Monday, 18 March 2019 13:03

ሆድና ጀርባ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

 የሁሉም ወንጀለኞች ልብ ደረታቸውን እየደበደበ በራሱ የሙዚቃ ስልት ሊደንስ ትንፋሻቸውን ዋጥ አድርገው በየተራ ገቡ፡፡ ፖሊሶቹ ሁለቱ ከፊት፣ ሁለቱ ከኋላ ሆነው ካስከተሏቸውና ከተከተሏቸው በኋላ አለቃ ወደሆነውና ከትከሻው ግራና ቀኝ ሶስት ኮከቦች ከደረደረው ሰው ፊት ቀረቡ፡፡ ሁሉም ልባቸው ተሰብሮ፣ ዐይናቸው በሰቀቀን ተቀፍድዶ ነበር፡፡
“በየክልላቸው፣ ወይም ባደጉበት አካባቢ ባህል መሰረት ወደየክፍላቸው አስገባቸው” አለ አዛዡ፡፡
ሁሉም በድንጋጤ አፈጠጡ፡፡ ለወንጀለኛ ክልልና ሰፈር ምን ዐመጣው? በሚል ዓይነት እየተያዩ ሳሉ፤
“በል አስገባቸው! ሁሉም ጠመንጃ ነጋዴዎች ናቸው!”
“አዎ-የተጠረጠሩበት ወንጀል እርሱ ነው”
“በቃ ቀፅል!”
የአዛዡ ግንባር ያስፈራል፡፡ ሁሉም ተስፋ ቆረጡ።
ምንተስኖት እያቃሰተ ቀልብ ለመሳብ ሞከረ፡፡
“ምን ሆኛለሁ እያለ ነው?” አለ አዛዡ፡፡
“ጉዳት ደርሶብኛል! እያለ ነው”
“ለማምለጥ ሲሮጥ ነዋ!”
“አይደለም - ጌታዬ!”
“እርሱን ምርመራ ክፍል ስትደርስ ታወራለህ!”
ለመለመን - ሞከረ
“ነገርኩህኮ!”
በሦስት ቡድን ለያይቶ፣ ይዟቸው ሲሄድ፣ የምንተስኖት እንባ ዐይኑ ላይ ተንጠለጠለ፡፡ በዚያ ላይ ከተወለደበት አካባቢ ሲወጣ ብዙ ደስ አይለውም፡፡ ንግድም ቢሆን እዚያው ቀባዶና ተፈሪኬላ፣ አለታ ወንዶና ይርጋለም እንጂ ሃዋሳ እንኳ ሲደርስ ይቀፍፈዋል፡፡ አሁን ጉድ ያደረገው አብሮ አደጉ ደርቤ ዘውዴ ነው!
“ጌታ ይይለት! በሰላም እንዳልኖር ነጀሰኝ?”
እስር ቤት ውስጥ አስገብተው በር ከዘጉባቸው በኋላ ትንሽ ቆይቶ ፖሊስ መጣ፡፡
“በየተራ ወደምርመራ ክፍል ትገባላችሁ!” ሲላቸው ላቡ ጠብ ጠብ አለ፡፡
ፖሊሱን ተከትሎ መጀመሪያ የሄደው ምንተስኖት ነበር፡፡ ከንፈሩ ደረቀ፡፡ ምራቁ የት እንደገባ ሳያውቀው ከስሩ ሸሸ፡፡ ዐይኖቹ እንባ አጡ፡፡ ግንባሩ ነደደ፡፡ አሁንም ፖሊሱ መጣና ወደሌላ ክፍል ወሰደው፡፡ ክፍሉ ደስ የሚል ነው፡፡ “ቶርች ማድረጊያ ይሆናል!” አለና የበዓሉ ግርማን መጽሐፍ አስታወሰ፡፡ በቆንጆ ቪላዎች ውስጥ አሰቃቂ ግርፊያና ጥፍር ነቀላ ይካሄዳል፡፡
ከዚያ ከወደ ጓዳ የቢለዋ ፉጨት ድምፅ ሰማ፡፡ አንቀጠቀጠው፤ ጥርሶቹ የረገፉ መሰለው፡፡
“በምን ጎዶሎ ቀን እዚህ ጣጣ ውስጥ ገባሁ!”
