Saturday, 30 March 2019 13:52

«መነጠል”

Written by  ከዳግማዊ እንዳለ (ቃል፡ ኪዳን)
Rate this item
(12 votes)

  የዓለምን ከንቱነት በያዝኩት ወንፊት አጥልዬ ማረጋገጥ ባልችልም፤ ልቤን ሳዳምጥ፤ እንደ ዘበት ዳብሶኝ ያለፈዉ እምክ አየሯ፤ ‹ከንቱ ናት› ሲል ሹክ አለኝ፡፡ ደርሼ የባህር በሬን ዘግቼ፣ እራሴን ከዓለም ነጠልኩ፡፡ መነጠሉ፤ መቋረጥ ሆኖ፤ ተሻግረዉ ካሉት ሁሉ ተቆራረጥኩ፡፡
ብዙም ሳይቆይ ግን ሲሻቸዉ በጀልባ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በዋና እየመጡ፤ የባህር በሬን አንኳኩተው እያስካኩ የሚመለሱ ህጻናት በረከቱ፡፡ ህጻናቱን እንዲረብሹኝ የሚልኳቸዉ ባህሩን የሚጋሩት አገራት ወላጆች ናቸዉ፡፡ ቆንጥጦ አለማሳደጉስ ይሁን፤ ግና ልጅን መረን መልቀቅ ምን የሚሉት ተግባር ነዉ?
በኩባያና ኩባያ ላይ እንደታሰረ ገመድ፤ ከጎረቤቶቼ የሚያገናኘኝ ባህር እስካለ ድረስ ሰላም ማግኘት እንደማልችል ተረዳሁ፡፡ አንኳኩተዉ የሚሮጡትን ለመያዝ አድብቶ መጠበቁ ደግሞ፤ ገዳም ገብቶ፤ ሻይ ቡና ለማለት ከተማ እንደመውጣት ነዉ የሚሆነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ሌላ መንገድ መኖር አለበት ስል አሰብኩ፡፡
ከሰባት ቀን ጥሞና በኋላ የባህር በሬን ከፍቼ፤ ዳርቻዉ ላይ እግሮቼን እንደ ቀጭኔ አንፈራጥጬ ቆሜ፤ አፌን ባህሩ ላይ ተክዬ፤ ዉሃዉን ጭልጥ አድርጌ ጠጣሁት፡፡ ይህንን ሲመለከቱ ባህሩን የሚጋሩት አገራት ነዋሪዎች፤ ደማቸዉን እንደመጠጥሁት ሁሉ ባንዴ ገረጡ። በጨለጥኩት የባህር ዉሃ ጉንጬ ሲወጠር፤ ሆዴ ሲቆዘር ጊዜ፤ ወደ አገሬ ዞሬ፤ በቀዩ አገሬ እምብርት ላይ፤ ሰማያዊዉን የባህር ዉሃ ተፋሁት፡፡ አገሬን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፍ ታላቅ ሀምራዊ ወንዝ ተፈጠረ፡፡ ወንዙ አገሬን አልፎ ከጎረቤት እንዳያገናኘኝ፤ አፍና ጅራቱን አገናኘሁት፤ ወድያዉ እንደ ጽዮናዉያኑ እባብ፣ ታላላቅ ኮረብቶችንና ገደሎችን ዉጦ ክበብ ሠራ፡፡
