Thursday, 21 March 2019 00:00

የሞባይል ቫይረስ ጥቃቶች በእጥፍ ጨምረዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በሞባይል ስልኮች አማካይነት በሚላኩ ቫይረሶች የሚደረጉ ጥቃቶች ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት በእጥፍ መጨመሩንና በአመቱ 100 ሺህ ያህል ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመልክቷል።
በሞባይል ስልኮች አማካይነት ቫይረሶችን በመላክ የተጠቃሚዎችን የተለያዩ የግል ሚስጥራዊ መረጃዎች የመዝረፍ ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱን በጥናት ማረጋገጡን ካስፐርስኪ የተባለው ተቋም ሰሞኑን ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በተለይ በሞባይል አማካይነት የወሲብ ድረገጾችን የሚጠቀሙ ሰዎች ለመሰል ጥቃቶች የመጋለጥ እድላቸው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ጥቃቱን የሚሰነዝሩት ቡድኖች የግለሰቦቹን የባንክ ሚስጥሮች ጨምሮ ቁልፍ መረጃዎችን በመመንተፍ የማጭበርበር ድርጊቶችን እንደሚፈጽሙ አመልክቷል፡፡
መሰል የቫይረስ ጥቃት ሰለባ የሆኑ የሞባይል ተጠቃሚዎች የኢሜይል አድራሻዎቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ አካውንቶቻቸውን ከፍተው መግባት ስለማይችሉ፣ ለጥቃቱ አድራሾች እስከ 150 ዶላር ያህል ለመክፈል እንደሚገደዱም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ግለሰቦች ለመሰል ጥቃቶች ላለመጋለጥ በሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ያለው ሪፖርቱ፣ ትክክለኛ ያልሆኑ ድረገጾችን እንዳይከፍቱ፣ የይለፍ ቃሎችን ጨምሮ የግል መረጃዎቻቸውን ሲጠየቁ እንዳይሰጡ፣ አዳዲስ የቫይረስ መከላከያ ሶፍትዌሮችን እንዲጠቀሙ፣ እርግጠኛ ያልሆኑባቸውን ፋይሎች ዳውንሎድ እንዳያደርጉና ተመሳሳይ የይለፍ ቃሎችን ለተለያዩ አካውንቶቻቸው እንዳይጠቀሙ መክሯል፡፡

Read 3629 times