Tuesday, 12 March 2019 15:32

ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  (ገራገር ወግ)

        በቴፑ ከተከፈተው የዘማሪ ይልማ የንስሃ መዝሙር ጋር የቻልኩትን ያህል እየዘመርኩ የማታውን የሠርክ ጉባኤ እጠባበቃለሁ፡፡
አመሻሹን ስራዬን ጨርሼ ከቢሮ እንደወጣሁ የተለየ ጉዳይ ከሌለኝ በቀር የቦሌውን መድሃኔዓለም የመሳለም ልማድ አለኝ፤ በርግጥ ደብሩ አጥቢያዬ አይደለም፤ ታድያ አጥቢያሽ ካልሆነ አዋሬ ቤተክርስትያን ጠፍቶ ነው እዛ የምትሄጂው…. እንዳትሉ (ሞልቶ…. ስላሴ አሉ፣ ጊቢ ገብርኤል፣ በአታ ማርያም አለች ኪዳነምህረት ኧረ ራሱ መድሃኔዓለምም ቤልኤር 15 ሜዳን አለፍ ብዬ አለልኝ) ታድያ እዚያ ምን? ትሠሪያለሽ እንዳትሉኝ፤ (አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ያ ልጅ ኦሪጅናል የቦሌ ልጅ፣ አይደለሽም ያለሽ እውነቱን ነው…. የሃብታም አጎብዳጅ በሉኝ አሏችሁ)
እውነት ግን ዙሪያዬ ካልጠፋ ታቦት እዛ የምሄደው ለምንድነው???…. የዶላርና የፓውንዱ ስብከት ስለሚማርከኝ ይሆን? እንጃ…. ከሠፈሬ ደረቅ ፊት ምዕመናን ይልቅ ወዛቸው እንደ ኪሳቸው ጢም ብሎ የሞላ ምዕመናንን በማየት ከስብከቱ ልቤ እየተሠረቀ ለመጃጃል ይሆን? እንጃ…. የየሠዉ የሽቱ መዓዛ (የሴቱ ለብቻ የወንዱ ለብቻ) አመሻሹን እንደማይገኝ የሚጥም የቤተክርስትያንን መዓዛ እየመሠለኝ እየተማረኩ ይሆን?.... (ቱ.ቱ. ይቅር በለኝ) ብቻ እንጃ…. የቦሌው መድሃኔዓለም ይመቸኛል፡፡
የዕለት ዕለቱን ፀሎት ከልቤ የማደርሠው እንኳ ቦሌ መድሃኔዓለም ስገኝ ነው፡፡
አንደምታው ሳይገባችሁ ጌታ በወንጌሉ…. “ባለጠጋ መንግስተ ሠማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል” ብሏል ብላችሁ፣ የቦሌዎቹን ባለጠጋ ምዕመናን የሲኦል መግቢያ ቪ አይ ፒ ቀድሞ እንደታደላቸው እንዳትቆጥሩ። እናም ራሳችሁን ቆለል አድርጋችሁ፣ እኔንም “ከኑግ የተገኘህ ሠሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዲሉ የሲኦል ዕድምተኚት፣ ፀሎትሽ ከደመና በታች ነው እንዳትሉኝ፤ መሠፈር በሠፈሩት ቁና ነው ወዳጄ፡፡
ብዙ ሠዎች ወደ ደጀ ሠላሙ ይመጣሉ፡፡
ተሳልመው ይወጣሉ፡፡
ተሳልመው ይቀመጣሉ፡፡
በዚህ መሃል ፍም የመሠለች ሴት አልፋኝ፣ እኔ ከተቀመጥኩበት ሁለት መቶ ሜትር ገደማ ላይ ተቀመጠች፡፡
ቆየት ብሎ ካለችበት የመጣ የመሠለኝ የለቅሶ ሳግ ተሠማኝ፡፡
እሷ መሆኗን ለማረጋገጥ ወደ እሷ ዞርኩ፡፡
ለቅሶዋ እየበረታ ሲመጣ ዝም ማለት ከብዶኝ ሄድኩ፡፡
