Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ የመንግስታቸውን ስድስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች አስታወቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ሰላም - ዲሞክራሲ - ብልፅግና - አገራዊ አንድነት - ፍትህ - አገራዊ ክብር

ለኢትዮጵያ ዳግም እድገት፣ ብልፅግናና አንድነት ምሰሶዎች ናቸው የተባሉ ስድስት የትኩረት አቅጣጫዎች መለየታቸውን  የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይፋ ያደረገው መረጃ አመልክቷል፡፡
በሚቀጥሉት አመታት ሃገሪቱ የምትገነባባቸው ስድስት ምሰሶዎች ብሎ መንግስት ያስቀመጠው ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ብልፅግና፣ ሃገራዊ አንድነት፣ ፍትህና ሃገራዊ ክብር የሚሉት ናቸው፡፡
“ሰላም ከሌለ አብሮ መኖር፣ ሰላም ከሌለ ሃገር መገንባት፣ ወጥቶ መግባት አይቻልም ያለው መግለጫው፣ ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ቀዳሚው የመንግስት ስራ ይሆናል ብሏል፡፡
ዲሞክራሲን በተመለከተም እንደከዚህ ቀደሙ የአፍ ዲሞክራሲ ሳይሆን የተግባር ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ማረጋገጥ እንደሚገባ የጠቆመው መግለጫው፤ ፍትህ ከሌለ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ብልፅግናና ሃገራዊ አንድነት ማረጋገጥ ስለማይቻል ፍትህ፣ ኢኮኖሚ፣ በሰላም፣ ወጥቶ መግባት፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በእኩል የሚያይ፣ በእኩል ዓይን የሚዳኝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህግ ፊትና በሃገራችን እኩል የሚሆንበት ስርአት መፍጠር አንዱና ዋነኛው ትኩረት ነው ብሏል፡፡
መሬት፣ ውሃ፣ ማዕድን፣ ለቱሪዝም ምቹ የሆነ ሃብት ያላት ሃገር አለችን የሚለው የትኩረት ማመላከቻ ሰነዱ፤ ሃገሪቱ ያላትን ሰፊ ወጣትና የተማረ ኃይል በመሰብሰብ፣ በመደመርና የሚሻለውን አቅጣጫ በማመላከት፣ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻላል ሃብት ያላት፡፡
ምንም ሰላም ቢኖር፣ ምንም ዲሞክራሲ ብናስፋፋ፣ ብልፅግና ብናመጣ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የማናስቀጥል ከሆነ፣ ጥረታችን ሁሉ ከንቱ ነው ያለው የማመላከቻ ሰነዱ፤ የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠል እንደ አራተኛ ምሰሶ ይዘን የምንሰራበት ይሆናል ብሏል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ክብር መሆኑን፣ የኢትዮጵያን ፓስፖርት መያዝ እንደማያሳፍር፣ በሄድንበት ሳንሸማቀቅ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” የምንልበትን ክብር መመለስ ያስፈልጋል ብሏል የትኩረት አቅጣጫ ማመላከቻ ሰነዱ - ስለ ሃገራዊ ክብር ባሰፈረው ትንተና፡፡

Read 1356 times