Sunday, 17 March 2019 00:00

ቤታቸው ይፈርሳል የተባሉ የሱሉልታ ነዋሪዎች ጠ/ሚኒስትሩን ተማፀኑ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 በ7 ቀን ውስጥ ቤት እንዲያፈርሱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል

          የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር በርካታ ቤቶችን ህገ ወጥ ናቸው በሚል ለማፍረስ የ7 ቀናት ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲታደጓቸው ተማፅነዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር እንዲፈርሱ ውሣኔ ባሳለፈባቸው መኖሪያ ቤቶች በር ላይ በቀይ ቀለም የኤክስ ምልክት ያደረገ ሲሆን የቤቱ ባለቤቶች በ7 ቀን ውስጥ ንብረታቸውን ሰብስበው ቤቱን ካላፈረሱ፣ ቤቱ በአፍራሽ ግብረ ሃይል ፈርሶ፣ የቤቱ ባለቤቶችም ለህግ እንደሚቀርቡ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል፡፡
ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ ቤታቸው ይፈርሳል የተባሉት ነዋሪዎች ከትናንት በስቲያ  በሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ደጃፍ ተሰባስበው አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ሰሚ እንዳላገኙ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
እንዲፈርሱ ምልክት የተደረገባቸው ቤቶች በሱሉልታ ሚዛን፣ ገበያ አስር ኪሎ በተባሉ አካባቢዎች እንደሚገኙ የጠቆሙ ምንጮች፤ ከተማ አስተዳደሩ 35ሺህ 6 መቶ ቤቶችን በህገ ወጥነት ለማፍረስ ስለማቀዱ መረጃው እንዳላቸውም አክለው ገልፀዋል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ ቤታችሁ ይፈርሳል የሚል ማስጠንቀቂያ የደረሰን በድንገት ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ይፈርሳል ሲባል የነበረው በአረንጓዴ ቦታ ላይ እና ባዶ ሜዳ ላይ የተሰሩ ቤቶች ናቸው የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ አሁን ግን ከግለሰቦች ላይ የተገዛና ወና በአጥር ብቻ ከሻጮች የለየናቸው ቤቶቻችን ናቸው እንዲፈርሱ ነው የተወሰነው ይላሉ፡፡
ሌሎቻችን ህጋዊ እንደሆንን በቀድሞ አስተዳደር ተረጋግጦልን ነበር የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በጅምላ ቤቶች እየተለዩ ነው እንዲፈርሱ ምልክት የተደረገው ብለዋል፡፡
ቅሬታቸውን ለከንቲባዋ ለማሳወቅ በተደጋጋሚ በአስተዳደር ፅ/ቤቱ ደጃፍ ደጅ ቢጠኑም ማንም አካል ጥያቄያቸውን ለመቀበልና ለማስተናገድ ፍቃደኛ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
ቤቶቹ ህገ ወጥ ናቸው በሚል እንዲፈርሱ ከመወሰኑ ውጪ ቦታው ላይ ምን ሊሰራ እንደሆነ አይታወቅም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ቤቶች እንዲፈርሱ የተወሰነውም መደዳውን ሳይሆን አልፎ አልፎ በመንደር ውስጥ እየተመረጡ ነው ብለዋል፡፡
“የለገጣፎ ሰቆቃ በኛ ላይ ሊደገም ነው” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚወዷት ሃገራቸው ስም ይድረሱልን፤ ከጥፋት ይታደጉን ሲሉ” ተማፅነዋል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ለገጣፎ - ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር፣ ከ6ሺህ በላይ ቤቶች በተመሳሳይ ማፍረሱ የሚታወስ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ዛሬም በየመጠለያው እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡  

Read 5901 times