Monday, 18 March 2019 13:16

የአደገኛ ጭንቅላት ኑዛዜ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(2 votes)

 (የአጭር አጭር ልብ ወለድ)
         
           ቄስ ፒተር ዶምኒኮ ጧፋ አብርተው፣ ግድግዳው ላይ ከተሰቀለው የማርያም ሥዕል ፊት ተንበርክከው፣ የዘወትር ፁሎታቸውን አደረሱና ቀጥለውም “በትክክልና በሃቅ በእግዚአብሄር ፊት እንድቆም እርጂኝ” የሚለውን ፀሎት አከሉበት፡፡
መካከለኛ ቁመት ያላቸው እኚህ አባት፤ እዚህ ፓሪስ ውስጥ ባለው የቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ ሲያገለግሉ፣ እግዚአብሄርና እሳቸው በሚያውቁት አንድም ቀን፣ ምእመናንን በድለው አያውቁም፤ ሁል ግዜ በእግዚአብሄር ፊት በሃቅ በመናገር የታወቁና ከበሬታ ያገኙ አባት ናቸው፡፡
እንደ ሁልግዜው ሃጥያታቸውን ለመናዘዝ የሚመጡ ምመእመናን እንደሚጠብቋዋችው የታወቀ ነው፤ ስለዚህ ወደ ኑዛዜ መስጫው ሳጥን መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ወደ ሳጥኑ ሲራመዱ አንድ ሰው ተንብርክኮ ሲፀልይ ጀርባውን ከማየታቸው ውጭ ብዙም ሰው አልነበረም፡፡ ሳጥኑ ውስጥ ገብተው መቁጠሪያቸውን ይዘው ተቀምጠዋል፡፡
ጥቂት ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ ነበር ሳጥኑ ውስጥ ሰው የገባው፡፡
“ሃጥያተኛ ….. ነኝ … አባት፡፡” አለ አንድ ሻካራ የወንድ ድምፅ፣ ከመጋረጃው በስተጀርባ ፡፡
“እግዚአብሄር መሃሪ ነው” መለሰለት፡፡
“የሚምረኝ አይመስለኝም”
“ለሱ ምን ይሳነዋል” አሉ፤ የሆነ ነገር ውስጣቸው ገባ፣ ድምፁን ያዉቁታል፤ ነገር ግን የማን እንደሆነ ሊያስታውሱ አልቻሉም፡፡ ለነገሩ ማስታወሱ ምን ያስፈልጋል? እሳቸው በዚህ ሰአት የሰውየውን ማንነት ማወቅ አለባቸው እንዴ? በእግዚአብሄር ፊት እያገለገሉ እኮ ነው፡፡
“ወንጀሌ በጣም ከባድ ነው”
“ወደሱ ከተመለስክ እግዚአብሄር መሃሪ ነው”፡፡ መለሱለት፡፡ ድምፁ በጣም ያስታውቃል፤ “በስመአብ ምንድን ነው ይሄን ድምፅ የማወቅ ፈተና ያመጣብኝ ሰይጣን” ብለው አልጎመጎሙ፡፡
“ሰው ገድያለሁ” ተናዘዘ ሰውየው
“መቼ ነው ልጄ?”
“ባለፈው ጥቅምት ወር”
“ምነው አልተግባባችሁም ነበር?”
“አንድ ሰው አይደለም” መለሰ ሰውየው”፡፡
“ሁለት ናቸው?” ልባቸው መታ፤ ለዚህ ሰው ምን አይነት ፀሎት ወይም ስግደት ሊያዙለት እንደሚችሉ እያሰቡ፡፡
“ከሃያ በላይ ናቸው”
መቁጠርያቸው ከእጃቸው ወደቀ፤ ትንፋሻቸውን ውጠው ዝም አሉ፡፡
“ሰሙኝ አባት?”
“አዎን፡፡” አሁንም ድምፁን በጣም እያስታወሱት ነው፤ የት አካባቢ ነበር ይህን ድምፅ የሚያውቁት፡፡ በውል ባይለዩትም እዚያው መኖሪያቸው አካባቢ እንደሆነ ግን እርግጠኛ ሆነዋል፡፡
“ምን ነበር ልጄ ትዕግስት ቢኖርህ”
“እግዚአብሄር አይምረኝም?”
“እግዚአብሔር ሁል ግዜ መህሪ ነው” በረጅሙ ተነፈሱ፡፡
“ወድጄ አይደለም፤ ህፃናት አልወድም፤ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል”
“ህፃናት ናቸው ሟቾቹ?” “ቀዝቃዛ ላብ አላባቸው”፡፡
“አዎን፤ ባለፍኩበት መንገድ ሁሉ ሰካራሙ መጣ እያሉ…..ይሰድቡኛል”
“ምን ነበር ትንሽ ብትታገስ”
“ምን ሰካራም ብሆንም ደደብ አይደለሁም፤ ፈንጂውን የደበቅሁት አሻንጉሊቱ ውስጥ ነበር፡፡ ዝምብዬ የመናፈሻው ወንበር ላይ አስቀመጥኩትና በርቀት መከታተል ጀመርኩ፡፡ አውቶቡሱ የመጣው ያኔ ነበር”፡፡
“የምን አውቶቡስ ልጄ?”
“የተማሪዎቹ”
“እሺ”
“አንድዋ ሹል ምላስ ያላት ሞጥሟጣ ልጅ፤ አሻንጉሊቱን አንስታ፤ አውቶቡሱ ውስጥ ገባች፤ ያኔ ነበር የሪሞቱን ቁልፍ የተጫንኩት” አለ፤ በሚንቀጠቀጥ ድምፅ፡፡
ነገሩ ወለል ብሎ ታያቸው፡፡ የጥቅምት ወር የፓሪሱን የተማሪዎች አውቶቡስ ፍንዳታ ማንም አይዘነጋውም፡፡ በተለይ እሳቸው፡፡ የእህታቸው ሶስት ልጆች አውቶቡሱ ውስጥ ነበሩ፡፡
አሁን ድምፁን አስታወሱት፡፡ በአቅራቢያቸው የሚገኘው የፅህፈት መሳሪያ መሸጫ መደብር ተቀጥሮ የሚሰራው ሮቢን ኖሯል ለካ፡፡ እንድያውም ዛሬ ጠዋት ብእር ሸጦላቸዋል፡፡ የሸጠላቸው ብዕር እንዳለና እንደሌለ ለማየት የግራ እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ ሲልኩ፣ብዕሩን ሳይሆን ስልካቸውን ያዙ፤ የቀኙ እጃቸው ግን መቁጠሪያቸውን ይዟል፡፡

Read 1198 times