Sunday, 17 March 2019 00:00

ይድረስ ለ23ቱ የአዲስ አበባ የተወካዮች ምክር ቤት ተመራጮች፤

Written by  በሙሼ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)


                                           ያለ ውግንና ውክልና ትርጉም የለውም!!
                                               
        “የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት....  ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገ መንግስት ጉባኤ ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል፡፡”
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት መግቢያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ከተሞች የፖለቲካውም ሆነ የኢኮኖሚው እንዲሁም የማህበራዊ መስተጋብሩ ቁልፍ መዘውር ናቸው። ከተሞች በአጠቃላይ የሃገራዊ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው እንዲሁም የእውቀቱ ምንጭ ናቸው፡፡ ሀገርን ለመገንባትም ሆነ ለማፍረስ ከተማዎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከዚህ ጽንሰ ሃሳብ በመነሳትም የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደ ክልል ከተሞች፣ ዞኖች ወይም ወረዳዎችና ቀበሌዎች በአንድ ወገን ፍላጎትና ምኞት ላይ ብቻ ተመስርተን መደምደሚያ ላይ የምንደርስበት ጉዳይ አይደለም፡፡
አዲስ አበባ ከነዋሪዎቿ ቁጥርና ስብጥሯ አኳያ ክፍተቶች ቢኖሯትም እልፍ አእላፍ ኢትየጵያውያኖች ከየክልሎቻቸው፣ በግል ተነሳሽነታቸው እየፈለሱ፣ ራሳቸውን በራሳቸው የወከሉባት፣ ሃብት ያፈሩባት፣ ሃብት ለማፍራት የሚታገሉባት በጥረታቸው፣ በላባቸው፣ በጉልበታቸው፣ በእውቀታቸውና በሃብታቸው የገነቧት ዋና ከተማችን ናት፡፡ አዲስ አበባ ካላት ውስብስብ ባህርይ ስንነሳ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አጀንዳ ጀምሮ ውስብስብ ፍላጎቶች፣ እምነቶች፣ ማንነቶችና የማንነት መገለጫዎች የሚንጸባረቁባት ከተማ ነች፡፡
በአንድ በኩል ይህ እውነታ የገሃዱ ዓለም ነጸብራቅ ሆኖ እያለና የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትም ከዚህ ባህርይዋ በመነጨ ለአዲስ አበባ ከበርካታ ክልሎች በተለየ፣በተወካዮች ምክር ቤት ውክል እንዲኖራት ሰፍሮ፣ ለክቶና ቆጥሮ ሰጥቷታል፡፡ አዲስ አበባ በሕገ መንግስቱ የተሰጣትን መብትና ግዴታዎች ወደ ጎን በማድረግ ሕጋዊ መሰረቷንና ማህበራዊ መስተጋብሯን ስለ ለውጥ በሚዘመርበት በዚህ ጊዜ ላይ መናድ (Disfranchise) ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ተገደናል፡፡ ይህ አካሄድ በአንድ በኩል የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም አዲስ አበባን በባለቤትነት ስም የመጠቅለልና የአንድ ክልል ብቸኛ መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎት የሚንጸባረቅበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ መንግስቱ ውስጥ የተቀመጠውን ያልተብራራና ግልጽ ያልሆነ ልዩ ተጠቃሚነት በመንተራስ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን የዜግነት መብት፣ በሌላ ተቀጥላና ተጨማሪ መብቶች ለመቀዳጀት በማሰብ ውስጥ የሚዋዥቅ አጀንዳ ነው፡፡
