Print this page
Saturday, 30 March 2019 13:45

ወሎ አግላይ ወይስ አቃፊ?

Written by  ዶ/ር ሁሴን አዳል መሐመድ
Rate this item
(6 votes)

 “--ለዜጎች የሚሻለው በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ መታጠር ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮ፣ በዕኩልነት የሚኖርበት ሐገር ባለቤት መሆን ነው፡፡--”              
                ወሎ የዘርም ሆነ የኃይማኖት አግላይነት የሌለበት ሁሉን አቃፊ ክ/ሐገር ወይም ብሔር ነው፡፡ የ1960ዎቹ የብሔር ትግል አቀንቃኝ ተማሪዎች በተገነዘቡት ልክ ከቀሰሙት የማርክሲስት-ሌኒኒስት አስተምህሮ በመነሳት፣ ለብሔር/ብሔረሰብ የሰጡት፣ “ያልጠራ አፋጅ ትርጉም” አለ፡፡ ይህን ከባዕድ የተወሰደ ጽንሰ-ሐሳብ መርሳት ከተሳነው የዋህ ሰው ወይም “ጅግራዋን ዶሮ ናት” በማለት ለቡድን ጥቅም ለማዋል “ጥቂት ቆሎ ይዞ ከአሻሮ ከተጠጋ” የፖለቲካ ልሂቅ በስተቀር፤ “ብሔር” ማለት በአጭሩ “አገር ወይም ሕዝብ” ማለት እንደሆነ፤ “ብሔረሰብ” ማለት ደግሞ “የዚያ አገር ሰው” ወይም “ከዚያ ሕዝብ የወጣ ሰው” ማለት እንደሆነ ብዙዎች ይቀበላሉ፡፡ ላለፉት ረዥም ዘመናት ሰዎች የተወለዱበትን አካባቢ ወይም የወጡበትን ሕዝብ ለመግለጽ “ዘ ብሔረ ወሎ፤ ዘ ብሔረ አድዋ” ወዘተ ይሉ እንደነበረ ለሚያውቅ ሰው፣ ይህ እንግዳ ነገር አይሆንበትም፡፡
ከባዕድ ቋንቋ የተወሰደው በፖለቲካ መርዝ የተለወሰው “ያልጠራ አፋጅ ትርጉም”፣ ከዚህ አገር-በቀል ትርጉም ጋር አይስማማም። የብሔር/ብሔረሰብ አገር-በቀል ትርጉም ከላይ የተገለጸው የአበው ትርጉም ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አገራችን የምትታመስበትን “ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች” ድርብ ድብልቅ ቃል ለመተንተን ሳይሆን የገዥ መደቦች በሚፈጥሩት የአገር አስተዳደር አወቃቀር ችግር፣ አገርና ሕዝብ እንዴት እንደሚታመስ የወሎን ሕዝብ በምሳሌነት ወስዶ በማስቃኘት፣ የመፍትሔ ሃሳብ ለመጠቆም ነው፡፡
ባለፉት አራት አስርተ ዓመታት የተከሰተውን የአንድ - ሶስት - ስድስት የአገር አስተዳደር አወቃቀር ነገረ-ምስጢር ስንመረምር ዓላማው፣ የወሎን ሕዝብ በየወቅቱ ለመጡት የገዥ መደቦች አገዛዝ ማመቻቸት ነበር፡፡ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት በሆኑት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ (1884-1967ዓ.ም) ከ14ቱ ጠቅላይ ግዛቶች አንዱ የነበረው ወሎ፣ 12 አውራጃዎች፤ 38 ወረዳዎች ውስጥ የጋራ ማንነት አለን ብለው የሚያምኑ ስድስት ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ጠቅላይ ግዛት ነበር፡፡ ንጉሡን በተካው የደርግ መንግሥት ወሎ ክ/ሐገር በተደጋጋሚ ተከልሏል። ከ1976-1980 ዓ.ም 14ቱን ክ/ሐገራት በ7 የፕላን ቀጣናዎች ዙሪያ ሲያዋቅር፣ ጥንት የወሎ ክ/ሐገር አካል የነበረውን የአሰብ አውራጃና የትግራይ ምሥራቃዊ ክፍልን በማካተት፣ የሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ፕላን ቀጣና በማለት የቀጣናውን ጽ/ቤት ደሴ ከተማ አደረገ፡፡
