Print this page
Sunday, 17 March 2019 00:00

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎ ወያኔ ይሁኑ!

Written by  ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(5 votes)

  ኢትዮጵያን፣ ኦሮሚያንና “ፊንፊኔን” የምታስተዳድሩ እናንተ ታዲያ ሰልፉ ማንን ለመቃወም ነው?
                                  
          ባለፈው ሳምንት በሀገራችን ጎልተው ከተደመጡት የፖለቲካ ክስተቶች አንዱ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ “ሰላማዊ” የሚል ሽፋን የተሰጣቸው የተቃውሞ ሰልፎች ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባም ተቃራኒ ሀሳብን የሚያቀነቅኑ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡ የዛሬዋ ጽሁፌ ትኩረት የምታደርገውም በሁለቱ ክስተተቶች ዙሪያ ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ህዝብን ስለሚያንቀሳቅሱ “የፖለቲካ ልኂቃን” (Political Elites) አንዳንድ ነጥቦችን ልጥቀስ፡፡
በፖለቲካና በማህበራዊ ሳይንስ ንድፈ-ሃሳብ “ልኂቅ” (Elite) ማለት “በቁጥር ጥቂት የሆኑ፣ ተጽእኖ መፍጠር የሚያስችል ሞቅ ያለ ሃብት ያላቸው፣ ልዩ ጥቅም የማይፈልጉ፣ የፖለቲካ ስልጣን የሌላቸው፣ ላቅ ያለ ክህሎትና እውቀት እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ስብስብ” ነው፡፡ ከዚህ ትርጉም በመነሳት “ልኂቅ” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በተለያዩ ዘርፎች ሊገለጽ እንደሚችልም መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የወታደራዊ… ልኂቅ የሚል አገላለጽ ሊኖር ይችላል፡፡
በአሜሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ተንታኞች እይታ፤ የአሜሪካ የፖለቲካ ልኂቃን በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ላቅ ያለ የወሳኝነት ስፍራ አላቸው፡፡ እነዚህ ተጽእኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ልኂቃን በእድሜ፣ በፆታ፣ በጎሳ (በቀለም)፣ በትምህርት ወዘተ. ተለይቶ ቁጥራቸው ጭምር ይታወቃል፡፡ የእነዚህን ልኂቃን ይሁንታ ያላገኘ ሰው የአሜሪካ እጩ ፕሬዝዳንት ሊሆን እንደማይችልም ይነገራል፡፡ በእኛ ሀገር ተለይቶ የሚታወቅ ቅርጽ ያለው የፖለቲካ ልኂቃን ቡድን የለም፡፡ ጽንሰ ሃሳቡም በቅጡ ይታወቃል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት በኛ ሀገር “ልኂቅ” የሚለውን ቃል “ምሁር” ከሚለው ትርጉም ጋር ብቻ የማዛመድ ሁኔታ ይታያል፡፡
ያም ሆኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “ማህበራዊ ሚዲያውን ተጠቅሜ ተጽእኖ መፍጠር ችያለሁ” ብለው የሚያምኑ “አክቲቪስቶች” እንዳሉ አስባለሁ። ይሁን እንጂ እነዚህም የፖለቲካ “አክቲቪስቶች” ቢሆኑ ተከታዮቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን የሚመሩበት መርህም ሆነ የአሰራር ስርዓት አስቀምጠው፣ ስትራቴጂ ነድፈው አመራር የሚሰጡ እንዳልሆኑ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ዓላማና ግብም ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቹ በዘር ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ያላቸው