Sunday, 10 March 2019 00:00

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆኑ

Written by  ሠላም ገረመውና ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

“አዳዲስ ሃይሎችን ወደ መሪነት ለማምጣት ነው ሥልጣን የለቀቅሁት” - አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

የሥልጣን መልቀቂያቸውን ባቀረቡት የአማራ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምትክ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ ልማት ጉዳይ አማካሪ የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል፡፡
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአዴፓ ምክትል ሊቀ መንበርነታቸው ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡
ላለፉት 6 ዓመታት ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የስልጣን መልቀቂያቸውን ያቀረቡት ትናንት አርብ ጠዋት ሲሆን ጥያቄያቸውም ተቀባይነት ማግኘቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
አቶ ገዱ ስልጣናቸውን መልቀቅ የፈለጉበትን ምክንያት አስመልክቶ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የስልጣን መልቀቁ ሂደት ያስፈለገበት ምክንያት አዳዲስ ኃይሎችን ወደ መሪነት ለማምጣትና የመተካካት ሂደቱን ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡
ተተኪያቸው ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ ውስጣዊ አሠራርና አካሄድ ፀረ ዲሞክራሲያዊነትን በግምባር ቀደምነት ሲታገሉ የነበሩና በበርካታ የስራ ኃላፊነቶች ልዩ የአፈፃፀም ብቃቶች የነበራቸውና በትምህርት ዝግጅታቸውም ብቁ በመሆናቸው፣ በምክር ቤቱ ሙሉ ድምጽ መመረጣቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አሠማኸኝ አስረስ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የህዝብ ጥቅምን ማዕከል አድርጐ በመንቀሳቀስ ወሳኝ ሚና ያላቸው መሆናቸውም አዲሱን ርዕሰ መስተዳደር በክልሉ ም/ቤት ተመራጭ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አምባቸው መኮንን፤ በክልሉ የተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ማለትም የከተማ ልማት ቢሮና የሲቪል ሠርቪስ ቢሮ ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በትምህርት ዝግጅታቸው ሁለት የማስተርስ ድግሪ፣ አንድ የዶክትሬት ድግሪና በርካታ የምርምር ጽሑፎች ያዘጋጁ መሆናቸውን አቶ አሠማኸኝ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ም/ቤቱ በመደበኛ ጉባኤው ልዩ ልዩ ሹመቶችን የሠጠ ሲሆን፤ አቶ ምግባሩ ከበደ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲሁም አቶ ዮሐንስ  ያለው ደግሞ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡
አዲስ አድማስ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ያደረገውን አጠር ያለ ቆይታ በውስጥ ገጽ ላይ ይመልከቱ፡፡

Read 7854 times