Sunday, 10 March 2019 00:00

“ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

         
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ግማሹ ዓመት አለቀ! የቀን መቁጠሪያችሁን ወሩን ጠብቆ መገለባበጥ ረስታችሁ አሁንም ገና ሦስተኛ ወር ላይ ነው! ጊዜው ይሮጣል፣ እድሜ ይሮጣል፣ የዳቦ ዋጋ ይሮጣል… እነኚህ ሁሉ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ‘ፖለቲካችንም’ በሁሴን ቦልት ፍጥነት ይሮጣል፡፡ ‘እንክት አድርጎ’ ነዋ የሚሮጠው! እንደውም… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ቦተሊካው’ ባለፈው ዓመት ገደማ ወደ አስር ዓመት ሮጧል። ችግሩ ምን መሰላችሁ… ‘ቦተሊካው’ መሮጡን ብናውቅም ግራ የገባን ወደ ጎን ይሩጥ ወደ ኋላ ማወቅ ስላቃተን ነው።  ልክ ነዋ… የዚህን ዘመን ‘በእውቅት ጢም ያለ ጭንቅላት’ ይዘው በአስራ አምስተኛ ክፍለ ዘመን ቅኝት የሚያስቡ የሚመስሉ በዙብና! (ወይ ዘመንና ሀሳብ እኩል እስኪመጡላቸው ድረስ ረጅም እረፍት ይውጡልንማ!)
እንዴት ነህ እንዴት ነሽ አንባባልም ወይ
ሰው ከአባቱ ገዳይ ይታረቅ የለም ወይ
የሚሏት ነገር ነበረች…አገር እንዲህ ዓይንና ናጫ ሳይሆን ማለት ነው፡፡ የምር እኮ… ዘንድሮ አይደለም ሰው ከአባቱ ገዳይ ሊታረቅ፣ አገር አንደኛው ጫፍና ሌላኛው ጫፍ ሆኖ የማይተዋወቀው ሰው ሁሉ የጎሪጥ እየተያየ ያለ ነው የሚመስለው፡፡
እንክርዳድ እንክርድድ የተንከረደደ፣ የተንከረደደ
ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ
ለራስሽ አትሆኚ ወይ ለሰው አታስቢ
ገንዘብ ይገድልሻል ስትስገበገቢ
አንቺ ባለጠላ ሰው የምትጎጂበት
ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት
--- ተብሎ ተዘፍኗል፤ እናላችሁ… ዘንድሮ “ስንዴ መስሎ ገብቶ ሰው እያሳበደ…’ ያለ ስንት ነገር አለ መሰላችሁ! በምናምኑም በምናምኑም መተማመን ያቃተን እኮ ለዚሁ ነው… ስንዴ  የሚመስል እንክርዳድ በዝቶብን፡፡ ዘንድሮ የጤፍ ‘ጄሶ’ ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ውስጥ ጄሶና የተፈጨ ቀይ ጡብ አለላችሁ፡፡
ግራ ሲገባን… “ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት…” እንላለን፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ፖለቲካችንን እዩትማ! ዛሬ የተናገረውን ነገ  ዓይኑን በጨው አጥቦ የሚገለብጥ፣ ዛሬ “አገር ቀን ወጣላት፣” ሲል ይቆይና ነገ ገና በማለዳው ምንም ነገር ሳይለወጥ (ማታ ድስት ውስጥ የቀረችው ፍርፍር ጠዋት ገና ቁርስ አንኳን ሳትሆን ማለት ነው፣) ግልብጥ ይልና “አገር አለቀላት፣” የሚልበት ዘመን ነው፡፡  አሁን አሁንማ ማን ምን ይሁን፣ ማን ምን እያለ እንደሆነ፣ ማን እውነተኛው ዓላማው ምን እንደሆነ ግራ እየገባን ነው፡፡ እናላችሁ… ይቺ አገር እንክርዳድ እየበዛባት ነው፡፡ እናም እየሰከርንም ነው…ዝም የሚያሰኝ ስካርና የሚያስለፈልፍ ስካር፡፡
“እንደሚታወቀው በፊት የነበሩት ባለስልጣኖች ሰዉ ላይ ከባድ በደል ሲያደርሱ ኖረዋል፡፡ በተጨማሪም በመሀላችን ከፍተኛ የሆነ ክፍፍል እየፈጠሩ እንዳንተማመን አድርገውናል፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ እርሶ ምን የሚሉት ነገር አለ?”