ሌላው መከራከርያ አዲስ አበባን በባለቤትነት ለመጠቅለል በሚመስል መልኩና ጊዜው ፈቅዷል ከሚለው መነሻ ባሻገር አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለምትገኝ ንብረትነቷ የኛ ነው የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ በታሪክና በዘመን አጋጣሚ በከተማው ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ የኦሮሚያ ተወላጆችን መነሻ በማድረግ ላይ ያጠነጠነ ነው። ወጣም ወረደ መሰረታዊ ሃሳቡ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አጼዎቹ ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያን በተለያየ ቅርጽና ይዞታ ስር ሆነው ለመግዛት የቻሉት አዲስ አበባን በበላይነት መቆጣጠር በመቻላቸው ስለሆነ ዛሬም የአዲስ አበባን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በመቆጣጠር በቀጣይ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚል ዝንባሌዎች ውጤት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በእርግጥ በአዲስ አበባ ውስጥ በበቂ ቁጥር አልተወከልንም ወይም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስለሌለ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ አለበት የሚል እኩልነትን ማዕከል አደርጎ የሚነሳ መከራከርያ ርዕስ አለ፡፡ በዚህ አጀንዳ ዙርያ ስለ አፈጻጸሙ ከመነጋገር ውጭ ሌላ የማነሳው ሃሳብ የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ኃይማኖቶች ለዘመናት በቆየ የታሪክ ሂደት የተፈጠረ የመወከል ልዩነት እንዳላቸው ሁሉ ብሔሮችም በተመጣጣኝ ደረጃ የመወከል ጉድለት ሰለባ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኦሮሞው ትግራዋይ ወይም ቀሪዎቹ ሰማንያ ብሔርና ብሔረሰቦች ተመጣጣኝ ውክልና እንደሌላቸው አጠቃላይ ስምምነት አለ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ዛሬ ላይ ብድግ ብሎ እኩልነቱን ለማጣጣም የሚወሰደው እርምጃ ለዘመናት የቆየውን የተዛባ የውክልና ታሪክ በአንድ ለሊት የሚቀለብስና ታሪክን እንደገና በጉልበት የሚጽፍ ሊሆን አይገባም፡፡ ካለፈው ስህተት ለመማርና ዘለቄታ ያለው ስራ ለመስራት ከተፈለገ፣ ሌሎችን ስጋት ውስጥ የሚከት፣ ዛሬ ጊዜው የኔ ነው ከሚል የተዛባ አመለካከትና ስነልቦና መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም ነገር በሂደት ለማረም ሁሉም ዜጎች ተገቢውንና ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው፣ በጥንቃቄ በሁሉም ንቁ ተሳትፎ የሚሰራ መሆን አለበት፡፡   
አዲስ አበባ ማንም ሊረዳው እንደሚችለው መናገሻ በሚባል የዛሬን አንድ ቀበሌ በማታክል የእንጦጦ ተራራ ላይ ተመስርታለች፡፡ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ማንንም የማታጓጓ፣ ብርድና ቁር የቆፈነናትና የአውሬ መፈንጫ የነበረች፣ነዋሪዎቿ በሺዎች የማይቆጠሩ እጅግ ደቃቃ መንደር ነበረች። ዛሬ የምናውቃትና ስፋቷ 527 ሜትር ካሬ የምትሸፍነው አዲስ አበባ በወቅቱ ጉለሌ፣ ፊንፊኔ፣ በረራ፣ ወጂ፣ መናገሻ፣ አዶጥና በሚሉ የተለያዩ የመንደር መጠርያዎች የምትታወቅ፣ ነዋሪዎቿ የተለያየ ስብጥር ያቀፈች የመንደሮች ስብስብ ነበረች፡፡ ያኔም ቢሆን በርካታ ብሔሮችና ጎሳዎች የሚኖሩባት መንደር ነበረች፡፡ አዲስ አበባ የሚለው ስሟም ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት የጀመረውና ከተንጠለጠለችበት እንጦጦ መውረድ የጀመረችው ዓለምን ካስደመመው የአድዋ ድል በኋላ የአጼ ሚኒሊክ መንግስትን ለመወዳጀት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት መስጠት ሲጀምር ነው፡፡ በወቅቱ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ የራሻና የሌሎችም ሃገራት ልዑካን መጉረፍ፣ አዲስ አበባ በርካታ ፍላጎቶች እንዲኖራት አደርጓል፡፡ አዲስ አበባ ከዜጎቿ ጥቅም