በመሆኑ፤ የሆነ ነገርን ማጋጋል ሲፈልጉ ብድግ ብለው የሆነ መልእክት በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት ዘመቻ ይከፍታሉ፡፡ ያ ዘመቻ “ዓላማው ምንድነው? ሂደቱ ምን ችግር ይፈጥራል? ግቡስ ምንድነው?” የሚለው አያስጨንቃቸውም። የሆነ ነገር መወርወራቸውን እንጂ የወረወሩት ነገር ምን ላይ እንደሚያርፍ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ዓላማቸው መንግስትን ወጥሮ መያዝና ማስጨነቅ ብቻ ይመስላል፡፡
እነዚህ “አክቲቪስቶች” ሁሉም የህዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ ሰልፍ ምላሽ የሚያገኙ ሳይመስላቸው አይቀርም፡፡ ፖለቲካ የድርድር ውጤት እንጂ የሰላማዊ ሰልፍ ውጤት አለመሆኑንም በአግባቡ የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠራው፤ ጆሯቸውን የደፈኑ አምባገነን መሪዎች ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ግፊት ለማድረግ ነው፡፡ ጆሮውን በጥጥ የደፈነው መንግስት መስማት ከጀመረና መሰረታዊ ማስተካከያ በማድረግ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲሰፋ ካደረገ በኋላ፤ ቀሪ የህዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በሰላማዊ ሰልፍ ሳይሆን ሀገሪቱ ባላት ህግና መደበኛ አሰራር መሆን አለበት፡፡ ይህንን በቅጡ ያልተገነዘቡ ሰዎች፤ ለሹሮውም ለበርበሬውም መወደድ፣ ለወጡ መቅጠን፣… ነጋ ጠባ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ አባዜ የተጠናወታቸው መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ህዝብን ስራ ማስፈታቱ ብቻ ሳይሆን አፈጻጸምና ውጤቱም አደገኛ ነው፡፡ የሀገሪቱን ገጽታ ያበላሻል፡፡ ኢንቨስትመንት ይጎዳል፡፡ የቱሪዝም ፍሰቱን ያስተጓጉላል፡፡ የሰርቶ በሌውን ህዝብ እንቅስቃሴ ይገታል፡፡
ታሪክ ራሱን የሚደግመው ከታሪክ ለመማር ካልቻልን ነው፡፡ ደርግ የመጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ላይ ያኔ ተቀናቃኞቹ ከነበሩት ከህወሓት እና ከሻዕቢያ ጋር ድርድር ጀምሮ ነበር፡፡ ደርግ ይህንን ድርድር ማድረግ የነበረበት ነገሮች ተባብሰው መውደቂያው ሲቃረብ አልነበረም፡፡ ደርግ በጉልበት መተማመኑን ትቶ ቀድሞ ቢደራደር ኖሮ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ፣ ሀገሪቱን አፍርሶ፣ አሁን ችግር እየፈጠረ ያለውን ህገ መንግስት አዘጋጅቶ ስራ ላይ አያውልም ነበር፡፡ ደርግ ቀድሞ ቢደራደር ኖሮ፣ የኤርትራ ጥያቄ “የቀድሞው ፌዴሬሽን ይመለስ” ከማለት የዘለለ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ በደርግ ግትርነት ኤርትራ ተገነጠለች፣ ሀገሪቱ የባህር በር አጣች፣ ሀገሪቱ በዘር ፌዴሬሽን ተሸንሽና፣ አሁን ያለንበት ውጥንቅጥ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኗ በየጋዜጣው ሲጻፍ፣ በየአደባባዩ ሲለፈፍ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ፤ “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” ብሎ፣ “ባላዬ፣ ባልሰማ” አለፈው፡፡ ከታሪክ ለመማር ያልቻለው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ፣ ባልጠበቀው ሁኔታ ከ“ዙፋኑ” ላይ ወረደ፡፡ ታሪክ ራሱን ደገመና በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ግትርነት በዘር የተሸነሸነቺው ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ ተጋረጠባት፡፡ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ የህዝብ እልቂትና መፈናቀል ተከሰተ፡፡
