Saturday, 30 March 2019 13:53

ለመከራ ያለው ቢነግድ አይተርፈው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“--ሚዲያው ባለፉት ወራት ለያዥ፣ ለገናዥ በሚያስቸግር ሁኔታ የድፍረትን ‘በርሊን ዎል’ ሰብሮ የወጣ ቢመስልም…አለ አ ይደል…ውስጡ ‘ ፍርሀት’ የፈጠረው ድ ፍረት ያለ ነ ው የ ሚመስለው፡፡--”
                            

             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እናማ “እዚህ አካባቢ መጸዳዳት ክልክል ነው፣” አይነት ‘የጨዋ ደንብ’… ማስጠንቀቂያዎች አሉ፡፡
እኔ የምለው…ከዚህ በፊት ያወራናት የ‘ማስቦካት’ ነገር በቃ የሁላችንም ዲ.ኤን.ኤ. ነገር ሆነች ማለት ነው! ማለት…አለ አይደል…ከአገጭ ማውለቅ ላንላቀቅ ነው!
ደግሞላችሁ… አለ አይደል..አንድ ሰሞን ከተማዋን አጥለቅልቀዋት የነበሩ ‘ጣትን ቃታ ላይ’ አይነት ማስጠንቀቂያዎች አሉ፡፡
“ትሸናና ትሸነሸናለህ!”
“ትሸናና ዋ!”
ስሙኛማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… መንገድ ላይ መጸዳዳትን በተመለከተ ገቢ ተኮር ማስጠንቀቂያም ነበር፡፡ “ከመሽናትዎ በፊት ኪስዎን ይዳብሱ!” ይላል፡፡ እናላችሁ… መንገድ ላይ መጸዳዳት እንኳን ገንዘብ ላለው የተፈቀደባት ሀገር! ኪሳችን ባዶ ስለሆነ ፊኛችን ሙሉ መሆን አለበት እንዴ! (ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ…ጨዋታም አይደል…“እርምጃ ይወሰዳል” የሚሏት ነገር አለች፡፡
“እንዲህ ባላደረጉት ላይ እርምጃ ይወሰዳል!…”
“እንዲህ በማያደርጉት ላይ እርምጃ ይወሰዳል!”
“እንዲህ አይነት ክፍያ ባልከፈሉት ላይ እርምጃ ይወሰዳል!”
ይቺ “እርምጃ ይወሰዳል” የሚሏት ነገር ከዘመን ዘመን አትለወጥም፡፡ (ስሙኝማ…ድሮም እኮ በቀለም የተለዩት ‘ሽብሮች’ ላይ መግለጫው “እርምጃ ተወስዷል” የሚል ነበር፡፡
እናላችሁ ….እንዲህ አይነት የ“ዋ!” ማስታወቂያዎች፣ ማስጠንቀቂያዎች በየቦታው አሉ፡፡
ምን ይመሰለኛል መሰላችሁ…“በቃ፣ ይሄ ህዝብ ከጉልበት ሌላ የሚገባው ነገር ስለሌለ ‘ማስቦካት’ ነው” አይነት ውሳኔ የተላለፈብን ነው የሚመስለው፡፡ እናማ…አሁንም ህብረተሰባችን በፍርሀት ባህር ውስጥ ነው፡፡ እንደውም አሁን፣ አሁን “ቀረልን…” ያልነው ነገር እየተመለሰ… “አንተ ከእነሱ ሰዎች ጋር ምንም ነገር አታውራ፡፡ ምን እንደሚያደርጉ ማን ያውቃል!” እየተባባልን ነው። እንፈራለና! 
