Saturday, 30 March 2019 13:16

ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሳ

Written by  ከስንሻው ዘኮተቤ
Rate this item
(1 Vote)

 ጎሳ ሳይለይ የዚህች አበሳዋ የማያልቅ አገር ዜጎች፣ በአራቱም ማዕዘናት ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተውና አጥንታቸውን ከስክሰው በስደት በሚኖሩባቸው ሀገራት ሳይቀር፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው፣ ከሃዲውንና እጁ በደም የተጨማለቀውን ብልሹ የዘረኞች አገዛዝ፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማጋለጥ በከፈሉት መስዋዕትነት ያነበሩት ለውጥ፣ ይኸው አንድ ዓመት ሞላው፡፡ ለውጡ ባሳለፈው የአንድ ዓመት ዕድሜ፤ የፖለቲካውን ምህዳር በማስፋት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ የሚዲያ ነፃነትን በማስፈን፣ ሰላምና መረጋጋት እጅጉን በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል የወንድማማችነትና የትብብር መንፈስ በመፍጠር፤ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ከሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከለጋሽ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መንግስት ያስመዘገበው ስኬት፣ ከአርባ ዓመታት በላይ በረሀብና በጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ሀገራችን ታላቅ ተስፋን የፈነጠቀ ሆኗል። በተጨማሪም መንግስት ለውጡን ለማስቀጠልና አስተማማኝ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ዲሞክራሲያዊና አስተዳደራዊ ተቋማትንና ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ረገድም ጠቃሚ አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰዱ የሚያስመሰግነው ነው። ሆኖም ግን የለውጡ መንኮራኩር በብቸኝነት በኢህአዴጋውያን መዘወሩ፣ ስፋት ላለው ህዝባዊ ተሳትፎ ትኩረት መንፈጉና “እኔ አውቅልሀለሁ በሚል የብልጣ ብልጥ ስልት” መመራቱ፤ ዘላቂነት ያለው ህዝባዊ ጥቅምና ደህንነት ለማረጋገጥ መቻሉ ላይ ጥርጣሬን በማጫሩ፣ ህዝባችን ለውጡን በተደበላለቀ ስሜት እንዲመለከተው አድርጓል፡፡
ክቡር የሆነውን ሀገር የመምራትና ህዝብን ከድህነት የመታደግ ታላቅ ተልዕኮን በመዘንጋት፣ ውሱን የሆነውን የሀገር ሀብት ለጥቂት የወያኔ ባለስልጣናትና በዙሪያቸው ለተኮለኮሉ ምንደኞች የግል ብልፅግናና ጥቅም ያዋለው ብልሹ የዘረኞች አገዛዝ፣ ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት የፈፀመው ግፍ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ዘረፋ ሳያንሰው የትግራይን ህዝብ እንደ ጋሻ በመጠቀም፣ መቀሌ ላይ መሽጎ ለውጡንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተዳደር በመገዳደር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የወንጀለኞች ቡድን በስልጣን ላይ በቆየበት ወቅት በግፍ ያካበተውን የደም ገንዘብ ለመንጋ ፍትህ አራማጆች፣ ፅንፈኛ ብሄረተኞች፣ በየክልሉ ላሉ ብልሹ የመስተዳድር አካላት፣ የፀጥታ አባላትና አጉራ ዘለል አክቲቪስቶች እየበተነ፣ እዚህም እዚያም በቀሰቀሰው ግጭትና መፈናቀል ህዝባችን የለውጡን ትሩፋቶች በወጉ እንዳያጣጥም ከማድረጉም በላይ የሚሊዮን ዜጎች ማህበራዊና ቤተሰባዊ ህይወት እንዲቃወስ በማድረግ ላይ ነው። በተጨማሪም የሀገሪቱ ህገ መንግስትና ፌዴራል አስተዳደሩ ከሚፈቅደው ውጭ ቁጥሩ ለማይናቅ የክልሉ ወጣት (ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚገመት) የመደበኛ ጦር ስልጠና በመስጠትና  የነፍስ ወከፍና ለመከላከያ ሰራዊት ብቻ የተፈቀዱ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎች በማስታጠቅ፣ ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል!! መንግስት ይህንን ህገወጥና ፀረ ሰላም ድርጊት በዝምታ መመልከቱና ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት የህግን የበላይነት ለማረጋገጥ ፈጥኖ አለመንቀሳቀሱ በህዝቡ ዘንድ ግርምትን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል። ዝምታውን አንዳንዶች ከአቅም ማነስ ጋር ሲያያይዙት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ምናልባት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለእርሳቸው ያለውን አዎንታዊ ገፅታ እንዳይበላሽ አጥብቆ ከመንጠንቀቅ የመነጨ መሆኑን ይገምታሉ፡፡
