Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

የቡድን ኅሊና ስህተት ብቻ ሳይሆን ክፉም ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ጥጋዊ፣ ጽንፋዊው፣ ዋልታዊ

          የቡድን ኅሊና -
በማህበራዊነትና በሉአላዊው ግለሰብ (Sovereign self)  መካከል ሁልጊዜ ውጥረት አለ። “እኔ” ያለ “እኛ” ትንፋሽ ሲያጥረው፣ “እኛ”ም “እኔ” ከሌለ ህልውናም የለውም። ተፈላላጊም ናቸው፣ ተጠፋፊም ናቸው። “እኛ” “እኔ”ን ውጦ አይጠረቃም፣ “እኔ”ም የ “እኛ” ፍላጎቱ አያቆምም። ባጭሩ ማህበራዊነት ያለ ግለሰብ፣ ግለሰብም ያለ ማህበራዊነት ሊኖሩ አይችሉም። ይሁን እንጂ ማህበራዊነትን የጠላ ግለሰብም ሆነ ግለሰብነትን ያጠፋ ማሕበረሰብ፣ አንዱ የተናጠል፣ ሌላውም የስብስብ ስነ ልቡና ቀውስ ይገጥማቸዋል። ከእነዚህ የቀውስ ምልክቶች አንዱና ግጭት ፈጣሪ ወይም የተፈጠረን ግጭት አሻቃቢ የሆነው “የቡድን ኅሊና” ግሩፕ ቲንክ ነው።
ትርጓሜው፦ “የቡድን ኅሊና ማለት ግለሰቦች በቅጡ ድብልቅ ያለ ቡድን ውስጥ ጭልጥ ብለው ሲቀላቀሉ፣ አንድ ድምጽ ለመሆን ሲባል አዙሮ ማሰብንና እውነታን ወግድ የሚልና አማራጭን የማያይ፣ “ይሆንን?” ተብሎ ያልተጠየቀ ተግባር የሚመራው አስተሳሰብ ነው።” ድንገት ማሰብ ከቻለም የሚያስበው ከእኩይ ድርጊቱ በኋላ ነው።
ክፋቱ የአንድ ዘመን ወቅት ሆኖ አለማለፉ ነው። በእኩያን የግብ መምቻ የተመረጡ ትርክቶች (Selected victims’ narrative) እየተመራ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የስብስብ ኅሊና (collective mindset) ባህል ይሆናል። በእውቀትና በኢኮኖሚ ድሆች በሆኑ አገሮች ለሰንሰለታማ ቍርቍስ ምክንያት ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም በአጠቃላይ እውቀትና ብልጽግናም አይቸግራቸውም የምንላቸውን ምእራባውያንን የማይምር፣ የሰው ልጅ የተቻችሎ ኑሮ ጸር ነው።
አንድ ቡድን የሚከተሉት ስምንት ምልክቶች ካሉት የቡድን ኅሊና (Groupthink) እያዳበረ ነው ማለት ይቻላል።
ስምንት ባሕሪያት አሉት
ህልማዊ አይበገሬነት - Illusions of Invulnerability:
ሊደረግ አይችልም ተብሎ የሚታሰብን ተግባር ለማድረግ የሚያነሳሳ፣ ከልክ ያለፈ፣ የድላዊነት ስሜት የሚመራው ህልማዊ አይበገሬነት አለው።
ለማስጠንቀቂያዎች ምክንያት መስጠት Rationalization of Warnings:
ቡድኑ አለኝ የሚለውን ምግባር ልክነት የማይጠይቅ ስለሆነ የቡድኑ ውሳኔ በተግባር ለሚያስከትለው የሞራል እኩይ ውጤት ደንታ የለውም። “ከዚህም በፊት እንዲህ ተብሏል፣ ያኔም አሁንም ልክ” ብሎ ያልፋል።
ቸልተኛነት Complacency:
እንደ ቡድን ማስጠንቀቂያዎችን ዋጋ ያሳጣቸዋል። ቡድኑ የውሳኔውን አሉታዊ ውጤቶች ችላ ይላል።….
