Sunday, 17 March 2019 00:00

ኢዴፓ፣ ከእነ አርበኞች ግንቦት 7 ጋር እንዲዋሃድ ተወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ቀድሞ አመራሮች ቅሬታቸውን ለምርጫ ቦርድ አቅርበዋል

         የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጠቅላላ ጉባኤ፤ ፓርቲው ከእነ አርበኞች ግንቦት 7 ጋር እንዲዋኃድ የወሰነ ሲሆን በአመራሩ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት ከፓርቲው የወጡት የቀድሞ አመራሮች ውሣኔውን አስመልክቶ ቅሬታቸውን ለምርጫ ቦርድ አቅርበዋል፡፡
ኢዴፓ ባለፈው እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል የምርጫ ቦርድ ተወካይ በተገኙበት ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው፣ የፓርቲው የተናጠል ጉዞ አብቅቶ አርበኞች ግንቦት 7፣ ሠማያዊ ፓርቲ፣ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራሮች አማካይነት የሚመሠረተው ውህድ ፓርቲ አካል እንዲሆን መወሰኑ ታውቋል፡፡
በእለቱ በተካሄደው ጉባኤ የፓርቲው አባላት ውህደቱ ተፈፃሚ የሚሆንባቸውን መንገዶች በአጽንኦት ማስቀመጣቸውን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የፓርቲው አመራር አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ “በዋናነት የኢዴፓ የትግል መሠረቶች የሆኑት ህብረ ብሔራዊነት፣ ሀገራዊ አንድነት፣ ዲሞክራሲያዊነት፣ አዲሱ ውህድ ፓርቲ ውስጥ ተፈፃሚ ሲሆኑ፣ ውህደቱ ያለፈውን የፖለቲካ ስህተት የማይደግም መሆኑ ሲረጋገጥ እንዲሁም ውህደቱ ከወረዳ ጀምሮ ሁሉንም አባላት እያሳተፈ መሄድ ሲረጋገጥ ውህደቱ ይፈፀማል” ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ሠማያዊ ፓርቲ በዚህ መልኩ ውሣኔ አሳልፎ ራሱን ያከሰመ ሲሆን በቀጣይ አርበኞች ግንቦት 7 ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመጋቢት (በያዝነው ወር) ውህደቱ ይፈፀማል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ሂደቱ በተፈለገው ፍጥነት ባለመጓዙ በቀጣይ 3 ወራት ውስጥ ውህደቱን ለመፈፀም እቅድ ተይዟል ብለዋ - አቶ ዋሲሁን፡፡
የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤን የተቋወሙት የቀድሞ የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ልደቱ አያሌው የተካተቱበት የአመራር ቡድን በበኩሉ፤ የተወሰነው ውሣኔ ተገቢ አይደለም በሚል ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
የአባላቱን ቅሬታ ምርጫ ቦርድ ተመልክቶ ኢዴፓን ከመፍረስ የማይታደግ ከሆነ  በፍ/ቤት ክስ እንደሚመሰርቱ የቡድኑ መሪ የሆኑት አቶ አዳነ ታደሠ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡   

Read 5649 times