ለዘመናት ከኖሩበት የትውልድ ስፍራቸው በኦነግ ታጣቂዎች ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎ፣ በገደብና ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የዕምነት ተቋማት ተጠልለው ለሚገኙና ለረሃብ፣ ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውሶች የተጋለጡትን ቁጥራቸው ከ800 ሺህ በላይ የሆነ የጌዲኦ ተፈናቃዮችን በተመለከተ መንግስት መፍትሄ አለመስጠቱና ደንታቢስ ሆኖ መታየቱ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ ለወራት የቆየው የጌዲኦ ተፈናቃዮች ሰቆቃና ችግር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት የዜጎቹን መብትና ደህንነት (በየትኛውም ክልል ውስጥ ይኑሩ) የማስከበር ኃላፊነቱን ጨርሶ መዘንጋቱን ያሳያል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ፣ “ዘር ማጥራት ሊባል በሚችል መንገድ” በዕብሪተኛና ዘረኛ ታጣቂዎች ሲፈናቀል፣ በወንጀለኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ ተፈናቃዮችን በቀዬአቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ አመራር መስጠት ዳገት የሆነባቸው፣ ተፈናቃዮቹ ሰፍረውበት የነበረው ቦታ ታጣቂዎቹ በጠመንጃ ከሚያስተዳድሩት የምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ይዞታ ውስጥ ስለተቀላቀለ ይሆን? ይህንን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አትኩሮት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል እላለሁ!! አለበለዚያ ግን “በጥልቀት ታድሻለሁ፣ ተለውጫለሁ”፣ “የበደልኩትን ህዝብንም ለመካስ ተነስቻለሁ” በማለት በተደጋጋሚ በእርሳቸው አንደበት የሚያደነቁረንና ለህዝብ ሰቆቃ ደንታ-ቢስ ከሆነ ባህሪው ሊላቀቅ ያልቻለው ድርጅታቸው ኢህአዴግን “ፍየል መንኩሳ አመሏን አትረሳ” በማለት እንተርትበታለን፡፡
ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ  ኦሮሞዎችን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ “በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለማስፈር ሌት ተቀን እየሰራን ነው” ማለታቸውና የአዲስ አበባን ባለቤትነት በተመለከተ መስተዳድራቸው አበክሮ በመስራት ላይ መሆኑን ማስታወቃቸው ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮብኛል፡፡ የፓርቲውም ሊቀ መንበር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በኦዴፓ የተሰጠውን መግለጫ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ሲጠየቁ፤ “ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም” በማለት መመለሳቸው አስገርሞኛል። በተጨማሪም ክቡር ኦቦ ለማ፣ 500 ሺህ ከሚሆኑት ከሱማሌ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች ውስጥ መስተዳድራቸው እስካሁን ስምንት ሺህ የሚሆኑትን በአዲስ አበባ ክልል እንዲሰፍሩና የከተማን ኑሮ እንዲለማመዱ በማድረግ ላይ መሆኑንና ቁጥራቸው ግማሽ ሚሊዮን ለሚጠጋ የክልሉ ሰራተኞች በከተማዋ ክልል ውስጥ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉንም ነግረውናል፡፡
የኦሮሚያ መስተዳድር የከተማዋን የቦታ ይዞታ ለፈለገው ጉዳይ ያለ ምንም ከልካይ መጠቀሙ ታዋቂው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ” ብሎ የሰየማት አዲስ አበባ፤ ዛሬም ተቆርቋሪና ሃይ ባይ ያጣች ከተማ መሆኗን እንድገነዘብ አስችሎኛል፡፡ ምክንያቱም ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ፤ ይህቺ የአፍሪካ መዲና ተብላ የተሰየመችና በዓለማችን ካሉ ጥቂት ዓለማቀፋዊ ዕውቅና ከተሰጣቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው አዲስ አበባ፤ በአዋጅ የተሰጣትን ራስን በራስ የማስተዳደር ሉዓላዊ መብት በእናት ድርጅታቸው እንዲደፈር በማድረጋቸው ነው!! ቀደም ብለው የተጠቀሱትን የሰፈራ ታሪኮች የከተማው ምክር ቤት በትክክል የሚያውቀው፣ በውል የመከረበትና የወሰነበት መሆኑንም እጠራጠራለሁ!!  
