Sunday, 17 March 2019 00:00

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ክፍል-፲፬ ‹‹እውነት›› - ማህበረሰብን የማደራጃ መርህ
Rate this item
(1 Vote)

    ክፍል-፲፬ ‹‹እውነት›› - ማህበረሰብን የማደራጃ መርህ   
በክፍል-13 ፅሁፌ፣ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ክሽፈት ጉዳይ ሲነሳ በምሁራኑ አእምሮ ውስጥ ወዲያው የሚመጣው ሐሳብ፣ የኢትዮጵያ ባህል የአውሮፓን ዘመናዊነት ለመሸከም ምን ያህል ዝግጁ ነው? ከሚለው ጥያቄ ይልቅ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ጉዳዮች ብቻ እንደሆኑና፣ በእነዚህ ምሁራን ጥናት ውስጥ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተመሰረተበት የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል›› በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ክሽፈት ላይ የነበረውን ሚና በተመለከተ ምንም ዓይነት ትኩረት እንዳላገኘ ተመልክተናል፡፡
ለዚህ ድምዳሜም መነሻ የሚሆነን ዘመናዊውን ቢሮክራሲ፣ ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን የሚከውነው ሰው የሚወጣበት የራሱ የሆነ የባህል መሰረት ያለው መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የራሱ የሆነ የቢሮክራሲ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አስተሳሰብ ቢኖረውም፣ በከዋኙ በኩል ግን ከባህል ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ ስለዚህም፣ በዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ በጣም ወሳኝ ሆኖ የሚወጣው ጉዳይ ፕሮጀክቱ ከነባሩ ባህል ጋር ያለው መስተጋብር ነው፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ቢሮክራሲው፣ ኢኮኖሚውና ፖለቲካው ላይ ያለው አፈፃፀም የሚወሰነው ፕሮጀክቱ ከነባሩ የሀገሪቱ ባህል ጋር ባለው መስተጋብር ነው፡፡ ይሄ ድምዳሜ ደግሞ ዝም ብሎ ከንድፈ ሐሳብ ብቻ የመጣ ሳይሆን በሀገራችን በንጉሱ ዘመን በተጨባጭ ያጋጠመን ችግር ነው፡፡
ደራሲ ሐዲስ አለማየሁ በ‹‹ወንጀለኛው ዳኛ›› መፅሐፋቸው መግቢያ ላይ ይሄንን ሐቅ እንዲህ በማለት ፅፈውታል፣ ‹‹የቆየው የኢትዮጵያ የኑሮ ሥርዓት ከስር እንዳለ፣ እንግዳ የሆነው የፈረንጆች የፍትሕ ሥርዓት ባዋጅ በላዩ ላይ ተጫነበት። ነገር ግን፣ እንግዳው ሥርዓት ለጠቅላላው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለባለሥልጣኖች እና ለየስራው ክፍል መሪዎች ጭምር ባዕድ ስለነበረ በሥራ ላይ ማዋሉ ከባድ ሆኖ ነበር። (በመሆኑም) በፈረንጁ ሥርዓትና በነባሩ አሰራር መሀከል አለመግባባት ስለነበረ የኢትዮጵያ የልማት እርምጃ ተስፋ እንደ ተደረገው ሊፋጠን አልቻለም።›› በመሆኑም፣ ‹‹ለዘመናዊነት ፕሮጀክቶች መክሸፍ በወቅቱ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ መሰረት አለመገኘት ነው›› (ባህሩ 2003፡ 31) የሚለው የምሁራኑ መከራከሪያ የመጨረሻ መልስ አይደለም፡፡
የአውሮፓ የዘመናዊነት ፕሮጀክትም ሆነ የሀገራችን ነባሩ አሰራር የበቀሉበት የየራሳቸው የሆነ የባህል መሰረት አላቸው፡፡ በመሆኑም፣ የአውሮፓ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በሀገራችን የሚገጥመው ተግዳሮት ዞሮ ዞሮ መነሻው የባህል ቅራኔ ነው፡፡ ይሄንን የባህል ቅራኔ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የመንፈስ ችግር›› (2003፡ 75) ይሉታል፡፡ ‹‹የመንፈስ ችግር›› አንድ ህዝብ ከነባሩ ባህል ወደ አዲሱ ባህል ሊሸጋገር ሲል የሚያጋጥመው ችግር ነው፡፡
