Print this page
Wednesday, 06 March 2019 10:47

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

ክፍል- ፲፪ ሥልጣኔውን የማዘመን ሙከራዎች


እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የሰው ልጅ ህይወት ሁለት መንገዶች አሉት - አንድም የመንፈስ፣ ሌላም የህሊና›› ይላል፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የመጀመሪያውን መንገድ መርጧል (2003፡ 64)፡፡ መንፈሳዊው መንገድ ደግሞ ከተፈጥሮ ህግና ከሰው ልጅ ዕውቀት በላይ የሆኑ ‹‹ተአምራት›› የሚከናወኑበት መንገድ ነው። ይሄ የተአምራዊነት መንገድ ግን ለዘርዓያዕቆብ ከተፈጥሮ ህግ ጋርም ሆነ ከሰው ልጅ ልቦና ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ራሱን የሚያስበው፣ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ (Transcendence of Nature) ሥልጣኔ አድርጎ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ሥልጣኔው ለተፈጥሮ ከፍተኛ የሆነ ንቀት አለው፡፡
ዘርዓያዕቆብ ከያሬዳዊው ሥልጣኔ የተነጠለበት አንደኛው ሐሳብ በመንፈሳዊነትና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ነው፡፡ ለዘርዓያዕቆብ፣ መንፈሳዊነት የሚመጣው ተፈጥሮን በደንብ ካወቁ በኋላ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ተፈጥሮን ሳያውቁ መንፈሳዊ መሆን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም፣ የተፈጥሮ ህግ ወደ መንፈሳዊነት ይመራናል፡፡ ለያሬዳዊው ሥልጣኔ ግን መንፈሳዊነት የሚመጣው ተፈጥሮን ማወቅ ሳያስፈልገን በቀጥታ ተፈጥሮን በመሻገር (transcend በማድረግ) ነው፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ለተፈጥሮ ካለው ንቀት የተነሳ፣ ተፈጥሮን ለማወቅ እንኳ ምንም ዓይነት ፍላጎት የለውም፡፡
ያሬዳዊው ሥልጣኔ ተፈጥሮን የሚንቀው ደግሞ ቁስ አካል በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ብህትውናዊ በሆነው አስተምህሮ፣ ቁስ አካል ከመንፈስ ዝቅ ያለ ክብርና ዲበ አካላዊ እውነታ (lower metaphysical reality) ያለው ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ተፈጥሮን የሚንቀው ቁስ አካል በመሆኑ ብቻ እንጂ ተፈጥሮን አውቆትና መርምሮት አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ የንቀቱ መነሻ ዕውቀት ሳይሆን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ነው፡፡
ይሄ ንቀት ግን ለያሬዳዊው ሥልጣኔ አላዋጣውም። ምክንያቱም፣ ሥልጣኔው በተለያዩ ወቅቶች ላይ በተፈጥሮ ኃይላት (ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ፣ ድርቅ፣ ርሃብ፣ ወረርሽኝ…) ሲፈተንና ኃይሏንም መቋቋም ሲሳነው ታይቷል፡፡ በዚህም፣ ከተፈጥሮ ኃይላት ጋር ሲነፃፀር ያሬዳዊው ሥልጣኔ ደካማ መሆኑን አሳይቷል፡፡