ባላጋራን የክፉ ተመሳስሎት ገጽታ መስጠት Stereotyping:
የጠላት ተብዬ መሪዎችን የክፉ ተመሳስሎት ገጽታ (Stereotype) እያበጁለት፣ እያሰየጠኑ (Demoniz) ወይም እያናናቍና እንደ ጅል እየቆጠሩ፣ የቡድኑ ሐሳብ አደናቃፊ እንደሆኑ እንዲታዩ ያደርጋሉ፤ እንዲህም በማድረግ ለሶስተኛ ወገን መካከለኛነት አስቸጋሪ ይሆናሉ።
የታማኝነት ተጽእኖ - Loyalty Pressure:
ውልፊጥ የሚል የቡድን አባልም ካለ ቀጥተኛ ተጽእኖ ይገጥመዋል፣ እያደርም ቡድኑ ይህንን ዓይነቱን አባል እንደ ከሀዲ እንዲቆጥረው ይደረጋል።
ራስን መገደብ/መቆጣጠር Self-Censorship:
ግለሰቦች ከቡድኑ የጋራ ስምምነት እንዳይወጡ ራሳቸውን ይቆጣጠራሉ። … ከቡድኑ የተለየ ማስተዋል እንዳላቸው ቢያውቁም ግለሰቦች ይህንን በመግለጥ መሳለቂያ ላለመሆን ራሳቸውን ያግታሉ።
ቡድኑ አንድ ድምጽ ያለው እንደሆነ የሚያስብ ቅዠት አለው Illusion of Unanimity:
የቡድን ኅሊና፣ ቡድኑ አንድ ድምጽ ያለው እንደሆነ የሚያስብ ቅዠት አለው። ይኽም በከፊል ግለሰቦች ለቡድኑ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳዩበት ሲሆን ከራስ ቍጥጥርም የሚመነጭ ስለሆነ ተቃውሞ የሌለበት ዝምታ ሁሉ ስምምነት እንደሆነ ያስባሉ።
የቡድን ኅሊና ጠባቂዎች Mind-guards:
ራሳቸውን የሾሙ የቡድኑን ኅሊና ጠባቂዎችም አሏቸው። እነዚህ ጠባቂዎችም ቡድኑ ከያዘው አቋም ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚመነጭን ይከላከላሉ።
ቡድኑ ተከታይ ነው እንጂ ሀሳብ አፍላቂ አይደለም፣ የተጫነ ነው። አንድ ወይንም ጥቂት መሪ እንዳዘዘው ይጓዛል፣ መነሻቸው አንድ ዓይነት ማህበራዊ ወይም ርእዮተ ዓለማዊ መነሻ መሆኑ ብቻ በቂ ነው፣ ጎሳም፣ ሃይማኖትም፣ የፖለቲካ ርእዮትም ሊሆን ይችላል። አንድ ቡድን አጋጥሞኛል ለሚለው ቀውስ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለብኝ ብሎ ሲያምን፣ በዚህ እምነት ጥላ ሥር የሚሰባሰቡ ሁሉ መጀመሪያ የሚያጡት በእርጋታ የሚገኘውን ትክክለኛ የአስተሳሰብ ደረጃ ነው።
እንዴት ይፈጠራል? እንዴትስ ለግጭት ሽቅበት ምክንያት ይሆናል?
