Saturday, 09 March 2019 00:00

“ሮሃ ሙዚቃ የጥበብ ምሽት” አድዋን በመዘከር 3ኛ ዓመቱን ያከብራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


         በአዳማ ወጣት ገጣሚያን የተመሰረተው ሮሃ ሙዚቃ የኪነ ጥበብ ምሽት፣ አድዋን በመዘከር 3ኛ ዓመቱን ነገ በአዳማ ራስ ሆቴል የባህል አዳራሽ በድምቀት እንደሚያከብር መስራቾቹ አስታወቁ፡፡
በ121ኛው የአድዋ ድል በዓል ማግስት የተመሰረተው “ሮሃ ሙዚቃ“ የኪነ ጥበብ ምሽት፤ ባለፉት ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም በተለይም ለአዳማና አካባቢው የጥበብ ብርሃን ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት ገጣሚያኑ፤ ዘንድሮ በስኬት ያሳለፏቸውን ሶስት ዓመታት በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ያከብራል ተብሏል፡፡ በዕለቱ የጉዞ አድዋ መስራቾች ከሆኑት አንዱ ያሬድ ሹመቴ በክብር እንግድነት የሚገኝ ሲሆን ግጥም፣ ዲስኩር፣ “ፍራሽ አዳሽ” የአንድ ሰው ተውኔት፣ ታሪክ ነገራ፣ አድዋን የሚዘክር ሙዚቃና ሌሎች መሰናዳዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ፣ በቃሉ ሙሉ፣ ኤፍሬም መኮንን፣ ሄለን ፋንታሁን ዳግም ህይወትና ሌሎችም የግጥም ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን በአንድ ወንድና በአንድ ሴት ግጥም በውዝዋዜ እንደሚቀርብ ገጣሚና ተወዛዋዥ ኤፍሬም መኮንን (ኤፌማክ) አስታውቋል፡፡   

Read 709 times