Wednesday, 06 March 2019 10:46

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


“ታስረው ከሚቀለቡ እንስሶች እየተራቡ በነፃነት የሚኖሩ አውሬዎች ይሻላሉ”


የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በፋሽስት ኢጣሊያ በጅምላ የተጨፈጨፉበት፣ ሰቆቃ የታወጀበት፣ ገሃነም የወረደበት ዕለት ነበር፤… በየዓመቱ በሃዘን እናስታውሰዋለን፡፡ የዛሬውን ቀን ደግሞ እነዚሁ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች፤  ቀደም ሲል የተዋረዱበት፣ ህልማቸው ጨንግፎ፣ አንገታቸው ዝቅ ብሎ ወደ መጡበት የተባረሩበት ዕለት ነው። … ይቺ ቀን ኢትዮጵያውያኖች ሃይማኖትና ዘር ሳይለያቸው፣ ማንነታቸውን ያሳዩበት፣ አፍሪካውያን አንገታቸውን ያቀኑባት … “ኩራት፣ ኩራት አይልሽም ወይ!?” የተዘፈነባት ናት… ሁለቱንም የጣሊያን ወረራዎች ስናስታውስ፣ ከአገራችን ጎን ቆመው የነበሩትን የሌሎች ሃገራት ዜጎችን ወይም አለም አቀፍ ሰብዓውያንን ጭምር በማሰብና ለነሱም መጪው ትውልድ፣ ሐውልት ያቆምላቸዋል በሚል ተስፋ ነው፡፡ … እንኳን ለታላቁ የዐድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!!”
*   *   *
የገሃነም ስም ከተነሳ አይቀር ‹Live› የምትባል ቀልድ ሰምቼ ነበር፡፡ … ገሃነም ውስጥ ስልክ የሚደወልበት ቦታ አለ አሉ፡፡ ‹ቴሌ ሴንተር› ዓይነት። እንደ ሌሎቹ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም አውሮፓ፣ አሜሪካና ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት ሌሎች ቦታዎች ስልክ ሲደውሉ በሺ የሚቆጠር ገንዘብ ይከፍላሉ …. ውድ ነው፡፡ ደስ የሚለው ግን ‹ሃሎ!› የሚሉት ወደ አገር ቤት ከሆነ ክፍያው ትንሽ መሆኑ ነው … የነፃ ያህል፡፡ ‹ለምን?› ብለን ስንጠይቅ፤ … ”የአገር ውስጥ ጥሪ ስለሆነ፡፡” አሉ፡፡ … ይቺን እንጨምርባት፡-
ጋዜጠኛ፡- “ኢትዮጵያን ከገሃነም ክልል ለመገንጠል የሚታገለውን ቡድን ትረዳለህ ይባላል?” ተብሎ ሲጠየቅ፤ “በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም” በማለት መለሰ አሉ፡፡ … እሱ ማን ነው?
*   *   *   
ታላቁ ዊሊያም ብሌክ፡- “ታስረው ከሚቀለቡ እንስሶች (Caged animals) እየተራቡ በነፃነት የሚኖሩ አውሬዎች ይሻላሉ፡፡” ይለናል፡፡
ወዳጄ፡- አንዳንድ ሰው ነፃና ራሱን መሆን የሚያስቸግረው፣ ህገ መንግስታዊና ተፈጥሯዊ መብቶችን ተግባራዊ ማድረግ ጣጣ የሚያመጣበት ወይም ትልቅ ዋጋ እንዲከፍል የሚያደርገው፤ ባልተመረመሩ ዕምነቶች፣ ጭፍን ስሜትና አጓጉል ቅዠቶች በተተበተበ ኋላቀር ማህበረሰብ ውስጥ ስለሚኖር ይመስለኛል፡፡ የአምባገነንና ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግስታት ጉዳይ ሳይዘነጋ፡፡  
በነፃ ፈቃድ ላይ የተመሰረቱ አስተሳሰቦች፣ ወጎች፣ ልማዶችና በሰለጠነው ዓለም ዕምነቶች የሌሎችን መብትና ነፃነት እስካልተጋፉና ማህበራዊ ጠንቅ እስካላስከተሉ ድረስ እምነታቸውን የማስፋፋት ፈቃድ አይነፈጉም፡፡ ምክንያቱም እንደነዚህ ዓይነት አስተሳሰቦች፣ በስልጣኔ ሂደት እየደበዘዙ፣ ከዕምነትነት ወደ ኑሮ ዘይቤነት፣ ከቀኖናዊነት ወደ ማህበራዊ ልማድ የሚሸጋገሩበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ ነው፡፡ እስከ ዘለቁበት ድረስም የልዩነት ጌጥ ወይም ምልክት ሆነው ስልጣኔን ያደምቃሉ፡፡ ጠለቅ ብዬ ባላውቅም ‹ራስ ተፈሪያኒዝም› ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