በ1981 ዓ.ም 14ቱን ክ/ሐገራት (ከአዲስ አበባ በስተቀር) ለ31 የአስተዳደር፤ ልዩ ራስ ገዝና ራስ ገዝ አካባቢዎች በመከፋፈል የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ሕ.ዴ.ሪ.) ሲዋቀር የወሎ ክ/ሐገር ደቡብ ወሎ፤ ሰሜን ወሎና የአሰብ ራስ ገዝ ተብሎ ተከፈለ፡፡ “የአስተዳደር ክፍፍሉ ዓምዳዊ እርክን ለማሳጠርና ጎናዊ እርከንን ለማስፋት፣ በሕዝቡና በመስተዳደሩ የበላይ አካላት መካከል ያለውን ርቀት ለማጥበብ” በሚል ዓላማ ላይ በመመሥረት አውራጃ የመጨረሻው መንግሥታዊ የአስተዳደር አካል ሆነ፡፡ ወረዳዎች እንዲታጠፉ ተደርጎ በእያንዳንዱ አውራጃ ውስጥ በርካታ የቀበሌ ገበሬ ማህበራትና ከነማት ተዋቀሩ፡፡
የቀድሞዎቹን የወሎ 12 አውራጃዎች በመከለስና ወረዳዎችን በማዋሃድ በሰሜን ወሎ 8፤ በደቡብ ወሎ 9 አውራጃዎችን መሰረተ፡፡ ማዕከሉን አሰብ ባደረገው ልዩ ራስ ገዝ የአውሣ፤ አሰብ ዙሪያና የቀይ ባሕር አውራጃዎች ተካተቱ። አዳዲሶቹን የአስተዳደር አካባቢ/ልዩ ራስ ገዝ/ራስ ገዝ አካባቢዎችን በማዋለድ ኢ.ሕ.ዴ.ሪ. ከተመሰረተ በኋላ ሰባቱ የፕላን ቀጣና ጽ/ቤቶች ታጥፈው በየአስተዳደር አካባቢ ጽ/ቤቶች ስር በመምሪያ ደረጃ ተዋቀሩ፡፡ የፕላን ቀጣና ጽ/ቤቶቹ የተቋቋሙት የገዥ መደቡን ዕድሜ የሚያራዝም አዲስ የአገር አስተዳደር ለማዋቀር እንዲቻል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው ተባለ፡፡ የተፈጠረውን ውጥረት በማስተንፈስ ዕድሜውን ያራዘመ ቢመስለውም ነፍጥ አንስተው በበረሐ የሚታገሉትን ባለተራዎቹን ገዥ መደቦች የልብ ልብ የሰጠና ለሚፈልጉት ዓላማ ስኬት የመንጠላጠያ ድንጋይ ያቆመ ታላቅ ስህተት ፈጸመ፡፡ በወረዳ አስተዳደራዊ መዋቅር መታጠፍ ምክንያት ሕዝቡ ጭራሽ ከማዕከላዊ መንግሥት ግንኙነት በመራቁና ለአስተዳደርና ጸጥታ ሥራ ባለመመቸቱ ደርግ የራሱን ውድቀት አፋጠነ፡፡
የሰሜኑ ጦርነት በአስደናቂ ፍጥነት ወደ መኻል አገር በመግባቱ ማዕከሉን ወልዲያ ላይ ያደረገው የሰሜን ወሎ አስተዳደር ጥቂትም ሳይቆይ በጦርነቱ ተፈናቅሎ በመምጣት የወሎ ሕዝብ ማዕከል በሆነችው ደሴ ከተማ በጊዜያዊነት ተቀመጠ፡፡ ከሰሜን ወሎ አስተዳደር መፈናቀል ቀደም ብሎ በየካቲት ወር 1982 ዓ.ም ደርግ ትግራይን በአላዋቂነት ሙሉ በሙሉ ለቆ ወጥቷል፡፡ ከጥቅምት 1982 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ ወሎ ምዕራብ ወረዳዎችን ጥሎ ወጥቷል፡፡ ቀጥሎም ከሰሜንና ደቡብ ጎንደር ወጥቷል፡፡ ደሴን ለመያዝ በተደረገው ጦርነት፣ የደርግ ጦር ተደምስሶ፣ ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ደሴ ከተማ በኢ.ሕ.አዴግ ቁጥጥር ስር ገባች፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ደርግ ተወግዶ፣ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። በዚሁ ኢሕዴሪ የተባለው የደርግ አስተዳደር አወቃቀር አበቃለት፡፡
