Monday, 18 March 2019 12:34

የጡንቻ ምንቸት ውጣ፣ የአእምሮ ምንቸት ግባ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ዘንድሮ መቼም እነኚህ ዱባይ፣ ቻይና ምናምን የሚባሉ ቦታዎች የማይሄድ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ በቀደም አንድ ወዳጃችን “እንዴት እስከዛሬ ቻይና አልሄድክም?” የሚል ወዳጅ ቢጤ ሲጨቀጭቀው ነበር፡፡
“በነገራችን ላይ እስካሁን የት፣ የት ሄደሀል?”
“ማለት…”
“ማለትማ ለጉብኝት…”
“እዚህ በታች በኩል እስከ ሦስት ቁጥር ማዞሪያ፣ ወደ ላይ ደግሞ እስከ ሱሉልታ ፍተሻው ድረስ…”
“እውነቴን ነው የምጠይቅህ፣ እስካሁን የት፣ የት አገር ሄደሀል?”
“አንድም አገር አልሄድኩም…”
“ምን! የትም አልሄድክም?”
“የትም አልሄድኩም…”
“ቻይና እንኳን አልሄድኩም እንዳትለኝ!”
እንግዲህ ቻይና ማንም ሊሄድባት የሚችልባት መሆኗ ነው፡፡ እንዲህ የሚላችሁ ሰው እኮ አይደለም ቻይና ሊሄድ የት እንዳለችም ላያውቅ ይችላል፡፡ ግን ምን ይደረግ…የጭምብል ዘመን ሆነ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እውነት ግን ሁሉም ጭምብል ያጠለቀባት፣ ሁሉም ጉልበተኛ የሆነባት አገር ትሁን! የሁላችንም ገጽታ የተፈጥሮ ጭምብል ሆነ እኮ! እውነተኛ ‘ፖለቲከኛ’፣ እውነተኛ ‘የኳስ ደጋፊ’፣ እውነተኛ ‘የሚዲያ ሰው’፣ እውነተኛ የኃይማኖት አባት ማግኘት እየቸገረን እኮ ነው። የምር ግን… እንዴት ነው እንዲህ ቀንድና ጭራው የማይያዝ፣ ፊቱና ኋላው የማይለይ፣ ጥቁሩና ነጩ የሚያደናግር ውስብስብ ውስጥ ልንገባ የቻልነው! ሳናውቀው በሆነ ምስጢራዊ ዘዴ የዲ.ኤን.ኤ. ‘ጥልቅ ተሀድሶ’ ምናምን ነገር ተካሂዶብናል እንዴ!
የምር ግን…የምናየውና የሚሆነው አልገጥም እያለን ተቸግረናል፡፡ ከእያንዳንዱ ፈገግታ ጀርባ፣ ከእያንዳንዱ ቃል ጀርባ የተደበቁ ነገሮች ብቅ እያሉ ተቸግረናል፡፡ ለምሳሌ…ዘንድሮ የኳስ ደጋፊ ማለት… አለ አይደል… የኳስ ደጋፊ ብቻ አይደለም፡፡ መሀል ሜዳ ለተደረገ ጥፋት… “ለምንድነው ፍጹም ቅጣት ምት የማይሰጠው!” የሚል አይነት ደጋፊ የበዛበት ጊዜ ነው፡፡ እናላችሁ…“እከሌ መደገፍ ትችላለህ፣ እከሌ መደገፍ አትችልም፣” ተብሎ የብቃት ማረጋገጫ ምናምን የሚባል ነገር አይሰጥ ነገር ሆኖ ግራ ተጋብተናል፡፡
ስለ ኳስ ምንም የማናውቅና…ስታዲየም በዓመት ሦስት ጊዜ እንኳን ገብተን የማናውቅ… “እንዲህ ሲረግጠው ተኝቶ ከመንከባለል ተነስቶ አናቱን አይፈልጠውም እንዴ!” ምናምን አይነት ልንል ምንም የማይቀረን፣ ራሳችንን ‘የኳስ ደጋፊ’ የምንል መአት ነን፡፡ እንደግፈዋለን የምንለውን ቡድን ከስፖርት ስብስብነት ይልቅ… “መሬት ሰርስሮ የገባ ጠላት ሚስትህንና እርስትህን ሊነጥቅህ ነውና ጨርቄን ማቄን ሳትል ዝመት ተብለሀል…” አይነት ለማለት የሚዳዳን፣ የሥራ ውጤታችንን በድንጋይ መወራወር የምናሳይ በዝተናል፡፡ እናማ…ስንፋቅ ሌላ የምንሆን የኳስ ደጋፊዎች በዝተናል!
ሁለቱ ሰዎች ይጣሉና አንዱ ሌላውን ይፈነክተዋል፡፡
“አንተ ምን ማለትህ ነው፣ ምስኪኑን ዱላውን ጭንቅላቱ ላይ ሰበርከው?”
“አደጋ ነው፡፡”
“እንዴት ነው አደጋ የሚሆነው! ሆነ ብለህ ነው አይደል እንዴ የመታኸው?”
