Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

የይርጋዓለም ሰዎች

Written by  መኩቲ
Rate this item
(3 votes)


     በቀደም ሌሊት፣ በህልሜ፣ ይርጋለም መናኸሪያ የሚባለው ሰፈር ነበርኩ። ይርጋለም ሲዳማ ነው ተወልጄ ያደግኩት፤ 12ኛ ክፍል ድረስም የተማርኩት እዚያው ነበር። በየዓመቱም እሄድ ነበር። አሁን አራት ዓመት ሆነኝ ከሄድኩ። በልጅነታችን መናኸሪያ የሚባለው ሰፈር፣ ከቤት ተልኮ ካልሆነ በቀር የታየ ልጅ፣ ወደ ቤቱ ሲመለስ ጉድ ይፈላበት ነበር። እና መናኸሪያ ያገኘኋቸው ሰዎች. . .
ይርጋለም፤ ሁሉም ሰው እርስ በርሱ ይተዋወቃል፤ የኔ ቢጤው (በልመና የሚተዳደሩ) እነ እሰዬ-ልጅ እያለሁ ልመና እንደ ሙያ የምርጫ ጉዳይ ይመስለኝ ነበር፣ ምክንያቱም አንዳንዶቹ በር ላይ መጥተው “ስለግዚያብሔር” ሲሉ “ና እስቲ እንጀራ ልጋግር ነው፣ ይህቺን እንጨት ሸንሸን አርጋት” ሲባል ክምር እንጨት ፈልጦ፣ የተሰጠውን እንጀራ እዚያው በልቶ ይሄድ ነበር። እሰዬ ሸምገል ያለ ጣሊያንኛ የሚናገር ሰው ነበር። ቱሚላ የሚባል  ነበረ ደግሞ - ቱሚላ ዋና ገብስ ፈታጊና በርበሬ ደላዥ ሲሆን የራሱ የሥራ ዘፈንም ነበረው፣ የሚላላኩ እነ አጋ (መስማት የተሳነው ነው)፣ በገንዘብ ተገዝተው ሰዎችን ያስፈራራሉ የሚባሉት እነ ቆልማሜ - አቤት የቆልማሜ ቁመት! ሁሌ ከሚለብሰው ቁምጣ ጋር ረጅም ቅልጥሙ እንዴት እንደሚያስፈራ! “ለቆልማሜ ብር ሰጥቼ እንዳላስጠፈጥፍሽ” የሚባባሉ፣ የተጣሉ የሰፈር ሴቶችን መስማት የተለመደ ነበር።  
ወደ ወንዝ ወርደው የሰዎችን ልብሶች የሚያጥቡት ማን ነበር ስማቸው? ቆይ አንዴ ጓደኛዬ ጋ ልደውል. . .ሃሎ ሃይ ምግባር (አብሮ አደጌ ነው ምግባር) ሰላም ነው? እኔ የምልህ-- ሥራ ካልያዝክ ይርጋለም ቆልማሜ አለ እንዴ? “አዎ አለ”። ልብስ የሚያጥቡት ሰውዬ ማን ነበረ ስማቸው? “ጋሽ ባፋ? እሳቸው ግን ሞቱኮ”. . .
ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ ጋሽ ባፋ ትልቅ በአንሶላ የታሰረ የልብስ ክምር ተሸክመው፣ ወይ ወደ ወንዝ ሲወርዱ፣ ወይ ከወንዝ ሲመለሱ ማየት የተለመደ ነበር። ሁልጊዜ የሚለብሱት ከአሮጌ ጂንስ ሱሪ ተቆርጦ ያጠረ ቁምጣና ቀለም ከማጣቱ የተነሳ ድርቅ ያለ “ካምቡሽ” የሚሉት የወታደር ጫማ። ጋሽ ባፋ፤ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሄዱ፣ ከወንዝ እየተመለሱ ወይም ገና እየሄዱ መሆኑን ማወቅ ቀላል ነበር። እግራቸውን በማየት- አመድ ከመሰለ እየተመለሱ ነው ማለት ነው።
አባቴ በናፍጣና በዘይት የቆሸሸ የሥራ ቱታውን “ይሄን ለጋሽ ባፋ ስጠው” ብሎ ከ 1ብር ጋር ሲሰጠኝ አብሮ የሚነግረኝ መልዕክት “በቆሮቆንዳ አትሸው በለው እንዳይቀደድ” የሚል ነበር። ቆሮቆንዳ በቆሎ ተፈልፍሎ የሚቀረው እንጨት መሰሉ ነው።
በዚያ ጊዜ የፈለገ የየቀበሌው ነዋሪ ጓሮ ይሰጠኝ “አለማለሁ” ብሎ ቀበሌውን ያስፈቅድና ወደ ወንዝ አካባቢ ያለ ሰፋፊ መሬት ይሰጠዋል። እዚያ መሬት ላይ የጫካ ቡና፣የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች በተለይ ዘይቱን፣ሙዝ፣ ዋንዛ፣ ቢርቢራ፣ ዝግባና ብሳና የመሳሰሉት ዛፎች አሉ። “አለማለሁ” ብለው መሬቱን የሚወስዱት ሰዎች ግፋ ቢል በአመት አንዴ በቆሎ ቢዘሩ ነው እሱንም ጎበዝ ከሆኑ። ሌሎቹ ቡናው በደረሰ ጊዜ መልቀም ብቻ ነው። ታዲያ መሬቶቹ የጋሽ ባፋ ጓሮ፣ የጋሽ በካሎ ጓሮ፣ የመምሬ አየለ ጓሮ እየተባሉ ይጠራሉ።
እኛና ከኛ ከፍ ከፍ የሚሉት ልጆች ደህና ደህና የደረሱ የሸንኮራ አገዳዎች ወይም የበሰለ ዘይቱን ያለበትን ጓሮ ሳናስፈቅድ (ዘረፋ) እንገባና ሆዳችን እስኪወጠር በልተንና የቻልነውን ያህል ተሸክመን ወደየቤታች እንመለሳለን። የጋሽ በካሎ እና የጋሽ ባፋ ጓሮ በዘይቱን ምርቱና ጥራቱ የታወቀ ነበር። የቀለሟ እናት ጓሮ ደግሞ በሸንልጅ እያለሁ ኮራ አገዳውና ጥርት ባለ የምንጭ ውሃው።
የአንዳንድ ሰዎች ጓሮ ደግሞ ጣሬ አለው ተብሎ ይፈራ ነበር። ጣሬ በሲዳማ ባህልና እምነት ሰዎች ሰብሎቻቸውን ከሌባ የሚጠብቁበት የረቀቀ መላ ነው። እንዴት? የደረሰ እርሻ ያለው ሰው ጣሬ የሚሰሩ ሰዎች ጋር ይሄድና በእራፊ ጨርቅ የተቋጠረች ነገር ከድግምት ጋር ትሰጠዋለች። ያቺን እርሻው መሃከል በረጅም ቀርከሃ ወይም ሌላ እንጨት ጫፍ እንድትታይ አድርጎ ይሰቅላታል። ታዲያ በሌቦችም በሌላውም ዘንድ ምን ተብሎ የታመናል? ጣሬ ካለበት እርሻ ሰርቆ የበላ ሰው “እሱ ይርጋለም ቁጭ ብሎ ሆዱ ብቻውን እየተነፋ ሻሸመኔ ወይም አዲሳባ ይደርሳል።” 300 ኪሎ ሜትር። እንዴት እንደሚያስፈራ አስቡት። ድርሽ የሚል የለም እዚያች ጓሮ። ከጦጣና ከዝንጀሮ ለመጠበቅ ደግሞ በቡቶቶ የተሰራ ሰው መሳይ ፈረንጆቹ ከኛ ወስደው “ስኬር ክሮው” የሚሉት ዓይነት ይሰቀላል። (በሌላ ጊዜ ስለ ጣሬ እና አካኩ-ፍርድ የሚሰጥበት የእምነት ቦታ የተሻለ እፅፋለሁ)
እነ ታደለ ጫማ ሰፊው -ታደለ ጫማ ሰፊው ጋር ብዙ በኳስ የተገነጠሉ ጫማዎቼን አሰፍቼአለሁ ታዲያ አንድ ጊዜ የካራቴ ጫማ የሚባል ተገዝቶልን በመጀመሪያው ቀን ትምህርት ቤት አድርጌው ኳስ ተጫውቼ ዙሪያው ለቀቀ ማንም ሳያየኝ ወደ ቤት ሄድኩና ሽቦ ቀጥቅጬ መስፊያ ሰራሁና ታደለ ጋር ባየሁት መሠረት ሰፍቼ ከአባቴ ቁጣ ማምለጤ ትዝ ይለኛል ።
 እልፍኝ ጠጅ፣ አብዬ ተሻለ ቅመማ ቅመም ነጋዴው- 12ኛ ክፍል ሆኜ እንኳ እናቴ አብዬ ተሻለ ጋር “ሮጥ በልና ጥቁር አዝሙድ የስሙኒ፣ ኮረሪማ የ1 ብር ነጭ አዝሙድ የ50 ሳንቲም ይዘህ ና ትለኝ ነበር” ቅመሞቹን ትሸጥ የነበረችው የአብዬ ተሻለ ባለቤት ፅጌ ሁል ጊዜ አፍንጫዋ እርጥብ ሆኖ ያስነጥሳት ነበር። ሳይነስ መሆኑ ነው?. . .