ኢሕአዴግ እና ሻዕቢያ በጥምረት ደርግን ካስወገዱበት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ወዲህ የአውሳ አውራጃና የአሰብ አስተዳደር ተፈናቅሎ፣ የሕዝቡ የጋራ ማዕከል ወደ ሆነችው ደሴ ከተማ መጣ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅሎ የመጣው የሰሜን ኢትዮጵያ ሰው፣ የወሎ ሕዝብ መዲና የሆነችውን ደሴ ከተማ ልትሰምጥ የደረሰች በየብስ ላይ የምትንሳፈፍ መርከብ በምትመስል ደረጃ አጥለቅልቋት ነበር፡፡ ከየካቲት ወር 1982 እስከ መስከረም 1984 ዓ.ም የተፈናቀሉ መምህራንና ተማሪዎችን በደሴ ከተማና አካባቢው ባሉ ት/ቤቶች በማረጋጋት፤ ኗሪው የመኖሪያ ቤቱንና ምግቡን በማጋራት፤ ነጋዴው በከፍተኛ የሐገር ፍቅር ስሜት የንግዱን ሥራ ለተፈናቀሉ ነጋዴዎች በማካፈል፤ በሸማቾች ላይ ዋጋ ባለመጨመር ሁሉም ተፈናቃይ የችግሩን ዘመን በደሴ ከተማ በቤተኛነት አሳለፈ፡፡
ኢሕአዴግ የሽግግር ወቅት ቻርተር በማርቀቅ በወቅቱ የፖለቲካ ድርጅት ኖሯቸው ትግል በማድረግ ላይ ከነበሩት ቡድኖች በተጨማሪ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተወከሉበት ጉባኤ፣ የሽግግር ወቅት ቻርተሩ፣ ሐምሌ 1983 ዓ.ም ጸደቀ፡፡ በሽግግሩ ወቅት ኤርትራና የአሰብ ልዩ ራስ ገዝ (ከአውሣ አውራጃ በስተቀር) በሻዕቢያ አስተዳደር ሥር ሆኑ፡፡ የአውሣ አውራጃ የአስተዳደር ግንኙነት ተመልሶ በደቡብ ወሎ ሥር ሆኖ፣ በደርግ ኢሕዴሪ የተዋቀሩት የደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ እህትማማች ዞኖች በነበሩበት ቀጠሉ፡፡
ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራ እንደተጠናቀቀ መስከረም 1986 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ.) ምሥረታና የሽግግር ወቅት ቻርተሩ ዘመን መጠናቀቂያ ምዕራፍ ሆነ፡፡ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ፤ ኤርትራ ከእናት አገሯ እንድትገነጠል በመፍቀድና የአውራጃ አስተዳደር እርከንን በማስቀረት፣ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፋሽስት ኢጣሊያን ትልም ተገበረ፡፡ የወሎ ሕዝብ ይሁንታው ሳይጠየቅ “እንዶድ በሞኝነቱ ወንዝ ወረደ” እንዲሉ፣ በኢሕዴሪ መንግሥት ለሶስት ተከፍሎ የነበረው በኢፌ.ዴ.ሪ መንግሥት በእጥፍ ለ6 አስተዳደር ተከፈለ፡፡ ከኢሕአዴግ በፊት ገዥ መደቦች ለአገር አስተዳደር አወቃቀር የአስተዳደር አመቺነትን፤ የጋራ ስነልቦናንና መልክዓ ምድርን ያተኩሩ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት በደርግ መንግሥት ዘመን መጨረሻ ደቡብ ወሎ ይባል የነበረው የወሎ ክ/ሐገር ግማሽ አካል ዳግም ተሸንሽኖ ደቡብ ወሎ፤ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና የአፋር ክልል ተብሎ ለሶስት እንዲከፈል