ተጠቅተናል ብሎ በቡድን የሚያስብ አንድ ጎራ ፍርሃት፣ ጭንቀትና ቍጣ ስለለበት ፈጣኑ ተግባር አጥቂ ተብዬውን መጉዳት ነው። ለዚህ ምክንያት በመሆን ወይም ከዚህ ተግባር በኋላ ደግሞ ሃፍረትና ውርደት የተባሉ የዝቅታ ስሜቶች ስለሚኖሩ በቀል የሚል ተግባር ይከተላል፣ ይህ ደግሞ አዳዲስ ማሕበራዊ ግጭቶችን ይፈጥራል፣ ወይም የተፈጠረ ግጭትን እንዲያሻቅብ ያደርጋል። ትንንሽ ቡድኖች፣ ተቋሞች፣ ወይም አገሮች፣ በጣም ተፎካካሪ የሆነ ግጭት ውስጥ ሲገቡ ከግጭቱ በፊት ከነበራቸው ሁኔታ በእጅጉ በብዙ ነገር በፍጥነት ይቀየራሉ፣ ይኽም ቅያሬአቸው ለግጭት ማሻቀብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ጥጋዊ፣ ጽንፋዊው፣ ዋልታዊ ይሆናል፦ ውይይቶቻቸውና የቡድኑ አባላት በግንዛቤአቸውም ሆነ በባህሪያቸው ያከረሩና ጠላት ተኮር ይሆናሉ፦ አንድ ርእሰ ጕዳይ በቡድኑ መካከል ሲወሳ አባላት አባላት ቀድሞ ከነበራቸው ግንዛቤ የበለጠ የጠነከሩ ይሆናሉ፤ ከቡድናቸው ያልተቃረነ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ያገኛሉ፤ እያንዳንዱም የሚያደርገው አስተዋጽኦ ቡድኑን የበለጠ የሚያከር እንዲሆን በማድረግ የቡድኑ አጠናካሪ በመሆን ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋል። ጥላቻና አለመተማመንም ወደዚያኛው ጎራ ይወረወራል።
ደንብ ይፈጥራል፦ ውዝግቡን በሚመለከት የቡድኑ ግንዛቤ በአብዛኛው አባላት አንድ ዓይነትነት ያለው ልማዳዊ ይሆናል። ወደ ሌላው ያለው አመለካከት አሉታዊ ግንዛቤ ያለው፣ የሌሎችን ጉዳት እንደትርፍ የሚቆጥርና (ዜሮ ሰም) እነዚህም ነገሮች በተፈጸሙ መጠን የጥንካሬና የድለኝነት መረጋጋት ስሜት የሚኖረው አስተሳሰብ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱም ልማድ (ኖርም) የተፈጠረን ግጭት አሻቃቢ ይሆናል።
የማጥፊያ ግቦችን ያዳብራል፦ በግጭት ጊዜ ሌሎችን ማሸነፍ ወይንም ማጥፋት ቡድናዊ ተግባር ይሆናል። ይህ ተግባር ዑደታዊ ስለሆነ ያለፈ የቡድኑ ልምድ ይኸው ከሆነ አሁንም ግጭት ሲፈጠር እዚያው ማሸነፍና ወይም ማጥፋት ዑደት ውስጥ ይገባል። ይህ የቡድን ኅሊና የሚመራው ተግባር ቢያስፈልግ ከራሱ ውስጥ ንኡስ ቡድን በመፍጠር በግድ አሸናፊ ቡድን ይፈጥራል። የተፈጠረውን ግጭት ማሻቀብም በራሱ እንደ ድል ይቆጠራል።
የተመሳስሎት ግንባር ይፈጥራል፦ ይህ ግንባር ነክ ገጽታ አባል ማራኪ ነው። የተመሳሰለ ቡድን ከተሰባጠረ ቡድን የሚለየው ሌላውን ቡድን እንደ ተፎካካሪ ሳይሆን፣ እንደ ተቃዋሚ ስለሚቆጥር ትግሉ “ሁሉ” ዐመጻዊና አድማዊ ነው።
መለዮ ባይለብስም ይህ የቡድን ኅሊና ራሱን በወታደራዊ ገጽታ ያደራጃል
መደበኛ የሆኑና ተቀባይነት ያላቸው ግጭቶች ልዩ ልዩ ረብሻ አልባ ወደ ግብ መድረሻ መንገዶች ሲጠቀሙ የቡድን ኅሊና ያሰባሰበው ቡድን ያመነው ትራኬ፣ ከሃይማኖት ስለሚጠነክር ተአማኒ መሪ ተብሎ የሚሰየመው ከዲፕሎማሲ ክህሎትና ዝንባሌ ይልቅ ወታደራዊ ተክለ ማንነት ያለው ነው።    