ነገሩ በዚህ ቢቆም ጥሩ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በልምድ-ዐልባ አማተር ፖለቲከኞች የተሞላው ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ የያዘውን ስልጣን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ባለመቻሉ ሰርቶ መኖር አዳጋች መሆኑ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሥራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ሊተገበርና የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ባለመቻሉ፣የህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መልፈስፈስ እየተስተዋለ ነው፡፡ ክልሎችና ፌዴራል መንግስቱ ያላቸው ግንኙነት ከመላላቱም በላይ የተኳረፉ ጎረቤታሞች መስለዋል፡፡
ሀገሪቱ የ“ክልል ልሁን” ጥያቄ እንዴት እንደሚስተናገድ በህገ መንግስቷ ውስጥ እውቅና ሰጥታ፣ የአፈጻጸም ስርዓት ዘርግታ ሳለ፤ ይህንን ከምንም ባለመቁጠር በተናጠል የ“ክልል ነኝ” አዋጅ አውጆ፣ በየመንደሩ ታፔላ የለጠፈው የሲዳማ ዞን ተግባር፣ በዚህ ሳምንት ካየናቸው አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው በማን አለብኝነት የሚፈጸም ሀገር የማፍረስ ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባር በጀት በመያዝ ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ ጭምር እልባት ሊሰጠው በተገባ ነበር። በዚህ ዓይነት የኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ፣ አማተር ፖለቲከኞች ድክመት፣ ነገ ከኢትዮጵያ የተገነጠሉ ሉዓላዊ መንግስታት ላለማየታችን ዋስትና የለንም፡፡
የኦዴፓ መራሹን ኢህአዴግ አማተር ፖለቲከኞች ሌላ ድክመት ልጨምር፡፡ ባለፉት ሳምንታት እንደታየው የኦሮሚያ ወጣቶች መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር ጥያቄ ለማቅረብ መነሳታቸው ተገቢ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አንደኛ ነገር፤ ከቆዬ ፈጬ ኮንዶሚንየም ጋር የተያያዘው ጥያቄ አካባቢያዊ ጥያቄ በመሆኑ የወለጋው፣ የአርሲው፣ የሐረርጌው፣… ሰልፍ አስፈላጊ ነበር የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁለተኛው ነገር፤ እነዚያ ደመ-ነውጠኛ ወጣቶች ያካሄዱት ሰልፍ “ሰላማዊ ነው” ከተባለ፣ ጥያቄያቸውም ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ነው ከተባለ፣ በሰልፉ ላይ ይዘው መታየት የሚገባቸው ከጥያቄው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መፈክሮች መሆን ሲገባው ያ ሁሉ ቆንጨራ፣ ያ ሁሉ ዱላ፣ ያ ሁሉ ሚስማር የተመታበት ጣውላ፣… ለምን አስፈለገ? ያ ሁሉ አካል የሚያጎድል ድምፅ አልባ መሣሪያ በማን ላይ ለማሳረፍ የተዘጋጀ ነበር? በገዛ ወገኑ ላይ በጭካኔ የተሞላ እርምጃ መውሰድ ለምን አስፈለገ? በሦስተኛ ደረጃ ላነሳው የምፈልገው ነገር ሰልፉን ያነሳሱትና ግንባር ቀደም ሆነው የመሩት የኦሮሚያ ልኂቃንና አክቲቪስቶች ከሆኑ፤ ኢትዮጵያንም፣ ኦሮሚያንም ሆነ “ፊንፊኔን” ዋነኛ አጋፋሪ ሆነው