ተደረገ። የደቡብ ወሎ ማዕከል ደሴ ከተማ፤ የሁለቱ ብሔረሰቦች አስተዳደር ማዕከላት ደግሞ ከሚሴና ሠመራ ሆኑ፡፡ የሰሜን ወሎ ከፊል ራያና ዋግ ወደ ትግራይ፤ ከዚህ የተረፈው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ተብሎ ማዕከሉ ሠቆጣ እንዲሆን ተደረገ፡፤ የተቀረው ደግሞ ሰሜን ወሎ ተብሎ ማዕከሉን ወልዲያ ከተማ አደረገ፡፡ ከአሰብ በተጨማሪ አፍአምቦ ወረዳ ከአውሣ አውራጃ ተነስቶ ለኤርትራ ተሰጠ፡፡
“ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉ፣ በወሎየነት ሕብር ለረዥም ዘመን የኖሩትን ህዝቦች በመነጣጠል ወሎና የወሎየነት ድባብ እንደ ጥጥር ጨው ተከስክሶና ተበጥብጦ እንዲሟማ ተደረገ፡፡ የአገርን አስተዳደር በብሔረሰብ ማዋቀር፣ የመኖሪያ ቤትን በእሳት እንደ ማቃጠል ይቆጠራል፡፡ ሕዝቡ በእሳቱ ሲቃጠል፤ ትርኳሹ የገዥው መደብ ቆፈን ማባረሪያ የሙቀት ምንጭ፤ የኋላ ኋላ ረመጡ መቃጠያው ይሆናል፡፡
ጨቋኝ ገዥ መደብን በጋራ ታግለው የጣሉ፣ የወሎ ብሔረሰቦች ስትራቴጂካዊ የጥቅም ግጭት ያላቸው ይመስል ፈቃዳቸው ሳይጠየቅ እንዲነጣጠሉ ተገደዱ፡፡ የወሎ 6 ብሔረሰብ ሕዝቦች፣ የጋራ ማንነት ያላቸው፤ አሁን ለደረሱበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውጣ ውረድ አብረው ዋጋ የከፈሉ፤ በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ከወሎ ገባር የተሰበሰበ የትምህርትና የጤና ታክስ ገንዘብ በሁሉም የወሎ አካባቢዎች ት/ቤት ለማቋቋምና ክሊኒኮችን ለመክፈት ውሏል፡፡
በወ/ሮ ስኂን ት/ቤት በአንድ ላይ የተማሩ የየብሔረሰቡ ተወላጆች፣ ለአገራቸውና ለየአካባቢያቸው የልማት ዕድገት ፋና ወጊ ዜጎች ሆነዋል፡፡ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በተፈጥሮ ሐብት ተጋሪነት ስሜት ከብቶቹን ወደ ወሎ ዝቅተኛ ቦታዎች በመንዳት፣ ከአጎራባች የወሎ ኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ከብቶች ጋር የሚያከርመው ወሎዬው፤ የአፋር አርብቶ አደር እንደ አባት አደሩ ዛሬም ከብቶቹን ነድቶ ያውላል፡፡ በመሆኑም የየብሔረሰቦቹ ሕዝቦች ዛሬ በአገር አስተዳደር አወቃቀር ተጽዕኖ ስር ቢወድቁም፣ ይህ የጋራ ማዕድ ተጠቃሚነትና አብሮነት በጽኑ አስተሳስሯቸዋል፡፡ የብሔረሰብ ሕዝቦቹን ታሪካዊ ትስስር፤ የጋራ ስነልቦናና የተዛመደ ሕልውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጥፋት፣ በአገር አስተዳደር እንዲነጣጠሉ የማድረግን ያህል አይፈጥንም፡፡
ዳሩ ግን በትስስራቸው ላይ ምንም ጉዳት አላስከተለም ማለት አይደለም፡፡ በጋራ አዳብረው ያቆዩትና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚገባቸው አኩሪ ባህልና ታሪክ የመረሳት ምልክት በግልጽ መታየት ጀምሯል። ሌሎች ባህላቸውን በዓመታዊ ፌስቲቫል ሲያበለጽጉ፣ በአንጻሩ የወሎ ማዕከል በሆነችው ደሴ ከተማ በበዓላት ጊዜ ይቀርቡ የነበሩት የ12ቱ አውራጃዎች የባህል ጨዋታዎች እየተዳከሙና እየተረሱ መሄድ፣ የዚህ ጉዳት መኖር ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡  