ወዳጄ፡- ስልጣኔ እያለዘባቸው የመጡ፣ እርስ በራሳቸው ለ‹ሺ› ዘመናት ሲዋጉና ሲጨፋጨፉ የነበሩ እምነቶች፤ “እኔ ያመንኩትን ካላመንክ፣ እኔ የፈለግኩትን ካላደረግህ ወዮልህ” በማለት ብዙ ታላላቅ ሊቃውንቶችን፣ ታላላቅ አሳቢዎችን ሲጨፈልቁና ሲያስደነብሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አጓጉል አስተሳሰብ በማይታይበት ወቅትና ቦታ፣ ማህበረሰቡ የአክራሪዎችን ጥቃት ስለሚፈራ፣ በጎና የሰለጠነ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፣ በነፃነት ሃሳባቸውን እንዲገልፁ አያበረታታም፡፡ ከማዳመጥ፣ ከማንበብና ከመመርመር ይልቅ መጽሃፍቶችን በማቃጠልና ግለሰቦችን በሀሰት በመወንጀል ድንቁርና ሲተገበር ተስተውሏል፣ ስልጣኔንም አደናቅፏል፡፡ በእንደነዚህ ዓይነት ቦታዎች የሚገኙ መናፈሻና መዝናኛዎች፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆችና የመንግስት ቢሮዎች፡- እስር ቤት፣ የባዶ ወሬና የቅዠት ገነት ናቸው፡፡
ወዳጄ፡- የዘር ፖለቲካ ባሰከራቸው ሰዎች መሃል መኖርም በገሃነም የመኖር ያህል ነው፡፡ እንደውም ከሊቃውንት፣ ከዕኩዮችና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ደረጃቸውን በጠበቀ መደበኛ እስር ቤት መቆየት ትርፍ አለው፡፡ የቀድሞ የባህልና ቱሪዝም ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሀብተስላሴ (ካልተሳሳትኩ) ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፡- በታሰሩበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ተጠይቀው ሲመልሱ፤… “አሁን ያለው እስር ቤት እንደ ያኔው ቢሆን በፈቃደኝነት እታሰራለሁ፡፡ … ያውም ገንዘብ እየከፈልኩ” ብለው ሲናገሩ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያሉት የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ገሃነም ሊባሉ እንደሚችሉ፣ ከ3 ቀን በፊት፣ በሚዲያ የተገለፀው የጥናት ውጤት አረጋግጧል፡፡
ወዳጄ፡- እኔ እንደሚገባኝ፤ ገሃነም ማለት ሰማይ ላይ የተንጠለጠለ፣ የስቃይ ዓለም ሳይሆን አዕምሯችን ውስጥ የሚንቦገቦግ ክፋት ወይም የአስተሳሰብ ነውር ነው፡፡ … ለዚህ ይመስላል የአገራችን ሰው፡-
“ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” -- በማለት የሚመክረን፡፡ ወዳጄ፡- ቅንነት ያቀናል፣ ምክንያታዊነት ያስከብራል፣ የሌሎች ፍቅር ላንተ ፅድቅ ነው፡፡ ዜጎች እንኳን በገዛ ሃገራቸው ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ በሌሎች ሃገራት የመኖርና በሚመርጡት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመተዳደር መብት አላቸው፡፡ ዜጎችን ማገዝና መርዳት ሲኖርብህ፣ ከመኖሪያቸው ማፈናቀል ማለት፣ ነፍስህን ከገነት ማፈናቀል መሆኑን፣ ለዜጎች ህመም መሆን ማለት፣ ራስን በሽተኛ ማድረግ መሆኑን አትርሳ፡፡ የሌሎች ገሃነም ላንተ ፅድቅ አይሆንም፡፡ ባልተመረመረ የጅምላ አስተሳሰብ ከተጠለፍክ፣ የምትወድቀው የቁጭት ማጥ ውስጥ ነው፡፡
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው የራሱ ፀጋ፣ የራሱ ምህዋር፣ የራሱ የቤተሰብ መሰረት፣ ዓለምን የሚመለከትበት የራሱ መነፅር፣ ኑሮውን የሚስልበት ሰሌዳና ብሩሽ፣ ዘመኑን የሚያትምበት የጣት አሻራና የዓይን ቀለም አለው፡፡ አንድ ነገር ልብ በል፡- ብታምን በራስህ ልብ፣ ብታተርፍ በራስህ ስፍር፣ ብትቀበል የራስህን ደሞዝ፣ ብትጫወት በራስህ ችሎታ፣ ተፈትነህ የምታልፈውም በራስህ ውጤት ነው። የቶታሊቴሪያኒዝምና የመንጋ አስተሳሰብ ጊዜው አልፎበታል፡፡ በራስ መቆም ስልጣኔ ነው!!
‹በራስ መቆም› የምትል፣ ለ‹ቀድሞው› መሿለኪያ የተፃፈች ‹ግጥም› ትዝ አለችኝ፡፡
ጉራሽን ለወታደር፣
ድንግልሽን ላራዳ ልጅ፣
ሃድራሽን ለጥበበኛ፣
ባንኮኒሽን ደግሞ ለኛ!!
አደላድለሽ
ማታ ማታ
ትዘፍኚያለሽ …
“በራሳቸው የሚቆሙ
ሙሽሮቼ ናቸው”
ብለሽ!
*   *   *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- “በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም” ያለው ማ‘ነው?› ብዬ ነበር፡፡ … ‹እግዜር› እንዳትለኝ ብቻ!
በድጋሚ መልካም በዓል!!
ሠላም!!Read 480 times