በዚህም፣ ሥልጣኔው በመንፈሳዊና በዓለማዊ ገፅታው መንታ መልኮችን ተላብሶ እናገኘዋለን - ከፍታንና ዝቅታን፣ ሀብትንና ድህነትን፣ ልህቀትንና መራቆትን፡፡ ይሄንን የሥልጣኔውን ጉድለት ግን ለዘመናት ከማስታመምና ለመንስኤውም ሌላ ተአምራዊ ትርክት ከማላበስ ውጭ፣ ሥልጣኔው ባፈራቸው ልሂቃን ዘንድ ጉድለቱን አምኖ የመቀበል ነገር አልታየም፡፡ ዘርዓያዕቆብ፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ከተፈጥሮ ጋር በማስታረቅ፣ ጉድለቱን ለመሙላት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
ያንቀላፉት የሥልጣኔው ልሂቃን
ያሬዳዊው ሥልጣኔ እርሾውን ከግብፅ የበረሃ አባቶች በ5ኛው ክ/ዘ መጨረሻ ከወሰደ በኋላና በ6ኛው ክ/ዘ የቀይ ባህሩን የንግድ መስመር በሙስሊሞች ከተነጠቀ በኋላ፣ ለረጅም ዘመናት ከየትኛውም ባህልና ህዝብ ጋር ሳይገናኝ የታሪኩን ምዕራፍ በራሱ ልሂቃን እየቀየደ የኖረ ሥልጣኔ ነው፡፡ እንግሊዛዊው የታሪክ ፀሐፊ ኤድዋርድ ጊበን ይሄንን ክስተት፤ ‹‹ኢትዮጵያኖች ለአንድ ሺህ ዓመታት ዓለምን ረስተው ተኙ፤ ዓለምም እነሱን ረሳቸው›› (1946፡ 327) በማለት ይገልፀዋል፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ራሱን አጥሮ በኖረባቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ፣ ልሂቃኑ ስለ ሥልጣኔው የፈጠሩት ምስል በጣም የተጋነነ፣ በሁለመናው የተሟላና የሥልጣኔዎች ሁሉ ቁንጮ አድርገው ነው፡፡
ልሂቃኑ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከሌሎች ሥልጣኔዎች አንፃር ያለበትን ደረጃ ለመገምገም፣ በ16ኛውና በ17ኛው ክ/ዘ - በግራኝ መሐመድ ወረራ እና በሚሲዮናውያን ወቅት - መልካም ዕድሎችን አግኝተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ ሥልጣኔው ያቋረጠውን እንቅልፍ ከመቀጠል ውጭ፣ የሥልጣኔው ልሂቃን ንፅፅሩን ወደ ውይይት አላመጡትም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከ16ኛው ክ/ዘ ጀምሮ በክፉም ሆነ በደግ ከሌሎች ሥልጣኔዎች ጋር የመገናኘት ዕድል ቢኖረውም፣ ሆኖም ግን፣ ግንኙነቱ በሥልጣኔው ልሂቃን ውስጥ ለውይይት የሚሆን ምንም ነገር አላጫረም፡፡
ያሬዳዊው ሥልጣኔ ለራሱ የነበረው ምስል በጣም የተጋነነ መሆኑንና ጉድለት ያለበትም እንደሆነ በይፋ መታመን የተጀመረው ከልሂቃኑ ይልቅ በነገስታቱ ነው፡፡ ይሄም ‹‹የልሂቃን ሀገር›› ተብሎ ለሚጠራ መንግስት ያልተለመደ ነገር ነው። በምዕራባዊው ሥልጣኔ፣ መንግስታት የፖሊሲ ለውጦች የሚያደርጉት ጉዳዩ በመጀመሪያ በሀገሬው ምሁራን ዘንድ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ነው። ይሄም፣ ሐሳቡ በባለሙያዎች ዘንድ ከተለያየ አቅጣጫ በደንብ እንዲፈተሽ ዕድል ይሰጣል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውይይቶች በያሬዳዊው ሥልጣኔ ልሂቃን ዘንድ ስላልነበረ፣ ለውጡ የሚጠበቀው በቀጥታ ከመንግስት ነበር፡፡
በመንግስት ደረጃ፣ በይፋ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ጉድለት እንዳለበትና ጉድለቱንም ለመሙላት ተፈጥሮን በመቆጣጠር ላይ ከተመሰረተው አውሮፓዊ ሥልጣኔ ቴክኖሎጂን በመቅዳት መዘመን እንዳለበት ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ አቋም የተወሰደው በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ነው፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ከአውሮፓ ሥልጣኔ ጋር በማነፃፀር፣ ለኢትዮጵያ ነፃነትና የወደፊት ዕድገት እስከ ዛሬ ድረስ የመጣንበት ‹‹የመኮፈስ መንገድ›› እንደማያዋጣና ኢትዮጵያን በአውሮፓዊው ‹‹የህሊና መንገድ›› ማዘመን እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ የደረሱት በራሳቸው እንጂ፣ ከልሂቃኑ በመጣ ሐሳብ አይደለም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ሐሳብ በልሂቃኑ ታሽቶ የመጣ ስላለሆነ፣ በርካታ ግርድፍ ነገሮች ነበሩት። ለዚህም ነው የንጉሱ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ገና ከመነሻው በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት፤ ዋነኛ ተገዳዳሪዎችም ራሳቸው ልሂቃኑ ነበሩ፡፡
ምንም እንኳ፣ አፄ ቴዎድሮስ ሐሳባቸው ባይሳካላቸውም፣ ለኢትዮጵያ ነፃነትና የወደፊት ዕድገት ‹‹ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ማዘመን ያስፈልጋል›› የሚለውን ሐሳብ ወደ ቤተ መንግስት በማስገባት አጀንዳው ከእሳቸው በኋላ የሚመጡ ነገስታትም ጭምር እንዲሆን አድርገዋል፡፡
ሆኖም ግን፣ ዘመናዊነቱ ከትውፊታዊው ዕውቀትና ባህል ጋር ሊኖረው የሚችለውን መስተጋብር በተመለከተ ከልሂቃኑ ምንም ዓይነት ሐሳብ ስላልመጣና በዚህ ረገድ ልሂቃኑ ሀገራዊ ሚናቸውን ስላልተወጡ፣ ‹‹የዘመናዊነቱን ፕሮጀክት›› ነገስታቱ በራሳቸው መንገድ እንዲሞክሩት አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ሀገራችን ‹‹የዘመናዊነት መሞከሪያ ላብራቶሪ›› እስክትመስል ድረስ ላለፉት 150 ዓመታት በአምስት መንግስታት (በአፄ ቴዎድሮስ፣ በአፄ ምኒሊክ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ) አምስት የዘመናዊነት ፕሮጀክቶችን ስትቀያይር ነበር። ከአንደኛው ፕሮጀክት ወደ ሌላኛው ፕሮጀክት ሽግግር ሲደረግም ልሂቃኖቻችን ምንም ዓይነት ውይይት አላደረጉበትም፡፡
በልሂቃኖቻችን ዘንድ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ‹‹ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ ማምረት›› የሚለው ፖሊሲ ለምን እንዳልተሳካ ውይይት ሳይደረግበት፣ አፄ ምኒሊክ ‹‹ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ ከማምረት ይልቅ፣ ወደ ሀገር ማስገባት›› በሚለው ፖሊሲ ተተካ። አፄ ኃይለ ሥላሴ የፈረንጅ ትምህርትን በማምጣት የጀመሩትን መንገድ፣ የአብዮቱ ተማሪዎች ደግሞ ‹‹ርዕዮተ ዓለም በመዋስ›› ቀየሩት፡፡
ሁሉም ግን፣ የውጭ ቴክኖሎጂ፣ ትምህርትና ርዕዮተ ዓለም ላይ ሲያተኩሩ፣ አንድ መሰረታዊ ነገር ረስተው ነበር፡፡ ቴክኖሎጂ፣ ትምህርትና ርዕዮተ ዓለም ከውጭ ሀገር ሲዋሱ፣ የተዋሱትን ነገር በሀገር ውስጥ ምን ዓይነት መሬት ላይ እንደሚያሳርፉት ረስተውት ነበር - ባህሉን - ብህትውናና ተአምራዊነት ላይ የተመሰረተውን ባህል!! ያሬዳዊው የብህትውና ባህል ከአውሮፓ ትምህርትና ቴክኖሎጂ ጋር የሚኖረው መስተጋብር ምንድን ነው? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ፣ በአምስቱም የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች የተረሳ ነበር፡፡ ይሄንን ጥያቄ በክፍል-13 እመለስበታለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡




Read 1072 times