ዉሃዉ ሲነጥፍ የሞቱና ለመሞት የሚያጣጥሩ አሳዎችና ሌሎች የባህር እንስሳት፤ ባህሩን ገረጋንቲ የተደፋበት አውራ ጎዳና አስመሰሉት፡፡ በማይመለከታቸዉ ጭዳ ለሆኑት ለባህር ፍጡራኑ አብዝቼ አዘንኩ፡፡ በርግጥ በህይወት ዉስጥ አንዱ እንዲሆን ሲባል ብዙ እንዳይሆኑ የሚደረጉ ይኖራሉ፡፡ መራመዱ፣ መቀመጡ፤ በእንቅፋት ተጠልፎ መሬት ላይ መዉደቁ እንኳን፤ የሚታዩና የማይታዩ ብዙ ህይወት ያላቸዉ ፍጡራንን መስዋዕትነት የሚጠይቅ ጉዳይ ነዉ፡፡
ለሟቾቹና እየሞቱ ላሉት የባህር ፍጡራን ክብር፤ ከያዝኩት ጠርሙስ ዳግም አረቄ፤ የቀድሞዉ ባህር ጠርዝ ላይ ሰባት ጊዜ አፈሰስኩላቸዉ፡፡ ድንገት ያፈሰስኩት አረቄ ጅረት ሆኖ፤ በወላጆቻቸዉ የባህር በሬን እንዲያንኳኩና እንዲሮጡ ተልከዉ የነበሩ፤ የባህሩ ዉሃ ሲነጥፍ ማጥ ዉስጥ ተዘፍቀዉ የቀሩ፤ ሰባት ህጻናትን እያንከባለለ ወደ ወላጆቻቸዉ መለሳቸዉ፡፡ ህጻናቱን አላየኋቸዉም ነበር፡፡ ወይም ደግሞ ማጥ ዉስጥ ተዘፍቀዉ ሲንፈራገጡ፤ ሊሞቱ የሚያጣጥሩ ትልልቅ አሳዎች መስለዉኝም ይሆናል፡፡
ቀትር ላይ ጸሐይቱ፤ ምጣድ ዉስጥ ድርቆሽ እንዲሆን እንደተተወ የመጨረሻ ስፍ፤ እረግረጉን ቋ አድርጋ አደረቀችዉ፡፡ ትንፋሻቸዉን ነጥቄ የገደልኳቸዉ የባህር ፍጡራን፤ ከአናት ላይ በሚወጣ ጸሐይ ታግዘዉ መሽተት ጀመሩ። ‹እኛን ገድላችሁ እናንተ በጤና አትኖሩም!› በሚል ነዉ መሰል ክርፋታቸዉ የከፋ ሆነ። ከበላያቸዉ እንደ ጦር ካምፕ መብራት የሚሽከረከሩት የሙት መንፈሶቻቸዉ እንኳን አፍንጫቸዉን ይዘዉ ይዞሯቸዉ ጀመር፡፡
አሳ አጥማጅና የባህር ላይ ዘራፊ የነበሩት፤ ባህሩን ሲጋሩን የነበሩት አገራት ሰዎች፤ የእርሻ መሣሪያ ታጥቀዉ፤ ከብቶቻቸዉን እየነዱ፤ የባህሩን ትራፊ ለማረስ ከተፍ አሉ፡፡ ግና የባህሩን ቅሪት የሞላዉ የበድን ሽታ አላስጠጋ አላቸዉ፡፡ ከብቶቻቸዉ ሽታዉን መቋቋም ስላልቻሉ፤ ደጋግመዉ እያነጠሱና ‹ይማርህ/ይማርሽ› እየተባባሉ፤ ገበሬ ሊሆኑ የመጡትን አሳዳሪዎቻቸውን ትተዉ ተመለሱ፡፡ ምድሩን የወረረዉ የበድን ሽታ ከባሻገር አገር ሰዎች ክፋት ጠረን ጋር ተደባልቆ፤ እኔም ለመቆም ስለከበደኝ፤ ወደ አገሬ ተመልሼ በሬን ቆልፌ ተቀመጥኩ፡፡
የበሩ መቆለፍ ሽታዉን ሙሉ፣ በሙሉ በሚባል መልኩ አጠፋዉ፡፡ ግና ለክፉም ለደጉም ብዬ ሲኦልን የሚያክለዉ ጊርጊራዬ ላይ፤ እሳተ ጎመራ ከማያጣዉ ተራራ፤ እሳት ጭሬ አደረግሁበትና ከእጣን ዛፎቼ ሰባቱን ቆርጬ ጨመርኩበት፡፡ ከዛም ጊርጊራዉን የባህሩ ልጅ በሆነዉ ክብ ወንዝ መሀል፤ ደሴቱ ላይ አስቀመጥኩት፡፡ ወንዙንም ጊርጊራ ወንዝ ስል ሰየምኩት፡፡ ከጊርጊራ በሚወጣዉ የእጣን ጭስ፤ ቀዩ አገሬ መልካም፣ መልካም ሸተተ፡፡