አእምሮው ለእውነት ሲዘጋ የሆነ ሰውን …በቃ “እሱ መጥፎ ነው” ከተባለ ‘መጥፎ’ ነው…የሆነ ቀንድና ጭራ ያበቅሉለትና የተለየ ፍጥረት ያደርጉታል፡፡ እና… ምንም ደግ ሥራ አልሠራም ማለት ነው? አይደለም! እዚህ አገር አምስት በመቶ ስህተት ወይም ድክመት፣ ዘጠና አምስት በመቶውን በጎ ሥራ ጎል ትከታለች፡፡
የምር ግን አስቸጋሪ ነው…ሰው የሚመዘነው በዓላማና በአመለካካት ሳይሆነ በአገር ልጅነት በሆነበት ዘመን ጉድጓድ እየማሰ የሚወጣ ‘አስፈሪ ጉልበተኛ’ በዝቶብናል፡፡
(ያኔ እሷዬዋን እያባበልን እያለ ዜናው ከዘንድሮ ፌስቡክ በባሰ ፍጥነት ታላቅ ወንድሟ ጆሮ ይደርሳል፡፡ ከዛማ ምን አለፋችሁ…ኑሮ አይበለው። ስንወጣና ስንገባ ከሆነ ስፍራ… ብቻ ከአየር ላይ ዱብ ብሎ፣ አንገታችንን አንቆ የማይክ ታይሰንን ‘አፐርከት’ ምናምን የሚያሳርፍብን ይመስለናል…ከያዘንም አይቀርልንም፡፡)
የምር ግን አሁን፣ አሁን  ፍርሀት፣ ፍርሀት የሚሉን ነገሮች እየበዙብን ነው፡፡ ‘እንደፈለግን መናገሪያ’ ጊዜ ነው እያልንም፣ ያቺ ውስጥ ያለች ፍርሀት ጓዟን ጠቅልላ ለመውጣት ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ እናላችሁ… ስንፈራ ደግሞ ለዛሬው ብቻ ሳይሆን… “ነገ ምን እንደሚመጣ ማን ያውቃል!” በሚል ነው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታ ጨዋታን ያነሳው የለ…ሰማንያዎቼ መጀመሪያ ላይ የመንግስት ለውጥ ሰሞን በመንግስት ሚዲያዎች ‘ማጋለጥ’ የሚባል ነገር ነበር፡፡ እናላችሁ… አንዱ ይነሳና… “እከሌ ደህንነት ነው፣ ለደርግ ሲሰለል ነው የኖረው፣” ይላል፡፡ (በነገራችን ላይ የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ለምንድነው የእኛ ሀገር ፖለቲከኞች ተቃራኒ የሚሏቸውን ማዋረድ ደስ የሚላቸው! በዛን ወቅት ዋናው ትኩረት እነኛ ሰዎች ‘ፈጸሙ’ የተባሉትን ነገሮች ማሳወቁ ላይ ሳይሆን እነሱን ‘ማዋረድ’ ላይ  ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በየመድረኩ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት ሳይሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ‘ማሳጣት’ እና ‘ማዋረድ’ ነው፡፡ ያሳዝናል!)
እናማ… ‘ደህንነት ነው፣ ምናምን ነው’ የተባለው ሁሉ ቢሮ ገብቶ እቃዎቹን ለመሰብሰብ እንኳን አልተፈቀደለትም፡፡ በቀጥታ ከግቢ ውጡ ነበር የተባለው፡፡ ይህን ያህል መጠላላት አያስፈልግም ነበር እኮ! አሁንም ይህን ያህል መጠላላት አያስፈልግም እኮ! አንዱ ‘አባራሪ፣’ ሌላው ‘ተባራሪ’ ሆነም፣ አንዱ ‘ባለጊዜ’ ሌላው ‘ጊዜ የጣለው’ ሆነም፣ አንዱ ‘ባለገንዘብ’ ሌላው ‘ባለዝንብ’ ሆነም፣ ሁላችንም አንዲቱ ጀልባ ውስጥ ነን! አለቀ!
ስሙኝማ…በዛ ጊዜ ደህንነት ምናምን ከተባሉት ሌላ አንዳንዶቹ ‘የተከሰሱት’ በምን መሰላችሁ… ‘በጆክ!’ “ይሄ እኮ በራሱ ብሄር ላይ ሳይቀር ጆክ ሲናገር የነበረ ነው!” ተብለው ለጊዜውም ቢሆን የእንጀራ ገመዳቸው የተበጠሰ ነበሩ፡፡ እናላችሁ…‘ትምህርቱ’ ምን መሰላችሁ… ምንም አይነት መስመር ሳታበጁ በጨዋታ ስትቀላለዱ የነበራችሁት ሁሉ ‘የቤተ መንግስቱ አወቃቀር’ ሲለወጥ እዳ ይዞባችሁ ሊመጣ ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ በራስ ከመሳቅ የበለጠ በራስ መተማመን የለም፡፡ ግን እሱን ሁሉ አጥተነዋል። ለምሳሌ አሁን እኔ ስለቁመት ሆነ እኔን ሊመለከተኝ ስለሚችል ሌላ ነገር ቀልድ ቢጤ ጣል ባደርግ የሚስቅ ሊስቅልኝ ይችላል…ሌላው ደግሞ ሊያሳቅቀኝ ይችላል… “አጭር፣ አጭር የሚለው በማን ላይ ለማሾፍ ፈልጎ ነው!” ብሎ የሆረር ፊልም ሊለቅባችሁ ይችላል፡፡
