Sunday, 17 March 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብና የነዋሪዎቿ ናት”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 • ከጠባብነት ካልወጣን እንደ አገር አንቀጥልም
                  • አዲስ አበባ ስንል አስተሳሰቧን…መንፈሷን---መቻቻሏን…ማለታችን ነው


          ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ መሀል መርካቶ ነው፡፡ ከአገር የወጡት እ.ኤ.አ በ1996 ዓ.ም ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ ብላቴ ማሰልጠኛ በገቡበት አጋጣሚ ነበር፡፡ መጀመሪያ ወደ ኬንያ፣ ከዚያም ወደ አሜሪካ ተሻገሩ፡፡ በህክምና ሙያ የተመረቁት ክሊኒካል ፕሮፌሰር ዶ/ር መኮንን ብሩ፤ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማር ላይ  ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ ለማሻሻል በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እኛም ያገኘናቸው ባለፈው ረቡዕ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው የምክከር ፕሮግራም ላይ ሲሳተፉ ነበር፡፡  
ዶ/ር መኮንን ከህክምና ሙያቸው ባሻገር በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአሜሪካ ሲካሄዱ በነበሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት መሳተፋቸውን ይናገራሉ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ የነበረውን ጨቋኝ ሥርዓት ለማስወገድ በተካሄደው ትግል ላይ የአቅሜን ያህል ተሳትፌያለሁ ይላሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ መጥቷል በሚባለው ለውጥ ላይ ግን ጥርጣሬ አላቸው፡፡ በአሜሪካ የ“አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ንቅናቄ” እና የ“አለን” ኦንላይን ሚዲያ መስራች ሲሆኑ የዚህን ንቅናቄና ሚዲያ ቅርንጫፍም በአዲስ አበባ ከፍተዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውዝግብ ባስነሳው በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ፈርጣማ አቋም ይዘው በ”አለን” ሚዲያ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በመሰረቱት ንቅናቄና ሚዲያ ዓላማ እንዲሁም በአገሪቱ የጤና ፖሊሲ ዙሪያ ከዶ/ር መኮንን ብሩ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡  


        ከአገር የወጡበት ዋና ምክንያት ምን ነበር?
የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ በግርግሩ ወቅት ኬንያ ሄድኩኝ። አጋጣሚው ሲመጣ በትምህርቴ በመግፋት የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ አስቤ ነው  ከአገር የወጣሁት። ትልቁ ዓላማዬ በትምህርት መግፋት ነበር፡፡ በትምህርቴ መግፋቴ ከራሴ አልፎ አገሬንም ይጠቅማል  የሚል ጠንካራ እምነት ነበረኝ፡፡ በወቅቱ ብላቴ ማሰልጠኛ የገባሁትም፣ አገሬ ሰላም ሳትሆን እኔ እንዴት ተረጋግቼ መማር እችላለሁ በሚል ነበር። አጠር ባለ አማርኛ ለጠየቅሽኝ ጥያቄ ለመመለስ፣ ከአገሬ  የወጣሁበት ምክንያት፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ቢኖረውም፣ መማርና አገርን ማገልገልም ፍላጎቴ ነበርና እሱ የተሳካልኝ ይመስለኛል፡፡
ኢህአዴግ የገባ ሰሞን ነበር ከአገር የወጡት፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት፣ አገርዎን በማገልገል ረገድ ተሳካልዎ?
ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበረች፡፡ አሁንም አገሪቱ እጅግ ውስብስብ ችግር ውስጥ ነው የምትገኘው፤ መግባት  የሌለብን ነገር ውስጥም ገብተናል፡፡ እኔ በበኩሌ፣ አገሪቱን ለማገዝ በንቃት ስንቀሳቀስ ነው የቆየሁት። እርግጥ ነው የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም፣ ሆኜም አላውቅም፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ በሚደረጉ የትኛውም የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በንቃት እሳተፍ ነበር፡፡ አገሪቱ ከህውሓት ጨቋኝ አገዛዝ እንድትወጣ ሲደረግ ከነበረው  ትግል ቦዝኜ አላውቅም፡፡ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ይሄን ጨቋኝ ሥርዓት በቀጥታ በመቃወም፣ በፌስቡክ ገፄ ላይ ስፅፍ ቆይቻለሁ፡፡ ምንም እንኳን የግንቦት ሰባት ንቅናቄ አባል ባልሆንም፣ ከእነ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር በመሆን ብዙ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ ምክንያቱም አገሬ ላይ የሚደረገው ነገር ያናድደኝ ይቆጨኝ ነበር፡፡
አሁን የመጣውን ለውጥ  እንዴት ያዩታል?