ንጋቱ “እብዱ”-የአዕምሮ ህመምተኛ ነው ንጋቱ ወደ ይርጋለም መጀመሪያ እነደመጣ እጅና እግሩ በሰንሰለት የታሰረና ቁልፍ ነበረ ኋላ ተፈትቶ ደህና ነበረ። አልሽቴኪ- ይሄኛውም የአዕምሮ ህመምተኛ ሆኖ ማጅራቱ ላይ ተሸክሞት ይዞር የነበረ ትንሽ ወንድ ልጅ ነበረው። በኋላ ይህ ልጅ አድጎ የሊስቲሮ ሥራ ጫማ ማሳመር ይሰራ ነበረ።
አባባ ገደቡ- አባባ ገደቡ የነ ቁምላቸው ገደቡ አባት ሁል ጊዜ ነጭ ተነፋነፍ የሚሉት ሱሪና ጋቢ ለብሰው ከቀርከሃ በተሰራ ወንበር ላይ ከቤታቸው ደጅ ይቀመጡ ነበረ። ታዲያ ልጅ ሆኜ ሁል ጊዜ ማታ ማታ በረደኝ ስለምል ቤተሰቦቼ ጋቢ ይሰጡኝና “አባባ ገደቡ” እያሉ ያበሽቁኝ ነበረ።
እነ ጋሽ ሳሊክ ታክሲ ነጂው -ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻዬን በታክሲ ተሳፍሬ ከአፖስቶ (ዘመድ ቤት) ይርጋለም የተሳፈርኩት በጋሽ ሳሊኩ ታክሲ ነበረአደራ ተብሎ ያን ቀን ሜርሰዲስ ታክሲው ውስጥ አዲስ የወጣው የአረጋኸኝ ዘፈን “እስኪ ዘለል ዘለል. . .” ተከፍቶ ነበር፣
ጋሽ ቀቀቦ ጋራጅ- ጋሽ ቀቀቦ “የአውሮፕላን ካምቢዮ ሳይቀር እጠግናለሁ” ይላል እያሉ ይሳሳቃሉ የይርጋለም ሰዎች ።
አባባ እሳቱ ገራዡ (ወንድ ልጆችን የሚገርዙ) “ከእነ እንትና ቤት 4 ከነእንትና 3 ከነእንትና ቤት የ7ቱንም የቆረጠው አብዬ ነው” ሲል ሰምቸዋለሁ ልጃቸው እንዳለ እሳቱ የሶሪያ እሳቱ ወንድም። እስቲ አንዴ እንዳለ ጋር ለደውል. . .ሃሎ እንዱ መኩቲ ነኝ እንዴት ነህ? “ውይ ሞኪዬ እንዴት ነህ ጌታዬ ጠፋህብኝኮ በቀደም እንደውም ይርጋለም ሄጄ (አዋሳ ነው የሚኖረው) ትዝ ብለኸኝ ነበር ምነው ጠያቂዬ ዘጋኸኝ?” ስንፍና ነው እንዱ ይቅርታ አድርግልኝ። እኔ የምልህ ሶሪያ ደህና ነው? ደህና ነው ሞኪዬ አሁንማ ሶሪያ ጡረታ ወጥቶ ቤት ቁጭ ብሎ ነው ያለው ያቺ ስኳሯም አጣፍጣው. . .ኪኪኪ. . .” እሺ እንዱ ጤንነትህ ደህና ነው አይደል? የሚመጣው ሳምንት ውስጥ እደውልልሃለው ቻዎ። የይጋለም ሰው መቼም በራሱ መቀለድ የሚወድ ኮሚክ ነው “ስኳሯ አጣፍጣው”. . . በተለይ የነእንዳለ ቤተሰብ። ዱሮ ይርጋለም ስኳር ያዘው የሚባል ሰው ሰምቼ አላውቅም ነበር። ሶሪያ እሳቱ ግን የሚገርም ስም እኮ ነው። ትንቢት።
ጋሽ ስጦታ የ 06 ቀበሌ እድር ጥሩንባ ነፊ ነበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ “ጥንዳሻም” የሚለውን ስድብ የሰማሁት ከርሳቸው ነው በ1980። ይኮላተፉ ነበር “ጥ ጥ ጥ ጥ. . . ጥንዳሻም!”።