የቢላዋው ድምጽ ደምቆ ይሰማው ጀመር፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለት ቆንጆ ልብስ የለበሱ ወይዛዝርት በትንንሽ ጎድጓዳ ሳህኖች ዳጣ፣ ሰናፍጭ ያለበት  አዋዜ ጠረጴዛው ላይ ደረደሩ፡፡
ሁኔታው ሊገባው አልቻለም፡፡
አሁንም ሌላ ነገር ከወደ ጓዳ መጣ፡፡ በትልልቅ የትሪ ሳህኖች ላይ፣ ከሽንጥ፣ ከታናሽና ከዳቢት የተመረጡ ስጋዎች ድርድር መጣ፡፡ ነገሩ ህልም እየመሰለው ሄደ፡፡
“እዚያ ወንበር ላይ ተቀመጥ!” አለው ፖሊሱ፡፡
ቀጥሎ ሁለት ወጠምሻ ሰዎች በጥሩ አቆራረጥ ስጋውን እየጎመዱ በቅቤ ባበደው አዋዜ ያጠቅሱ ጀመር፡፡ በዚያው ሁኔታ ሳሉ ነጭና ቀይ የወይን ጠጅ የዋንጫ ቅርጽ ባላቸው ብርጭቆዎች፣ በሚያምር ሁኔታ ተቀዱ፡፡
ከዚያ - ፖሊሱ፤
“ወንድሜ ቀጣዩ ያንተ ጊዜ ነው፡፡ ቶሎ ቶሎ ተናገርና ወደዚህ ማዕድ ተቀላቀል!” አለው፡፡
“በምን አወቁበ ሥጋ እንደምወድድ!” ዐይኑ ተጎልጉሎ ሊወጣ ደረሰ፡-
“አንዴ ብቻ አጉርሱኝና ብትፈልጉ ምቱኝ! በባለወልድ በሀገሬ ታቦት! ስለወንድ ልጅ አምላክ!” ተማፀናቸው፡፡
“ነገርኩህኮ! ያኛው ሳህን ላይ የሚታየው ስጋ ያንተ ፋንታ ነው፡፡ ጎኑ ላይ ያለው ዳጣና ወይንም አንተን ይጠብቃል፡፡ አንተ የሚጠበቀው መሳሪያውን የምትነግደው በምን ዐላማ እንደሆነ መናገር ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይህን ቁርጥ ቆርጠህ መሰናዳት ነው፡፡ ዕድልህን ተጠቀም!”
ከወደ ጓዳ የሲዳሞን ሉካንዳ ቤቶች ሙዚቃ የሚያስታውስ የቢላ ፉጨት ቀጥሏል፡፡ አመነታ፡፡
“እሺ ሁለቱን ጓደኞቼን ጥሩልኝ!” ከማለቱ ጓደኞቹ ከተፍ አሉ፡፡ እያንዳንዱን ነገር ነገራቸው፡፡ ተያዩ፣ ከዚያም ፖሊሱን ጠሩት፡፡
“ስለደከመን ቀድመን አንድ ሁለቴ እንጉረስ፤ በዚያ ላይ አንድ ጊዜ ወይን እንጎንጭ! አለዚያ ደክሞናል!”