ለእኔ ጥያቄው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ያለንበትን የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ አንዳንዶች “ለውጥ”፣ ሌሎች ደግሞ “ነውጥ” ይሉታል፡፡ አሁን እኔን ኢትዮጵያ ውስጥ እንድገኝ ያደረገኝ፣ ለውጡ እውነት ከሆነና ካለ፣ ከለውጡ ኃይል ጋር ሆኜ፣ በተለይ በጤናው ዘርፍ አገሪቱ ያለባትን ክፍተት ለመመልከትና ምን ቢደረግ ይሻላል በሚለው ምክክር ላይ ለመሳተፍ ነው፡፡ ይሄ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ሳይሆን የጤና ተማሪዎችን ሥርዓተ ትምህርት፣ የሆስፒታሎችን የኤሌክትሮኒክ ሪከርድ ለማስተካከልና በአጠቃላይ የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ ደካማና ጠንካራ ጎን ምንድነው የሚለውን ለማየትና በሙያዬ አስተዋፅኦ ለማበርከት ነው። እግረ መንገዴን በውጭ ሆኜ አለ የተባለውንና የሰማሁትን ለውጥ፣ የምር አለ የለም የሚለውንም በቅርበት ለማየት ያስችለኛል፡፡ አሁን ለውጥ አለ ወይ ካልሺኝ አላውቅም፡፡ ለውጥ አለ ካልን፣ የለውጡ አራማጅ ኃይሎች የገጠማቸው ችግር አለ፡፡ አሁን በተጨባጭ መሬት ላይ የምናያቸው ችግሮች ለመግለፅ ያስቸግራሉ፡፡ በጌዲኦ፣ በቡራዩና አካባቢው፣ በቅርቡም በለገጣፎ ሰዎች ከሞቀ ኑሯቸውና ከቀያቸው ተፈናቅለው፣ በረሃብና በችግር እየተሰቃዩ፣ በረሃብም በጥይትም እየሞቱ ነው፡፡ ቀደም ሲል እኛም “አለን” በተባለው ዓለም አቀፍ ሚዲያችን፣ የአራት ኪሎውን መፈናቀል በደንብ ዘግበናል፡፡ ሰዎች ለ30 እና 40 ዓመታት የልጅ ልጅ ካዩበት ቦታ ተፈናቅለው፣ ቦታቸው በውድ ዋጋ እየተቸበቸበ፣ ሜዳ ላይ ተጥለዋል፡፡ የለገጣፎውን ሁኔታ የምታይው ነው፡፡ ለምን ይህ ሆነ ተብለው አፈናቃዮቹ ሲጠየቁ፣ የመንግስት ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ተሿሚዎች የሰጡት ምላሽ፣ ዜጎች ከተፈናቀሉበት መንገድ በላይ የሚያሳምም ነው። እነዚህ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው የሚያላግጡ አካላት፣ የለውጡ አደናቃፊ እንጂ የለውጡ ደጋፊዎች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡
አሁን እኔና አንቺ እዚህ ቁጭ ብለን በምንነጋገርበት ወቅት እንኳን ቆንጨራና ዱላ ይዘው በመውጣት፣ የሩዋንዳን የሁቱና የቱትሲን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያስታውስ አደገኛ ምልክት የሚያሳዩ ነገሮች አሉ፡፡ አሁን እንግዲህ ያለውን ሁኔታ ዝም ብሎ መናገር ሳይሆን፣ ለዚህ ነገር እልባት ለማበጀት  ምን ማድረግ አለብን? መፍትሄው ምንድን ነው? የሚለው ላይ መነጋገርና መወያየት በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ፣ የአገራችን ትልቁ የችግር መንስኤ፣ ኢህአዴግ/ህውሓት  ለ27 ዓመታት የዘራብን የዘር ነቀርሳ ነው፡፡ አሁንም ትላንት ከህውሓት የጭለማ አገዛዝ ወጥተን፣ ወደ ሌላ ተረኛ ባለ ጊዜ ቡድን የምንገባ ከሆነ፣ ለሌላ ቀጣይ 27 ዓመታት ጭንቅና መከራ ውስጥ ልንገባ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ አደገኛ ነገር ተመልሶ እንዳይመጣ ሁሉም አካል የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡
“አለን” ሚዲያ ላይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አቋም ተመልክቼአለሁ፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ ይሄ ሁሉ ውጥረትና ውዝግብ ከምን የመጣ ነው ይላሉ?