ይልቅ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረትን ማዕከል አድርጋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብርድን ሽሽትና የማገዶ እንጨት ፍለጋን ተከትሎ  በተፈጠረው መሳሳብ እየሰፋች በመሄድ ዋና ከተማ ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ በጣም ቀረብ አድርገን ወደ ደርግ ዘመን ስናመጣት ደግሞ በወቅቱም እንደዚሁ የምታጓጓ ከተማ አልነበረችም፡፡ አዲስ አበባ የገጠር አስቸጋሪ ሕይወት ግፊትና የተሻለ የኑሮ አጋጣሚ ስበትና ውጤት ነች፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከሚፈልሱት ዜጎች መካከል ቁጥራቸው በርከት የሚሉት ሕይወት በእጅጉ የከፋባቸውና የተወለዱበት ቀዬ ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚያስችል እድል የነፈጋቻቸው ነበሩ፡፡ እነዚህ ዜጎች ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው የከተማዋን ፈታኝ ኑሮ ተቋቁመው፣ በወቅቱ የነበረውን ስርዓት ታከው፣ሃብት የፈጠሩትን ጥቂት ሃብታሞች በማገልገል ሕይወትን ለማስቀጠል የቆረጡ ወጣቶች ስለነበሩ የከተማዋም እድገት አመርቂ አልነበረም፡፡ ሌላው ይቅርና በቅርብ ርቀት አዲስ አበባን ዙርያዋን የከበቧትና በውስጧ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆችም ቢሆኑ በአንጻራዊነት ከተደላደለው የግብርና ህይወታቸው ተፈናቅለው እንዲቀላቀሏት የምትጋብዝ አልነበረችም፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ከጥቅሟ ይልቅ መከራዋ የበረታ፣ የድሆች ከተማ ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍልሰት ከነበረም በስፋት የነበረው ወደ አዲስ አበባ ሳይሆን የገበያ ሰብሎች ወደሚበቅልባቸው ከተሞችና የሰብል ምርት በስፋት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ነበር፡፡
አዲስ አበባ ከማኅጸኗ ነዳጅ ፈልቆ ወይንም የተፈጥሮ ሃብት ተገኝቶ የበለጸገች ከተማ አይደለችም፡፡ አዲስ አበባ አቅም ያለው በእውቀቱና በሃብቱ ያልቻለው ደግሞ በጉልበቱና በሙያው የገነባት የሁሉም ዜጋ መናኸርያ ነች፡፡ አዲስ አበባ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ስታልፍ የአንድ ብሔር ወይም የአንድ ክልል መገለጫነት ይዛ የዘለቀችም አይደለችም፡፡ አዲስ አበባ በ150 ዓመት ታሪኳ ውስጥ የራሷን እሴቶች የፈጠረች ከተማ ነች። እሴቶቿም የኦሮሞ፣ የአማራ ወይም የትግራዋይ አሊያም የቀሪዎቹ ከ80 በላይ የሚቆጠሩት ብሔርና ብሔረሰቦችም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከሁሉም ተቀይጦና ተዳቅሎ የተወለደ፣ ሁሉንም ያቀፈና  ያጣመረ አዲስ አበባዊ ባህል፣ የቋንቋ ዘይቤ፣ ስነልቦና፣ የአኗኗር ዘዴ፣ ማህበራዊ መስተጋብር ፈጥራለች። አዲስ አበባ የተቀበለችውን ሁላ ያስተናገደችው በቀላሉ እራሱን እንዲሆን ፈቅዳ አልነበረም። ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ማንነቱን፣ ማህበራዊ መስተጋብሩን እያዋሃደች፣ እያጣጣመች፣ እየዋጠችና እየሰለቀጠች ቅድመ ሁኔታ እየፈጠረችና የራሷ ልዩ ገጽታ በማላበስ ነው፡፡ አዲስ አበባ፤ በአዲስ አበቤነት ቅድመ አያቶቻቸውን ለመጥራት የደረሱ ነዋሪዎቿን ቀርቶ ራቅ ካለ ዘመን ጀምሮ የተቀላቀሏትን ግሪኮች፣ አረቦች፣ አርመኖችና ባንያኖች አፍሪካዊያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የተቀላቀሏትን ቻያናውያን፣ ህንዳውያንና አውሮፓዊያንን አንዲሁም ሌሎችን በማጣጣም ከፈጠረችው አዲስ ስነልቦናና ማህበራዊ መስተጋብር ጋር ያዋሃደች የሁላችንም የተስፋ መዲና (Land of opportunity) ነች፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸው ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች በሂደት የተፈጠሩና በሰነድ ያልሰፈሩ፣ በጋራ መግባባት የተደረሰባቸው እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች ከእምነት ባሻገር ምን ሕጋዊ መሰረት አላቸው፡፡ የትኛውም ክልል ቅጥያ ላድርግሽ ሳይላት አዲስ አባባ  የራሷ ህልውና አስጠብቃ ለመኖር ምን ሕጋዊ መሰረት አላት፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49  ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ ንዑስ አንቀጽ 5 ድረስ ስለ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር (Self Administration) በማያሻማ መልክ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ንዑስ አንቀጽ 3 የአዲስ አበባ ከተማ ተጠሪነት ለኦሮሞ፣ ለአማራ ለደቡብ ወይም ለሌላ ክልል ሳይሆን በተለይ ለፌደራል መንግስት መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፊደራሉ መንግስት ውስጥ እንደ ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ (በ23 ድምጽ) እንደሚወከሉ በዚሁ አንቀጽ በተለይ በንዑስ አንቀጽ 4 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ሕገ መንግስቱ ከላይ የተዘረዘሩትን ልዩ ባህሪያት በማጤን አዲስ አበባ ከ11ዱ ክልሎች (ድሬደዋን ጨምሮ) ከግማሽ በላይ ሊባል በሚችል ደረጃ የላቀ፣ የተናጠልና የድምር ውክልና እንዲኖራት አድርጓል፡፡

ክልል    የተወከሉበት ወንበር
ሱማሌ    24
አዲስ አበባ    23
ቤንሻንጉል ጉሙዝ    9
አፋር    8
ጋምቤላ    3
ሐረሪ    2
ድሬዳዋ    2
ድምር    24


ከላይ በሰንጠረዡ እንደምንመለከተው አዲስ አበባ ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት ክልሎች በቁጥር የሚልቅ የተናጠል ውክልና 23 መቀመጫ አላት፡፡ አዲስ አበባ ከሱማሌ ክልል በ1 ደምጽ ብቻ የምታንስ ሲሆን የአምስቱ ክልሎች አጠቃላይ ውክልና ድምር 24 መቀመጫ በመሆኑ ምክንያት ከአዲስ አበባ ጋር ሲነጻፀር የከተማዋ ውክልና ከአምስቱ ክልሎች መቀመጫ በአንድ ድምጽ ብቻ ያንሳል፡፡፡
ከላይ የቀረበው ሰንጠረዥ፤ በኢፌድሪ ሕገ መንግስት ላይ  ለአዲስ አበባ የተሰጠው ቦታ ምን ያህል መሰረት ያለው እንደሆነ  በቅጡ ያሳያል፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግስቱ ለአዲስ አበባ የሰጠው ቦታ በሽግግር መንግስቱ ዘመን የነበራትን የክልልነት ቦታ የነፈገ ቢሆንም፤ ከላይ ከጠቀስኳቸው አምስቱ ክልሎች ጋር ሲነጻጸር፣ አዲስ አበባ የተወከለችበት ደረጃ በተናጠል ከብዙዎቹ ክልሎች በእጅጉ የላቀ ነው። ይህ ደግሞ የሚያመለክተው አዲስ አበባ  የተለየ ማንም ባለቤት እንዳይኖራትና በውስጧ የሚኖሩት ዜጎች ከመቶ ሃምሳ ዓመት በላይ በዘለቀ የታሪክ ሂደትና አብሮ በመኖር ትስስር ውስጥ ያዳበሩትን የራሳቸውን ስነልቦናና ማንነት እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብር ተገቢውን ቦታ በመስጠትና አርቆ በማስተዋል ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
አዲስ አበባ በተወካዮች ምክር ቤት ያላት ድምጽ እስከ ዛሬ በተለይ የክልሎችን ጥቅም ለማስከበርና ሚዛናዊ ለማድረግ በሚል ከተማዋን በቅጡ በማያውቋትና በማይወክሏት ሰዎች ስትወከል መኖሯ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው ደግሞ ሃያ ሶስቱ አዲስ አበባን ወክለው በተወካዮች ምክር ቤት የተሰየሙት ተመራጮች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለቅጥ እያወዛገበን፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የደረሰ እስኪመስል ድረስ አጀንዳ ስትሆን ድምጻቸውን አለመስማታችን ነው። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 4 የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች መሆናቸውን ጠቅሶ ተገዢነታቸውም ሲያብራራ፡-
