Sunday, 10 March 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


                                     “ከፍ ብለናል… ወይስ ወደ ኋላ ተመልሰናል?”
                                          
        “ተፈጥሮ ከነፃነት የበለጠ ለሰው ልጅ የሰጠችው ፀጋ የለም፡፡ የማንነት መሠረትና የእኔነት ልክ የሚታወቀው፣ ሰው ራሱን ሆኖ መኖር የሚችልበት ስርዓት ሲኖር ነው፡፡ ምንም እንኳ ጉሮኖ ውስጥ የምኖር ድሃ ብሆንም ከግል ፍላጐቴ በላይ ለፆታ እኩልነት እቆማለሁ”
ሜሪ ዎልስቶንክራፍት (1856)
“ፅድቁ ቀርቶብን በቅጡ በኮነነን” የምትለን ደግሞ አልዛቤጥ ብራውኒንግ ናት፤ የዛው ዘመን ብዕረኛ፡፡ ክብር ለማርች 8!!
***
አውሮፕላኑ ሊነሳ ጥቂት ደቂቃዎች ነበር የቀሩት። ሁለቱ የፀጥታ ሰራተኞች የጉዞ አስፈላጊ ሂደቶችን አሟልተው ለመብረር ወደሚጠባበቁት መንገደኞች ተመልሰው መጡ፡፡ አንድ ፀጉሩን በአጭሩ የተስተካከለና ኮፍያውን እስከ ግንባሩ የደፋ ወጣት ጋ ሲደርሱ፣ ቆም ብለው፣ ፓስፖርቱንና ሌሎች መረጃዎችን ጠየቁትና ሰጣቸው፡፡ ከተመለከቷቸው በኋላ “አንድ ጊዜ እናነጋግርህ” ብለው ይዘውት ወጡ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አንገቱ ተቆርጦ እንዲሞት ተፈረደበት፡፡ እውነተኛ፣ አሳዛኝ፣ የፍቅርና የበደል ታሪክ ነው፡፡ በልቦለድ መልክም ተዘጋጅቶ መጽሐፍ ታትሟል፡፡
አንዳንድ ሊቃውንት፤ የሴቶች ጭቆና የተጀመረው ሰው እንደተፈጠረ ነው ይላሉ። ለዚህ ማስረጃ አይቸግራቸውም፡፡ የብሉይ ኪዳን ነገስታት፣ እያንዳንዳቸው፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሚስቶችና ዕቁባቶች ነበራቸው፡፡ እሱም አልበቃ እያላቸው፣ ከሌሎች ሰዎች ሚስቶች ጋር ይዳሩ ነበር። የዳዊትና ኦሪዮን ጉዳይ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል፡፡ አንዳንድ እስላማዊ ነገስታትም እንደዛ ነበሩ፡፡ አረቢያን ናይት ያለ ምክንያት አልተፃፈም። ሴት የተሰራችው ከወንድ የግራ ጐን አጥንት ነው መባሉ፣ ለሴቶች መብት አቀንቃኝ ልሂቃን ምቾት አይሰጥም፡፡
“በዘመነ ባርነት ከወንዱ የበለጠ የተጠቁት ሴቶች ናቸው፤ ድርብ ጭቆናና መከራ የተሸከሙት፡፡ ሴት ከወንድ አጥንት ተሰራች ከማለት ወንድ ከሴት ማህፀን ተገኘ የሚለው አሳማኝ ነው፡፡ ክርስቶስ የተወለደው ከድንግላዊት እናት ነው” ይላሉ፡፡ በአጋጣሚውም ሴቶችን ከጭቆና ለማላቀቅ የተጋፈጠ የመጀመርያው ወንድ እሱ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡
“ከናንተ መሃል ሃጢዓትን ያልሰራ እሱ ይውገራት (He Who is without sin among you let him cast a stone) ብሎ በመናገሩ ከሞት የዳነችው ምስኪን ሴት ታሪክ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ክብር ለሱ ይሁን! እንዲሁም ለማርች 8!
ወዳጄ፡- እስካሁን ድረስ ሴት ወንድን ለማገልገልና ልጆች ለመውለድ የተፈጠረች ናት ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ እስልምና የመሳሰሉ እምነቶችም ይህን አስተሳሰብ ሲያበረታቱ እንደነበር ተፅፎ አንብበናል፡፡ አንድ ወንድ የማስተዳደር ዓቅም እስካለው ድረስ ሶስት አራት ሚስት (Polygamy) ቢኖረው ችግር የለውም ይላሉ፡፡ አሁን ግን ጊዜው ተለውጧል፡፡ ሴቶቹ ለባርነት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ክብር ለማርች 8!
