Saturday, 23 March 2019 13:41

‘ጠያቂ’ና ‘ተጠያቂ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

“የዓለም ፖለቲካ ማለት የተረበሸ ቤተሰብ ማለት ነው”
             
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ዛሬ ቴሌቪዥን ላይ መቅረቤ ነው፡፡ አሀ...አገር ሁሉ ሱፍና ከረባቱን ግጥም እያደረገ “እዚሀ ነኝ፣” ሲል እኛ ምን ቤት ነን!
ጠያቂ፡— ተመልካቾቻችን የዛሬው እንግዳችን ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ብዙ ሥራ የሠሩ ናቸው፡፡ (ቆይ…ቆየኝማ ወንድም ጋሼ…‘ብዙ ሥራ’ ያልካትን ነገር ብታስረዳኝ፡፡ እንደውም ተወው፣ አታስረዳኝ… ዘንድሮ ራሴን ያልካብኩ መቼ ልክብ ነው!) የፕሮግራማችን እንግዳ ሆነው በመገኘትዎ…
ተጠያቂ፡— (እባከህ… ምንድነው የምትለው…‘ወደ ገደለው’ ግባ…አንድ ሰዓት ሙሉ ቢሮው ውስጥ የበሶ ሚስቶ የሚመስል ሻይ ሲግተኝ አርፍዶ “እንኳን ደህና መጣህ…”! ይለኛል!…) ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎች አስመልከቶ ተመልካቾቻችን ስለእርሶ ማወቅ ስለሚፈልጉ  (“በለው!”አለ ቲያትረኛ!) ስለራስዎ ቢነግሩኝ፡፡
(አንደኛ ነገር ተመልካቹ አይደለም ስለእኔ ማወቅ ሊፈልግ እንደውም ቤቱ እሚለውን አውቃለሁ…“መቼም ዘንድሮ ቴሌቪዥኑን እንደ ህጻናት ጨርቅ ኳስ መጫወቻ አድርገውታል፡፡ ይሄ ደግሞ ማን የሚሉት ነው! ልክ እኮ ያቺ ከይሲ ሱልጣናን አይመስልም!” ካልጠፋ አክቲቪስት ከሱልጣን ጋር ያመሳስሉኛል! ግን ደግሞ ዘንድሮ ተራ ወታደርነት እንኳን ሳይሞከር ባለ አራት ኮከብ ጄኔራል የሚኮንበት ጊዜ ነውና ሰዉ ‘ስለእኔ ማወቅ ከፈለገ’ ልቸገር እንጂ ምን አደርጋለሁ! ኮራ ጀነን፣ ይሄ የፈረደበት የታሸገ ውሀ ብድግ፡፡)
ተጠያቂ፡— እኔ እንኳን ይሄን ያህል የሰው ስሜት የሚስብ ሥራ ሠራሁ ማለት አልችልም። ይህን ያህል የሚነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ደግሞ በተፈጥሮዬ ስለራሴ ማውራት አልወድም። (ይቺ ‘ዲፕሎማሲ’ ሳትሆን ትከሻን ሦስት ሜትር ማስፋት ነው፡፡ ትንሽ ልጨምራባትማ! ያው በካሜራ ፊት “እርገጥ” ብለውኛል፤ ደህና አድርጌ ‘እረግጠዋለሁ!’) እንደ እውነቱ አኔ ሥራዎችን ስሠራ አንዲወራልኝ ወይ ለእይታ ብዬ አይደለም። ዋነው ነገር የወገኖቼን ችግሮች እያየሁ ስለማያስችለኝ ነው፡፡ እንዳልኩህ ግን እኔ ብዙም ማውራት ደስ አይኝም፡፡
(የቅርብ ወዳጆቼ ልክ የሚስተር ቢን ኮሜዲ አይነት እየሠራሁ ይመስል በሳቅ ፍርፍር ሲሉ ይታዩኛል፡፡ ሰፈርተኛው ውስጥ እኮ “ይሄ ሰውዬ ሀያ አራት ሰዓት እንደሚሠራ ወፍጮ ሲለፈለፍ ሀኪም ቤት የሚያደርስ ጓደኛ እንኳን የለውም!” ማለት ከጀመረ ቬንገርና ሞሪንሆ “ቻዎ…” ተብለዋል፡፡)
ጠያቂ፡—  እሺ…የትውልድ ስፍራዎት የት ነው?