ቀዩ አገሬ የምንጅላቴ ነዉ፡፡ ምንጅላቴ የአገሩ ባለቤት እንደሆነ ከሚያምሩ፣ ከማያምሩ፣ ከማያስከፉ፣ ከሚያስከፉ፣ ከማይሸቱ፣ ከሚሸቱ የወገን አፎች ስሰማ ነዉ የኖርኩት፡፡ ግን ግራ ይገባኝ ነበር፡፡ ግራ ሲገባኝ ደግሞ እጠይቃለሁ፡፡
‹‹ጠፍጥፎ ካልሠራዉ በቀር እሱ እንዴት ያገሩ ባለቤት ሆነ?››
ከጠየቅኋቸዉ ብዙዎቹ የተረኩበትን አፎቻቸዉን አንሻፈዉ አሽሟጠዉኝ ሄደዋል፡፡ ቃል አውጥቶ መልስ የሰጠኝ ግን የለም፡፡
አንድ ቀን ዉቅያኖስ ተሻግሮ ካለዉ ምድር፤ ኮሎምብያ ከሚባለዉ አውራጃ ዉስጥ የምትኖረው፤ ሽርኬ የነበረች ስድስተኛ ቤተ ዘመዴ (አንድ ስድስት ጊዜ ስድስት መቶ ዶላር ልካልኛለች)፤ ለእናቷ ደውላ እያለቀሰች፤ የድዷን ምራቅ ላቦራቶሪ ልካ፤ ትክክለኛ የዘር መነሻን የሚመረምሩት ባለሙያዎች፤ እንደምታስበው የቀዩ አገር ዝርያ፣ ያን ያህል በህዋሶቿ ዉስጥ እንደሌለባት፤ ይልቁንም ምላሷን እያወጣች የምታሽሟጥጥባት፤ በስተምሥራቅ የምትጎራበትን ቀይ-ሀምራዊዋ አገር፤ የተሠራችበትን ግማሽ ያህሉን አፈር እንደሰጠቻት፤ በተጨማሪም የአረብም፣ የአይሁዱም ዝርያ እንዳለባት እንደነገሯት ጠቆመቻቸው፡፡
‹‹በፍጹም እንደዛ ሊሆን አይችልም፡፡ እኛ ጥርት ያልን ቀዮች ነን፡፡›› አሏት እናት፡፡
 ዘመዴ የባሰ ተናደደች፡፡ በቁጣ፤
‹‹እስካሁን እናንተ እንኳን ያልሆናችሁትን እንዲህ ነሽ እያላችሁኝ፣ በተረት አኖራችሁኝ፤ ይኸዉ የማንነት ቀዉስ ዉስጥ እገኛለሁ›› ተንሰቀሰቀ፡፡
እናት በባዕድ አገር ያለችዉ ልጃቸዉ ስታለቅስ መቋቋም አቃታቸዉ፡፡ ትንሽ ሲያስቡ ከቆዩ በኋላ፤
‹‹በቃ በአገርሽ እንደሚገኙት መፍቅሬ ነጮች፤ ትልቅ መስታወት ፊት ቆመሽ ‹እኔ የቀይ-ሀምራዊዉ አገር ዝርያ ደሜ ዉስጥ አይታየኝም። እኔ የቀዩ አገር ቀይ ሴት ልጅ ነኝ፡፡ ቀይ ብቻ ነኝ!› ብለሽ ሰባት ጊዜ እየጮህሽ ለራስሽ ንገሪዉ›› አሏት፡፡
የእናትና ልጅን ንግግርን ስሰማ ምንጅላቴ የዚህ አገር ባለቤት እንዴት እንደሆነ ግራ ገባኝ። የቤታችንን አንጋፋና የአገሩ ሽማግሌ የሆኑት አዛዉንት ጋር ሄጄ (በጭቃ ሹምነት የመረጡኝ እሳቸዉ ናቸዉ)፤ በስድስተኛ ቤት ዘመዴና በእናቷ መካከል የተደረገዉን የስልክ ንግግር፤ ከነገርኳቸው በኋላ፤