የቦሌ ሠው ያለቅሳል እንዴ? እንዳትሉኝ፤ እኔም መልሼ እጠይቃችኋለኋ ምን? ጎድሎበት?፡፡ ተሳስተሻል… ምናልባት ልጅቷ እንዳንቺ አጎብዳጅ ምዕመን ትሆናለች እንዳትሉኝ ለማረጋገጥ፣ አስቀድሜ አፍንጫዬ የለመድኩትን መዓዛ እንዲጠራኝ ልኬው ነበር፡፡ መልሡን አቀብሎኛል። “አዎ…. የቦሌ ልጅ ናት”(ጉደኛ አፍንጫ)
“ጓደኞቼ… ሙሉ ወጪያችንን እኔ እሸፍናለሁ ስላቸው፣ ቦይፍሬንድ ስለሌለሽ ከእኛ ጋር አትሄጂም ብለው ጥለውኝ በረሩ” አለችኝ፤ ምን? ሆነሽ ነው ብዬ ሳስጨንቃት፡፡
አናቱን እንደተመታ ሠው ትርክክ ብዬ “በረሩ? ወዴት?”…. አልኳት
የጠየቅኳት የገረማት…. ከጓደኞቿ ድርጊት ጋር ተደምሮ ያበሳጫት መሠለች፡፡
አይ የእኔ ነገር… በመ.ድ.ሃ.ኔ.ዓ.ለ.ም. የቦሌ ቋንቋ ከሠፈሬ ቋንቋ እየተደበላለቀብኝ ደነዘዝኩ ማለት ነው፡፡ እኔ አሁን ላይ መብረርን የማውቀው በአዕዋፋት ነው፡፡ ምሳሌ አንድ…. የፒያሳው ቢሯችን ጣራ ላይ(ቢሮው የመጨረሻው ፎቅ ቴራዝ ላይ ነው) የሚያርፉ አሞሮች እኛ ወደ ቢሮ ስንገባና ከቢሮ ስንወጣ በሚሠሙት ድምፅ ተነስተው ሲበሩ ስለማይ ነው፡፡
“ከዱባይ ከተመለስኩ አራት አመት አልፎኛል፡፡ መብረር በፕሌን መሆኑን መርሳቴ ሊያስፈርድብኝ አይገባም” ልላት አልኩና መልሼ ዋጥኩት፡፡
“ዱባይ” አለችኝ፡፡
“ኦው!” (በመደነቅ አፌን ከፍቼ) “ምን ሊሠሩ?” አልኳት
አፈጠጠችብኝ፡፡
“እንዴ? ምን አስፈጠጠሽ እንደእኔ ለሠው ቤት ስራ መስሎኝ ነው” ልላት አልኩና አሁንም ዋጥኩት፡፡
“የምታፈጪው የማስበውን ብነግርሽ የጀመርሽልኝን የዶላር ወሬ ልታቋርጪብኝ ሞኝሽን ፈልጊ” ልላት ስል፤
“ለመዝናናት…. 10 ቀን ይቆያሉ”
“እና ሙሉ ወጪያችንን እኔ ልሸፍን ስትያቸው እምቢ አሉ??” አልኳት ሽምቅቅ ብዬ፤
የዱባይን የመዝናኛ ስፍራዎች እንኳን እሷ የሆሊውድና የቦሊውድ የጥበብ ሠዎች፣በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግና በአውሮፓ የተለያዩ ሊጎች የሚጫወቱ እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ የዓለማችን ሃብታሞች ጭምር የእረፍት ጊዜያቸውን ጠብቀው ለመዝናናት መዓት መዝናኛ ካሏቸው ሃገሮቻቸው አብልጠው በፍቅር ሊከትሙባት የሚቋምጡላት ቦታ አይደለች ዱባይ!፤ ሃገራችንንና ምስኪን ህዝቦቿን የሚዘርፉ ባለስልጣናትና ተባባሪዎቻቸውስ ከዱባይ ሃቢቢቲዎቻቸው ጋር የሚምነሸነሹባት አይደለች ዱባይ!፤ ደግሞ ምን? ሠርተው እንዳመጡት የማይገባን የተከማቸ ገንዘብ ያላቸው ሃብታሞቻችንስ ውሽሞቻቸውን (ሚስቶቻቸው ያኔ ይመቻቸዋል አሉ፤ እነሡም ሸገር ላይ ካስቀመጧቸው ቤቢዎቻቸው ጋር አለማቸውን ይቀጫሉ) ይዘው አለማቸውን ለመቅጨት አየር መንገዳችን ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩላት አይደለች ዱባይ!