በእውነቱ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” በማለትና አምባገነኑንና ሰው በላውን የጥቂት ወሮበላ ወያኔዎች አስተዳደርን “ይህቺ አገር እንዴት ልትተዳደር እንደሚገባት ውሳኔውን ለህዝባችን አሳልፈን መስጠት ይገባናል” በማለት የተገዳደሩት “ኢትዮጵያዊው ሙሴ” የሚል ሙገሳ የተቸራቸው ኦቦ ለማ መገርሳ፤ ፓርቲያቸው በከተማዋ ያለውን የህዝብ አሰፋፈር ለሚያዛባ ድርጊት (illicit social re-engineering) ቡራኬ መስጠታቸው፣ በከተማው ነዋሪ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም ፍትሃዊ ሊሆን የሚችለው መፍትሄ፣ ከፌዴራል መንግስቱና ከሱማሌ ክልል መስተዳድር ጋር በመምከር የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና አስፈላጊውን የሞራል፣ የገንዘብ፣ የማቴሪያልና የሎጂስቲክስ ድጋፍ አድርጎ፣ ተፈናቃዮች ተመልሰው ወደ ቀዬአያቸው እንዲቋቋሙ ማድረግ ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ የተፈናቃዮቹን በከተማ የመኖር መብት አልቃወምም። ሆኖም ግን ይህንን መብት ለማረጋገጥ የኦሮሚያ መስተዳድር አካሄድ ላይ አልስማም፡፡ ምክንያቱም መስተዳድሩ የነዚህን ተፈናቃዮች በከተማ የመኖር ህልም ቀድሞ በሰፈሩበት ቦታ፣ አካባቢያቸውንና አኗኗራቸውን የሚያዘምንና የሚለውጥ፣ የከተማ እድገትና ልማት ዕቅድና ስትራቴጂ በመንደፍ፣ ራሳቸው የሚሳተፉበትና አሻራቸውን የሚያኖሩበት የትግበራ ስልትን መጠቀም ይገባው  ነበር ብዩ ስለማስብ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ “የሚበጅልህን እኛ አውቅልሃለን” በሚል በተለመደው ኢህአዴጋዊ አካሄድ፣ ዜጎችን የሰለጠነና የተወሳሰበ ከባቢያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ባለበት ከተማ ማስፈር፣ ጅምላ የመብት ጥሰት ከመሆኑም በላይ ድርጊቱን በነጠላ ላይ በካኪ ጨርቅ ኪስ መስፋት ያደርገዋል።
 በ1994 ዓ.ም በወያኔ አገዛዝ ውሳኔ “የበረሃዋ ዕንቁ” አዳማ፤ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆና በተሞሸረች ወቅት የኦሮሚያ ክልል ሰራተኞች ጓዛቸውን ሸክፈው፣ ከእነ ቤተሰባቸው በከተማዋ ሰፍረው ነበር፡፡ የ1997 ምርጫን ውጤት ተከትሎ ውሳኔው ተቀልብሶ፣ ጎዞው እንደገና ወደ አዲስ አበባ በመሆኑ፣ በዥዋዥዌው ዜጎች ለከፍተኛ መጉላላት መዳረጋቸውን ያስታውሷል፡፡
ከላይ ለመጣጥፌ ርዕስ አድርጌ የተጠቀምኩትን አባባል የሚያሳይልኝ ሌላ ሰሞነኛ ጉዳይ ላንሳ፡፡ ይኸውም፡- የአዲስ አበባን ባለቤትነት በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር፣ አበክሮ በመስራት ላይ መሆኑን የሰጠውን መግለጫ ያመለክታል። ጦረኞቹ የኦሮሞ ፈረሰኞች ቀደምት ያዲስባ ነዋሪዎችን በኃይል ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲቀበሉ በማስገደድ (ኦሮማይዜሽን)፣ አሰቃቂ ግፍ የፈጸሙባት ከተማ መሆኗን የታሪክ ተመራማሪዎች ይጠቅሳሉ፡፡