ለምሳሌ ለ‘ሞዴልነት’ ብላም ቢሆን፣ የምሳና የእራት ድርሻዋን ታላቅ ወንድሟ እየገነደሰባትም ቢሆን፣ ብቻ የሆነች ቀጨጭ ያለች ወዳጃችንን፤ “አንቺ… ምንድነው! ሰውነትሽን በሲሪንጅ የሚመጥብሽ ሰው አለ እንዴ!” እያላችሁ ብትቀላለዱ ሌላ ‘ቀጭን የሀበሻ ልጅ’… አለ አይደል… “በተዘዋዋሪ እኔን መስደቡ እኮ ነው!” ብሎ የኑ ካምፕን ጩኸት ሊለቅባችሁ ይችላል፡፡
“ያለባቸውን እዳ በአስር ቀን ውስጥ በማይከፍሉ ተገልጋዮች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል…” ማሳሰቢያና ማስታወቂያዎች  የ“ወዮልህ” ቃና ሲበዛበት ልክ አይደለም፡፡
አንዳንድ ተቋማት “ከእንትን ወር ጀምሮ ሒሳቡ በዚህ ያህል ፐርሰንት ጨምሯል፣” ሲሉን …አለ አይደል.. ‘የኪስ ድንኳን ሰበራ’ ይመስለናል። እናላችሁ… “ልክ አይደላችሁም፣ ፍሬሽ ቲማቲም በሶስት ሳምንት ሁለት ፍሬ ብቻ በምንቀምስበት ጊዜ ዋጋ ትጨምሩብናላችሁ” ብለን ማጉረምረም እንጀምራለን፡፡ ግን ደግሞ አገልግሎት በማቋረጥ ‘ሀይል በማን እጅ እንደሆነች’ ያሳዩናል ብለን ስለምንፈራ ከዛ አልፈን አንሄድም፡፡
እናማ… እውነት እንነጋገር ከተባለ ፍርሀት አለ። እልም ያለ ‘ድፍረት’ በሚመስል ነገር ውስጥም ትንሽ ጊዜ ወስዶ ለሚያይ ሰው ‘ፍርሀትም’ አለ። ሚዲያው ባለፉት ወራት ለያዥ፣ ለገናዥ በሚያስቸግር ሁኔታ የድፍረትን ‘በርሊን ዎል’ ሰብሮ የወጣ ቢመስልም…አለ አይደል…ውስጡ ‘ፍርሀት’ የፈጠረውም ድፍረት ያለ ነው የሚመስለው፡፡ 
ታዲያላችሁ… እንደተሞክሯችን ከሆነ ዛሬ የምንላቸው ነገሮች ነገ፣ ከነገ ወዲያ ‘ጦስ’ ይዘው ላለመምጣታቸው እርግጠኛ ልንሆን አንችልም። አሀ…ነገራችን በአብዛኛው “አንዴ ብዠልጠው እኮ ከአስኮ አምስት ሰዓት ላይ መሮጥ የጀመረ ቦሌ አምስት ሰዓት ከሩብ ይደርሳል፡” አይነት ነው።  ‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ  ጌት’ ምትለዋ ነገር ፌዝ ሆናለች፡፡ (በስሱ ፋቅ ማድረግ ብቻ ይበቃል።)
እናላችሁ… የሰው መኖሪያ በአንድ ምክንያትም ሆነ በሌላ እየፈረሰና ሰዎች ሜዳ ላይ እየወደቁ፣ ቢያንስ “የሰዎቹ መንገላታት ቢያሳዝነንም መደረግ ስላለበት አድርገነዋል፣” ምናምን አይነት ትንሽ ‘ሂዩማኒቲ’ ቢጤ ጣል ያለበት ነገር ወርወር ማድረግ ሲቻል፣ “ገና ምን አይተሽ!” አይነት የ“ዋ!” አነጋገር ልክ አይደለም፡፡
እናላችሁ……ከልምድ ተነስተን ብዙ፣ ብዙ ነገሮች እንፈራለን!
ቀበሌ አንፈራለን!
የአትናዬን ታላቅ ወንድም እንፈራለን!
ፌዴራል እንፈራለን!
የሥራ አስኪያጁን ጸሀፊ እንፈራለን!
ደንብ ማስከበርን እንፈራለን!
ታዲያላችሁ… አለ አይደል… ብዙ ጊዜ የምንፈራው ጥፋት ስላለብን ሳይሆን፤ ያጎደልነው ነገር ስላለ ሳይሆን…አንገት የሚያሰብር ተግባር ስለፈጸምን ሳይሆን… ‘ዱላው’ ወገባችን ላይ ካረፈ በኋላ… “እሺ ችግሩ ምንድነው?” አይነት ነገሮች እስኪያንገሸግሸን ሲገጥመን ስለኖርን ነው፡፡ አዎ…ብርሀኑ ከዋሻው ጫፍ እየታየን ነው እያልንም፣ ነገራችን አሁንም…  “ለመከራ ያለው ቢነግድ አይተርፈው፣” ከሚለው ለመውጣት ገና ረጅም መንገድ ይቀረናል…ያውም መሰናክሎቹ የሚቀነሱልን ከሆነ ማለት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2189 times