Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

እጣ የወጣባቸው የኮዬ ፈጬ ቤቶች ለባለ እድለኞች እንዳይተለለፉ ክልሉ አገደ

  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወሰን ጥያቄ በተነሳባቸው የኮዬ ጨፌ አካባቢ የተገነቡና እጣ የወጣባቸው ቤቶች ባለ ዕድለኞች የማስተላለፍ ሂደት እንዳይተገበር ያሳሰበ ሲሆን የቤቶቹ ጉዳይ በክልሉ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖርያ ቤቶች በእጣ መተላለፋቸው ተገቢ አይደለም ያለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ክልሉ ጥያቄ እያነሳባቸው ባሉና የክልሉን ወሰን አልፈው  የገነቡ የጋራ መኖርያ ቤቶች የማስተላለፍ ሂደት እንዳይተገበር አቋም መያዙን ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ጉዳይም ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል የክልሉ መግለጫ፡፡
ለዚህ የኦሮሚያ ክልል የአቋም መግለጫ መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳትና ከሰሞኑ የወጣውን የኮንዶሚኒየም ቤቶች እጣ ድልድልን በመቃወም በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ሲካሄድ መሰንበቱ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈጬ ያስገነባውን ከ30 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለ እድለኞች በእጣ ማከፋፈሉን ተከትሎ፣ የወሰንና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን ያነሱት የተቃውሞ ሰልፈኞቹ፤ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄም እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ የተገነቡት ከአዲስ አበባ ወሰን ውጪ በኦሮሚያ ክልል መሬት ላይ ነው የሚሉ የተቃውሞ ማጠንጠኛ ሲሆን እነዚህ በክልሉ ወሰን ላይ የተገነቡ ቤቶች ባለቤትነት ለአዲስ አበባ አስተዳደር ሳይሆን ለኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ነው፤ ቤቶቹን ለቤት ፈላጊዎች ማከፋፈል የሚችለውም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ነው የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ቤቶቹ የተሰሩበት መሬት ላይ ለነበሩ አርሶ አደሮች በወቅቱ ተገቢ ካሳ ባለመከፈሉ ችግሩ መፈጠሩን ጠቅሶ ለካሳ ይሆን ዘንድ የአካባቢው አርሶ አደሮች ያለ እጣ ከተሰሩት ቤቶች 50 በመቶ እንዲወስዱ ወስኗል።
ይሁን እንጂ ተቃውሞ አቅራቢዎች “ይህን ውሳኔ አንቀበልም፤ መሬቱ ከእነ ቤቶቹ ለባለቤቱ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሊመለስ ይገባል” ሲሉ በተቃውሟቸው ሲቀጥሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ መጀመሪያ ቤቶቹ ከመተላለፋቸው በፊት ድንበር ማካለል ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ተቃውሞ አቅራቢዎቹ በአንድ በኩል አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካልነቷ መረጋገጥ አለበት የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፤ በሌላ ጎን አዲስ አበባ ከራሷ ወሰን አልፋ የኦሮሚያ መሬት በህገ ወጥ መንገድ ወስዳለች የሚል መከራከሪያ እያቀረቡ መሆኑ ጥያቄውን ያልጠራና ግራ አጋቢ እንዳደረገው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
“በኦሮሚያ ወሰን ውስጥ የተሰሩትን እነዚህን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአዲስ አበባ ነዋሪ መስጠት ማለት 5ሺህ ወጣቶች የተሰዉበትንና ተቃውሞ ሲቀርብበት የነበረውን ማስተር ፕላን ማስቀጠል” መሆኑን ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን ሰላማዊ ሰልፍ ከተካሄደባቸው የኦሮሚያ ከተሞች መካከል አዳማ፣ አሰላ፣ ባሌ አዳባ፣ ጉደር፣ ባሌ ሮቢ፣ ኢጄ፣ ሃረር-ሂርና፣ ቁልቢ፣ ጅማ፣ ጭሮ፣ ወሎ-ከሚሴ፣ ጉደር፣ ሻሸመኔ እና ሆለታ ተጠቃሽ ሲሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በሚገኙበት ኮዬ ፈጬ አካባቢም ሰልፍ ተደርጓል፡፡

Read 7324 times