Print this page
Saturday, 30 March 2019 13:22

ከ37 በመቶ በላይ አፍሪካውያን መሰደድ እንደሚፈልጉ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አፍሮባሮሜትር የተባለው የጥናት ተቋም በ34 የአፍሪካ አገራት ላይ በቅርቡ ባከናወነው ጥናት፣ ከ37 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደሚፈልጉ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
ተቋሙ ይፋ ያደረገውን ጥናት ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ከሚፈልጉ አፍሪካውያን መካከል አብዛኞቹ ወጣቶችና የተማሩ መሆናቸውንም ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ለመሰደድ ከመፈለግ ባለፈ ለስደት ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት አፍሪካውያን 3 በመቶ ያህል እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ አገራቸውን ጥለው መሰደድ ከሚፈልጉት አፍሪካውያን መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት ለስደስት ያነሳሳቸው ምክንያት የተሻለ ስራ ፍለጋ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ 29 በመቶ ያህሉ ደግሞ ከድህነትና ከኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ለማምለጥ ሲሉ ስደትን እንደመረጡ ገልጸዋል፡፡
የጥናት ውጤቱን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ መሰደድ እንደሚፈልጉ ከገለጹት አፍሪካውያን መካከል አብዛኞቹ በወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ሳይሆን ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለመሰሰድ እንደሚፈልጉ ቢገልጹም፣ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውም ወደ አውሮፓ ለመሄድ እንደሚፈልጉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጥናቱ በተሰራባቸው 34 የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚኖሩ ወንዶች 40 በመቶው ወደ ሌሎች አገራት የመሰደድ ፍላጎት ያላቸው ናቸው ያለው ዘገባው፤ ተመሳሳይ ፍላጎት ያሳዩ ሴቶች ደግሞ 33 በመቶ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያን ያልዳሰሰው ጥናቱ ካካተታቸው አገራት መካከል ለመሰደድ የሚፈልጉ በርካታ ዜጎች መኖሪያ በመሆን ቀዳሚነቱን የያዙት ኬፕ ቨርዴና ሴራሊዮን ሲሆኑ፣ ከሁለቱም አገራት ዜጎች መካከል 57 በመቶ ያህሉ ለመሰደድ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
ጋምቢያ 56 በመቶ እንዲሁም ቶጎ 54 በመቶ ዜጎቻቸው ለመሰደድ እንደሚፈልጉ የገለጹባቸውና ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ አገራት ሆነዋል፡፡
ለስደት ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ያሉባቸው አገራት በመሆን የአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አገራት ዚምባቡዌና ሌሴቶ ሲሆኑ፣ በአገራቱ 7 በመቶ ያህሉ ህዝብ ለስደት በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ 6 በመቶ የሚሆነው ህዝባቸው ለስደት እየተዘጋጀ የሚገኝባቸው ጋምቢያ፣ ኬፕ ቨርዴና ኒጀር ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ 5 በመቶ ህዝቧ ለስደት እየተዘጋጀ የሚገኝባት ሳኦ ቶሜና ፕሪሲፔ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

Read 1481 times
Administrator

Latest from Administrator