የወሎ የባህል እሴቶችን ለማዳከም ኢሕአዴግ ግንቦት 1983 ዓ.ም አገሪቱን እንደ ተቆጣጠረ ለወሎ ባህል ዕድገት የጎላ አስተዋጽዖ ሲያበረክት የቆየውን ስመ ገናናውን የወሎ ባህል አምባ አፍርሶት ነበር፡፡ የደቡብ ወሎ አስተዳደር ጽ/ቤት ነባር ባለሙያዎችን በማሰባሰብና የጎደሉትን በአዲስ በማሟላት፣ የባህል አምባው ከመስከረም 2006 ዓ.ም ጀምሮ መልሶ እንዲቋቋም አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባህል ቡድኑ በወሎ ዩኒቨርስቲ ስር ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በየመ/ቤቱ የሚሠሩ የወሎ ተወላጅ የመንግሥት ሠራተኞችን በቀድሞ አውራጃዎች ስም እየለያዩ እርስ በርስ አጋጭቶ ሕብረት በማሳጣት፣ የአካባቢውን ልማት በጋራ እንዳያፋጥኑ እንቅፋት መፍጠርና በቁ ሰዎች ወደ መድረክ እንዳይመጡ ማፈን፣ ወሎ ከደረሰበት ፈርጀ-ብዙ በደል ውስጥ አንዱ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ የኃይማኖት ልዩነትን አጀንዳ በማድረግ፣ ሕዝቡን በሁለት ጎራ ለይቶ ለማጨፋጨፍ የሚደረገው ጥረት ሌላው ነው። ከሌሎች በመማር፣ ለወጣቱ ትውልድ ሞዴል የሚሆን፤ ሐውልት የሚቆምለት ስመ-ጥር እንዳይለይ፤ የተጀመሩ ጥረቶችንም በማቋረጥ፣ ትናንትን የማያውቅ ትውልድ ለመፍጠር፣ የወሎ አንጋፋዎችን የማጣጣል ዕኩይነት አለ፡፡
የወሎ ሕዝብ በብሔረሰብ ቋንቋ ሰበብ ለስድስት አስተዳደር እንዲከፋፈል ሲደረግ፣ በአንጻሩ በቋንቋ የተለያዩ በርካታ ብሔረሰብ ህዝቦች በአንድ አስተዳደር እንዲኖሩ እንደ ተደረገ ወሎየው ልብ ማለት አለበት፡፡ ትግሬ፤ ኩናማ፤ አማራ፤ አፋር፤ ኢሮብ ብሔረሰቦች በትግራይ ክልል፤ 56 ብሔረሰቦች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር እንዲታጨቁ ተደርጓል፡፡ ሌሎች ያገኙትን ዕድል በመንፈግ የዕኩልነትና የአብሮነት ሞዴል የሆነው ወሎ፣ ብሔረሰቦቹን ለምን ተገፈፈ ለሚለው ጥያቄ መልስ ያሻል፡፡
ከኢትዮጵያዊነት/ሕብረብሔራዊነት አኳያ በወሎ የዘርም ሆነ የኃይማኖት አግላይነት ባለመኖሩ፣ ወሎየነት እንደ አማራነት አቃፊ ነው። ወሎየነት ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በወሎየነት ድር የተሳሰሩ ከአማራ ጋር ጥብቅ የጋራ ሕልውና ያላቸው ተጨማሪ 5 የወሎ ብሔረሰቦች አሉ፡፡ በትግራይ ዳብሯል እንደ ሚባለው “ትግራዋይነት” እና ኢትዮጵያዊነት፣ ለማንም ወሎየ ብሔረሰብ “ወሎየነት” እና ኢትዮጵያዊነት አንድ ናቸው፡፡ በወሎየነት ዘውግ ከሚመሰረት ሕብረብሔራዊነት ተነስቶ ኢትዮጵያዊነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባት የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ይቀለዋል፡፡ በሌሎች የአገራችን ክ/ሐገራትም ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ብዝህነት እንዳለ ሁሉ፣ በአንድ ክ/ሐገር ወይም ብሔረሰብ ሕዝብ ውስጥ ተነጻጻሪ የሆነ መከበር ያለበት ውስጣዊ ብዝህነት መኖሩ ገሃድ ነው፡፡