ዓላማው መግባባት ያልሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት ይደራጃል
አንደኛ፣ የእንቅስቃሴው ተነሳስቶት ማሸነፍና ማሸነፍ ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ ብዙ መሪዎቹ “ረጅም ጊዜ” ባላጋራ ተብየውን ተገዳድሮ ለመጣል ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው።    
የቡድን ኅሊና ስህተት ብቻ ሳይሆን ክፉም ነው
የቡድን ኅሊና የማያጠፋው የለም፣ የተፈጠረው ሊያጠፉኝ ነው ከሚል ስጋት በመሆኑ ቀድሞ ማጥፋት ግቡ ነው። ጓደኝነት ትዳር ቤተሰብ፣ ቤተ እምነትንና አገርን የሚፈታ ነው። የራሳችን ኅሊና አብሮን ተፈጥሮ፣ ሳንኖርበት ዳኝነት ሳንሰጥበት፣ በጭፍልቅ ኖረን እንድንሞት የሚያደርገን፣ ያለ ዐዋጅ የተለቀቀብን ኮሚኒስት ነው፣ ይሆንን ብለን እንዳንጠይቅ፣ ነው የተባልነውን ሁሉ ይዘን እንድንንጋጋ የሚያደርገን፣ እኛው የሰጠነው እልፍ እግሮች ያለው የመዋጮ አንድ ጭንቅላት ነው። የቡድን ኅሊና ተንኮለኞች የሚፈጥሩት፣ ያልተፈጠረ ዓለም ወይም የተጋነነ ዓለም ውስጥ ገብተን፣ በህገ አራዊት እንድንኖር የሚያደርገን፣ የሕልም ዓለም ነው። ድንገት ስንባንን ያጠፋነው ጥፋት ሲታወሰን ቀጥሎ ያለውን የነቃውን ኑሯችንን ሲበጠብጠው ይኖራል።
እንዲህ ዓይነት ቡድኖች፣ የተግባሮቻቸው ገጽታ በራሱ እና በራሱ ብቻ ሲታይ ቅን ስለሚመስል ለወቀሳም ለሙገሳም አስቸጋሪ ነው፣ ከዚህም በተጨማሪ በየክስተቱ የሚሰለፉት ሰዎች በትምህርት ዘለቅነት፣ በነባርነት ወይም እንደ ገንዘብና ሥልጣን ባሉ በተመሳሳይ ማሕበራዊ እሴቶች የሚታወቁ ግለሰቦች በመሆናቸው በየአካባቢው በሚፈጠረው ችግር የፈጥኖ ደራሽ ጣልቃ ገብነታቸው ወዲያው ተቀባይነት ማግኘት ይችላል፣ የተጽእኖ አቅማቸው ግን እንደ የአካባቢው ይለያያል። አንዳንድ አካባቢዎች ትሥሥራቸው ጠንካራ ስለሆነ በቀላሉ አይደፈሩም። በግራም ሆነ በቀኝ ወደውም ሆነ ሳይወዱ፣ አስበውበትም ሆነ ሳያስቡ ግን በውጤቱ ተግባራቸው በአብዛኛው አፍራሽ ነው፣  አሰራራቸው ጀምስቦንዳዊ ነው  በድንገት ከፓራሹት እንደሚወርድ ይወርዳሉ፣ ባጭር ጊዜ ተደራጅተው የሚፈጽሙትን ፈጽመው ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ፤ እንዲህ ዓይነት ኃይል ለመሆን የሚያስፈልጉ አብይ መስፈሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የተጨቋኝ/ተገፋሁ ባይ ትራኬ (Appealing narrative of the “oppressed”) እውነቱና ውሸቱ፣ የተደባለቀ ነው
የጨቋኝ ተብየው ስሱ ጎን (Vulnerability of the so called “oppressor”) ይህ የድል ተስፋ ማርኬቲንግ ማግኛ ነው።
የዘመቻ ፊት አውራሪዎች (Vanguards for a campaign)
በምግባራቸው ግብ እንጂ መርህ ጠያቂ ያልሆኑ አስተባባሪዎች (Pragmatic and goal oriented individual coordinators)
ኃይል፣ ሥልጣን፣ ታዋቂነት፣ ተጽእኖ ፈጣሪነትን የተጠሙ አንደበተ ርቱአንና ደፋር ተግታጊዎች (Power mongers, cheap popularity seekers,…) እነዚህ ራሳቸውን ሰውረው ሊቀላቀሉ ይችላሉ።  