እነ ጋሽ ካሳ ባለሱቁ (ዘመድ ናቸው)፣ ጋሽ ኩማ መካኒኩ( አባቴ ነው) እነ ዘሪሁን አጂፕ፣ እማማ ቆሎ፣ ዘሪቱ ቴሌ፣ አበዙ ቀበሌ፥ ለታይ አንባሻ፣ ታደሰ ቡዋንቧ፣ንግስት ታይፒስቷ፣ እነ ቦጋለ ፖሊሱ ክፍሎም ትራፊኩ፣ እነ ጋሽ ነጋሽ ባለ ወፍጮው፣ዶክተር አብረሃም፣ እነ ጋሽ ሻኪር ባለዳቦ ቤቱ (የየሺ እመቤት ዘፈን ትዝ አለኝ “ሻኪር ባለዳቦው አይ ደስ ሲል አዋሳ ቤት ሰርቶ...” እያልን እንዘፍን ነበር። ምን የመሰለ አሁን ኬክ የሚሉት ዓይነት ዳቦ 10 ሳንቲም። እነ ጋሽ አስፋው ልብስ ሰፊው፣ ጋሽ ለገሠ ሊቀመንበሩ፣ ጋሽ መንገሻ ፋርማሲው-እዚያው ፋርማሲ ውስጥ የክሊኒክ አግልግሎትም ነበረ ስንት መርፌ ጠጥቼያለሁ። ጋሽ መንገሻ ግዙፍ ነው። የሆነ ነገር ታመን እዚያ ስንሄድ የክሊኒኩ ጓዳ ከገባን መርፌ አይቀርም ሽታውና ንፅሕናው ግን ደስ ይለኝ ነበር ዓይናችንን ገለጥ ገለጥ አርጎ ያይና መርፌ ይወጋናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ሱቅ የተላክሁት አበበ ሱቅ ነው። የጋሽ አበበ ሱቅ ዘይትና አቧራ ተደባልቆ እንደ ጭቃ የተለጠፈበት የቆየ የሱቅ መደርደሪያ በላዩ ላይ የተቀመጠውን ሚዛን አጣብቆ ይዞት ትዝ ይለኛል።
ታደሰ ሪዶ የሚባል ግዙፍ ሰው አለ ደግሞ ዱሮ የዜሮ አምስት ቀበሌ ኳስ ቡድን ተገዳጋጅ (ተከላካይ) ነበር። (አሁን የቀበሌ የኳስ ቡድን ቀርቷል አይደል?-የሃገራችን አካሄድ ለምን እንደ ማይክል ጃክሰን ዳንስ እንደሚያምታታን አላውቅም ወደ ፊት ነው ወደ ኋላ?) ታዲያ ሪዶን (ታደሰ ሪዶን ሰዎች ሪዶ ብለው ነው የሚጠሩት) አልፎ ጎል ማስቆጠር ዘበት ነበር። ታደሰ የመብራት ሃይል መስሪያ ቤት የጥበቃ ባልደረባ ሆኖ ሰፈር ውስጥ ደግሞ ዋና የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ነው አሁንም።
ይርጋለም ሰዎች ወይ በሙያቸው ወይ በሌላ የቀልድ ቅጽል ሥም ነበር የሚጠሩት። ዘርና ሃይማኖት የሚጠይቅ የለም። በየነ ሾፌሩ- በየነ 7 ዓመት ሆኖኝ ጥርሴን የነቀለልኝ ጎረቤታችን ነው አባቴ ጥርሳችንን መንቀል አይወድም ነበረ እኔም አልወድም አሁን ልጄ 7 ዓመት ሊሆናት ነው እግዜር ያውቃል። “በደንብ ተነቃንቆ ሲበስል በጠዋት ና” ይለኝና ጥርሶቼ በተነቃነቁ ጊዜ ጠዋት ጠዋት እቤቱ እሄድና በክር እያሰረ ይነቅልልኝ ነበረ የአብተው ከበደ ዘፈን “ሳውንድ ትራክ”፣ ኮልት ኮሚኩ. . . አልታዬ ክትፎ፣  ታደሠ ወርቅ ሠሪው.. .