Sunday, 10 March 2019 00:00

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)


                                        ክፍል- ፲፫ ሥልጣኔውን የማዘመን ሙከራዎች - 2
                                          
         አጭርና ግልፅ በሆነ ቋንቋ፣ ዘመናዊነት ማለት ተፈጥሮን ማወቅ ማለት ነው፤ አሰራሩን፣ ህግጋቱንና ባህሪውን ማወቅ፡፡ ተፈጥሮን ካወቅከው ዕጣ ፋንታው በአንተ ፍላጎት ስር ይሆናል፤ ከፈለክ ትንከባከበዋለህ ወይም ደግሞ ትቆጣጠረዋለህ አሊያም ቴክኖሎጂ ሰርተህ ታስገብረዋለህ፤ በዚህም የበላዩ ትሆናለህ፡፡ እናም፣ ዘመናዊነት የሰው ልጅ በዕውቀት አማካኝነት ተፈጥሮ ላይ የሚጎናፀፈው የሥልጣን የበላይነት ነው፡፡
በመሆኑም፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ማዘመን ማለት ‹‹ሥልጣኔው ለቁስ አካል ያለውን ንቀት ትቶ ተፈጥሮን እንዲያውቅ ማድረግ›› ማለት ነው፡፡ በባለፈው ሳምንት ፅሁፌ ላይ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ራሱን ‹‹ከተፈጥሮ የተሻገረ›› ሥልጣኔ አድርጎ ስለሚያስብ፣ ‹‹ቁስ አካል ለሆነው›› ተፈጥሮ ከፍተኛ የሆነ ንቀት እንዳለው ተመልክተናል፡፡ በዚህም የተነሳ ሥልጣኔው ከተፈጥሮ ጋር የተገናኘ የረባ ዕውቀትም ሆነ ቴክኖሎጂን ማመንጨት አልቻለም፡፡ ይሄም ሁኔታ ሥልጣኔውን ከጊዜ በኋላ ለተፈጥሯዊና ሰዋዊ ጥቃቶች በቀላሉ ተጋላጭ አድርጎታል፡፡
የያሬዳዊው ሥልጣኔ ልሂቃን ይሄንን እውነታ መረዳት የጀመሩት ከነገስታቱ በኋላ በጣም ዘግይተው ሲሆን፣ አጋጣሚውም የተፈጠረው ምሁራኑ የምዕራባዊውን ትምህርት መማር መጀመራቸው ነው፤ ይሄም የሆነው ከ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ጀምሮ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ የማዘመኛ ስልቶችን በተመለከተ ምሁራኑ ለሦስት ተከፍለው ይታያሉ፡፡
የመጀመሪያው ቡድን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጣም የቆየና የታፈነ ድምፅ ያለው ሲሆን ብቸኛ ትኩረቱም ባህል ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ በዚህም ትኩረቱ ቡድኑ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተመሰረተበት የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል ለህብረተሰብ ለውጥና ዕድገት ዕንቅፋት ነው›› የሚል አስተሳሰብ አለው፡፡ ይሄን አስተሳሰብ ቀድሞ ማራመድ የጀመረው ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ሲሆን፣ ከእሱ በመቀጠል ወልደ ህይወት፣ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝና አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ ተመሳሳይ አቋም አራምደዋል፡፡
ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ከመጀመሪያው በተቃራኒ፣ የያሬዳዊው ሥልጣኔ ባህላዊና ፖለቲካዊ መሰረት ሳይነካ ኢኮኖሚውንና ቢሮክራሲውን ብቻ በአውሮፓ ሞዴል የማዘመን ሐሳብ ያለው ነው፡፡በሌላ አነጋገር፣ ይሄ ቡድን፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ በኢኮኖሚና በቢሮክራሲ የአውሮፓን አሰራር እየተከተለ፣ ባህሉና ፖለቲካዊ አመራሩ ግን ጥንት በነበረው   ትውፊታዊ አኗኗርና አስተሳሰብ እንዲቀጥል ይፈልጋል። የዚህ ሐሳብ ዋነኛ አቀንቃኞች ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ያሉት ነገስታቶችና ባለ ሥልጣኖቻቸው፣ እንዲሁም የወቅቱ ምሁራን ናቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን አብዛኛዎቹ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ (2002) ‹‹የለውጥ ሐዋርያት›› በማለት የጠሯቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ትውልድ ምሁራን ሲሆኑ፣ እነሱም የጃፓንን ተሞክሮ እንደ ሞዴል የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ምሁራን ውስጥ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ጠ/ሚ አክሊሉ ሃብተ ወልድ እና እጓለ ገብረ ዮሐንስ … ይገኙበታል፡፡
ሦስተኛው አስተሳሰብ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለቱን ሐሳቦች አጣምሮ የያዘ ነው፤ ማለትም ‹‹ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ማዘመን የሚቻለው ባህሉንና ፖለቲካል ኢኮኖሚውን ለየብቻ ነጥሎ በማሻሻል ሳይሆን፣ ሁለቱን በአንድነት ‹‹ሁሉን አቀፍና ሥር ነቀል›› በሆነ መንገድ መለወጥ ሲቻል ነው›› የሚል አብዮታዊ ሐሳብ አለው፡፡ ይሄንን አስተሳሰብ ሲያራምዱ የነበሩት ደግሞ የአብዮቱ ዘመን ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ደርግና ኢህአዴግም የዚህ አስተሳሰብ ተከታየች ናቸው፡፡