አዲስ አበባ የማን ናት የሚለው ጉዳይ ትክክል ነሽ የውጥረት መነሻ ነው፤ ነገር ግን አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብና የነዋሪዎቿ ናት፤ አራት ነጥብ። እኛ እንደ “አለን” ሚዲያ የምንታገልለት ሶስት ዋና ዋና አላማዎች አሉን፡፡ አንደኛው፤ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ፤ አዲስ አበባ ፊንፊኔም በረራም አይደለችም፡፡ በቃ አዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ ናት የሚል እምነት አለን። ይህንን እንገልፃለን፣ እናስተምራለን፤ ይህንን የበለጠ ለማጉላትም ንቅናቄያችንን አጥብቀን እንቀጥላለን፡፡
በፌስቡክ ገፅዎ ላይ ግን አዲስ አበባ ከማለት ይልቅ “ሸገር” እያሉ ነው በብዛት የሚገልጿት---
አሁን እኔ በልጅነቴ ከቤተሰብ የተሰጠኝ የምወደው የቤት ስም አለኝ፡፡ በዚያ ስም አሁንም የሚጠራኝ ሰው ሲኖር፣ አቤት እላለሁ እንጂ የመዝገብ ስሜ መኮንን ነው፡፡ አሁን ሸገር የሚለው የአዲስ አበባ የቤት ስሟ ነው የሚመስለኝ፤ ምንም ዓይነት ጭቅጭቅ ስላልተነሳበትም  ችግር የለውም በሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ “ፊንፊኔም” አዲስ አበባ የሚለውን እስከ ማስቀየር የጭቅጭቅ መነሻ ባይሆንና ዝም ብሎ ለመጥራት ያህል ቢሆን ችግር አልነበረውም፡፡ ነገር ግን  በዓለምም የምትታወቅበት ስሟ አዲስ አበባ ነው፤ ይሄ የሚያሻማ ጉዳይ አይደለም፡፡
እሺ የ “አለን” ሚዲያን ሦስተኛ ዓላማ ይንገሩኝ?
ሦስተኛውና ዋናው ዓላማችን ብለን የተነሳንበት ጉዳይ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሊሆን የሚገባው በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ባስቀመጥናቸው ዓላማዎች የሚያምን መሆን አለበት፡፡ ያ ካልሆነ በንቅናቄያችን አጥብቀን እንታገለዋለን፡፡ በቀጣይ በምርጫው ውስጥ ተሳትፎ ይኖረናል፡፡ ለዚህም በየወረዳውና በየቀበሌው አባላትን አሳትፈንና በሚዲያውም ገብተን የምንታገለው ከላይ ለጠቀስኩልሽ ሶስት አላማዎች ነው፡፡ ወደፊት በሚዲያም በንቅናቄም የምታይንና የምታገኚን ከላይ የጠቀስኩልሽን ጥያቄዎች ስንጠይቅ ነው የሚሆነው፡፡ ጥያቄያችንን የማይመልስ አካል ካለ፣ በንቅናቄያችን ዘመቻችንን እንቀጥላለን፡፡
በህገ መንግስቱ ላይ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እንደሚያገኝ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ትልቁ የአገራችን ችግር ህውሓት ያመጣው፣ ህዝብ ያልተሳተፈበትና ያላመነበት ህገ መንግስቱ ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስት አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባን ህዝብ መብት በግልፅ የነፈገ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ውስጥ በደል የደረሰበት የአዲስ አበባ ህዝብ ነው፡፡
እንዴት? በምን ምክንያት?
በጣም ጥሩ! በፌዴሬሽን ምክር ቤት የአዲስ አበባ ህዝብ ተወካይ የለውም፡፡ እንደ ግለሰብ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ አይታወቅም፡፡ ምን ማለት ነው? ሁሉም ክልሎች በምክር ቤቱ ተወካይ ሲኖራቸው፣ አዲስ አበባ ተወካይ የላትም፡፡ ህገ መንግስቱ ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦች ብሎ ነው የሚጠቅሰው፡፡ ብሔር ብሔረሰቦችን ካስቀመጠ አዲስ አበባ እንደ ብሔር ብሔረሰብ ካልታየች፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ተወካይ የለውም ማለት ነው፡፡ በህገ መንግስቱም አይታወቅም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በንቅናቄያችን እስከ መጨረሻው የምንታገለው፣ የአዲስ አበባንና የነዋሪዋን መብት የነፈገውን ህገ መንግስቱን እስከ ማስቀየር ይሆናል ማለት ነው፡፡