ሞገስ አስተማሪው- ሞገስ ለእኔ እንደ አባት ነው ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ያስጠናኝ ነበረ እሱ የሃይ ስኩል መምህር ሆኖ። ስድስተኛ ክፍል ሆኜ የወለደው ልጅ የክርስትና አባት እኔ ነኝ። አሁን ያ ልጅ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ነው።  
እነዚህ ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁ አብረው ለብዙ ዘመናት ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው ቤተሰብ መስርተው፣ ተዋደው፣ ተሳስበው፣ እድር መስርተውና እቁብ ተጣጥለው የሚኖሩ የይርጋለም ሰዎች ናቸው። ከይርጋለም ጋር ያላቸው ትስስር እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ለምሳሌ ጋሽ ካሣ አዋሳ እንቅልፍ አይወስዳቸውም። ምን ቢመሽባቸው ይርጋለም መጥተው ያድራሉ እንጂ።
በህልሜ ይርጋለም መናኸሪያ ሰፈር ቆልማሜ፣ አጋ እና ሌሎች ተሰብስበው ካቴናው የወለቀ ብስክሌት እየጠገኑ ነበረ። እኔ ደግሞ መናኸሪያ መሃል በመገኘቴ ግራ ተጋብቼ መሃላቸው ቆሜያለሁ። ብንን አልኩና በምናቤ ወደ ልጅነቴ ምድር ይርጋለም በሃሳብ ነጎድኩ። አንዳንዴ ህልምና እውኑ ይምታታሉ።
እኛ ቤት ያኔ የመኪና ባትሪዎችን ቻርጅ የሚያደርግ ማሽን ነበረ እና የባትሪ አሲድም ከአዲስ አበባ እየተጫነ ይሸጥ ነበረ። ታዲያ አንድ ቀን (ልጅ እያለሁ ነው) ቆልማሜ እንደ ጀሪካን ነገር ይዞ አሲድ ሽጡልኝ ብሎ መጣ እኔ ነበርኩ በር የከፈትኩለት። ደግነቱ አባቴ በደንብ አስረድቶናል “አሲድ ለማንም ሰው በዕቃ አይሸጥም ባትሪ ውስጥ ብቻ ይጨመራል እንጂ”። ይሄንኑ ነግሬ መለስኩት። ኋላ እዚህ አዲስ አበባ በአሲድ ምን እንደተደረገ ስሰማ ከቆልማሜ አጉል ስምና አስፈሪነት ጋር ምን እንዳሰብኩ ገምቱ።
ባትሪ ቤት ገባ ብለን የወጣን እንደሆነ የለበስነው ልብስ ከጥጥ የተሰራ እንደሆነ ቡጭቅ ቡጭቅ እያለብን አባቴ “ለምን እሱን ለብሰህ ገባህ” እያለ ይቆጣን ነበረ።
ከአዲስ አበባ ወደ ይርጋለም ስሄድ እየተቃረብኩ መሆኔን የማውቀው በመንገዱ ዳር እና ዳር ላይ በማያቸው የተክል ዓይነቶች ነው። እንዲያውም አንድ ሲቀጠፍ ወተት ዓይነት ፈሳሽ የሚወጣው ቀይ ቅጠል ያለው ቁጥቋጦ ዋናው ምልክቴ ነው። ከተለያዩ ሃገራት የመጡ የአፈር ናሙናዎች ቢሰጡኝ የይርጋለምን አፈር አይቼም አሽትቼም እለየዋለሁ።. . .እንባ”