ጥቂት የዋሃን አጃቢዎች “መናጆዎች” (Few innocent crowed)
ሌሎች ፍጆታዎችና የግለሰብ ዓይነቶች እንደ አስፈላጊነቱና በየደረጃው ጥቅም ላይ ይውላሉ፣ ዘመቻው ይዘመታል፤ የተፈለገው ግብ ዘንድ ይደረሳል:: ከዚያ በኋላ በሚኖሩ እንቅስቃሴዎች “ተመልካች አለ”፣ “ተሳስተን ሊሆን ይችላል”፣ “የምንሰራው ስራ የረጅም ጊዜ ችግር ይፈጥራል”፣ “ተዉ የሚሉንን ሰዎች እንስማ” እና የመሳሰሉት አስተሳሰቦች የሌሉበት “ቡልዶዘራዊ” አካሔድ መሔድ ነው።
በውጤቱም ዚሮ ሰም (Zero-sum)  ድምዳሜ ላይ ይደረሳል። ዋናው ቁም ነገር የግጭት ባለ ድርሻዎች በማንኛውም የድርድር መንገዶች አለመስማማት ላይ ሲደርሱ “አልቦ ግብ ድርድር”  ላይ ለመቆም ይወስናሉ (አልቦ ማለት ዜሮ ማለት ነው)። በዚህም ቡድኖች በሙሉ ይከስራሉ፣ ይሁን  እንጂ አንደኛው ወገን የሚጠቀመው፣ ከሌላው ወገን በሚቀነሰው ነገር ነው፣ ባጭሩ “ጥቅሜ ያለው ጉዳትህ ውስጥ ነው” ማለት ነው፣ ወይም “ጉዳትህ ጥቅሜ  ነው” እና “ኪሳራህ ትርፌ ነው” የሚል የግጭቱ ባለድርሻዎች አይቀሬ ጉዳት ላይ ያተኮረ የግጭት መፍትሄ ነው። እንዲህ በመሆኑ የግጭት ባለድርሻ አረጋግጦ መሔድ የሚፈልገው ጥቅሙ የሚመሰረተው በሌላኛው ወገን ጉዳት ላይ መሆኑን ነው። በፖለቲካውና በንግዱ ዓለም ይህንን ምርጫ ለመምረጥ የሚገደዱበት ጊዜ አለ። ማህበራዊ ኑሮን ግን ያንኮታኩታል።
ጥቂት እንደ መፍትሄ
የ“ባላጋራን” አመለካከት ለመረዳት መመርመር። ትክክልም ሆኖ የተገኘ ያልተመለሰ ጥያቄ ካለ መመለስ። በዚህም ሒደት ውስጥ እውቅና ሊሰጣቸው የሚገባቸው በደሎች ካሉ እውቅና መስጠት
ገንቢና የተሻለ የግጭት መንገዶችን መፍጠር ሶስተኛ ወገን መካከለኛነትን በባህላዊና በዘመናዊ መንገድም መፈጸም
የቡድን ኅሊናን የሚመሩ ሰዎችን ተጽእኖ ከመጀመሪያው መቅጨት - የቡድን ኅሊና ውጤት የሆኑ ተግባራትን በፍጥነትና በግልጽ ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ማሳየት
ትክክለኛና ሊረጋገጡ የሚችሉ መረጃዎችን መስጠት። የማሕበራዊ ድረ-ገጾችንና የመገናኛ ብዙኻን አውታሮችን በመጠቀም ግለሰቦች ከቡድን ኅሊና ወደ ነጻ ራስ ገዝ ወይም በስምምነትና በውይይት በዳበረ የጋራ ሀሳብ እንዲያምኑ ማድረግ፣ ሆን ብሎ ሰው በመመደብ የተሳሳቱ ትራኬዎችን በጭብጦች እንደተፈተኑ በመጋበዝ የቡድን አባላት ወደ አስተውሎት የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት።
የቡድን ኅሊና ወደ መዋቅራዊ ረብሻ/አመጽ/ (Structural violence) እንዳይሸጋገር የአገር ሰራዊትን፣ ፖለቲካውንና የኢኮኖሚውን መዋቅር የተሰባጠረ ቡድንን የሚያስተናግድ የሚሆንበትን ፖሊሲዎች መቅረጽ።
መካከለኛ የሆነን ቡድን ማብዛት፣ እንዲኖርም ጥረት ማድረግ፣ “ወይ ከኛ ጋር ነህ አለዚያ ተቃዋሚያችን ነህ” ከሚል አሰልቺ ሰንሰለት ተፈትቶ ሌሎችን መፍታት።

Read 1642 times
Administrator

Latest from Administrator