ቅድም ከአዲስ አበባ የኦሮሚያን ጥቅም በተመለከተ ላነሳሺልኝ ጥያቄ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ። አሜሪካ ውስጥ ኔቫዳ የሚባል ስቴት አለ። ላስቬጋስ ውስጥ የሚገኘው የኒዩክሌር ማብላያ ተረፈ ምርትና ቆሻሻ የሚደፋው ኔቫዳ  ውስጥ ነው። ለኔቫዳ ለሰርቪስ የሚከፈል ክፍያ አለ፤ ይሄ ፍትሃዊ ነው። የአዲስ አበባ ቆሻሻ ኦሮሚያ ክልል ላይ የሚደፋ ከሆነ፣ ለዚያ የሚከፈል ክፍያ አግባብ ነው።  ዋሽንግተን ዲሲን ውሰጂ፣ ከዚህም ከዚያም ተቆርሳ የተቆረቆረች ከተማ ናት፡፡ የትኛውም ከተማ የሚመሰረተው በዚህ መልክ ነው፡፡  
በነገራችን ላይ በዓለም ላይ ያሉ ከተሞች በዚህ መልኩ ስለሚመሰረቱ ከጠብ የራቁ አይደሉም። የአሜሪካ መንግስት ኔቫዳ ውስጥ ለሚደፋው የኒኩሊየር ማብላያ ተረፈ ምርት በጀት አለው። በኔቫዳ አየሩን ለማጽዳት፣ ዕፅዋትን ለመትከል፣ ለነዋሪዎቹ የጤና አገልግሎት በነፃ ለመስጠት፣ በቆሻሻው ምክንያት የተጐዱ ካሉ ለመካስ ለኔቫዳ አስተዳዳሪ ይከፍላል፤ ከተማዋም ገንዘቡን ለህዝቡ ጥቅም በሚፈለገው መልኩ ታውለዋለች፡፡ ይሄ ማለት ግን ልዩ ጥቅም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቆሻሻውን ለምን ጣልክብኝ ብሎ ቢጠይቅ፣ የኔቫዳ መንግስት እንጂ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል፤ እኔ ለምሳሌ፡- ከቴክሳስ ወደ ኔቫዳ ሄጄ ስድስት ወር ብቆይ ኔቫዳዊ እሆናለሁ፤ ቴክሳሳዊ መሆኔ ይቀራል አለቀ፡፡ ከዚህ መጣህ፣ ዘርህ ይሄ ነው የለም፡፡ እኔ ቤተሰቦቼ ኦሮሞ ናቸው፤ ነገር ግን አማርኛ ብቻ ነው የምችለው፤ እኔ ራሴን ኢትዮጵያዊ ነኝ ነው የምለው፤ ራሴንም የምገልፀው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ ነው፡፡
በአጠቃላይ በዘረኝነትና በጐጠኝነት ህመም ተይዘን አገር ልንገነባ አንችልም፡፡ ከዚህ ጠባብነት ካልወጣን እንደ አገር አንቀጥልም፡፡ አሜሪካን የመሰለች ሀገር የገነቡት እኮ ቻይናዎች ህንዶች፣ ኢትዮጵያኖችና የሌሎች ሀገር ዜጐች ናቸው፡፡ እኔ አሁን ባለው ሁኔታ፣ በኦሮሚያ ክልል የምክር ቤት ምርጫ ልወዳደር አልችልም፡፡ ኦሮምኛ አልችልማ፡፡ ኦሮሚያ ሄጄ ክሊኒክ መክፈት አልችልም፡፡ ለምሳሌ አክሜ የማድናት አንድ ሴት ወይም ሁለት ሴት፣ እኔ ባለመኖሬ ልትሞት ትችላለች፡፡ ማን ነው የተጐዳው? ስለዚህ ይሄንን ኋላቀርና ያረጀ አስተሳሰብ ይዘን ከቀጠልን፣ ማንም የማይጠቀምበት ባዶ መሬት ብቻ ይዘን እንቀራለን፤ መጨረሻችንም አያምርም፡፡
በቅርቡ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በእጣ ሊከፋፈሉ የነበሩ ከ51ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኦሮሚያ ላይ ስለተገነቡ እንዳይከፋፈሉ በአንዳንድ ፅንፈኛ ብሔርተኞች ሲቀሰቀስ ነበር፡፡ በአንድ በኩል አዲስ አበባ የኦሮሚያን ድንበር ገፍታለች፣ በሌላ በኩል አዲስ አበባ የኛ ናት የሚል በተቃርኖ የተሞላ እንቅስቃሴም ይስተዋላል,,,,,