አሁን ቦይ ፍሬንድ ስለሌለሽ ተብሎ ወጪ ልቻል ያለችን ልጅ፣ ከእኛ ጋር አትሄጂም ማለት ፌር ነው?....፡፡
በቅርቡ አስር ደቂቃ በማይሞላ የስልክ ወሬ የተለየሁት ሁለተኛው ቦይ ፎሬንዴ ትዝ አለኝ፡፡
ነፍስህን ይማረው፡፡
እናንተ ደግሞ መድሃኔዓለም የስራችሁን ይስጣችሁ፡፡
አድቫንስ ሳልወስድ…. ወሬን ጠብቄ የወር ደምወዜን ወስጄ፣ የደጉ አለቃዬ ቦነስ ታክሎበት ለአንድ ቀን ደረቴን ነፍቼ ልዝናና ብዬ የምወጣባቸው የፒያሳው ጣይቱና የአምባሳደሩ ጊዮን ሆቴሎች ትዝ አሉኝ፡፡
የዛሬ ሳምንት እነዚሁ የቦሌ ልጆች፣ እዛው ቦሌ መድሃኔዓለም ለስብከት ከተቀመጥኩበት ቀልቤን ሠርቀውኝ ሳዳምጣቸው፣ አሜሪካዊቷን አቀንቃኝ ቢዮንሴን ከባለቤቷ ጄዚና ከቤተሠቦቿ ጋር አግኝተናት፣ አብረን ፎቶ ተነሳን ሲሉ…. ብቻዋን መጥታ አቡነ ጳውሎስ (ሙት ወቃሽ አያድርገኝ) ጥላ አስወጡላት ምናምን ሲባል የሠማሁት ወሬ ትዝ ብሎኝ አሁን ቤተሠቦቿን….  ጨምራ መጥታ ምን ይወጣላት ይሆን?.... ብዬ፣ ያቺ ምስኪን ቤተ ክርስትያን ትዝ ብላኝ ሃሳብ ገባሁ….እንደገና ብትት ብዬ የት? ጣይቱ? (ደግሞ በማንነቷ የምታፍር በሉኝ አሏችሁ፤ ለማንነት ለኩራት ለክብሬ ማን እንደሃገሬ የሚለው ዘፈን ውስጤ ነው ለምን? ታድያ እነ ክርስትያኖ ሮናልዶ ጣይቱ አይመጡም?) ቀና ስል አንደኛው ልጅ እግዜር ይስጠው ዱባይ እያለሁ፣ ሠዎቼ ማለትም አሠሪዎቼ “ደርሠንበት መጣን ቤት ጠብቂ” ብለውኝ ሲወጡ የሠማሁትን የአንዱን ሆቴል ስም ሲጠራ ተንፈስ አልኩ፡፡
ታድያ ያቺ መድሃኔዓለም ደጅ ላይ የምታላዝነው የቦሌ ሞልቃቃ ዱባይ ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኜ ስትለኝ መሸማቀቄ ሲያንሠኝ አይደል?(“ሲያንሠኝ ነው” ነው ያለው ኮሜዲያን ዶክሌ) ሲያንሠኝ ነው፡፡
“ለምን ታለቅሻለሽ መድሃኔዓለምንስ ምን አድርግልኝ ነው የምትይው” አልኳት የሠፈሬን…. የማውቀውን….ደግሞ ለቦሌ የሚቀርብ የመሠለኝን የማፅናኛ ቃላት እየመራረጥኩ፤
እሷ እኮ አታፍር… ብሮኝ የሚሄድ ሠው እንዲሠጠኝ…. አብረን እንሂድ… ትለኝ ይሆናል ሆ... ሆ. እዛው በፀበልሽ (በሠፈርሽ)፡፡