እየመሩ ያሉት የኦሮሚያ ፖለቲከኞች ስለሆኑ በጉዳዩ ላይ የጓዳ ድርድርና ንግግር በማድረግ ችግሩን መፍታት ሲችሉ ሀገሪቱ ባልተረጋጋችበት በዚህ ወቅት (በራሳቸው ላይ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ) ተጨማሪ ራስ ምታት መፍጠር ለምን አስፈለገ? እንዲህ ያለው አካሄድ “አፈርጣለሁ ሲል አደማ” የሚለውን ብሂል ከማስታወስ የዘለለ ትርጉምም ሆነ ፋይዳ አለው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መታየት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ያሉ የኢንቨስትመንት መሬቶችንና የማዕድን ማዉጫ ስፍራዎችን ካልወረስን፣ በለገጣፎ የተሰሩ ቤቶችን አፍርሰን መሬቱን ካላስመለስን፣ ማለታቸው ሳያንስ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ራሱ በቆዬ ፈጬ የተሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ ኮንዶሚንየም ቤቶችን ካልወሰድኩ ሲል መታየቱ የኦሮሚያ ልጆች የተሰራ ቤት መውረስ እንጂ የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው መኖር አልሆንላቸው አለ እንዴ? የሚል አስተያየት በስፋት እንዲነገር ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት የሚያሳዩት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ የሌሎችን ሀብትና ንብረት በመውሰድ ለመበልጸግ፣ ዜጎች ጥረው ግረው ባፈሩት ሀብት የሰሩትን ቤት በማፍረስ እኩል ድሃ የመሆን ፍላጎት መንጸባረቁን የሚናገሩም አጋጥመውኛል። እንዲህ ያለው አካሄድ ኦዴፓ እንደ ገዢ ፓርቲ ሆደ-ሰፊ ሳይሆን ከህወሓት የባሰ ስግብግብ ባህሪ ያለው መሆኑን ያሳየበት ነው የሚሉ ሰዎችም በርካታ ናቸው፡፡
“በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ፤ የኢትዮጵያም፣ የኦሮሚያም፣ የፊንፊኔም መሪ የሆነው ኦዴፓ የሰከነና የበሰለ የፖለቲካ አካሄድ አለመከተሉ ሁለት ክስተቶችን መፍጠሩ ታይቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአንድ በኩል፤ የኦሮሚያ “ጉሩ” ነን ብለው ራሳቸውን ከመንግስት በላይ “ያነገሱ” የኦሮሚያ አክቲቪስቶች በወሰዱት ራስን የመቃወም ሰልፍ ሀገር እየታመሰ፣ ተቃውሞ እየተቀሰቀሰ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “የኦሮሚያ ጉሩዎች” እና የኦዴፓ አማተር ፖለቲከኞች በአዲስ አበባ ጉዳይ ዙሪያ በያዙት አክራሪ አቋም የተከፉ አዲስ አበቤዎችና እነሱን እንመራለን የሚሉ የሸገር “ልኂቃንና ጉሩዎች” በማህበራዊ ሚዲያ የአፀፋ ፕሮፓጋንዳ ከማካሄድ አልፈው፣ መድረክ ፈጥረው ስብሰባ ማካሄድ መጀመራቸው እየተስተዋለ ነው፡፡ “በመላው ሀገሪቷ የተቃውሞ ማዕበል እንዲቀጣጠል በማድረግ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ከተን ወደ ሽግግር መንግስት ልናመጣው እንችላለን” የሚል አስተሳሰብን ማራመድም ጀምረዋል፡፡
በርግጥ አሁን በሀገሪቱ እየታየ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በመጪው ዓመት መካሄድ የሚገባው ሀገራዊ ምርጫ ሊከናወን እንደማይችል የተረጋገጠ ይመስላል፡፡ ምርጫው ካልተካሄደ ደግሞ በስራ ላይ ያለው ፓርላማ የስራ ዘመኑ ስለሚያበቃ ይበተናል። የሽግግር መንግስት ይቋቋማል፡፡ በሽግግሩ ሂደት ደግሞ በህገ መንግስቱና በፌዴራል አከላለሉ ላይ እንደገና ድርድር ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚፈጥረው የፖለቲካ ትርምስ ገና ሲያስቡት ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም “አሁን ያለው ህገ መንግስት ሊነካ የሚችለው በእኔ መቃብር ላይ ነው” የሚሉ ኃይሎች ነገሩን በዝምታና በአርምሞ የሚያዩት አይሆንም፡፡