ይሄ ትልቅ ቀውስ ነው፡፡ ይሄ ነገር አሜሪካን አገር ቢደረግ፣ “ኮንስቲትዩሽናል ክራይስስ” ይሉታል። አንድ ነገር እርስ በእርሱ የሚቃረንና በጤናማ አዕምሮ ሊፈታ የማይችል ከሆነ፣ ለምሣሌ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የአገሪቱን ህገ መንግስት እየጣሰ በዘፈቀደ የሚሰራ ከሆነ፣ “ኮንስቲትዩሽናል ክራይስስ” ነው የሚሉት፡፡ አንቺ ያነሳሽው ጥያቄ፣ ይሄ ዓይነቱ ቀውስ ነው፡፡ ይሄን ጥያቄ ለማንሳት መጀመሪያ የአዲስ አበባ ችግር መፈታት ነበረበት፡፡ አዲስ አበባ፣ የአዲስ አበባና የመላው ኢትዮጵያ ናት ከተባለ፣ አዲስ አበባ ገፍታ ገብታለች ወይ የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡ ገፍታለች ከተባለም የአዲስ አበባ ወሰንና ድንበር በግልጽ ሊቀመጥ (ዲፋይን ሊደረግ) ይገባል ማለት ነው፡፡ ወያኔ ለራሱ አመራር እንዲያመቸው፣ ከተማዋን አጉል አጉል አድርጓታል፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያዊ ናት ካልን በኋላም ስለ ድንበር እንነጋገራለን ማለት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ድንበር ሰበታ ነው ቢባል፣ ማን ነው ያለው? ታሪክ ምን ይላል? የሚለው ሁሉ መታየት አለበት፡፡
ከዚያ ውጭ ሀይል በእጄ ገብቷል ተብሎ፣ እንደፈለጉ ህግ መጣስና ሥርዓት አልበኝነት ውስጥ መግባቱ አያዛልቅም፡፡ በድንበር ተስማምተን ዲማርኬሽን ሳናስቀምጥ “የተሰራው ብሎኬት ቤት የኦሮሚያ ምድር ላይ ነው” ብሎ አተካራ ውስጥ መግባት ህጋዊ መሰረትም የለውም፤ አግባብም አይደለም፡፡ ህዝቡ ተገፍቶ ተገፍቶ ትዕግስቱ ከተሟጠጠ የሚመልሰው እንደሌለ ከቀደመ ታሪክ መማር አለብን፡፡ በቀደም በጣም የማደንቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ በጠራው ውይይት ምን ያህል ሰው ግልብጥ ብሎ እንደወጣ ታውቂያለሽ … ያውም ሩጫ በሚል ሰበብ ብዙ መንገድ ተዘጋግቶበት፣ ብዙ ተንኮል ተደርጐበት መንገድ ላይ የቀረው ሰው መዓት ነበር፡፡
እንደዚህ አይነት ነገር ከስድስት ወር በፊት አልነበረም፡፡ በዶ/ር ዐቢይ ተስፋ አድርጐና ተደስቶ ለድጋፍ ሰልፍ የወጣው ሰው፤ ነፍሱንና አካሉን ለቦንብ ሰጥቷል፡፡ ያ ደስታና ተስፋ አመት ሳይሞላው ህዝቡ ወደ መገፋት ሲመጣ፣ ትዕግስቱ ሲያልቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ህዝብ በቃኝ ካለ ሁሉም ነገር ያበቃለታል፡፡ እኛ የአዲስ አበባ ልጆች “ያራዳ ልጅ ብሔር የለውም” ብለን ነበር፡፡ አዲስ አበባ ማለት አዲስ አበባ የሚኖር አማራውም፣ ትግሬውም፣ ኦሮሞውም፣ ጉራጌውም፣ አፋሩም ሶማሌውም፣ ጋምቤላውም፣ ጉሙዙም … ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን አንድ ሰው በአንድ ጥግ ተቀምጦ፣ በነውጥም በጉልበትም ከመጡ ይዋጣልናል የሚል ፉከራ ያሰማል፡፡ እኔ ደግሞ ለዚህ ግለሰብ የምነግረው፣ አዋቂ እንደማይቸኩል ነው፡፡ ፈሪና አላዋቂ ነው የሚቸኩለው፡፡ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ በመላው ዓለም የተበተኑ ኢትዮጵያዊያን፣ የዚህ የአዲስ አበቤነት አመለካከት ተጋሪ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጽንፈኞችና ጐጠኞች የሚያደርጉት ያልተሳካ ተግባር የትም የሚያደርሳቸው አይደለም፡፡
የፖለቲካ ተንታኞች፤ አገሪቱ ላይ 30 እና 40 ትንንሽ መንግስታት ስላሉ አገሪቱን የትኛው መንግስት እንደሚመራት አይታወቅም፤ ሁሉም ጽንፍና ጽንፍ ላይ ቆሞ የሚያደርገው የገመድ ጉተታ አገሪቱን ለተወሳሰበ ችግር ዳርጓታል ይላሉ፡፡ ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ?