“ባቢ አሜሪካ ያለው ሆቴሉን ሊጎበኝ አሜሪካ ሲሄድ… ከጓደኞችሽ ጋር ተዝናኚበት ብሎ የሠጠኝን ዶላርና ፓውንድ ብቻዬን ምን ላደርገው? እያልኩት ነው” አለችኝ፡፡ አቤት የኑሮ ልዩነት፡፡ በአይኖቼ ሠማይ ደርሼ ምድር ተመለስኩ፡፡
“አብረን እንሂድ?” አለችኝ በድንገት፤
የፈራሁት አለች እማዬ፡፡
ብድግ ብዬ ቁጭ እንዳልኩ ትዝ ይለኛል፡፡
ልቤ ውድውድ…ውድውድው ብቻ ከመቶ ጊዜ በላይ እንዲህ ብሎብኛል እንድረጋጋ በየመሃሉ የመድሃኔዓለምን ስም እየጠራሁ ሁሉ፤
“ስለ ወጪው ችግር የለም፤ ለቪዛው አታስቢ” እኔን ማግኘቷ ከመድሃኔዓለም የተሠጣት የፀሎቷ መልስ እንደሆነ አስባለች፡፡
ለቪዛ አታስቢ! “እንዴት? ነው የማገኘው” ማሠብ ዳዳኝና ሳቄ መጣ፡፡
ፓስፖርቴ ትዝ አለኝ፤
ኤክስፓየር አርጓል፡፡
ኢምግሬሽን የት ነው ያለው?
እረስቼዋለሁ፡፡
ለመሆኑ ኤክስፓየር ያደረገው ፓስፖርቴን የት ነው ያስቀመጥኩት?
አላስታውስም፡፡
የዛሬው ስብከት አብይ ርዕስ “ክርስቶስ የሚመጣበት ቀን አይታወቅምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ” የሚል ነበር፡፡ አመሻሹን ስራዬን እየጣልኩ ሁሉ ለምስመው መድሃኔዓለም…. በህይወቴ የተሻለ ነገር እንዲያሳየኝ እጆቼን ዘርግቼ እማፀነው ነበር፡፡ ተዘጋጅቼ ባለመጠበቄ ያዘጋጀልኝን ሲሳይ እንዲህ ከአየር ላይ ላፍ አደረገኝ፡፡ (“ምነው? መድሃኔዓለም ምን? አደረግኩህ” ቤቴ እየገባሁ ያጉተመተምኩት)
ፀሎትሽ ከደመና በታች ነው ያላችሁኝ ሠዎች ይኸው ተሳካላችሁ፡፡ ምናለ አሁን ዱባይ ደርሼ ብመጣ… ምቀኛ ሁሉ፡፡
ለከባድ ተልዕኮ ስዊዘርላንድ ልበር እንደሆነ ነግሬያት እሷም አምናኝ አፅናንቼና አረጋግቼ ውሃ የመሠለች መኪናዋ ውስጥ አስገብቻት፣ ወረፋዬን ልጠብቅ ወደታክሲ ተራዬ አመራሁ፡፡
ስዊዘር ላንድ የት ናት?... እንዳትሉኝ፤
እንደ ፓስፖርቴ ያስቀመጥኩበትን አላውቅም እንዳልላችሁ (በራሴ አፈርኩ)
“የሚመጣው ቀን አይታወቅምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ”፡፡

Read 1238 times