በዚህ ዘመን አንድ ሰው ሌላውን በማታለል፣ በማስገደድ፣ አማራጭ በማሳጣት ወይም አለማወቁን ተጠቅሞ ፈቃደኛ እንዲሆን በማድረግ ሊጠቀምበት የመቻሉ ነገር አያዋጣም፡፡ አዲሱ የዓለም ስርዓትና የስልጣኔ መስፋፋት፣ በሴቶች ላይ የሚደርስን በደልና ጭቆና አይታገስም፡፡ ማርች 8 አሁንም ከአጉል ልማድና ወግ ላልተላቀቅነው እንደኛ ዓይነቶቹ ኋላ ቀሮች፣ የሚደወል የማንቂያ አስተሳሰብ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ያሳለፍነው ወር ፌብሩዋሪ “የጥቁሮች ወር” በመባል ይታወቃል፡፡ ማርች ደግሞ “የሴቶች ወር” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በእግረ መንገድ አንድ ወዳጄ ከዓመታት በፊት የነገረኝን እውነተኛ ታሪክ ላጫውትሽ፡- በስልሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ዩኤስ አሜሪካ ትምህርት ላይ የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጓደኛሞች፣ ሻይ ቡና ለማለት ወደ አንድ ሆቴል ለመግባት ሲሞክሩ፣ በር ላይ ቆሞ የነበረው እንግዳ ተቀባይ፤… “ለጥቁሮች አይፈቀድም” ይላቸዋል። እነ አጅሬም በሰውየው አለማወቅ እየሳቁ “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፣ የዚህ አገር ጥቁሮች አይደለንም” አሉት፡፡ ሰውየው ኢትዮጵያን አያውቃትም፡፡ ግራ ሲገባው ፊቱን ወደ ውስጥ መልሶ አንደኛውን አስተናጋጅ፡-
“Jim…how do you classify Ethiopians?” በማለት ይጠይቀዋል፡፡
“niggers” በማለት መለሰለት፡፡
“መግባት አትችሉም” በማለት ከለከላቸው። ያኔ የነጭ ዘረኝነት የነገሠበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደ አሸብር ከልካይ ሊያስረዱት ቢሞክሩም አልሆነም። ስልቻም፣ ቀልቀሎም ለነሱ አንድ ዓይነት ነበር፡፡ እያወቁና እየሰለጠኑ ሲመጡ ግን ጥቁሮች አይደለም ሆቴል. ሁዋይት ሃውስ ገብተዋል፡፡ …ፕሬዚዳንት፣ ስቴት ሰክሬታሪ፣ ቺፍ ኦቭ ስታፍ፣ ቺፍ ጀስቲስ ወዘተ ሆነዋል፡፡ የሚያዋጣውን መንገድ ተከትለው፡፡ እኛስ? ያኔ ከነበርንበት ከፍ ብለናል? እንደነሱ!
ወይስ ወደ ኋላ ተመልሰናል? እንደ ግመል ሽንት። መልሱን ላንቺ ትቸዋለሁ፡፡
የዛሬ ሰላሳና ሰባ ዓመታት ገደማ “ቀይ ኮከብ በቻይና ሰማይ ላይ” በሚለው መጽሐፉ የሚታወቀው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ኤድጋር ስኖው መካከለኛ ምስራቅ በምትገኘው፣ በሼርያ ህግ በምትዳደር እስላማዊት ሀገር ጐራ ብሎ ነበር፡፡ አይቶና ታዝቦ ከፃፋቸው ቁምነገሮች መሃል አንዱ አጋጣሚ ሲነበብ፡- “አንድ ቀን ከንጉሡ ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ፣ ሁለት ሴቶች መጥተው እጅ ነሱ፡፡ ተመልሰው ሲወጡ ንጉሡ አንደኛዋን ሴት በስሟ ጠርተው በማስቀረት፤
“ይቺ አብራሽ ያለችው ቆንጆ የማናት” ብለው ጠየቋት፡፡ ሴትየዋም በመገረም “ልጅዋ ናታ!” ስትላቸው፣ እኔ የምገባበት ጨነቀኝ፣ እሳቸው ምንም አልመሰላቸውም” ይላል፡፡ ሴቶቹ እናትና ልጅ ነበሩ።
ወዳጄ፡… ልጆቻቸውን እንኳ የማያውቁ ገዢዎች በሚያስተዳድሩበት ስርዓት፣ ሴት መሆን ባርነት ነው፡፡ ሴቶች ሃሳባቸውን መግለጽ፣ የፈለጉትን መልበስ፣ ወደሚፈልጉበት ቦታ መንቀሳቀስ፣ ያፈቀሩትን የማግባት ነፃነት የላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ አፈና የሚደረገው ደግሞ በሃይማኖት ስም መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹ የእነዚህ ሀገራት ሹማምንቶች ግን ውድ ሆቴሎችና ካዚናዎች በሚገኙበት ከተማዎች እየተመላለሱ የልባቸውን ያደርሳሉ፡፡ በዚህ ላይ ለዜጐች ድምጽ የሚሆኑ የመብት ተሟጋቾችንም እያሳደዱ ከማጥፋት ወደ ኋላ አልተመለሱም። በቅርቡ ቱርክ ውስጥ በግፍ የተገደለው ጋዜጠኛ ጀማል ኮሻጊም፣ የዚሁ ማን አለብኝነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህን ያነሳነው “ከአውሮፕላኑ ውስጥ ተይዞ ወረደ” ካልነው ወጣት ታሪክ ጋር ስለሚገናኝ ለማስታወስ ነው፡፡
ወደ ታሪኩ ስንመለስ፣ ከአውሮፕላኑ ውስጥ ተያዘ ያልነው ወጣት፤ ወንድ ሳይሆን እንደ ወንድ የለበሰች፣ እንደ ወንድ ፀጉሯን ተስተካክላ ኮፍያ ያደረገች፣ የሳዑዲ አረቢያ ልዕልት ነበረች፡፡ ከልማዳችን ውጭ ቀብጠሻል፣ ሃይማኖታዊ ስርዓታችንን አላከበርሽም ተብላ ነው የተከሰሰችው፡፡ የመብት ተቆርቋሪዎች ደብቀው ከአገር ሊያስወጡት ቢሞክሩም አልተሳካም፡፡ ማርች 8ትን ስናከብር፣ በፆታቸው ምክንያት የተገፉትን ሁሉ እያስታወስን ነው፡፡ አይመስልሽም ወዳጄ?
“I am a woman, sir
I use the woman’s” figures
naturally”
Marian Erle
ሠላም!!  

Read 515 times