Sunday, 10 March 2019 00:00

የአቶ ገዱ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአፍታ ቆይታ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

በትናንትናው ዕለት የስራ መልቀቂያቸውን አስገብተው ከአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደርነት የተነሱት አቶ ገዱ
አንዳርጋቸው፤ ከስልጣናቸው የለቀቁበትን ምክንያትና የወደፊት ዕቅዳቸውን አስመልክቶ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
ሰላም ገረመው ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ስልጣንዎን ለመልቀቅ የፈለጉበት ምክንያት ምንድነው?
ረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ ቆየሁ፡፡ በአንድ ቦታ መቆየት ደግሞ መሠልቸትም ይሆናል። አሁን ደግሞ መልቀቅ ያለብኝ ወቅት ነው፡፡ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስፈልገው አዲስ ሰው መሆን አለበት በሚል ነው የለቀቅሁት፡፡
የክልሉ ህዝብ ጠንካራ ድጋፍ እንዳለዎ ይነገራል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ስልጣንዎን ለመልቀቅ ምን አሳሰብዎ?
የህዝቡ ጠንካራ ድጋፍ ቢኖረኝም ስልጣን ረጅም ጊዜ ይዞ መቆየት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፤ ተተኪዬ ከእኔ የተሻለ በአዲስ መንፈስ ጥሩ ስራ መስራት ይችላል ብዬ አምናለሁ። ብዙ በክልሉ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ በአዲስ መንፈስ በአዲስ አቀራረብ የሚሰራ ሰው ያስፈልጋል፡፡ አቅጣጫ የሚያስቀምጠው ፓርቲው ቢሆንም ግን አዲስ ሀሳብ ቢመጣ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ክልሉ ከእርስዎ የስልጣን መልቀቅ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥመው ይችላል ብለው የሚያስቡት ችግር አለ?
ርዕሰ መስተዳድር ሆኜ በቆየሁበት ጊዜ፣ ከዛም በፊት በነበረኝ የስራ ደረጃ ሙሉ ጊዜዬን የክልሉ ህዝብ እንዲለወጥ  አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ወይም ክልሉ ከእኔ ስልጣን መልቀቅ ጋር በተያያዘ የሚገጥመው ችግር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
የወደፊት እቅድዎ ምንድነው?
ከዚህ በኋላ ቀለል ያለ ጥናቶችን መስራት፣ ማንበብ የምችልበት እድል ማግኘትና ያለኝን ልምድ ለህዝቡ ማካፈል እንዲሁም እታች ላሉ አመራሮች ልምዴን እያካፈልኩ፣ አብሬ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እፈልጋለሁ፡፡
ከፖለቲካው የመውጣት ፍላጎት አልዎት?
ከፖለቲካ የመውጣት ፍላጐት የለኝም። ዶ/ር አምባቸው ክልሉን በአዲስ የለውጥ መንፈስ እየመሩ የተሻሉ ነገሮችን ይሠራሉ ብዬ አምናለሁ - ብቃት አላቸው፡፡
በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው፡፡ ለውጥ ለማምጣት እድሉም አለ፡፡ ዶ/ር አምባቸው ጠንካራና ብቃት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡

Read 1972 times