ሳሩ ቅጠሉ ዛፉ ድንጋዩ ሁሉም ለእኔ ልዩ ናቸው። ያኔ ይርጋለም አንዱ የኔ ወይም የወንድሜ ጓደኛ ከቤተሰቡ ያኮርፍና እኛ ቤት ይገባል ከኔና ከወንድሜ ጋር ይተኛል። እኛ ቤት ምግብ የምንመገበው ሁላችንም አንድ ላይ ነበር በአንድ ትሪ አባቴ፣ እናቴ፣ እኔ፣ታናሽ ወንድሜ፣ ትንሿ እህቴ እንዲሁም ከቤቱ አኩርፎ የመጣው።  
ይርጋለም ሁሉም እንዲሁ ነበር። ባል እና ሚስት እንኳ ሲጋጩ ሚስት ካኮረፈች ዘመድም እያላት ጎረቤት ነው የምትሄድ። እኔም ባኮርፍ። ያ ልጅ በበነጋው ወደ ትምህርት ቤት የኔን ወይም የወንድሜን ጃኬት ወይም ሱሪ ለብሶ ሊሄድ ይችላል። በሶስተኛው ወይም በአራተኛው ቀን አባቴ ወይም እናቴ ይዘውት ወደ ቤቱ ይሄዱና ከቤተሰቡ ያስታርቁታል።
ሰዎች እርስ በርሳቸው እጅግ የተቀራረቡ፣ ጎረቤታሞች ቤቶቻቸውን እስከ መሶብ ድረስ የሚተዋወቁ አንዱ ቤት በርበሬ የተፈጨ እንደሆነ ይሸታቸዋል ተብሎ በጎድጓዳ ሰሃን ወደ ሌሎቹ ቤቶች ይላክ ነበረ። ዶሮ ወጥ ተሰርቶም እንደሆነ እንደዚሁ። በጓሮው እሸት ወይም ፍራ ፍሬ የደረሰ ከሆነም ለየጎረቤቱ ይሰጥ ነበረ።
ከጎረቤት አንዷ እርጉዝ የሆነች እንደሆን መውለጃዋ ሲደርስ ሌሎች የጎረቤት ሴቶች እናቴን ጨምሮ እንደ እቁብ ነገር ይጣጣሉና ለነፍሰ-ጡሯ መታረሻ የሚሆን የገንፎ እና የአጥሚት እህል አስፈጭተው ቤቷ ይዘውላት ሄደው (የሙከራ) ገንፎ ይበሉ ነበረ። ዛሬ ፈረንጆቹ “ቤቢ ሻወር” የሚሉትን ከ እኛ ነው የወሰዱት ማለት ነው እንደ ቁንጮ፣ “ባላቶሊ” እና ንቅሳት. . .ምን ያልወሰዱብን አለ. . . ኪኪኪ
ይርጋለም ምድረገነት የሚባል ሆቴል አለ ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድና ስንመለስ ከደጃፉ ላይ ኮርኪ እንለቅም ነበረ። ኮርኪ እንኳን የዱሮ ይሻላልኮ ጎበዝ በውስጡ የተለጠፈው ፕላስቲክ በቀላሉ ይወጣና ለትምህርት ቤት የእጅ ሥራ ቀበቶ እንሰራበት ነበር። የአሁን ኮርኪ እጣ እያለው እንኳ በሌላ ሹል ነገር ይፋቅ እንደሁ እንጂ መች ይላጣል።
ይርጋለም መቼስ የሌለ የፍራፍሬ ዓይነት አልነበረም። ሙዝ እንኳን በትንሹ ሦስት ዓይነት አለ። የፈረንጅ ሙዝ የምትባለው ልክ እዚህ አዲስ አበባ የምናውቀው ዓይነት ቢጫ ሆና አጫጭርና በጣም ጣፋጭ፣ የሃበሻ ሙዝ የምንለው ደግሞ አለ ሁለት ዓይነት ነው እሱ ሁለቱም ከበሰሉም በኋላ ወደ አረንጓዴ የሚያመዝን ቀለም ያለው ልጣጭ ነው ያላቸው። መዓዛቸውም እዚህ ከምናውቀው የተለየ በጣም የሚጥምና ጉልህ ነው። አንደኛው ረጅም ሌላኛው አጭር ሆኖ ድፉጭ ያለ-ከአንድ በላይ ለመብላት ይሄ ይመረጣል። ረጅሙን አንድ እንኳ መጨረስ ከባድ ነው።በጠረቂቾ የሚባል ፍሬ ያለው ዛፍ ነበር ደግሞ የተፈጥሮ ከረሜላ ከነማሸጊያው ማለት ነው። የበጠረቂቾ ዛፍ ትልቅ ስለነበር እላይ ወጥቶ ፍሬዎቹን ያወርድልን የነበረው ጠንካራው ያጎቴ ልጅ ቴዲ (አሁን ዶክተር) ነበር።  