ተጠያቂ፡— (የተወለድኩበት አካባቢ ሰዎች ቴሌቪዥናቸው ፊት ሆነው የሰፈራቸው ስም ሲጠራ ሊያጨበጭቡ አሰፍስፈው ይታዩኛል።) የተወለድኩትማ… (ቆይ...ቆይማ…ይቺ ነገር በቄጤማ የተሸፈነች እሾ ትሆን እንዴ! ምን ይደረግ…ዘመኑ እንዲሁ ሆኗላ! አይደለም አውራጃና ወረዳ  በጣም “እነ አከሌ ሰፈር” ማለትም… አለ አይደል… “የቡድንና የቡድን አባቶች ባልተባለበት… በቡድን አባልነትቨ ያስደለድላል፡፡ “ታዋቂው የመብት ተሟጋችና አክቲቪስት የእኛ አካባቢ ሰው ነው” በሚል ፕሮፋይል ፒክቸር ቢያደርጉኝስ! ቂ…ቂ…ቂ… እናማ ወጣቶቹ እንደሚሉት ‘ሽል’ ማለቱ ነው የሚያዋጣው…) የትም ብትወለድ ምን ዋጋ አለው… ዋናው መታየት ያለበት ምን ሠራህ የሚለው ነው፡፡
(አይደለም ዘመድ ወዳጅ ያቺ ‘ታዋቂ’ ሰው አድኖ በማጥመድ ‘ፌመስ’ የሆነችው … አለ አይደል…ያቺ እንኳን መቶ ‘ታዋቂ’ አንጂ አንድም አዋቂ ሰው ማታውቀው… እንትናዬ አንኳን አታጨበጭብልኝም። አሀ…አዲስ ‘ፕሮጀክቷ’ በመሆኔ እንኳን አይጨበጭብልኝም!)
ጠያቂ፡—  በእውነቱ በጣም ደስ የሚል ውይይት እያካሄድን ነው… (ሰውየው…ረጋ በላ! ቁልቁለቱን በአምስተኛ ፈጨኸው እኮ! ሦስት የተሟላ አረፍተ ነገር እንኳን ሳልናገር እንዴት ነው “ደስ የሚል ውይይት” የሚሆነው!) በአሁኑ ጊዜ የዓለም ፖለቲካ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
(ቆይ…እኔ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ ነኝ! ክርስቲያን አማንፑር ነኝ! ወይስ ድፍን አፍሪካ አንድ አገር ትመስላቸው ነበር የሚባሉት ጆርጅ ቡሽ ነኝ! የራሱ ሹሮ አርሮበት ስለሌላ ፒፐር ስቴክ ይጠይቀኛል! ቂ…ቂ…ቂ…ግን ደግሞ… አይደለም ስለዓለም ፖለቲካ ከፈለገ ስለ መንግሥተ ሰማያት ቢጠይቀኝ አርክቴክቶች እንኳን ሊቀኑበት የሚችሉት ስዕላዊ ገለጻ ልሰጠው እችላለሁ፡፡ ልጄ ዘንድሮ በሌለ ጠጠር ጎሊያድን በወንጭፍ አይነት ‘ሲንቴቲክ’ ድፍረት ለቴሌቪዥን እንግድነት የሚያስጠይቅበት ነው፡፡)
ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ዓለምን እንደ አንድ ጠቅልሎ የሚነገረው ነገር ልክ እኮ አይደለም! አይደለም ዓለም…ሀገራት እኮ እንደ ዘንድሮ ዥንጉርጉር የሆኑበት ዘመን አልነበረም…ከእኛይቱ ሀገር የተሻለ ምን ምሳሌ ይኖራል! እናማ ሚዲያችን ላይ ‘ዓለም እንዲህ ነች፣’ ‘ዓለም እንዲያ ነች፣’ የሚሉ ጥቅል አነጋገሮች ሲበዙ ሰው ያደናግራል፡፡
ካነሳነው አይቀር…ለምሳሌ ኢራን “ጫፌን ብትነኩኝ ውርድ ከራሴ፣” አይነት መግለጫ ብታወጣ ሲ.ኤን.ኤን. እና ቢቢሲ… “ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የኢራንን ጠብ አጫሪነት አወገዘ፣” ምናምን ይሉላችኋል፡፡ ሁለቱ ብቻ ናቸው ያወገዙት!  እናላችሁ…ለምሳሌ የሆነ ሙዚቃ ቡድን ሀላፊ ወይ ድምጻዊ ለቃለ መጠይቅ ይቀርባል…
“በአሁኑ ጊዜ የሙዚቃ ባንዳችሁ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?”
“በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው፡፡”
“የውጪ ጉዞ አድርጋችሁ ታወቃላችሁ?”
“በሚቀጥለው ወር ወርልድ ቱር እንወጣለን፡፡”
“በጣም ደስ የሚል ነው፣ መልካም ጉዞ፡፡”
እናማ…አለ አይደል… የሙዚቃ ባንዱ ‘ወርልድ ቱር’ የሚለውን ይወጣና ከአንድ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይመለሳል፡፡
“እንኳን ደህና ተመለሳችሁ…”
“አንኳን ደህና ቆያችሁን፡፡”
“ወርልድ ቱሩ የተሳካ ነበር?”
“በጣም የተሳካ ነበር…ሰዉ በጣም ነው የወደደው።”
“የት፣ የት፣ ሄዳችሁ?”
ፍራንክፈርት ሁለት ሾው፣ ሮም አንድ ሾው…..” (እናስ…በቃ! ጠያቂው እኮ የሚቀጥሉት ሀገራት እስኪዘረዘሩለት እየጠበቀ ነው! ከዓመት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ወርልድ ቱር እንወጣለን ብለን እናስባለን፡፡” (አንደኛውን ገና መቼ ጀመራችሁት!)
እናላችሁ…ይቺ ነገሮችን ለማግዘፍ ወረዳ አንኳን ለሚበዛለት ነገር ከ‘ዓለም’ ጋር አብሮ መስፋቱ የሆነ ጀማሪ ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲያን’ መለማመጃ እየመሰለች ነው፡፡ (ወደ ስቱድዮ እንመለስማ!)
ተጠያቂ፡— ምን መሰለህ…በአሁኑ ጊዜ የዓለም ፖለቲካ ማለት የተረበሸ ቤተሰብ ማለት ነው፡፡ (በለው!) በየስፍራው የምናየው ሁሉ ችግር ነው። እና...ዓለም ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለችም፡፡ (በቃ ወይ?! አዎ፣ በቃ…ጠያቂው ‘የልቡን ያደረሰለትን’ መልስ ሠጠሁት እኮ! ‘በልኩ የተሰፋ’ ጥያቄ ጠየቀኝ፣ ‘በልኬ የተሰፋ’ መልስ ሰጠሁት!)
ጠያቂ፡— በአሁ ጊዜ በአፈ ገራችን ላለው ችግር ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ!
ተጠያቂ፡— አሁን ገና ጥሩ ጠየቅኸኝ። አያጋጭ፣ አያናጭ!…ማን ላይ እንደምቀስር አውቃለኋ!
ዋናው ችግር የቀድሞዎቹ ትውልዶች ናቸዋ። (እሰይ! የፈለገው “የፈረደባቸው ትውልዶች” ይበል፣ የፈለገው “እሱ ያለፉትን ትውልዶች ለመውቀስ የትኛው የሞራል ብቃት ኖሮት ነው!” ይበል፣ ያለፉትን ትውልዶች ብያለሁ ያለፉት ትውልዶች ናቸው!) እነሱ ቆልፈው ቆላልፈው የሄዱት ነገር ነው አሁን እያባላን ያለው፡፡ (እፎይ…በጥልቅ ሀሳብ ከመፋጨት ይልቅ በአሰስ ገሰሱ መጋጨት የእለት ሥራው የሆነው የፖለቲካው መንደርን በዚህ ‘ሽል’ ካላሉት ስምን ‘መሸለቱ’ ስለማይቀር ጠንቀቅ ነው። ቂ…ቂ…ቂ…)
ጠያቂ፡— ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄው ምንድነው ይላሉ?
(ቤቴ ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት አቅቶኝ ሽማግሌዎች ተቀጥረዋል…እሱዬው ስለ “ሀገር መፍትሄ” ይጠይቀኛል፡፡ አሀ…ማን ከማን ያንሳል! እኔ ከመቶ የግል ችግሮቼ ዘጠና ዘጠኙን መፍትሄ ያላገኘሁላቸው ሰው፣ ለዚች አገር ችግሮች መፍትሔ ካልሰጠሁ ማን ሊሰጣት ነው!)
ተጠያቂ፡— ምን መሰለህ፣ ዋናው ነገር… (ከዚህ በኋላ የሚኖረው ሀኪም ሳያዝ እንደሚወሰድ መድሀኒት ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚኖረው፣ ከሂዩማኒቲ አንጻር ትተነዋል፡፡)
ደህና ሰንብቱልኛማ!

Read 2990 times