ከላይ ያቀረብናቸው መከራከሪያዎች ሁሉ፣ ዘመናዊነትን የባህል ጥያቄ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም፣ የሀገራችንን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ክሽፈት ስናጠና ‹‹የእኛ ባህል ምን ዓይነት አፈጣጠርና ባህሪ ቢኖረው ነው የአውሮፓን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ሊሸከመው ያልቻለው?›› የሚለው ጥያቄ በጣም ወሳኝ ሆኖ ይወጣል። የሀገራችን ነባሩ ባህል ‹‹በብህትውናና በተአምራዊነት አስተሳሰብ›› ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ቀደም ባሉት መጣጥፎች ላይ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። የብህትውና ባህል ደግሞ የነፍስና ስጋ ተቃርኖ ላይ የተመሰረተ ነው። በተቃራኒው፣ ዘመናዊነት የነፍስና ስጋ እርቅ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹ቅራኔ›› እና ‹‹እርቅ›› የሚሉ ሁለት ፅንሰ ሐሳቦች፣ ብህትውናንና ዘመናዊነትን በደንብ የሚገልፁ ፅንሰ ሐሳቦች ናቸው። ‹‹ቅራኔው›› ከእምነት የመጣ ሲሆን፣ ‹‹እርቁ›› ደግሞ ከአመክንዮ የመነጨ ነው፡፡
ከዚህ የባህሪ ተቃርኖ የተነሳም ብህትውናና ዘመናዊነት በአንድ ህዝብ ውስጥ በአንድ ዘመን ላይ በአንድነት ሊኖሩ አይችሉም፡፡ የምዕራቡ ዘመናዊነት ሊመጣ የቻለው የብህትውናን አስተሳሰብ በመሻገር ነው። በመሆኑም፣ የዘመናዊነት ዋነኛ ተግዳሮት የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል ነው፡፡ የእኛ ሀገር የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች የገጠማቸው ዋነኛ ፈተናም ይሄው ነበር፡፡
እስቲ ከዚህ አዲስ ምልከታ አንፃር፣ የአፄ ቴዎድሮስንና የአፄ ምኒሊክን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች የገጠማቸውን ተግዳሮት እንመልከት፡፡ የእነዚህ ሁለት ነገስታት የዘመናዊነት ሐሳብ ተመሳሳይ ሲሆን፣ ዋነኛ ትኩረቱም የምዕራቡን ዓለም ቴክኖሎጂ መቅዳት ነው - ሀገር ውስጥ በማምረት ወይም ደግሞ ወደ ሀገር አስገብቶ በመጠቀም። የሀገራችን ነባሩ የብህትውና ባህል እንዴት የአፄ ቴዎድሮስንና የአፄ ምኒሊክን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች እንዳከሸፋቸው ለማስረዳት ሁለት ታሪካዊ ክስተቶችን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ እነዚህ ሁለት ነገስታቶች የምዕራቡን ዓለም ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ለመቅዳት የነበራቸው ጥልቅ ምኞት ሲሆን፤ ሁለተኛው ክስተት ደግሞ፣ አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሳቸውን ከማጥፋታቸው በፊት ‹‹ሥርዓት››ን (Discipline) በተመለከተ ለእንግሊዙ የጦር መሪ ለጄነራል ናፒየር የተናገሯት ንግግር ነች፡፡ እስቲ ከመጀመሪያው እንጀምር።
በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ከቅኝ ግዛት ለማምለጥና ፈጣን ዕድገት ለማምጣት፣ እንደ ፐርሺያና ቻይና ያሉ የጥንት ሥልጣኔዎች የምዕራቡን አለም አስተሳሰብ መቅዳት ግዴታቸው ሆኗል፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔም እዚህ ግዴታ ውስጥ ወድቋል። ሆኖም ግን፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የአውሮፓን አስተሳሰብ የመቅዳት ግዴታ ላይ ወድቋል ስንል በትክክል ምንድን ነው ከአውሮፓ የሚቀዳው?
ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከአውሮፓ የሚቀዳው ሌላ ሳይሆን ህብረተሰብን የማደራጃ መርሁን (Organizing Principle of Society) ነው፡፡ ማንኛውም ማህበረሰብ የሚደራጀው ‹‹እውነት›› በሚለው ሐሳብ ዙሪያ ነው። ይሄም ‹‹እውነት›› በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የመጨረሻው ሥልጣን ተሸካሚ ነው፡፡ ከዚህ ‹‹እውነት›› ህብረተሰብን የማደራጃ መርህ ብቻ ሳይሆን የህይወት ትርጉምና የሥነ ምግባር መርሆዎች ይመነጫሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ‹‹እኔ እውነትም፣ ህይወትም፣ መንገድም ነኝ›› ብሎ የተናገረው ነገር የክርስትያን ማህበረሰቦች የማደራጃ መርህ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ፕሌቶም ‹‹The Noble Lie›› የሚል ‹‹እውነት›› በማምጣት ለአቴናውያን አዲስ የማደራጃ መርህ ለማስተዋወቅ ሞክሯል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚያሳየን ነገር፣ በ‹‹እውነት›› እና በሥልጣን (በኃይል) መካከል የባህሪ ግንኙነት እንዳለ ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ ‹‹እውነት›› ቋሚ፣ የፀናና የማይናወጥ ትርጉም ያለው ሳይሆን፣ ከሰው ልጅ ንቃተ ህሊና ጋር ተቀያያሪ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ለምሳሌ፣ ከላይ የጠቀስነው የፕሌቶ ‹‹The Noble Lie›› ሚስጢራዊና በአእምሮ የማይደረስበት እውነት (Mystical Truth) ነው፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ይሄንን ሚስጥራዊ እውነት ይጠቀማሉ፡፡ ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› (Mystical Truth) አንደኛው የእውነት ዓይነት እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ በአእምሮ የሚደረስበት ሌላኛው ዓይነት እውነት ደግሞ ‹‹አመክኖያዊ እውነት›› (Rational Truth) ይባላል፡፡
‹‹እውነት›› - ሚስጥራዊም ሆነ አመክንዮአዊ - ዋነኛ ተግባሩ የህብረተሰብ ማደራጃ መርህ ሆኖ ማገልገል ነው። ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› እንደ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላሉ በብህትውናና በተአምራዊነት ባህል ላይ ለተመሰረቱ ህዝቦች የማደራጃ መርህ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በብህትውናና በተአምራዊነት ባህል ላይ የተመሰረቱ ህዝቦች የሚሰባሰቡት በ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› ዙሪያ ነው፡፡ ይሄ ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› ህዝብንና ሀብትን ያንቀሳቅሳል፤ ተቋማትን ይፈጥራል፤ ፖለቲካን ይቀርፃል።
ዘመናዊ ማህበረሰብ የመጣው ማህበረሰባዊ የመደራጃ መርሁንና የሥልጣን ምንጩን ከ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› ወደ ‹‹አመክኖያዊ እውነት›› ሲቀይር ነው። እናም ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ማዘመን ማለት የኢትዮጵያውያንን ማህበረሰባዊ የመደራጃ መርህንና የሥልጣን ምንጫቸውን ከ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› ወደ ‹‹አመክኖያዊ እውነት›› ማሸጋገር ማለት ነው፡፡ ሳምንት እንቀጥለዋለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 596 times