‹‹ግራ የሚገባኝ አንድ ነገር አለ፡፡ እዚህ ጋር አግዚሀሩ ሰማይና ምድርን ፈጠረ ትላላችሁ፡፡ ሰዉንም በአምሳሉ ፈጠረም ትላላችሁ፡፡››
‹‹አዎ!›› አሉ ሽማግሌዉ፡፡
‹‹መልሳችሁ ደግሞ ጠፍጥፋችሁ እንደሠራችሁት ሁሉ ቀዩ አገር የኛ ብቻ ነዉ ትላላችሁ፡፡ እኛን አይመስልም የምትሉትን ደግሞ እንደ ባዳ ቆጥራችሁ፤ በእናንተ መልካም ፍቃድ ብቻ የሚኖር መጻተኛ ታደርጉታላችሁ፡፡ ታድያ እነዚህ ሁለት ነገሮች አይጋጩም?›› ስል ጠየቅኋቸዉ፡፡
ሽማግሌዉ በኩርኩም ሊያጋጩኝ ቃጥተዉ ተዉት፡፡ ከዛም ደረታቸዉ ላይ የደረሰዉ ጎፈሬ ጢማቸዉ፤ ሄዶ ጉሮሯቸው ዉስጥ እንደተሰነቀረ ሁሉ፣ ድምጻቸዉን አጎርንነው፤
‹‹እኛ ጠፍጥፈን ሠራነዉ አላልንም፡፡ ግና እግዜሩ በቃል ኪዳን የሰጠን፤ እንድንወርሰዉ የፈቀደልን አገር ነዉ፡፡ ስለዚህ እግዜሩ ለእኛ ብቻ ነዉ የሰጠን፡፡ እናንተ ወጣቶች ይሄን አምኖ ለመቀበል ለምንድን ነዉ የሚከብዳችሁ ግን?››
‹‹እግዜሩ የይዞታ ማረጋገጫ ሰጥቷችኋል?››
‹‹እንዴት? እንዴት?››
‹‹የይዞታ ማረጋገጫ ካላችሁ ኮፒዉን እንድትሰጡኝ እፈልጋለሁ፡፡››
‹‹ማለት?››
‹‹እግዜሩ ምንጅላታችንን ቀዩ አገር ላይ ኑርበት ቢለው እንኳን ከማን ጋር እንደኖረ፤ ከማን ተዳርቶ እንደወለዳችሁ አታውቁም፡፡ ጸሐፍቶቻችሁ ትዉልዳችሁን እየዘረዘሩ ቢጽፉ አባቶቻችሁን እንጂ እናቶቻችሁን አልጠቀሱም። እናቶቻችሁ ከማን ይዉለዷችሁ ከማን፤ እነሱ ብቻ ነዉ የሚያዉቁት፡፡ እኔ ቀዩ አገር የኛ መሆኑን ጠልቼ አይደለም፡፡ ሌሎች ወጣቶችም የሚጠሉት አይመስለኝም፡፡ ግና አገሬ የኔ ብቻ ስለመሆኗ በቂ ማረጋገጫ እፈልጋለሁ። ‹ይህቺን አገር ያንተ ብቻ ማን አደረጋት?› የሚሉትን መጤዎች አፍ፤ እንደ ሬሣ ሣጥን አፍ በአሥራ ሁለት ቁጥር ሚስማር ጠርቅሜ፤ ቃላቶቻቸዉ እንደ ሬሳዉ አፋቸው ዉስጥ በስብሰዉ እንዲሸቱ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ቀዩ አገር የእኛም ናት ብለው ዓይኖቻቸዉን፣ ዓይኖቼ ላይ የሚያፈጡትን፤ በማስረጃ ጨለማቸውን አብዝቼ የዓይኖቼን ብሌኖች ልበለጥጥባቸዉ እፈልጋለሁ፡፡›› በተመስጦ ዓይኖቼን ጨፍኜ ሳወራ ቆይቼ፤ ዓይኔን ብገልጥ ሽማግሌው የሉም።
