Sunday, 10 March 2019 00:00

ፎርብስ የአመቱን የአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ጄፍ ቤዞስ በ131 ቢሊዮን ዶላር ዘንድሮም ቀዳሚ ናቸው

     ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2019 የፈረንጆች አመት የአለማችን ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ በ131 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ዘንድሮም ቁጥር አንድ የአለማችን ባለጸጋ ሆነዋል፡፡
የኣማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ የኩባንያቸው የአክስዮን ዋጋ ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ አምና ከነበራቸው ሃብት የ19 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ በማድረግ ዘንድሮም ቀዳሚው የአለማችን ባለሃብት ሆነው መቀጠላቸው የጠቆመው የፎርብስ ዘገባ፣ የማይክሮ ሶፍቱ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በ96.5 ቢሊዮን ዶላር በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን አመልክቷል፡፡
ሌላው አሜሪካዊ ቢሊየነር ዋረን በፌት ምንም እንኳን የተጣራ የሃብት መጠናቸው አምና ከነበረው በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቶ 82.5 ቢሊዮን ዶላር ቢደርስም በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ የሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ የአውሮፓ ቁጥር አንድ ቢሊየነር የሆኑት በርናንድ አርኖልት በ76 ቢሊዮን ዶላር ከአለማችን ቢሊየነሮች የአራተኛነት ደረጃን ሲይዙ፣ ሜክሲኳዊው የቴሎኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አማኒኮ አርቴጋ በ62.7 ቢሊዮን ዶላር ስድስተኛ፣ ላሪ ኤሊሰን በ62.5 ቢሊዮን ዶላር ሰባተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ አምና በአምስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙከርበርግ የሃብት መጠኑ በ8.7 ቢሊዮን ዶላር በመቀነሱ ዘንድሮ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል፡፡ ፎርብስ መጽሄት ለ33ኛ ጊዜ ይፋ ባደረገው የአለማችን ቢሊየነሮችን ዝርዝር ውስጥ 2 ሺህ 153 ቢሊየነሮች የተካተቱ ሲሆን፣ የቢሊየነሮቹ አጠቃላይ ድምር የተጣራ ሃብትም 8.7 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
የአለማችንን ቢሊየነሮች ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ የተቀላቀሉት አዳዲስ ባለጸጎች ቁጥር 195 እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና 1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያስመዘገበው የሪያሊቲ ቲቪ ሾው ባለቤቱ የ21 አመቱ ካይሊ ጄነር የዘንድሮው ቁጥር አንድ የአለማችን የልጅ ሃብታም ተብሏል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ በድምሩ 3.1 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት ያፈሩ 607 ቢሊየነሮችን ያካተተቺው አሜሪካ በርካታ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን የያዘች ሲሆን፣ ቻይና 324፣ ጀርመን 114፣ ህንድ 106፣ ሩስያ 98 ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ይከተላሉ፡፡ በ16.6 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያፈሩት ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ አምና ከነበሩበት የ103ኛነት ደረጃ በእጅጉ መሻሻል በማሳየት ዘንድሮ 64ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋ ሆነው ከመቀጠልም ሆነ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት 13 ጥቁር ቢሊየነሮች መካከል አንደኛው ከመሆን የሚያግዳቸው ግን አልተገኘም፡፡  3.1 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያፈሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አምና ከነበሩበት የ766ኛ ደረጃ ወደ 715ኛ ደረጃ ከፍ ማለታቸውን ተነግሯል፡፡
በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት የአለማችን ቢሊየነሮች መካከል 252 ሴቶች ሲሆኑ፣ አሜሪካ 87፣ ጀርመን 30፣ ቻይና 26 ሴት ቢሊየነሮችን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት ቀዳሚ ሆነዋል፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ቢሊየነሮች መካከል 994 ያህሉ የሃብት መጠናቸው አምና ከነበረበት ቅናሽ ማሳየቱን የጠቆመው ፎርብስ፣ ሃብታቸው አምና ከነበረበት በእጅጉ ቀንሶ በቢሊዮን ከመቆጠር ወደ ሚሊዮን የወረደባቸው 247 ያህል ባለሃብቶች ደግሞ ከዝርዝሩ ውጭ መደረጋቸውን አመልክቷል፡፡

Read 3178 times