Sunday, 31 March 2019 00:00

ኬንያዊው የአለማችን ምርጥ መምህር 1 ሚ. ዶላር ተሸለመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

መምህሩ ከደመወዙ 80 በመቶውን ለት/ቤቱ ይረዳ ነበር


          በኬንያ በሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኘውና ከወርሃዊ ደመወዙ 80 በመቶውን ትምህርት ቤቱን በቁሳቁስ ለማሟላት በማዋል ተጠቃሽ ተግባር የፈጸመው ኬንያዊው ፒተር ታባቺ፤ የአመቱ የአለማችን ምርጥ መምህር ሆኖ በመመረጥ 1 ሚሊዮን ዶላር መሸለሙ ተዘግቧል፡፡
በኬንያ የገጠር መንደር በሚገኝ አንድ ኮምፒውተር ብቻ ያለበት ትምህርት ቤት ውስጥ የሳይንስ መምህር የሆነው ታባቺ፤ የደመወዙን 80 በመቶ ገንዘብ ኮምፒውተርና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ለማሟላትና ተማሪዎች በሳይንስ የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል ጥረት ሲያደርግ የነበረው መምህሩ፤ ጥረቱ ተሳክቶለት ትምህርት ቤቱን በአገር አቀፍ የሳይንስ ውድድር አንደኛ ማድረግ መቻሉንና በዚህ ተጠቃሽ ስራው ለታላቁ የአለማችን ምርጥ ሽልማት መብቃቱን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡  
ታባቺ በዱባይ በተከናወነው ደማቅ ስነስርዓት ላይ ተገኝቶ ከዱባዩ ልዑል ሼክ ሃምዳን ቢን ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም እጅ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ንግግር፤ በሽልማቱ በእጅጉ መደሰቱን ገልጾ በሽልማት ያገኘውን ገንዘብም ትምህርት ቤቱን ለማሻሻል እንደሚያውለው ተናግሯል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ በትምህርቱ መስክ ተጠቃሽ ስራን ያከናወኑ መምህራንን በማወዳደር በየአመቱ የአለማችን ምርጥ መምህር ከሚል ማዕረግ ጋር የ1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚሰጠው የዱባዩ ቫርኬይ ፋውንዴሽን፣ ከሰሞኑም ተማሪዎቹን በሳይንስ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ የተለያዩ ተጠቃሽ ድጋፎችን በማድረጉ የተመሰከረለትን ይህን ኬንያዊ መምህር፣ የ2019 ምርጥ መምህር በማለት ሽልማቱን አበርክቶለታል፡፡
ለዱባዩ ቫርኬይ ፋውንዴሽን የ2019 የአለማችን ምርጥ መምህር ሽልማት ከ179 የአለማችን አገራት 10 ሺህ መምህራን በዕጩነት ቀርበው እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፤ ተቋሙ የአመቱ ምርጥ መምህር ሽልማትን ሲሰጥ የዘንድሮው ለአምስተኛ ጊዜ እንደሆነም አስታውሷል፡፡

Read 1413 times