እንግዲህ አገሪቱን የሚመራት አካል ወይ እኛ የማናውቀው ፎርሙላ አለው፡፡ ወይ ደግሞ ሁሉንም መቆጣጠር የማይችል መንግስት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ አገር እየመራሁ ነው የሚል መንግስት አለ፡፡ ይሄንን ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብታቀርቢ የሚሰጡሽ መልስ ግልጽ ነው፡፡ እኛ ነን የምንመራው ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ላይ ብዙ ወንጀለኞች ከትመው ማንም የሚነካቸው የለም፡፡ ዛሬ ከአዲስ አበባ ያመለጠ ወንጀለኛ መቀሌ ቢሄድ ማንም ጫፉ የሚደርስበት የለም፡፡ እንግዲህ ሁለቱ አንድ አገር ናቸው፡፡ መንግስት እነዚህን ነገሮች መቆጣጠር ካልቻለ ችግር ነው፡፡ መንግስት መቆጣጠር ስላልቻለ ነው፣ ሁሉም መንግስት ነኝ ብሎ በራሱ መንገድ ትዕዛዝ የሚያስተላልፈው፡፡
ታዲያ የዛሬ አመት የጮህንበትና ተስፋ ያደረግነው ለውጥ ወደ ቀደመ እንቅስቃሴውና ተስፋው እንዲመለስ ለማድረግ፣ ከመንግስት ብቻ ተዓምር መጠበቅ የለብንም፤ በራሳችን በህዝቡ በኩል ከፍተኛ ስራ ይጠበቃል፡፡ ቀድሞ ያልሽው ገመድ ጉተታ በበረታ ቁጥር ወይ አንድ ጐጥ ያሸንፋል፡፡ አሊያም አገሪቱ በየሚጐትታት አቅጣጫ ትበታተናለች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለውና ትዕግስተኛ ሆኖ እንጂ እርስበርስ ለመጨራረስ የሚያነሳሱ ብዙ አደገኛና ቆስቋሽ ነገሮች አሉ፡፡ እኛም እንደ “አለን” ሚዲያና “አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ” የተነሳንበት አላማ፣ ከአዲስ አበባ ወደ መላው ኢትዮጵያ እንሄዳለን ብለን ነው፡፡ አዲስ አበባ ስንል መሬቷን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቧን መንፈሷን፣ የአኗኗር ስብጥሯን፣ መቻቻሏን … ሁሉ ወደ መላው ኢትዮጵያ እንወስዳለን፡፡ በአጠቃላይ አገሪቱ ላይ ትንንሽ መንግስታት አሉ? አዎ፡፡ አገር የሚመራው መንግስት እነዚህን መቆጣጠር ያቃተው ይመስላል? ትክክል ነው፡፡ ይህ ባለበት አገርን በሰላም ማስቀጠልና ማልማት የማይሞከር በመሆኑ፣ መፍትሔው አንድ ላይ ሆነን ህገ መንግስቱን አክብረን፣ ተወያይተንና ተቻችለን መኖር ነው፡፡
ስለ “አለን” ሚዲያ እና ስለ “አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ” ንቅናቄ አመሰራረት ይንገሩኝ?
ጥሩ! ለውጡ መጣ ሲባል ከተደሰቱትና ከተገረሙት ሰዎች ግንባር ቀደሙ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ በፌስ ቡክ ገፄም ላይ ከጨለማ ወጥተን ለብርሃን ስለ መብቃታችን በአግራሞት ጽፌ ነበር፡፡ በኋላ እያደር የማያቸው ነገሮች መጥፎ እየሆኑ ሲሄዱ፣ ከጓደኞቼ ጋር ተነጋግሬ፣ ነገሮች ወደ መጥፎ እየሄዱ ነው፣ አንድ ነገር እናደርግ አልኩኝ፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ ሁሉም ሲኖር፣ እከሌ ኦሮሞ ነው፣ አማራ ሳይባባል ነው፤ ይሄንን መንፈስና ሀሳብ ለመላው ኢትዮጵያ ማዳረስ አለብን ብለን ተስማማን፡፡ ከዚያም የተለያዩ ሰዎች፣ ከተለያዩ ዓለማት ለምሳሌ ከደቡብ አፍሪካ ከጀርመን፣ ከጃፓን፣ ከአሜሪካና ከሌሎችም አገራት መለመልን፡፡ ለምሳሌ የኮሙኒኬሽን ሰው ደቡብ አፍሪካ አለን፣ ዋና የሚዲያ ዳይሬክተራችን ማሳቹሴትስ ይገኛል፣ በኮሎራዶ እንደ ትሬዠሪ የምትሰራ የተከበረች ትልቅ ሴት አለች፡፡ እኔ ሂዩስተን ሆኜ፣ ሁሉንም እመራለሁ አስተባብራለሁ፡፡
ይህንን ካዋቀርን በኋላ የመጀመሪያ ስራችን ንቅናቄ ውስጥ መግባትና ህዝቡን ማነቃቃት ነበር። ይህንንም በሲቪክ ማህበርነት ነበር እንስራው የተባባልነው፡፡ ሆኖም በየጊዜው በምናደርገው ውይይት ድምፃችን እንዲሰማና ሁሉንም በመድረስ አላማችንን ማሳካት እንድንችል የሚዲያ ሥራ ውስጥ መግባት አለብን አልንና “አለን” የተሰኘ የኦንላይን ሚዲያ ሥራ ውስጥ ገባን፡፡ “አለን” ሚዲያ የንቅናቄው አካል ነው፡፡ በ“አለን” ሚዲያ አማካኝነት በአራት ኪሎ መሬታቸውን ተነጥቀው ሜዳ ላይ ስለወደቁት ዜጐች፣ በቡራዩ ስለደረሰው መፈናቀልና ሞት እንዲሁም በለገጣፎ ስለተከሰተው ችግር በመዘገብ ጉዳዩን ለአለም ማጋለጥ ችለናል፡፡ አዲስ አበባም ቢሮ ከፈትን፤ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሾምን፤ የሚዲያ ዳይሬክተር ቀጠርን፤ አስፈላጊውን መስፈርትና ቢሮ አሟልተን ንግድ ፈቃድ አውጥተናል፡፡ የሚዲያውን ፈቃድ ለማግኘት ከብድሮካስት ባለስልጣን መልስ እየጠበቅን ነው፡፡
የንቅናቄው አባል የሚሆኑ ሰዎችን ለመሰብሰብ በኦንላይን የአባልነት መስፈርትና ፎርም ለቀቅን፡፡ በዚያ መስፈርት መሰረት የንቅናቄው አካል ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑና የተመዘገቡ ወደ 13ሺህ 700 ያህል አባላት አገኘን፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሩብ ያህሉ ራሳቸውን ለአስተባባሪነት በበጐ ፈቃደኝነት መድበው ገብተዋል፡፡ በአሜሪካም 513 ወደተባለው በጐ አድራጐት ድርጅትነት ለመግባትና ለመንቀሳቀስ በሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ አሁን በቅርብ ወራት ውስጥ በሳተላይት ቴሌቪዥንነት ለመምጣትም ከዳላስ የሳተላይት ኩባንያ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በዋጋ ተስማምተናል፡፡ በቅርቡ የ24 ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ያለው ቅርንጫፍ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ዘላቂ ሥራችሁ ምንድነው የሚሆነው?
