Sunday, 10 March 2019 00:00

“ስለ አዲስ አበባ ምን እናድርግ?” የሚል ውይይት ነገ ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


አወዛጋቢ እየሆነ በመጣው የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ “ስለ አዲስ አበባ ምን እናድርግ?” በሚል አጀንዳ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ባልደራስ የስብሰባ አዳራሽ ውይይት ይካሄል፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ለይ ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ፣ ስለ አዲስ አበባ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ይዞታ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፅሑፍ የሚያቀርብ ሲሆን በእለቱም ስለ አዲስ አበባ ምን እናድርግ? በሚል ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡
ይህን ህዝባዊ ስብሰባ ያስተባበሩት በመዲናዋ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አክቲቪስቶች፣ አርቲስቶችና የህግ ባለሙያዎች ሲሆኑ ውይይቱን ማካሄድ ያስፈለገው አሁን ባለው የፖለቲካ አሰላለፍ የአዲስ አበባ ህዝብ የራሱን እጣ ፈንታ መወሰን የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣቱ መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ስንታየው ቸኮል ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡ የአዲስ አበባን ህዝብ ገፍቶ የመጣል ሁኔታ በስፋት እየተስተዋለ ነው ያሉት አቶ ስንታየው፤ ይሄ በውስጧ ያሉ ነዋሪዎችን እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ በመሆኑ፣ ተመካክሮ መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ የተጋረጠው ወቅታዊ ችግር በጥናቱ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያብራሩት አቶ ስንታየሁ፤ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የሚቀርቡ ሃሳብና አስተያየቶች በከተማዋ ጉዳይ በያገባኛል ስሜት የተሰባሰቡ አካላት ቀጣይ እንቅስቃሴን የሚወስኑ ይሆናል ብለዋል፡፡
በእለቱ የሚካሄደውን ውይይት ተከትሎም በየደረጃው ላሉ የመንግስት አካላትና አለማቀፍ ተቋማት የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎትና ሃሳብ የሚያሳስብ ኮሚቴ ይቋቋማል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ስንታየሁ አስረድተዋል፡፡

Read 5589 times