Sunday, 10 March 2019 00:00

መኢአድ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በደቡብ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ በህዝብ ላይ የሚደርሱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችና ሰቆቃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲሁም በደቡብ ክልል የታሰሩ አባላቱ እንዲለቀቁ መኢአድ ጠየቀ፡፡
“በደቡብ ክልል በህዝብና በአባሎችን ላይ የሚደርሰውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን” በሚል ትናንት (አርብ) ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጠው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በተለይ በቴፒ፣ በሸካ እና በሳውላ ከተሞች ዜጎች ላይ ኢ-ሰብሰዊ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ነው ብሏል፡፡
በክልሉ ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ከ6 ወር በፊት የታሰሩ 70 ያህል የፓርቲው አመራርና አባላት ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሰረትባቸው ያለ ፍትህ ታስረው እንደሚገኙ ያስረዳው የድርጅቱ መግለጫ ታሳሪዎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመባቸው ነው ብሏል፡፡
የአስተዳደር ጥያቄ በተነሳባቸው ቴፒ፣ ሸካ፣ ቦንጋ አካባቢ በዜጎች ላይ ሰቆቃ፣ እስር እና ማዋከብ እየተፈፀመ መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በዚህም የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ በህዝቡና በፓርቲው አባላት ላይ የሚፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ተግባር በአስቸኳይ እንዲያስቆም፣ የክልሉ መንግስት ጠቅላይ አቃቢ ህግም በፓርቲው አባላት ላይ የተፈፀመውን የመብት ረገጣ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ ፓርቲው በመግለጫው ጠይቋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ በለገጣፎ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ተዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ የዜጎች መፈናቀልና ቤት ማፍረስ ተግባራት እንዲቆም ፓርቲው ጠይቋል፡፡  

Read 776 times