Saturday, 23 March 2019 12:31

የኮዬ ፈጬ ኮንዶምኒየምን ለባለዕድለኞች አለማስተላለፍ የህግ ጥሰት ይፈጥራል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“የዜጐች መብት በፖለቲካ ግርዶሽና ፍጆታ መጣስ የለበትም”

            እጣ የወጣባቸው የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለእድለኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲሰጡ የጠየቀው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ቤቱን ዕጣ ለደረሳቸው ዜጐች አለማስተላለፍ የህግ ጥሰትን ያስከትላል ብሏል፡፡
የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ድንበር ሳይካለል ቤቶቹ ተሠርተው ከሆነም ለተፈጠረው ስህተት ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንጂ ገንዘብ እየቆጠቡ እድል ሲጠባበቁ የነበሩ ዜጐች መሆን የለባቸውም ብሏል ፓርቲው - በመግለጫው፡፡ የአዲስ አበባ ማዘጋጀ ቤት ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስና ከህግ አግባብ ውጪ ቤቶቹን ገንብቶ ከሆነም ህንፃውን ለመገንባት ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ባለመቻሉ ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ ይገባዋል ያለው መግለጫው፤ የዜጐች መብት በፖለቲካ ግርዶሽና ፍጆታ ምክንያት መጣስ የለበትም ብሏል፡፡ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ አስተዳደር መካከል የክልል ደንቦች ጥሰት ችግርን ለመቅረፍ ያልተቻለው አሁን ባለው የመንግስት ግልጽነት የጐደለው አካሄድ ችግር ምክንያት ነው ሲል ወቅጿል - ኢሶዴፓ፡፡ በሌላ በኩል፤ ጅግ በርካታ ዜጐች ማለትም የጌድኦ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ማረቆ፣ መስቃን፣ ቅማንት፣ ሸካ፣ ወዘተ የመሳሰሉት በሃይል ተፈናቅለው የሰው እጅ ጠባቂ መሆናቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ መንግስት ለሁሉም በእኩል አይን ተገቢውን ድጋፍና የመኖሪያ ቦታ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ በህገመንግስቱ አንቀጽ 32፤ ማንኛውም ዜጋ የመኖሪያ አካባቢውን መምረጥ እንደሚችል መደንገጉን የጠቀሰው መግለጫው፤ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በአዲስ አበባ ዙሪያ በእቅድ ለማስፈር የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት የለውም፤ የህገመንግስቱን መርህ ጠብቆ ሁሉም በመረጠው ቦታ መቋቋም አለበት ብሏል፡፡

Read 7385 times