ሀ/ ለሕገ መንግሥቱ፤
ለ/ ለሕዝቡ፤ እና
ሐ/ ለሕሊናቸው ብቻ መሆኑን ይገልጻል። የአዲስ አበባ ተመራጮች ግን ከተሰጣቸው ኃላፊነት አኳያ ውክልናቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ብለን ለማመን ያስቸግራል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድምጻቸውን የሰጧቸው የተከበሩ የህዝብ ምክር ቤት አባላት እያሉ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ባልመረጧቸውና በሹመት በሚሰየሙ ግለሰቦች አማካኝነት ህልውናዋ እንዲታይና ውሳኔ እንዲገኝ እየተደረገ መሆኑ ሊያሳስባቸውና በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ ሊገቡ ይገባል፡፡ ለዚህም የሕሊናም ሆነ የሕገ መንግስት ግዴታ አለባቸው፡፡
ይህ አካሄድ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሰጣቸውን ስልጣን የተጋፋና ውክልናቸውንም መና ሊያስቀረው የሚችል በመሆኑ በየተመረጡበትና ውክልና ባገኙበት አካባቢ የሚገኘውን የአዲስ አበባን ነዋሪ ጠርተው ሊያወያዩና ፍላጎቱን ሊረዱ ይገባል፡፡ የአዲስ አበባን ሕዝብ ፍላጎት በአግባቡ ሳያስተናግዱና ሳያወያዩ የፓርቲን አጀንዳ እያራመዱ፣ የከተማዋን ነዋሪ ጥያቄዎች በመርሳት በሚቀጥለው ምርጫ እጅን ታጥቦ ለምርጫ መሰለፍ ውጤቱን ከንቱ እንደሚያደርገው ከወዲሁ ሊረዱ ይገባል።     
ሕገ መንግስቱ ላይ ብዙዎቻችን በተለያዩ አንቀጾች ላይ ልዩነት ቢኖረንም መሰረታዊ ጥቅሞቻችን በጋራና በእኩልነት በጣምራ እስከተከበሩ ድረስ ሁላችንም በስምምነት ልንተዳደርበት ፈቅደን ቃል ኪዳን የገባንበት የውዴታ ግዴታ ገዢ ሰነድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሕገ መንግስቱ ላይ ስምምነት የተደረሰበትን ጉዳይ በጉልበት ለመጣስ መሞከር የጋራ መዳኛም ሆነ መፋረጃ እንዳይኖረን በማድረግ፣ የፌደራል ስርዓቱንና ሀገሪቱን  አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ውስጥ የምትገኝ ስለሆነች የኦሮሚያ አጥቢያ ነች የሚለውን መከራከርያ ደግሞ እንፈትሽ፡፡ እውነት ነው፣ አዲስ አበባ ከመልክአ ምድር አቀማመጥ አኳያ ስንፈትሻት፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ትገኛለች። ነገር ግን በዓለማችን ከአዲስ አበባ አቀማመጥ በላቀ ደረጃ በተወሳሰበ መልኩ ተሳስረው የሚገኙ ከተሞች ሉዐላዊ መንግስት እስከመሆን የደረሱበት የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ቫቲካንን እንውሰድ፡፡ በጣልያን እምብርት ውስጥ ትገኛለች፣ ደቡብ አፍሪካ እምብርት ውስጥ ሌሴቶና ስዋዚላንድ ይገኛሉ። እነዚህ ሃገሮች በተለያዩ ሃገሮች ውስጥ ደሴት ናቸው። ነገር ግን በሌሎች ሃገሮች እምብርት ውስጥ መገኘታቸው የፌደራል መንግስት ከተማ ከመሆን ባሻገር ሄደው ሃገር ከመሆን ያገዳቸው ነገር የለም፡፡ በተለይ ደግሞ የቦስንያን ሰርቦች፣ በቦስንያ ሄርዞጎቪና እምብርት ውስጥ የተለያዩ አደረጃጀት ያላቸው ቢሆን የሰርፕስካ ሪፖብሊክ ሆነው Constitutive Nation  ከመፍጠር ያገዳቸው ነገር የለም። ሌሎችን በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የክልል አመሰራረትን አስመልክቶ  አንቀጽ 46 ላይ ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች እንደሚዋቀር ደንግጓል፡፡ ክልሎቹ የሚዋቀሩበትን መንገድ የሚያስቀምጠው በዚህ መልክ ነው፡፡ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ ነው፡፡”