ዋና ሥራችን አገር ቤት እንደመሆኑ፣ በሲቪክ ማህበሩ በኩል እንቅስቃሴ ለማድረግ ከየቀበሌው 30 ሰው እየመለመልን ሲሆን በምርጫው ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና በተለይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ የሚፈታ ከንቲባ እንዲመረጥና ሶስቱን መጀመሪያ የተነሳንባቸውን አላማዎች ያሟላ እንዲሆን፣ በንቅናቄያችንም በሚዲያችንም አጥብቀን እንሰራለን፡፡ በአሜሪካ ሚዲያ አምስተኛው መንግስት ነው፡፡ በአገራችን አራተኛ መንግስት ነው ብለሻል፡፡ ያው አራተኛ መንግስት ሆነን እንንቀሳቀሳለን ማለት ነው፡፡ ስንቀሳቀስ ደግሞ ያለ ፍርሃት በሙሉ ወኔና በራስ መተማመን፣ ባለስልጣናትን በደንብ እየጠየቅን መረጃ ለህዝብ እናደርሳለን የሚል ጽኑ አቋም አለን፡፡
አሁን አገሪቱ ላይ ባለው ችግርና ግጭት ምክንያት ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የጌዲኦ ተወላጆች ተፈናቅለው በረሃብ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ትኩረት አልሰጠውም በሚል እየተወቀሰ ነው፡፡ “አለን” ሚዲያ በዚህ ዙሪያ ምን ሰርቷል?
እኛ በሚዲያችን መፃፍ ብቻ ሳይሆን በምስልና በቪዲዮ አስደግፈን ዘግበናል፤ ቀጥታ መልዕክታችንንም ለመንግስት አስተላልፈናል፡፡ መንግስት ትኩረት አልሰጠውም የሚለው ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን መንግስት የህዝብን በደልና ጥያቄ ሸፍኖ ማለፍ አይችልም፡፡ ጃንሆይ 60ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን በቅንጦት ሲያከብሩ፣ ወሎና አካባቢው ላይ ከፍተኛ ድርቅና ረሃብ ነበር፡፡ ያ ጉዳይ ያንገሸገሻቸው ወንድማማቾቹ መንግስቱ ነዋይና ግርማሜ ነዋይ መፈንቅለ መንግስት ሞክረው ነበር። ከዚያም በኋላ የ66ቱ አብዮትም የፈነዳው፣ የህዝብ ጥያቄና ብሶት ምላሽ ባለማግኘቱና ችላ በመባሉ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል። በነገራችን ላይ አሁን እኛም ከንቅናቄው አባላትና ከ “አለን” ሚዲያ ሰዎች ጋር በውስጥ እየመከርንበት ያለ ጉዳይ አለ፡፡ ዓለምአቀፍ የህግ ባለሙያዎችን አጋሮቻችን አድርገን፣ ጉዳዩን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እስከማቅረብ እያሰብን ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ወገን ችግርና ሞት ይሄ መንግስት መጠየቅ አለበት፡፡ አንድ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የህዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ እንጀራ ማቅረብ ብቻ አይደለም። አሁን ደሞ እንጀራውም ሆነ ሰላሙ የለም፡፡ ሰው በጌዲኦ፣ በቡራዩ፣ በለገጣፎ ተጐዳ ማለት መንግስት ሥራውን እየሰራ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስትን ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ እኛም መንግስትን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲጠየቅ እንሰራለን፡፡
አሁን በጌዲኦና በሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ለረሃብ የመጋለጥ ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል?
በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የተለያዩ አገራትን ኢንዴክስ አውጥቶ ተመልክቼው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ 0.34 የሚባል ወይም ከ189 አገራት 173ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ መንግስታቸው አገራዊ አገልግሎት (National Service) በማይሰጥበት ደረጃ ከደረሱት አገራት ተርታ ናት፡፡ ለምሳሌ የመጨረሻዋ አገር ኒጀር ናት፤ 20 ሚ. ህዝብ ነው ያላት፤ እኛ ወደ ኒጀር ተጠግተናል፡፡ በጌዲኦና በሌላ ቦታ ተፈናቅለው ያሉትማ ያው ወደ ሞት የተጠጉ ናቸው፡፡ ወደ አፋቸው የሚያስገቡት ነገርም የለም፡፡ ኢትዮጵያ 3ኛዋ ትልቅ የመንግስታቱ ድርጅት መቀመጫ ሆና እያለ፣ ህዝቦቿ እንደ ኒጀር ምግብ ፍለጋ ገንዳ አካባቢ የሚዞሩባት አገር ናት፤ አይደለም የWHOን ትርጓሜ ልታሟላ፡፡ ይሄንን ይዞ መኮፈስና ነገሮችን መደበቅ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም፡፡ አሁን ያለነው ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ ነው፡፡ እንዴት ነው በዚህ ዘመን አንድ ኢትዮጵያዊ ቢያንስ በቀን ሶስት ጊዜ ዳቦ እንኳን መብላት የሚሳነው፤ ይሄ ሊያሳፍረንና ሊያሳዝነን የሚገባ ነው፡፡ ለዚህ ሁላችንም መታገል አለብን፤ መፍራት አያስፈልግም፡፡ ሰው አንድ ህይወት ነው ያለው፤ ያንኑ አንዱን ህይወት ለሰላም ለብልጽግና፣ ለእኩልነት አውሎ ማለፍን የመሰለ ክብር የለም፡፡
እንግዲህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብዣ የአገሪቱን የጤና ክፍተት ለማየትና ማሻሻል ለማድረግ እንዲያግዙ ተጋብዘው ነው የመጡት፡፡ የአገሪቱ የጤና ዘርፍ ችግር ወይም ክፍተት ምንድንነው?
እንዳልሽው ግብዣው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ነው የደረሰኝ፤ የመጣሁትም ኢትዮጵያን በተለይ በጤናው ዘርፍ የበኩሌን ባደርግ ህዝቡ ይጠቅማል በሚል ነው፡፡ አሜሪካ የማስተምረው በጤናው ዘርፍ ስለሆነ በዚህ አገርና በሌላው አለም ያለው የጤና አገልግሎት ሰፊ ልዩነት ሁሌም ያሳስበኝ ነበር። ነገር ግን አማራጭ ስላልነበረኝና እድሉን ስላላገኘሁ ለረጅም አመታት እዛው ነጮችንና ጥቁሮችን ሳስተምር ነው የቆየሁት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጤናውም ዘርፍ ብዙ ችግር እንዳለ አውቃለሁ። እንግዲህ በየሆስፒታሎቹ ዞረን ያሉትን ችግሮች ፈትሸን ወደ አክሽን ፕላን እንገባለን፡፡ ገና ጉብኝቱና ፍተሻው እስከ አርብ ይቀጥላል፡፡ በእኔ አቅምና እገዛ አንዲት እናት በሰላም መውለድ ከቻለች፣ ህዝቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት ካገኘ፣ ይሄ ቀላል ስላልሆነ ግብዣውን ተቀብያለሁ፡፡ ዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአይቲ እና ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተናል። ከሰዓት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን እንጐበኛለን፡፡ እንግዲህ ፍተሻውና ጉብኝቱ ሲያልቅ አጠቃላይ ግምገማ ባደርግ የሚሻል ይመስለኛል። ነገር ግን ያየሁትን ክፍተትና ችግር ለማድበስበስ አይዳዳኝም፡፡ ፍርሃት የሚባል ነገር የለም፤ ምክንያቱም የአገሬ እናቶች በሰላም የሚወልዱበት፣ የጤና ባለሙያዎች ብቁና ተወዳዳሪ የሚሆኑበት፣ ሰው በቀን ሶስት ጊዜ የሚበላበት … ኢትዮጵያዊነታችን ተከብሮ ከዘርና ከክፍፍል ወጥተን እንደ ሰው ተቆጥረን በእኩልነት የምንታይባት አገር ሆና ማየት እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ የበኩሌን አደርጋለሁ፤ ስልጣን አልፈልግም፤ ፖለቲከኛም አይደለሁም፡፡ በ“አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ንቅናቄ” የሚሳተፉትም አባላት ሆነ የ“አለን” ጋዜጠኞች ስልጣን አይፈልጉም፤ ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ፤ በአገሬ የህዝብ ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ከተመለሰ፣ “አለን” የመዝናኛ ሚዲያ ይሆናል፤ ንቅናቄውም ይቆማል፡፡

Read 6556 times