ምሽቱን ቀዩ አደባባይ ላይ ከወይራ ጉማጅ ጋር ታሥሬ ‹‹ቀዩ አገር የቀዮቹ ብቻ እንድትሆን የሰጠህ ፈጣሪ የተመሰገንክ ሁን!›› እያልኩ መቶ ጅራፍ ተገረፍኩ፡፡ ኮርባጁ ላይ የተጎነጎኑት ቀይ የዘረኝነት ‹አኮፓንቸሮች›፤ ገላዬን እየበጡ፤ ከደምስሬ ጋር እየተገናኙ፣ ቀይነትን አዋረሱኝ፡፡ ከቀይ ዉጪ የማይጥመኝ፤ ኩሩ ቀይ ሆንኩኝ፡፡ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የቀዩ አገር ጭቃ ሹም ሆኜ፤ ቀይ ጭቃ ተቀባሁኝ፡፡
ባህሩን ጠጥቼ፤ በሬን ዘግቼ፤ ከቀድሞ ባህር ማዶ ከሚገኙ አገራት ጋር ተቆራርጬ መኖር ጀመርኩ። የባህር ፍጡራኑ በድን ሽታ አልጠፋም መሰል፤ ወይም አጥንቶቻቸዉ እሾህ ሆኖ እግረኛዉን እየወጋ አላስኬድ ብሎ ነዉ መሰል፤ ከአገራቱ እኔን ለመረበሽ ብቅ የሚል ማቲ ጠፋ፡፡ በደረቅ ጎረቤቶች የተከበበ፤ የተቆለፈ አገር ባለቤት ሆንኩኝ፡፡ ባህሩ ሲናፍቀኝ ክበብ በሠራዉ ሀምራዊ ወንዜ ዉስጥ አየዋለሁ፡፡ እንደ ልጅነቴ በጀልባ ወይ በዋና ባህሩን አቋርጬ፤ ከባህር ባሻገር ያሉ አገራትን የባህር በር አንኳክቶ መሮጥ ሲያምረኝም፤ ወንዜ ዉስጥ ተንቦራጭቄ ሳበቃ፣ የራሴን በር አንኳኩቼ፤ እየሣቅሁኝ እሮጣለሁ። ማነው አሳን ብቻ ነዉ ውሃ በተሞላ የመስታወት ሣጥን ውስጥ ማኖር የሚቻለዉ ያለዉ? ባህርንም፣ የባህሩ ትዝታንም ክበብ በሠራ ሀምራዊ ወንዙ ዉስጥ ማኖር ይቻላል፡፡
ብዙም ሳይቆይ ግን፤ ከአገሬ መሬት ጋር ክንድ ለክንድ የተጠላለፉት ጎረቤት አገሮች ደግሞ አስጠሉኝ፡፡ እንደጠላኋቸዉ እንዲገባቸው መጀመርያ ላይ ቡና ሲጠሩኝ የለም ማስባል ጀመርኩ፡፡ እንደ ቀድሞው ከእነሱ ዕቃ መዋስ አቆምኩ፡፡ እነሱ ሊዋሱ ሲመጡ ደግሞ ሰበብ ፈጥሬ እመልሳቸዉ ጀመርኩ፡፡
‹‹ማረሻ ፈልገን ነበር›› ሲሉኝ
‹‹ይቅርታ ቀጥቅጠን ጎራዴ ሠራንበት›› እላቸዉ ጀመር፡፡
አንድ ቀን ሲጠሏቸዉ የማይገባቸዉ በስተምሥራቅ የሚኖሩትን የቀይ-ሀምራዊዉ አገር መሬትን፤ በቀዩ የጠፍር ጫማዬ፤ አንዴ በኃይል እረግጬ፤ አገሬ ተነቅላ እንድትነሳና ከጎረቤቶቿ በላይ እንድትንሳፈፍ አደረግኋት። መሀል አገር ያሉ ህዝቦቼ፤ በተለይም ቀይ ዘመዶቼ ደስ አላቸዉ። ‹ታላቁ ጭቃ ሹም› የሚል ቅጽል ስሜን ቀደመ። ዉጪ አገር ያለችዉ ስድስተኛ ዘመዴ ብቻ ቀይ-ሀምራዊዉ አገርን እንደዛ መርገጤን አልወደደችዉም። ቀይ-ሀምራዊዎች የቀይና የሀምራዊ ሦስተኛ ትዉልድ ዲቃላዎች ናቸዉ፡፡ በየትኛዉ ዘመን ቀይ ዘመዶቼ ከሀምራዊያን ተዳቅለዉ እሷን እንደፈጠሯት እንጃ፡፡ እንደ ዘመዴ ሁሉ በየጠረፉ የሚገኙትና ከጎረቤቶቻቸዉ ጋር የተዋለዱትና የተደባለቁት የቀዩ አገር ዜጎች፤ ከጎረቤቶቻችን መነጠላችንን አልወደዱትም፡፡ ግና መቶዉን ጅራፍ ፍራቻ ዘንባባ ዘንጥፈዉ፤ ከበሮ እየደለቁ ‹ስለተነጠልን ደስ ብሎናል› እያሉ በእልልታና በጭፈራ ደስታቸዉን ገለጹ፡፡
ያዳቆነኝ ሴጣን ብዙም አልራቀም፡፡ በቀዩ አገር ላይ ከፍ ብለው እየኖሩ፤ ሁሉን ቁልቁል ማየቱ አልበቃህ እያለኝ መጣ፡፡ ጎረቤት አገሮች፤ ከፍ ማለታችን ለጥቃት እንደሚያጋልጣቸዉ አስበው፤ አገራቸዉን ሙሉ ለሙሉ ጣራ ሊያለብሱ፤ ቆርቆሮ ሲቀጠቅጡ ይውላሉ። ላባቸዉ በዦሮ ግንዳቸዉ እየተንቆረቆረ አገራቸዉን ጅረት በጅረት አድርጎታል። ከቀድሞ ባህር ባሻገር ያሉት አገራት ህጻናቶች፤ ጎልምሰዉ ሽቅብ ወደ ቀዩ አገር እያዩ፤
‹‹እኔ ህጻን እያለሁ የባህር በራችሁን አንኳኩቼ አልሮጥኩም!›› እያሉ በፍራቻ እየማሉ ይገዘታሉ፡፡
የአገሬ ክፍለ አገራት አስጠሉኝ፡፡ በተለይ ቀይነታቸዉን ንቀዉ፣ ከሌሎች ጎረቤቶች ሲዋለዱና ሲዳቀሉ የነበሩት አብዝተው አስጠሉኝ፡፡ በቀዩ ጠፍር ጫማዬ እረግጬ ሸርፌ ጣልኳቸዉ፡፡ ህዝቡ ‹እነዚህ ዲቃላዎች የእጃቸዉን አገኙ› ሲል እኔን እያደነቀ፣ እነሱን ሲሰድብ ከረመ፡፡ መልሶ ግን ከጎሳዬ ዉጪ ያለዉ አስጠላኝ፡፡ እነሱንም አስወገድኩ፡፡ ጎሳዬ ዘመድ አዝማዶቼ ተደሰቱ፡፡
ለሰባት ቀን ዓይኖቼን ከድኜ በጥሞና ሳስላስል፤ የኔን ቀይነት የሚተካከል ቀይ ፈልጌ አጣሁ፡፡ የወለድኳቸዉ ልጆች ቀይነት አንኳን፤ በሚስቴ የተበረዘና የሳሳ መስሎ ተሰማኝ። ሁሉንም አስወገድኩና ብቻዬን ቀረሁ፡፡ እልል የሚልና የሚያሞግሰኝ አጣሁ፡፡ ሙገሳ አለማግኘቱ ብቸኝነቴን እንድጠላውና እንድጸጸት እንዳያደርገኝ ፈራሁ፡፡ በሚያስገመግም ቀይ ድምጽ ለራሴ እንዲህ ስል ለፈፍኩ፤
‹‹ሁላችንም ከማይታወቀው ተነስተን ወደማይታወቀው የምንሄድ ብቸኛ መንገደኞች ነን። የቀረቡን የመሰሉንን የመንገዳችን አጫፋሪዎችን በመንገዳቸዉ የምናጫፍር ብቸኞች ነን፡፡ ጉዟችን በጭለማና በክረምት ሆኖብን፣ ከመንገዳችን አሻግረን ማየት የቻልናቸውንና አሻግረዉ ሊያዩን የቻሉትን፤ ድምጻቸውን መስማት የቻልነውንና ድምጻችንን መስማት የቻሉትን ዘመድ የምናደርግ ባዕዶች ነን፡፡