ክልሎች ሲዋቀሩ የነዋሪዎቹ ቀደምት ታሪካዊ አመጣጥ ወይም በአንድ ወቅት ይኖሩ የነበሩትን ነዋሪዎች ብዛት እንደ ክልል መመስረቻም ሆነ የባለቤትነት ማረጋገጫ መስፈርት አድርጎ አይወስደውም፡፡ በዚሁ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት፤ የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃደኝነትን ማዕከል አድርገው ኦሮሚያ፣ አማራና ትግራዋይ እንዲሁም ሶማሌን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ተመስርተዋል፡፡ በዚህም መሰረት አዲስ አበባ ላይ የሚነሳው ከታሪካዊ አመጣጥም ሆነ ከቀደምት ነዋሪነት ጋር የሚያያይዘው የይገባኛል ወይም የባለቤትነት ጥያቄ ሕገ መንግስታዊ መሰረት አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡
በተቃራኒው ይህንን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ፤ አዲስ አበባን ክልል ለማድረግ ተጨባጭ ሁኔታ ይመጥናል ወይ በሚል እንፈትሸው፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የአዲስ አበባ ነዋሪ አሰፋፈሩ ከዘመንም ሆነ ከማንነት ዳራ አኳያ የራሱ የሆነ ቅርጽ፣ ይዘትና ዘይቤ አለው፡፡ አማርኛም ቢሆን በራሱ ዘይቤ የተቃኘ፣ የራሱ መግባቢያ ቋንቋ አድርጎታል፡፡ የትኛውንም ብሔር ብሔረሰብ የማይወክልና የማይመስል፣ የራሱ የሆነ ማንነትም ፈጥሯል፡፡ በሂደት የሚታይ ቢሆንም የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ አዲስ አበባን ክልል ለማድረግ ፈቃደኛነቱን ቢያሳይ የሚያስገርም አይደለም፡፡
ይህንን እዚሁ ላይ ገታ አድርገን ወደ ሌላው ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ እንዝለቅ፡፡ መሬት በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት የአንዱ ወይም የሁለቱ ክልል አይደለም። የመንግስትና የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ንብረት ነው፡፡ ክልሎች በመሬት ላይ ያላቸው ስልጣን የባለቤትነት ሳይሆን የማስተዳደር ነው፡፡ ይህ መስተጋብር በአንድ ሉዐላዊ ሃገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦችና መሬት ሊኖራቸው የሚገባው ትስስር ውጤት ነው፡፡
የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ከንዑስ አንቀጽ 1 ጀምሮ እስከ ንዑስ አንቀጽ 8 ድረስ ያለው ድንጋጌ፤ የግል ንብረትና የመሬትን ትስስርን ይተነትናል፣ በተለይ ንዑስ አንቀጽ 3 የሚከተለውን ይደነግጋል፤ ”የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፡፡ የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው ማለት የትኛውም አካል መሬቱ የኔ ስለሆነ በመሬቱ ላይ የተፈጠረው ሃብት የኔ ነው ማለት አያዋጣም፡፡
ይህንን አስመልከቶ በተለይ ደግሞ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 2 እና 7 ላይ የግል የተቋምና የድርጅቶች ንብረትን መብት አስመልክቶ ሕገ መንግስቱ የሚቀጥለውን ይደነግጋል፡፡ “ለዚህ አንቀጽ ዓላማ «የግል ንብረት» ማለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት በሕግ የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ማኅበራት ወይም አግባብ በአላቸው ሁኔታዎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማኅበረሰቦች በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና የተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው፡፡” በመቀጠልም እንዲሁ አንቀጽ 7 ላይ ይህ የግል ንብረት አጠባበቅን አስመልክቶ የሚደነግገው የሚከተለውን ነው፤ “ማንም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ፣ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው። ይህ መብት የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነቱ ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት፣ ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብትን ያካትታል። ዝርዝር አፈጻጸሙ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡
መሬት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ከሆነና በመሬቱ ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብቱ ለገንቢው ወይም ለሚያሻሽለው አካል የተጠበቀ ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ መሰረት መሬትን በባለቤትነት ሊጠይቅ የሚችል ክልል ወይም አካል የለም፣ ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት በመሬቱ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት በመሬቱ ላይ ሌላ አካል ያሰፈረውን ቋሚ ንብረት መውረስ አይቻልም። የመሬት ተጠቃሚነት አጀንዳ የሚነሳም ከሆነ የመሬቱን ተጠቃሚነት ጉዳይ በሕገ መንግስቱ ስልጣን የተሰጠው አካል መንግስት በመሆኑ፣ ካሳ የመክፈል ሕገ መንግስታዊ ግዴታ አለበት፡፡
እነዚህ በሕገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች እስካልረጉ፣ ለአንዱ ክልል ሃቅ ለሌላው ክልል ሐሰት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ ማንኛውም የመብራት፣ የቴሌ፣ የውሃና ሌሎቹም መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በደረቅ ወደብ ላይ እስከ ተከማቸው የገቢና ወጭ ንብረት ወይም በባንኮች እስከ ተቀመጠው ጥሬ ገንዘብ ድረስ ሁሉም ክልሎች የመሬት ባለቤትነት በማንሳት የራሳቸው ንብረት ማድረግና መውረስ ይችላሉ እንደማለት ነው። በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር  የኮየ ፈጪ ላይ የተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶች ጉዳይም ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ ሊታይ አይችልም፡፡
ምን ይሻላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ቀጣዩ መሰረታዊ አጀንዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ ውስጥ በነበሩ ድርጅቶች ውክልና ልክ ቢሆን ለመወከል ችሎ ነበር።  ዛሬ ላይ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪ በሕገ መንግስቱ በተሰጠው የ23 መቀመጫ ልክ በተወካዮች ምክር ቤት መወከሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ተመርጠው የገቡት ተወካዮች፣ ለማንና ለየትኛው አካል ጥቅም እንደቆሙ መፈተሽና መልስ መሻት አለበት፡፡ ለአዲስ አበባ ነዋሪ የገቡትን ቃልና ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ባልተዘረዘሩና ግልጽነት በጎደላቸው፣ ድፍን በሆኑ የጥቅም ጥያቄ ስም ስጋት ውስጥ መጣል፣ግራ ማጋባትንና ማዋከብን አስመልክቶ ተወካዮቻችን ድምጻቸውን ጮክ አድርገው ማሰማት አለባቸው፡፡
የአዲስ አበባን አጀንዳ ወደ ሕጋዊ መድረኩ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመለስና በሕገ መንግስቱ ላይ የተመሰረተ መፍትሔ እንዲያገኝ መታገል አለባቸው። ለአዲስ አበባ ነዋሪዎችም መድረክ አመቻችተው ሊያወያዩትና ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ያለ ውግንና ውክልና ሊኖር አይችልም፡፡ 

Read 1632 times