ጽሁፌን የማጠቃልለው ሦስት ጸሐፊዎች በዚህ ሳምንት በማህበራዊ ሜዲያ ገፆቻቸው ላይ የጻፏቸውን ስጋት የወለዳቸው አስጠንቃቂ ሃሳቦች በማቅረብ ነው፡፡ በምሳሌያዊ አነጋገሮችና ብሒሎች እያዋዛ በሚያቀርባቸው መጣጥፎቹ የሚመስጠኝና የማከብረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በማህበራዊ ሚዲያ ባሰራጨው አንድ ጽሑፉ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ አዘል ሃሳብ አስፍሮ ነበር፡፡ “ለሁሉም የወጣችውን ጨረቃ ‘የእኔ ናት፣ የእኔ ናት፣ እኔ ነኝ መጀመሪያ ያየኋት’ ብለው እንደሚጣሉ ሕፃናት ያሉ የፖለቲካ ልሂቃንን ከማየት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ልጆች እንደ ዐዋቂዎች ሲሆኑ ያስደንቃሉ፤ ዐዋቂዎች እንደ ልጆች ሲሆኑ ግን ያሳቅቃሉ፡፡ አሁን ባለቺው ኢትዮጵያ የአንድን ወገን ጥቅም፣ ክብርና ልዕልና ለብቻ ለይቶ ለማስከበር በሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ እንዳይበላ ከከለከልነው ጭሮ ለማፍሰስ የሚያንስ ማንም የለም፡፡ ወይ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ትኖረናለች ወይም ለማናችንም የማትሆን ሀገር ትኖረናለች፡፡ አብረን መኖሩ የሚያዋጣን – አብረን አለመኖር የበለጠ ጣጣና ፈንጣጣ ስላለው ነው” ይላል ዲያቆን ዳንኤል፡፡
ናትናዔል አስመላሽ የተባለ ከወደ ትግራይ ያገኘሁት ወዳጄ ደግሞ “እኔ የሚያሳዝነኝ፤ አገር መምራት ‘ቤተሰብ መምራት’ የሚመስላቸውና ‘ዛሬውኑ ይህ ካልሆነ፣ ዛሬውኑ ይህ ካልተደረገ’ የሚሉት ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ የማይታሰብ ለውጥ አምጥቶ እያዩ፣ ጊዜ እንኳ ሊሰጡት አለመቻላቸው ያሳዝናል። አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንደሚባለው፣ ከፖለቲካ እረፍት አድርገው ነገሩን በደምብ አጥንተው መተቸት እየተገባቸው፣ ፍጥነታቸውና የስልጣን ስግብግብነታቸውን ሳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዘንኩ፡፡ እናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለስድስት ወር ወያኔ ቢሆኑ ይሻለዋል…” ብሎ ጽፎ ነበር- በዚሁ ሣምንት። (ናትናዔል ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ወያኔ ይሁኑ” ያለው የሚታሰረውን አስረው፣ የሚገረፈውን ገርፈው፣… እንደ ወያኔ ፀጥ ለጥ አድርገው ያስተዳድሩ ለማለት ነው)፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ በፌስቡክ ገጹ የሚከተለውን አስነብቧል፤ “በፈረሰ ሀገር ውስጥ የጦርነት አሸናፊ ሊኖር አይችልም። በፈረሰ ሀገር ውስጥ የሚከበርም መብት አይኖርም… በፈረሰ ሀገር ውስጥ ካለ ቤተ-መንግስት ይልቅ ሰላማዊ ሀገር ውስጥ ባለ የዛፍ ጥላ መኖር ይበልጣል” ይላል በፈቃዱ፡፡ ይህንንም ሃሳብ ገረሱ ቱፋ ከተባለ ወዳጁ ያገኘው መሆኑን ይነግረናል በፈቃዱ፡፡ ቀጥሎም፤ “ወቅቱ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ነው። የጥላቻና የበቀል ድምፅ አየሩን እየሞላው ነው፡፡ በእነ የመንና ሶማሊያ ስናየው የኖርነው፣ አሁንም እያየነው ያለው እሳት በእያንዳንዳችን ደጅ እየጨሰ መሆኑን ማስተዋል አለብን፡፡ በፖለቲካው መድረክ ላይ ከሚተውነው ማኅበረሰብም መከባበር፣ መቻቻል፣ መደማመጥ፣… ሊኖር ካልቻለ አይቀሬ አደጋ ይጠብቀናል፡፡ ሚዲያውን የሚቆጣጠሩ ሰዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋንያን ከመቼውም በላይ የኃላፊነት ስሜት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ ፉከራን፣ ዛቻን፣ ጥላቻን… ማስተጋባት ወንጀል መሆኑን ኅሊናችን ሊገነዘበው ይገባል፡፡ አሸናፊ በማይኖርበት ጦርነት ማንም ጀግና ሊሆን አይችልም” ይለናል በፈቃዱ፡፡
