳ ሆነው የሚያገለግሉ ሰው እንደነበሩ ጨመረለት፡፡ በዚህ ጊዜ ክብረት ክራንቹን እያወናጨፈ ማዜምና መፎከር ጀመረ፡፡በንዴት ፣በስካር መንፈስና በወኔ የተቀላቀሉ ስሜቶች
“ጀግና ነኝ በአያት ቅድመ አያቴ፣
የሚመሰክር የነጻነት ታሪኬ፣
የጸና እስከዛሬ የሚዘልቅ ለሁሌ፤
      ጀግና ነኝ የማልበላ እዳ፣
       ስለወረስኳት መሬት የማላወላዳ፣
      ጀግና አክባሪ ዘካሪ፣
      የማልተኛ ለማንም ውሪ” እጁን ከፍ አድርጎ ወደጣሪያው እያመለከተ
“የአድዋ ድል ይዘከራል፤
ሁሌም ጀግና ይከበራል፤
ስሩ ይለመልማል - ባንዳ ይደነብራል፡፡
ጠጪው በጋራ እንደ መፈክር ክብረት የሚለውን  መልሰው ይሉለታል፡፡ አንዳንዶቹ አጨበጨቡለት፡፡የጨበጣ ውጊያ እንደተቀላቀለ ወታደር በፍጹም ስሜታዊ ሆነ፡፡ የሚያደርገው ሁሉ በደመነፍስ ይመስል ነበር፣ ወዲያውም
 “የአድዋ ድል ይስፋፋ
 ጀግና ይኩራ ባንዳ ይጥፋ”  እያለ ግቢውን ለቆ ወጣ፡፡
የተወሰኑ አንድ ሁለት በሞቅታ ስሜታቸው የተቆሰቆሰ ሰዎች ተከተሉት፡፡ ጎዳናው ላይ ከፊት ሆኖ እየለፈለፈ እየጮኸ ሲጓዝ  እኩዮቹ  ይሄ አካል ጉዳተኝ አበደ ሲሉ ጥቂቶች ግን ተከተሉት። የሰፈር ኅጻናት ከኋላ አጅበውት የሚለውን መፈክር አብረው ማስተጋባት ያዙ፡፡ ክብረት ይበልጥ ሞራል እየተሰማው ማንም ወደ ኋላ የሚመልሰው አልሆነም፡፡
   የጀግና ልጅ ነኝ የማልበላ እዳ፣
   ስለወረስኳት መሬት የማላወላዳ፣
   ጀግና አክባሪ ዘካሪ፣
   የማልተኛ ለማንም መሰሪ”
 ድምጹ በአካባቢው ከሚሰማ ማንኛውም አይነት ድምጽ የበለጠ ጆሮ ላይ ይደርሳል፡፡ቢመቸው እንደሚከተሉት ህጻናትና ጥቂት ደጋፊዎቹ እንድ እጁን ከፍ አድርጎ በክንዱ አየሩን እየደቆሰ በአካላዊ እቅስቃሴም ጭምር ስሜቱን በገለጸ ነበር፡፡ እርሱ ብቻውን እንደ ፎካሪ ቀሪዎቹ ደግሞ እንደ አዝማች ሆነው ቀጠሉ፡፡
“የአድዋ ድል ይዘከራል፤
 ሁሌም ጀግና ይከበራል፤
 ስሩ ይለመልማል- ባንዳ ይደነብራል፡፡”
በከተማዋ መሃል አድርጎ  ቁልቁል ወረደ፤ በመንገድ ላይ ያለው ሰው ቆሞ መንገዱን ይለቅለታል። በግራና በቀኝ ያሉ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች እየተኮለኮሉ ወጥተው እስከሚርቅ ድረስ በአይናቸው ይሸኙታል። ጋሪዎች በፈረስ አንገት ላይ በተንጠለጠለው ቃጭል ኪልኪልታ በተጨማሪ ቆርቆሮውን እየደበደቡ አብረው የተወሰነ መንገድ አጀቡት፡፡ ከነሱ መካከልም ዋነኛው ሁካታ የሚወደው ሰንበቴ ነበር። ሞቅ ብሎ ግርግር ከማያጣው የከተማዋ ዋና አስፓልት ሲያልፍ ባጃጆችና መኪኖች እንደ ሰርግ ጥሩምባቸውን እያንጳጱ ከተማዋን አደመቋት። በዚ ጊዜ ነበር አብዛኛው ነዋሪ እለቱ የአድዋ ድል መታሰቢያ ስለመሆኑ ትዝ ያለው፡፡
ክብረት የጦዘ ስሜት ውስጥ ቢሆንም የብዙዎቹን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡
   “የአድዋ ድል ይስፋፋ
    ጀግና ይኩራ ባንዳ ይጥፋ…”
በዚህ ሁኔታ ሲዞር ቆይቶ ጸሀይዋ ከምዕራቡ አድማስ ስታዘቀዝቅ ሰውነቱ ዝሎ እንደተጠመቀ ሰው ላቡ መላ አካሉን አርሶት ጉሮሮው ተዘግቶ ቤቱ ደረሰ፡፡ ቤቱ እንደገባ ምን አላደረገም፡፡አልጋው ላይ ሄዶ ተዘረገፈ፡፡ እንደዛን ቀን አይነት እንቅልፍ በህይወቱ ተኝቶ አያውቅም፡፡ የሞተ ሰው አይነት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት እስከ ማግስቱ እኩለ ቀን አልተነሳም ነበር፡፡ በከተማው ሁሉም ክፍል የሳምንቱ ታላቅ መነጋገሪያ ባለክራንቹ ሰውዬ ነበር። ያ ጸጥ ያለውን የከተማዋን ነዋሪና ጎዳናዎችን በፉከራ ያነቃቃው ሰውዬ-ያ በከፍተኛ ስሜት ጩሀቱ ከድምጽ ማጉያ በላይ ሲያስተጋባለት የነበረው ሰውዬ! ክብረት የአድዋ እለት፡፡

Read 2527 times