“ተናገሩና ሁሉም ነገር የናንተ ነው! በምትወዱት ነገር እየለመንናችሁ ነው፡፡”
ሁሉም ተያዩ፡፡
ወዲያው አንደኛው ፖሊስ ሰላምታ ሰጥቶ ወደሌሎቹ ክፍሎች ሄደ፡፡ በመጀመሪያ የሀበሻ ቀሚስ የለበሱ ቆነጃጅት በአማረ ክፍል ውስጥ ጠረጴዛው ላይ ከተደረደረው ምግብ ፊት ለፊት ቆመዋል፡፡
ቄጠማ ተጎዝጉዞ፣ ፈንዲሻ ፈንድቶ፣ ስኒ ከነረከቦቱ ተሰይሟል፡፡ ከሚያምር ጀበና ቡና እየተንተገተገ ነው፡፡
ወዲያው የወንጀል ተጠርጣሪዎቹ እንደቆሙ ነጭ የማኛ ጤፍ እንጀራ በትሪ ላይ ተስተካክሎ፣ ሽታው የሚያናውጥ የዶሮ ወጥ ፈስሶበታል፡፡ ከክፍሉ በአንድ አፍታ የድግስ ቤት ዐውድ ያዘ፡፡ ከጎኑ የዶሮ ዓይን የመሰለ ጠላ በብርጭቆ ውስጥ ተንቆረቆረ፡፡
በወንጀል ተጠርጣሪዎቹ አንዳች ነገር ዐይናቸው ላይ ተውለበለበ፡፡ ከንፈሮቻቸው ዘመድ እንዳዩ ያህል እህል ናፈቃቸው፡፡ አምሮት ገረፋቸው፡፡ የፖሊሱ አዛዥ ግን አሁንም አተኩሮ ያያቸዋል፡፡
“የሰው ልጅ ሩጫ ሁሉ ለዚህና ለዚህ መሰሉ ምኞትና ጉጉት ነው!” አለና ተናገረ፤ መልስ አልሰጡም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን አንደኛው ካፉ ያመለጠው በሚመስል ዓይነት፤ “ጌታዬ እኛም ሌትና ቀን የምንሮጠው ለዚሁ ነው፡፡ ለቤታችንና ለልጆቻችን!” አለ፡፡
አዛዡ ፈገግ አሉ፡፡ ፈገግታቸው አሽሙር ይመስል ነበረና ሁሉንም ሸነቆጣቸው፡፡ ሌላኛው ክፍልም በተመሳሳዩ እርጎ በዳቦ፣ ክትፎና  ዐይብ በቆጮ፣ ተዘጋጅቶ ተጠርጣሪዎቹ ምግቡ ፊት ቀርበው፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደረገ፡፡
“እዚህ ስትቀርቡ ምን ይሰማችኋል?” አሉ አዛዥ አሁንም፡፡
“ጌታዬ ተስፋ ታይቶናል … እንደፈራነው አይደለም!”
“ምን ነበር የፈራችሁት?”
“ለሕይወታችን ፈርተን ነበር!”
አዛዡ ጥቁር ኑግ ከመሰለ ፊታቸው ላይ በረዶ የመሰሉ ጥርሶቻቸውን ብቅ አድርገው መለሱ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸው ውዝግብ ምጥና ፍርሃት፣ ተስፋና ምኞት ተቀፍድደው ነበር፡፡ ከዚያ አዛዡ ብዙም ሳይቆዩ ሌላ ቀጭን ትዕዛዝ አዘዙ፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በአስቸኳይ የፊጢኝ ታስረው፣ ዐይኖቻቸው በጨርቅ ተሸፍኖ፣ ከከተማ ወጣ ወዳለ ቆሻሻ ማስወገጃ አካባቢ እንዲወሰዱ የሚል መመሪያ ሰጡ፡፡
ፖሊሶቹ ወዲያው አጣድፈው የፊጢኝ እያሰሩ፣ ወደ መኪና ላይ ወረወሯቸው አንዳንዶቹ ማልቀስ፤ ሌሎቹ መንቀጥቀጥ ጀመሩ፡፡
“ምህረት ይደረግልን ጌታዬ! … ማዕድ አሳይታችሁ፣ እንዴት ጥይት ትጋብዙናላችሁ?... ይህ የኢትዮጵያዊ ባህል ነው? … ግፍ አይደለም…”
አንዳንዱ “ልጆቼን!”
አንዳንዱ “ፍቅዬን!”