ዜሮ ሰባት የሚባል ቀበሌ አለ ከዋናው መንገድ ዳርና ዳር በራሳቸው ጌዜ የበቀሉ የአቮካዶ (አቦካቶ ነበር የምንለው) ዛፎች ነበሩ እና ፍሬ ባፈሩ ቁጥር አስፋልቱ ላይ እየረገፉ መንገዱን ያበላሹ ስለነበር ቀበሌው ያስለቅምና በማዳበሪያ እየሞላ ለህዝቡ ይሸጥ ነበረ። ማዳበሪያ መልስ 50 ሳንቲም ከነማዳበሪያው 1ብር። ታድያ አሁን ሳስበው የሚገርመኝ ከሌላው ጊዜ የበለጠ አስፋልቱ ይቆሽሽ የነበረው ያን ቀን ነበረ። አቦካቶው የሚሸጥ ቀን።
ይርጋለም ማን ሃይማኖቱ፣ዘሩ ወይም ብሔሩ ምን እንደሆነ የሚጠይቅም የሚያውቅም አልነበረም። እኔ ራሴ አባቴ ከአቃቂ ለሥራ ሄዶ እዚያው የቀረ ኦሮሞ እንደሆነ የተረዳሁት ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ቅድም እንዳልኩት ሰዎች የሚተዳደሩበትን ሙያ ነበር እንደ አባት ስም የምንጠቀመው። ዛሬ ግን እነ እገሌ የእንትን ብሔር ሰዎች ናቸው ስለዚህ እዚህ መኖር አይችሉም እየተባለ ነው አሉ።. . .እንባ”
ሌላው ቀርቶ አሁን በቅርቡ እንኳ በተለያዩ ሌሎች ክልሎች የብሔር ግጭቶች ተነሱ ሲባል ስሰማ ይርጋለምን አይመለከትም ብዬ ነበረ የማስበው፤ ነገር ግን ይርጋለምም እንዲሁ መሆኑን ሳውቅ የተሰማኝን ስሜት በቃላት መግለፅ ይከብደኛል። . . .እንባ”
በበኩሌ ግን ይህ ነገር አሁንም ቢሆን በሲዳማ ምድር እኔን አይመለከተኝም። በሲዳማ ውስጥ በየትኛውም ገጠር ከሰማይ ብወድቅ እንኳ የሲዳማ ህዝብ ተንከባክቦ የምወደውን ዋሳ (ቡሪሳሜ) እና ወይራ በታጠነ ዕቃ የረጋ እርጎ አጥግቦ እንደሚልከኝ ከእርግጠኛ በላይ ነኝ። በየትኛውም የሃገራችን የገጠር ክፍል ያለው ሰው ይኸው ነው። ከተማ-ቀመሱ ሳይሆን አይቀርም የችግሮች ምንጭ።
ባለፈው የጋሞ አባቶች ያደረጉትን በጥሞና መመልከትና እንደዚያ ያሉ ብርቅዬ ባህሎቻችንን መኮትኮትና ማገዝ ከእነርሱም መማር ከምንም በላይ ተገቢና አስፈላጊ ነው።
በተለይ በዚህ የለውጥ ወቅት ሰዎች ሌሎችን የመበደል አዝማሚያ ሲሰማቸው ራሳቸውን በሌሎች ተጎጂ ወገኖች ቦታ ኣድርገው የመመልከት ልምድ ቢዳብር መልካም ነው እላለሁ።

Read 2852 times