እዚህ ላይ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝን ለብቻ ነጥለን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም፣ ገብረ ህይወትን በከፊል በመጀመሪያውና በሦስተኛው ቡድን አስተሳሰብ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ የብህትውናና የተአምራዊነት አስተሳሰቦች ላይ በሰነዘረው ትችት ከነ ዘርዓያዕቆብ ቡድን ውስጥ ስናገኘው፣ ‹‹ባህሉንና ፖለቲካል ኢኮኖሚውን በአንድ ላይ መለወጥ›› በሚለው ሐሳቡ ደግሞ የተማሪዎች ሐሳብ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡
ሆኖም ግን፣ ‹‹ባህሉንና ፖለቲካል ኢኮኖሚውን በአንድ ላይ መለወጥ›› በሚለው ጥቅል ሐሳብ ከተማሪዎች ጋር ቢያመሳስለውም፣ ዝርዝር በሆኑ ይዘቶች ላይ ግን ከተማሪዎች ጋር መሰረታዊ ልዩነት አለው፡፡ ገብረ ህይወት ‹‹አጤ ምኒሊክና ኢትዮጵያ›› እንዲሁም፣ ‹‹መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር›› በሚሉት ሁለት ሥራዎቹ ውስጥ ያሬዳዊው ሥልጣኔ በባህልና በፖለቲካል ኢኮኖሚ ማምጣት ያለባቸውን ለውጦች ዘርዝሮ ፅፏል፡፡
የኢትዮጵያን ዘመናዊ ታሪክ ስንመለከት፣ ከላይ ካነሳናቸው ሦስቱ አስተሳሰቦች ውስጥ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ የማዘመን ሁሉም (አምስቱም) ሙከራዎች በሁለተኛውና በሦስተኛው ቡድን አስተሳሰብ ሲመራ የነበረ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እነዚህ ቡድኖች በተለያየ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን ጨብጠው መገኘታቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ‹‹ያሬዳዊውን ሥልጣኔ የማዘመን ፕሮጀክቶች ለምን በተደጋጋሚ ከሸፉ?›› ለሚለው ጥያቄ ምሁራኑ መልስ ለመፈለግ የሚሞክሩት የሁለተኛውንና የሦስተኛውን ቡድን ሐሳቦች በመያዝ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ክሽፈት በተመለከተ የመጀመሪያው ቡድን ሐሳብ በምሁራኑ ዘንድ ትኩረት ተነፍጎታል፡፡
በሌላ አነጋገር፣ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ክሽፈት ጉዳይ ሲነሳ በምሁራኑ አእምሮ ውስጥ ወዲያው የሚመጣው የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ጉዳዮች ብቻ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ ‹‹ከዘመነ መሳፍንት የወረስነውን የማህበራዊና ፖለቲካዊ መዋቅር፣ እንዲሁም በወቅቱ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ መሰረት አለመገኘትን›› ለአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት መክሸፍ እንደ ምክንያት ያቀርቡታል (ባህሩ 2003፡ 31)፡፡
በእነዚህ ምሁራኖች ጥናት ውስጥ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተመሰረተበት የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል›› በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ክሽፈት ላይ የነበረውን ሚና በተመለከተ ምንም ዓይነት ትኩረት አላገኘም፡፡ የዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ፣ ይሄንን በምሁራኑ ዘንድ ትኩረት የተነፈገውን ክፍል ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በኢትዮጵያ የልሂቃን ታሪክ ውስጥ፣ ‹‹የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል ለኢትዮጵያ የማህበረሰብ ለውጥና ዕድገት እንቅፋት ሆኗል›› የሚለውን አስተሳሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያራመደው ዘርዓያዕቆብ ነው፡፡ በኋላ ላይ ሐሳቡን ወልደ ህይወት፣ ገብረ ህይወት፣ እጓለና ዳኛቸው በተለያየ ቅላፄ አስቀጥለውታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና የተጀመረው በዘርዓያዕቆብ ነው›› በሚለው ሐሳብ የምንስማማ ከሆነ ደግሞ፣ ምናልባት ይሄ የዘርዓያዕቆብ አቀራረብ፣ ‹‹የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ክሽፈት በተመለከተ ከተለመዱት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በመሻገር የኢትዮጵያ ፍልስፍና ያመጣው አዲስ እይታ ነው›› ብለን መደምደም እንችላለን፡፡ የዚህ ፅሁፍ ፀሐፊም ‹‹የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ክሽፈት›› በተመለከተ ይሄንን ፍልስፍናዊ አቀራረብ ይከተላል፡፡

Read 1161 times