መኪናው ወደተፈለገው አቅጣጫ ክንፍ አውጥቶ በረረ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ልባቸው ደረታቸውን እየደበደበ ነፍሳቸው በትካዜ እያፏጨች ወደፊት ገሰገሱ፡፡ ከፊሉ በትካዜ ሌላው በፀፀት፣ የባሰበትም በዕድሉ እያዘነ ወደ ሞት አደባባይ ደረሱ፡፡
“በል አንድ ጊዜ ዐይኖቻቸውን ፍታቸውና ዓለምን ለመጨረሻ ጊዜ ይዩዋት” ሁሉም እንባ ከጉንጮቻቸው ወረደ፡፡
ሥፍራው ያስጠላ ነበር፡፡ የቆሻሻ ክምር ወዲያና ወዲህ አለ፡፡ የተበጣጠሱ ልብሶች ፌስታሎች፣ የቤት ጥራጊዎች፣ አሮጌ የሳህን ስባሪዎች ሌሎችም ብዙ ቀለም ያላቸው ነገሮች አሉ፡፡
“አያችሁት … የቅድሙን ቤት ውበትና በቤቱ ውስጥ የነበረውን ምግብ ልዩነት?”
“አዎ ጌታዬ!” አለ ምንተስኖት ቀደም ብሎ፡፡
“የእናንተ ምርጫ ይህ ስለሆነ ነው ያመጣናችሁ!”
“ኧረ አይደለም! … ምርጫችን በሕይወት መኖር ነው!”
ጥቁሩ አዛዥ ነጫጭ ጥርሶቻቸውን ከስስ ከንፈሮቻቸው መሀል አሾለኩና ሳቁባቸው፡፡
“ሳትዋሹ መናገር ነበረባችሁ!”
“ጌታዬ ሁሉን ተናገርንኮ!”
“ስራችሁ ምን ነበር?”
“መሳሪያ ማዘዋወር!”
“በጣም ጥሩ!”
“መሳሪያ የምታዘዋውሩት ምን ለማድረግ ነው!”
“ራስን መከላከያ ነዋ! … ጌታዬ!”
አሁንም አዛዡ ተንከትክተው ሳቁ፡፡
“መሳሪያ መግደያ አይደለም እያልከኝ ነው?”
“እንደዚያ ማለቴ አይደለም - ጌታዬ!”
“መንግሥት መሳሪያውን ሲይዘው መከላከያ ነው፡፡ በሌላው ሰው እጅ ሲገባ ግን መገዳደያ ነው፡፡”
ሁሉም አቀረቀሩ፡፡
“ስለዚህ አሁን የመሳሪያን ጣዕም እንድታውቁት ይደረጋል፡፡”
“ለዛሬ ብቻ ማሩን!”
“ሀገራችሁን ትወዳላችሁ! ለወገናችሁ ታስባላችሁ?”
“አዎ፤ ጌታዬ አዎ!”
“ሀገራችሁን ከወደዳችሁ፣ ወገናችሁን ካሰባችሁ፣ ማድረግ የሚገባችሁ ይህ አልነበረም፤ ይልቅ ቅድም ያያችሁን ምግብ እንዲያገኝ ከማድረግና አሁን ፊታችሁ ላይ ካፈጠጠው አፈሙዝ የቱን ትመኙለታላችሁ?”
“ቢሳካለት ጠግቦ ቢበላ ያማረውን ቢያገኝ ይሻላል!”
“እናንተ ለህዝብ መሳሪያ የምትጋብዙ ሁሉ ወገናችሁን አትወድዱም፤ ዳቦ ያላገኘውን ህዝብ ጥይትን ታቀብሉታላችሁ”
ሁሉም ተንበረከኩ “ይቅርታ! … ተሳስተናል!”
“በል - ተኩስ!” አዛዡ አዘዙ፡፡
“እዚህ ሀገር ጠመንጃ በፌስቲቫል ላይ ለደስታ እንጂ ወንድም ወንድሙን ሊገድልበት መተኮስ የለበትም!!
ሰማዩ በህብረቀለማት አሸበረቀ፡፡ የአበባ ቀለማት ሰማዩ ላይ እስክስታ መቱ፡፡
ሁሉም ተነስተው እየተለቃቀሱ ተቃቀፉ፡፡
ርችቱ ቀጠለ …ቀጠለ….

Read 1677 times