“ማለት…ዱላውን መስበሬ አደጋ ነው ማለት ፈልጌ ነው፡፡”
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታ አይደል…የሆነ ችግር አለላችሁ፣ የጠበኝነት ነገር፡፡ ብዙ ቦታዎች በሆነ ምክንያት የሚፈጠሩ የግለሰቦች አለመግባባቶች “በጡንቻ ብቻ ይፈቱ…” የሚል የማናውቀው ሰርኩላር ተላልፏል እንዴ! ቀላል የመኪኖች ግጭት አንድ ባታሊዮን ጦር ወረራ የምናስመስለው ለምን እንደሆነ አይገርማችሁም! ስሙኝማ…በፊት እኮ እንዲህ በትንሽ ትልቁ በየስፍራው ግርግር ስናይ “ተዉት ጉርምስናው እስኪጎድልለት ነው፣” ምናምን እንል ነበር፡፡ አሁን ጉርምስናውን በብዙ አስርት ዓመታት ያለፉት ሁሉ ቀድመው የሸሚዝ እጀታ ጠቅላዮች ሆነዋል፡፡
በቅርቡ በአንድ የከተማው ክፍል የመኪኖች ግጭት ይፈጠራል፡፡ ሁለቱም አሽከርካሪዎች በእድሜ በሰል ያሉ ነበሩ፡፡ (“በሰል ያሉ…” የሚለው ‘ዲፕሎማሲያዊ’ አነጋገር እንደሆነ ልብ ይባልልንማ!) እናማ… “ካልተቧቀስን” ብለው እነሱን ለመገላገል የነበረው ትርምስ የሚገርም ብቻ ሳይሆን “ምን እየሆንን ነው?” የሚያሰኝ ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር እንኳን እድሜ የሚባለው ነገር ትንሽ የሚያስተምረው ነገር መኖር የለበትም እንዴ!
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ወጣቱ እንደ ምሳሌነት የሚያያቸው ሰዎች በቁጥር እያነሱ ሲሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ “ወጣቱ ተበላሸ፣ ተበላሸ…” ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ “ማንን እያየ ይደግ!” ማለትም አሪፍ ነው፡፡ አገር እየታመሰ ያለው እኮ በችኩልና ጭፍን ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ከዘመን ጋር አልስተካከል ባሉ የእድሜ ባለጸጎችም ነው!
እናላችሁ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ አገር ሁሉም ነገር የሚፈታው በጡንቻ ብቻ ነው አይነት ነገር እየበዛ አይመስላችሁም! አሀ…ደካሞች ወዴት እንሂድ! አሀ…ሁሉም በየመስኩ “ግነን በሉኝ፣” ባይ ሆኗላ!
“ሀሎ!”
“ሀሎ እመቤቴ፣”
“እቤት ነሽ?” (እንዴት ነው ነገሩ… ስልኩን ያነሳችው በመንፈስ ነው!)
“አዎ፣ እመቤቴ…”
“ምሳ ሠርተሻል?”
“እየሠራሁ ነው…”
“ስሚ ደግሞ ምግቡ ላይ ጨው ሞጅረሽበት በውሀ ጥም እንዳትጨርሺን…”
የምር ግን…እመቤቴ በጠዋቱ ሥራ አቋርጠው በመንግሥት ስልክ የደወሉት የጨው ነገር አሳስቧቸው ነው! እሱ ብቻ አይደለም…ጉልበታቸውን ማሳየት አለባቸዋ! የቅርብ አለቃቸው እሳቸው ላይ “ይሄን ሥራ እስከ ነገ ጨርሰሽ እንድትሰጪኝ…” ብሎ ‘ጉልበቱን’ ሲያሳያቸው፣ እሳቸው ደግሞ ‘በጨው መንገድ’ መሄድ አለባቸዋ!
“ስሚ ደግሞ ቁንዶ በርበሬውን ዘርግፊውና አንቺን አያድርገኝ!” (ይኸዋ! “አንቺን አያድርገኝ…” የምትለዋ ነገር እኮ የጉልበተኝነት ሻምፒየንስ ሊግ ምናምን ነገር ነች!)
እግረ መንገድ…ስለ ጉልበተኝነት ካወራን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
ሰውየው ጂም ገብቶ ቦክስና ካራቴ ምናምን ይለማመዳል፡፡ አንድ ወዳጁ ያየዋል፡፡
“ብለህ ብለህ ቦክስና ካራቴ መለማመድ ጀመርክ?”
“አዎ…”
“በዚህ እድሜህ ምን ልትሆን ነው?”
“እባክህ ከሆነች ጋር ግንኙነት ጀምሬ…”
“እና…”
“እናማ… ባሏ ያገኘኝ እንደሆነ መከላከያ ነው…” አሉ አሉ፡፡
ይሄ ሁሉ ጂም ከሞላው ሰው ስንቱ ነው ‘ባል ሽሽት’ ነጭ ላቡን ሲያፈስ የሚውለው! አሀ…ልንጠይቅ ይገባላ! የሰው ሰው መንትፎ ጡንቻ ማዳበር አለ እንዴ! የጉልበተኞች ቁጥር የሚቀንስበትን ጊዜ ያፍጥልንማ! “ለጣይም ፈንጋይ አለው፣” የሚባል ነገር አለ እኮ!
ትንሹ ልጅ አባቱን እያፋጠጠው ነው፡፡
“አባዬ፣ በሬ አትፈራም?”
“አልፈራም፡፡”
“ጡንቸኛ የሆነ ሰው ቢመጣ አትፈራም?”
“አልፈራም?”
“እብድ ቢመጣ አትፈራም?”
“አልፈራም፡፡”
“አባዬ፤ ከእማዬ ሌላ የምትፈራው ነገር የለም ማለት ነው!” አለውና አረፈው፡፡
ጡንቻ ተገፍቶ፣ አእምሮ ሙሉ ለሙሉ ስፍራውን የሚሞላበትን ዘመን ያፍጥልንማ! የጡንቻ ምንቸት ውጣ፣ የአእምሮ ምንቸት ግባ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3290 times