እንዴት ነው ነገሩ፣ ሁሉንም ከአፉ ነጥቀነው፣ የግል ቃለ አቀባዩ ይመስል እንግዳው ሊል ይችላል ያልነውን ተናግረን ከጨረስን በኋላ …“ምን የሚሉት ነገር አለ?” ብሎ አማርኛ ምንድነው! እናላችሁ… የሙያ ስነምግባርን ጥያቄ ውስጥ በሚከት መልኩ ጋዜጠኞች ራሳቸው ‘አክቲቪስት፣ አክቲቪስት’ መሽተት ሲጀምሩ፣ ሰዋችን “ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት፣” ቢል አይገርምም፡፡ እዚህ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባው ከሚያየውና ከሚሰማው ነዋ! ደግሞላችሁ ሚዲያ ውስጥ ስምን የማስጠራት እሽቅደድም ቢጤ ያለ የሚያስመሰል ነገሮች ብልጭ ድርግም ሲሉ እናያለን፡፡ በሥራ መታወቅ መፈለግ ክፋት የለውም… ነገርየው ከዚያ አለፍ ሲል ነው፡፡
ግራ ሲገባን… “ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት…” እንላለን፡፡
“እንደሚያውቁት ባለፉት ጊዜያት ሰዉ በመልካም አስተዳደር እጦት ሲጎዳ ኖሯል፡፡ ድምጹን እንኳን ማሰማት አይችልም ነበር፡፡ እርሶ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?” (እሳቸው ምን ይላሉ! ወዳጄ አንቺ እኮ ከእነመልሱ ነው የሰጠሽው!)
ሀሳብ አለን፣ ወይ ለህዝቡ በተለይ ፖለቲካና ‘ፖለቲካ የሚመስለንን’ ነገር በምናቀርብበት ጊዜ “ይህኛውን የማቀርበው በጋዜጠኝነቴ ሳይሆን በአክቲቪስትነቴ ነው፣” የሚል ይግባበት፡፡ ልክ ነዋ… ምናልባት “የዓመቱ ሀቀኛ ጋዜጠኛ” ተብለን ዋንጫ የሚመስል ነገር እናገኝ ይሆናል፡፡ ስሙኛማ… በዛ ሰሞን የሆነ ስፍራ ላይ በቴሌቪዥን ስለቀረበ አንድ ቃለ መጠይቅ ወሬ ተነስቶ አንደኛው ሰውዬ…
“እነሱ እናውቃቸው የለ እንዴ! አለቆቻቸው በሉ ያሏቸውን ነው እኮ የሚሉት፡፡ አሁን ምን አድርግ ብሎ ነው ሰወየውን እንደዛ መተነፈሻ ያሳጣቸው…” ምናምን አሉ፡፡ “በሉ ያሏቸውን ነው የሚሉት፣” ማለት ራሳቸው አስበው መሥራት አይችሉም እንደማለት ነው፡፡ እናማ… የሚዲያ ሰዎች ከ‘ስሜት’ መንገድ ወጥተው የ‘ምክንያት’ መንገድን ይዙልንማ!)