የእኔን ማጠቃለያ ላቅርብ፡፡ ባለፈው ሳምንት ሁለት አስገራሚ ትዕይንቶች ተካሂደዋል፡፡ በአንድ በኩል ገጀራ፣ ዱላና ሚስማር የተመታበት ጣውላ የያዙ ጉልበተኛ ሰዎች “ሰላማዊ” በሚል ሽፋን ባልተፈቀደ ሰልፍ ማስፈራሪያና ዛቻ ማቅረባቸው ታይቷል፡፡ ሰልፈኞቹ ይህንን በማድረጋቸው በኦዴፓ መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ምንም አልተባሉም፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ፣ ባዶ እጃቸውን የሆኑ ሰዎች በተፈቀደ ስብሰባ ተካፍለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በፖሊስ መታፈናቸው ተሰምቷል፡፡ ሁለቱም እውነታዎች አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ ጨፌ ኦሮሚያና አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ደርሰዋል የሚል እምነት አለኝ።
እንዲህ ያለው ተግባር “በኢትዮጵያ ፍትህ ተጓድሏል” ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው ዘረኛ አስተሳሰብ በኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ መንግስታዊ አመራር ውስጥ መኖሩን ከበቂ በላይ የሚያረጋግጥ ነው። ለዚህ ዓይነቱ ተግባር መልሱ “የበለጠ ሰላማዊ ተቃዉሞ፣ የበለጠ የቤት ውስጥ ቆይታ ተቃውሞ፣ የበለጠ የሥራ ማቆም አድማ ተቃውሞ… ማድረግና በመንግስት ላይ ጫና መፍጠር” መሆኑን የተቃውሞ ድምፆች እየተናገሩ ነው። የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ድሃዋን ሀገርና ህዝብ የበለጠ ራቁታቸውን የሚያስቀር፣ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነ እርምጃ ይሆናል፡፡ ስለሆነም፤ ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ አረፍ ብሎ ዙሪያመለስ ግምገማ ማድረግና ራሱን ማጥራት፣ የተዛባውን አስተሳሰብ ማቃናት ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻ፤ እንደ ፖለቲካ ሣይንስ ተማሪ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተደረጉትን ሰልፎች በተመለከተ አንድ ነገር ልበል፡፡ የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ መንግስት አሁን የደረሰበትን “የጥንካሬ ደረጃ” ለመገምገም ሆን ተብሎ የተደረገ ፖለቲካዊ ንዝረት (Political shock) ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አደገኛ የፖለቲካ አወቃቀር ባለው፣ በተሰነጣጠቀና የገደል አፋፍ ላይ በዘለቀ ሀገር እንዲህ ያለ “ፖለቲካዊ ንዝረት” ጥንካሬን ከመለካት አልፎ ያልታሰበ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል ግምት ውስጥ ማስገባት ብልህነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
    ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 6953 times