Sunday, 17 March 2019 00:00

ለውጡ በአክራሪ ሃይሎች ምክንያት ስጋት ተጋርጦበታል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 “የዘር ፖለቲካ በህግ መታገድ አለበት”
                                              - አቶ እንዳርጋቸው ፅጌ

            ከ11 ወራት በፊት በሀገሪቱ የተፈጠረውና በዜጐች ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የለውጥ ሂደት በአክራሪና ጽንፈኛ የፖለቲካ ሃይሎች የመክሸፍ ስጋት እንደተጋረጠበት “አርበኞች ግንቦት 7” አስታወቀ፡፡
“ለዘላቂው የሚበጀንን ለዘብተኛውን መንገድ ትተን፣ ዋልታ ለረገጡ አጥፊ ጽንፈኞች አገራችንን እንዳናስረክብ እንጠንቀቅ” በሚል ርዕስ የአቋም መግለጫውን ያወጣው ንቅናቄው፤ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የለውጥ ሂደትና ፖለቲካ ጽንፍ በያዙ ሃይሎች እየታመሰ ነው ብሏል፡፡
የ11 ወራት የለውጥ ሂደቱን ለቀናት በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ተሠብስቦ ሲገመግም መቆየቱን የጠቆመው “አርበኞች ግንቦት 7”፤ ለሀገሪቱ የለውጥ ሂደት እንቅፋትና ስጋት ናቸው ያላቸውን ጉዳዮችም ለይቶ አስቀምጧል፡፡
ስጋት ናቸው ብሎ ከገመገማቸው መካከልም በትግራይና በአማራ ክልል ያለው አደገኛ ውጥረትና የጦርነት ነጋሪት፣ በአማራ ክልል ውስጥ በቅማንትና በአማራ ስም እየደረሰ ያለው ግጭትና በቤኒሻንጉል በሶማሌ ክልልና፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዘርን መሠረት ያደረገ ዜጐችን የማፈናቀልና የሠብአዊ መብት ረገጣዎች መስፋፋት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አክራሪ ሃይሎች በሚያነሷቸው የተለያዩ አጀንዳዎች በህዝቡ ሠላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው ያለው መግለጫው፤ በተለይ አክራሪ የፖለቲካ ሃይሎቹ አዲስ አበባን በተመለከተ የሚያውቸው ፍፁም ሃላፊነት የጐደላቸው መግለጫዎች በአዲስ አበባና በኦሮሚያ አስተዳደሮች ላይ ጭምር ተጽእኖ እያሳረፈ ነው ብሏል፡፡
የነዚህ የፖለቲካ አክራሪ ሃይሎች አዲስ አበባን በተመለከተ የሚሠጡት መግለጫ በከተማዋ ህዝብ ላይ የፍርሃትና የስጋት ድባብ ፈጥሯል ያለው የንቅናቄው መግለጫ፤ በከተማዋ ያሉ ወጣቶች ልንወረር ነው” በሚል ጭንቀት ውስጥ በመግባታቸው ከተማዋ በውጥረት የተሞላች ሆናለች ብሏል፡፡
እነዚህ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ወቅታዊ ውጥረቶች በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም ያለው “አርበኞች ግንቦት 7”፤ ይህን ውጥረት በዋናነት የሚፈጥሩትም ከስልጣን የተባረሩ ሃይሎችና የጠባብ ቡድናዊ አላማን የሚያራምዱ ሃይሎች ናቸው ብሏል፡፡
በዚህ ምክንያትም እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በፈተና ስጋት ውስጥ ወድቋል ይሏል - መግለጫው፡፡  
ከዚህ ውጥረት  ወጥቶ የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ ከተፈለገ፣ ለዘብተኛ የፖለቲካ ሃይሎች የለውጡን አጀንዳና ሂደት መቆጠር አለባቸው ያለው ንቅናቄው፤ ለውጡን የሚደግፉና ግቡን እንዲመታ የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ከጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ይልቅ ለሀገር መረጋጋትና እውነተኛ ዲሞክራሲ መመስረት ከምንጊዜውም በላይ ተሰባስበው እንዲሠሩም  ጥሪ አቅርቧል፡፡
“የአክራሪ ሃይሎች” ክፍት የፖለቲካ መድረክ አግኝተው አስተሳሰባቸውን በወጣቱ እንዳያሰርፁ ለዘብተኛ ሃይሎች መታገል እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡
ማንኛውም ዜጋ የጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለሚፈጥሩት ጊዜያዊ የግጭት ስሜት ሰለባ እንዳሆንና ራሱን ከጽንፈኛ ሃይሎች መጠቀሚያነት እንዲከላከልም ንቅናቄው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ ጉዳይ ለጀርመን ድምጽ ቃለ ምልልስ የሰጡት የንቅናቄው ም/ሊቀመንበር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ በተንሠራፋው የዘር ፖለቲካ ምክንያት ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ስራ መስራት የማይችሉበት ደረጃ መደረሱንና የፖለቲካ ምህዳሩ በአሁኑ ወቅት ከወትሮ በበለጠ መዘጋቱን ጠቁመው በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የለውጥ ሃይሉ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
“ለዚህ ዋነኛ መፍትሔው በሀይማኖት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ማካሄድ በህግ ክልክል እንደሆነ ሁሉ በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ማካሄድ በህግ ሊታገድ ይገባዋል” ብለዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፡፡  

Read 6250 times