ግራ ሲገባን… “ምናልባት ይሆናል አንክርዳድ ያለበት…” እንላለን፡፡
እናላችሁ…አኛ ራሳችን ወስነን ከጨረስን በኋላ፣ ይግባኝ የሌለው ፍርድ የሚመስል ዲስኩር ቢጤ ካሰማን በኋላ “ምን የሚሉት ነገር አለ፣” ብሎ ነገር ምን አይነት ‘ማፋጠጥ’ ነው! ልክ እኮ አንድ ደራሲን… “ታሪኩን የጨረስከው ዋናው ገጠባሀሪ ራሱን ሲያጠፋ ነው፡፡ ለመሆኑ ታሪኩን እንዴት ነው የጨረስከው?” ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ (እንግዳው ምን የሚለው ነገር ሊኖር ይችላል! የሚለው ‘ተባለለት’ አይደል እንዴ!
(ጋሽ ይድነቃቸው፣ እንደዚሁ አንድ ምእራፍ ሁሉ አውርታ “እዚህ ላይ ምን ይላሉ?” ብትላቸው “አንቺ ብለሽ ጨረስሽው እኮ!” ብለዋት ነበር፡፡ ለዘንድሮ ‘እንግዶች’ ጥቆማ ይሆን እንደሁ ብለን ነው፡፡)
“ደፋርና  ጭስ መውጫ አያጣም፣” ጥሩ አባባል ነች፡፡ ዘንድሮ የደፋሮች ‘ተረፈ ምርት’ በመብዛቱ የተነሳ ስለ ‘ኤክስፖርት’ ማሰብ አለብን፡፡ ልክ ነዋ… “በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ደፋሮቿን ‘ኤክስፖርት’ ያደረገች ብቸኛዋ ሀገር…” ምናምን የሚል አንድ ተጨማሪ መለያ ሊያሰጠን ይችላል! እናማ… ድፍረታችን እየበዛ ሲሄድ፣ ሁሉንም አውቃለሁ ማለት ስናበዛ፣ “እናንተ አድምጡኝ እንጂ እኔ እናንተን የማደምጠው ምን በወጣኝ ነው!” አይነት ነገራችን ሲበዛ… አለ አይደል…ሰዋችን፣ “ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት፣” ቢል አይገርምም፡፡
እኔ የምለው… የሆነ ሀሳቦችን ከእኛ የተገኘ አስመስላችሁ የምትናገሩ ‘አንዳንድ’ የአይ.ቲ. ዘመን ‘ፍሪደም ፋይተርስ’… መቼ ነው እንደዛ በሉልን ያልናችሁ! መቼ ነው ሰብሰብ ብለን ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ የናንተ ሀሳብ ምንድነው ያላችሁን? ልክ ነዋ… አሀ በህዝብ ስም የማይሆኑ ነገሮች ሲተላለፉ እየሰማን ነዋ! ለዚህ እኮ ነው… “ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት…” የምንለው፡፡
ስሙኝማ…በትምህርት ቤት የክፍል ክርክሮች ነበሩ አይደል… “አንተ ኳስ ክብ ነች ትላለህ፣ አንቺ ደግሞ ኳስ አራት ማዕዘን ነች ትያለሽ፡፡” በቃ! ዋናው ነገር የመከራከር ችሎታን ማዳበር ነበራ! “ኳሷ አራት ማእዘን ነች፣” ያለችው ተማሪ ልታሸንፍ ትችላለች። ኳሷ ግን ያው ድቡልቡል እንደሆነች ትቆያለች… ቢያንስ፣ ቢንያንስ እኛ እስከምናውቃት ድረስ ማለት ነው፡፡ የዘንድሮ ፖለቲካችን ግን “እኔ ኳሷ አራት ማእዘን ነች ካልኩ አራት ማእዘን ነች። በዚህ እንካ ስላንትያ አላውቅም፣” አይነት ሆኗል፡፡ እናላችሁ… ችግሩ እውነቱን ማየቱ እዛ ላይ ይቆማል። ክቧ ኳስ አራት ማዕዘን ትሆናለች፡፡ ጥቁሩ ነጭ ይሆናል፣ አጭሩ ረጅም ይሆናል፡፡
ግራ ሲገባን… “ምናልባት ይሆናል እንክርዳድ ያለበት…” እንላለን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2942 times