በተጨማሪም የኦሮሞ ዝርያ ያላቸው ያንጎለላው ተወላጅ አፄ ምኒልክ የመሰረቱት ማዕከላዊው መንግስት መቀመጫውን በዚች ከተማ በማድረጉ፣ ንጉሱ ድብልቅ ዝርያ የነበራቸውን ሹማምንቶቻቸውን፣ ባለሟሎቻቸውንና ወታደሮቻቸውን በዙሪያቸው እንዲሰፍሩ ማድረጋቸውን ታሪክ ይመሰክራል። ከተማዋ ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ዜጎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በመፍለስ የሰፈሩባትና አሁን ላላት ገፅታ የራሳቸውን ጠጠር በመወርወር የገነቧት በመሆኑ ባለቤትነትዋ ያንድ ብሔር ሳይሆን የሁሉም የሆነች ከተማ ናት፡፡
ከሰሞኑ በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞችና ህግ በማይገዛቸው የጅምላ ፍርድ ተዋናዮች በተነሳው ህገወጥ የይገባኛል ጥያቄና የህዝብ አሰፋፈርን የማዛባት ድርጊት በመቆርቆር፣ ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ በባልደራስ አዳራሽ የጠራውን የተቃውሞ ስብሰባ፣ ያወጣቸውን የአቋም መግለጫዎች በመኮነን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ከንቲባው የሰጡት አስተያየት፣ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ዜጎች በግልም ይሁን በቡድን ህገወጥ ብለው ባመኑበት ጉዳይ ላይ ተቃውሟቸውን የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብት የጣሰ ጉዳይ ነው፡፡ ገጀራ ስለውና በእንጨት ላይ ሚስማር መትተው ህዝብን ሲያሸብሩ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች የዜጎችን ውድ ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲቀጥፉና ሲያፈናቅሉ በነበሩት የጅምላ ፍትህ ቡድኖች ድርጊት ላይ ዝምታን የመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የባልደራሱን ሰላማዊ የተቃውሞ ስብሰባ ለማውገዝና ጭራሹንም “ጦርነት እንገጥማለን” ለማለት መፍጠናቸው፣ በአንደበታቸው ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ በልባቸው ግን ብሔርተኛ መሆናቸውን ገሃድ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡
እዚህ ላይ በጋሞ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ በቡራዩ የተፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ዜጎች ላይ አስተዳደራቸው የፈፀመውን የግፍ ግድያና እስር ያስታውሷል!!
ሰሞኑን የለውጡን የአንድ ዓመት ጉዞ ለመገምገም በተጠራው “አዲስ ወግ” መድረክ ማጠቃለያ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር፤ መንግስታቸው በተለይም የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ ያሳየውን ድክመትና ሌሎች አስተዳደራዊ ግድፈቶችን በተመለከተ ከተሳታፊዎች ለተነሱት ሀሳቦች የሰጡት ምላሽ ቁጣን ያዘለና ጅምላ ወቀሳ ላይ ያተኮረ ነበር። ለዚህም እንደ ማሳያ “አቅላይ፣ የማያመሰግን ህዝብ” በማለት የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ስኬታማ ስራዎችን ማከናወናቸውን ብንቀበልም፣ የመንግስታቸውን አካሄድና የስራ አፈፃፀም ውጤት “እንከን የለሽ ነው” ብሎ  መበየን ግን ሚዛናዊነትን ያጓድላል፡፡   


Read 2066 times