ሕብረብሔራዊነት ከላይ በማቶት ታስሮ ወደ ታች የሚጣል የጣሪያ ክዳን አውራጅ እንጨት አይደለም፡፡ ከታች ጀምሮ በየእርከኑ ዙሪያ እየተገመደ፣ ወደ ጉልላቱ የሚዘልቅ ጸንቶ የሚቆይ ትስስር እንጂ! እንደ ወሎ ሕዝብ በአስተዳደር ተነጣጥለው ከድንበር ማዶ ለማዶ እንዲተያዩ፤ በቀበሌና ወረዳ ይገባኛል ጥያቄ ዘወትር እንዲጋጩ ሸር የተሠራባቸው ክ/ሐገራት ብሔረሰቦች ሕዝቦች ሁሉ የዚህን ክፍተት ተጽዕኖ ያውቁታል፡፡
እንደ ዕውነቱ ከሆነ ለአገር አስተዳደር ጥቅም ሲባል፣ ሕዝብን በቋንቋ ከመክፈል በወንዝ ተፋሰስ ወይም በኮምፓስ አቅጣጫ ተመስርቶ መክፈል ይሻላል፡፡ በመልክዓምድር የሚዋቀር የአገር አስተዳደር፣ ዜጎችን በጋራ የሚጋሩት ክ/ሐገር ባለቤት በማድረግ፣ እርስ በርስ ሲያግባባ፤ በቋንቋ የሚዋቀር አስተዳደር “አገሩ የእኔ ብቻ ነው” ለሚሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ባለቤቶች ሙሉ ልብ በመስጠት ዜጎችን ይለያያል፡፡ የመጀመሪያው ዓይነት የአስተዳደር አወቃቀር፣ የጎሳ ፖለቲካ ንግድን በማስቀረት፣ የአገራችን ኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲከኛን፣ ሠርቶ መብላት እንዲያውቅ ያስገድደዋል፡፡ ለዜጎች የሚሻለው በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ መታጠር ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮ፣ በዕኩልነት የሚኖርበት ሐገር ባለቤት መሆን ነው፡፡
በአጠቃላይ የወጣቱን ትውልድ ሰፊ የነቃ ተሳትፎ የሚሹ ፈተናዎችን በብልሃትና በቆራጥነት መጋፈጥ ወቅቱ የሚጠይቀው ብሔራዊ ግዴታ መሆኑን እያስገነዘብኩ፣ ሐተታው በሚከተሉት ነጥቦች ይጠቃለላል፡፡
በቋንቋ ሰበብ ወሎየነት ለስድስት አስተዳደር መዋቅር ተበታትኖ እንዲሟሟ የተሞከረው በመሰሪነት መሆኑን በመገንዘብ፣ የወሎን ሕዝብ የጋራ ትስስር ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስና አቃፊ የሆኑትን አማራነትና ወሎየነት ማጣጣም፤
በቀድሞ አውራጃና በኃይማኖት በመከፋፈል ሕብረት እንዲጠፋ የሚሠራው የሴራ ፖለቲካ ማርከሻው መድሐኒት የተጠናከረ የወሎየነት የጋራ ስነልቦና መሆኑን በመረዳት፣ አንድ በመሆን ሴራውን ማክሸፍ፤
 ከታላላቅ ወሎየ አባቶች መካከል ለወጣቱ ትውልድ ሞዴል የሚሆን አንጋፋ/አንጋፋዎች በመምረጥ የኩራት ምንጭ የሆነው የአባቶች ጉልህ ሥራ ሳይረሳ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ጥረት ማድረግ፤
በአገራችን ኢሕአዴግ የፈጸመው የአገር አስተዳደር አወቃቀር ግድፈት፣ ብሔረሰቦችን ለዘመናት ከየነበሩበት ዘውግ አፈናቅሎ፣ ያለፈቃዳቸው በማይፈልጉት ዘውግ በማካተት፣ አገራችንን መቋጫ ለሌለው የማንነቴ ይመለስልኝና የድንበር ይከበርልኝ ጥያቄዎች ተጋላጭ ስላደረገ፣ ግድፈቱ እንዲታረም በአገራችን የተጀመረውን ሰላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥና የሰከነ ውይይት ባህል ማጎልበት፡፡

Read 8975 times