የመንገዱ ስፍር ልክ እንደ መንገደኛው አይነኬና አይጠጌ ነዉ፡፡ ካንድ ሰዉ በላይ ሊሄድባቸዉ የማይችሉ እልፍ አዕላፍ መንገዶች ሁለት እግሮችን ብቻ ይጠብቃሉ፡፡ አንድ መንገድ ለሁለት እግሮች ብቻ! የወለዱን፤ በደም የተዛመዱንም መንገዳቸው ከመንገዳችን ቅርበት እንጂ አንድነት የለውም። በፍቅር ለጥቆም በጋብቻ የሚዛመዱንም ቢሆን መንገዳችንን የማይጋሩን ባለ መንገዶች ናቸዉ። እርቃናችንን ወደ መንገዳችን ተወልደን፤ ከመንገዳችን አንጻር የኛ ልንለው የምንችለው ምንም ነገርና ማንም ሰው ሳይኖረን፣ እርቃናችንን ወደማይታወቀው የምንሄድ መጻተኞች ነን፡፡ አንተም በቀዩ መንገድ ላይ ቀይ ሆነህ የተፈጠርክ፤ የምንም ቅልቅል ዉጤት ያልሆንክ ነህ።››
ብቸኝነቴን አጽንቼ፤ የቤቴን ስድስት መሸንቆርያዎች፤ ሸንቁሬ፤ ስድስተኛ ቤት ዘመዴ፤ ከስድስት መቶ ዶላር ጋር አብራ የላከችልኝ፤ ከዘረመል ምርመራው ዉጤቷ በኋላ፤ በእናቷ ምክር ቀይነቷን ያወጀችበትና ያጸናችበትን የቁም መስታወት ፊት፤ ኩርሲ ወንበር ላይ ተቀመጥኩ፡፡ እራሴን አየሁት፡፡ ነገር ግን አራሴን ፈራሁት፡፡
ለካ ብቸኝነት የሚባል የለም፡፡ ብቻችንን ነን ብንልም ለካ ከራሳችን ጋር ነን፡፡ እራሳችን ለካ ሁሌም አብሮን አለ፡፡ ሁልጊዜ ከእራስ ጋር እንደሆኑ ማወቁ፤ ብቻ ከመሆን በላይ እንዲህ ያስፈራል እንዴ? ስተኛም፣ ስነሳም፣ ሳሎን ውስጥም፣ መታጠቢያ ቤት ውስጥም፣ በጎዳናውም በሁሉም ቦታ ለካ ከእራሴ ጋር ነኝ። በመስታወት ዉስጥ እራሴ ላይ አፈጠጥኩ። እራሴ ሌላ አካል መስሎ ታየኝ፡፡ በሽታዬ ተነሳ። ቆይ ከእኔና ከራሴ ማን ነዉ ንጹህ የቀዩ አገር ዜጋ? እራሴን ከራሴ ላይ በቀዩ የጠፈር ጫማዬ እንዴት ነዉ ሸርፌ ጥዬ ብቻዬን መሆን የምችለዉ? ይሄን እያሰብኩ ሳለ፣ ጀምበር አዘቀዘቀችና ቀስ እያለች ከእግሬ በታች ወረደች። ድንገት እንደኔ እራሳቸዉን ነጥለዉ፣ አየር ላይ ከአገራቸው ጋር የሚንሳፈፉ፤ የቢጫና የሰማያዊ አገር ጭቃ ሹሞች፤ እራሳቸዉን ለማስተኛት፤ እራሳቸዉን ‹እሹሩሩ› ማለት ጀመሩ፡፡
“እሹሩ…ሩ…ሩ…ሩ
እሹሩ…ሩ…ሩ…ሩ
ስተኛም አብሬህ፤ ስነሳም አብሬህ
ስቀመጥ አብሬህ፤ ስቆምም አብሬህ
ስሄድም አብሬህ፤ ሳልሄድም አብሬህ
አብሬህ አብሬህ፤ አብሬህ አብሬህ
አብሮ(ነት) ሆኖ ምሴ
ሳስብህ ፈራሁ
ተዉ ተወኝ እራሴ
እሹሩ…ሩ…ሩ…ሩ
እሹሩ…ሩ…ሩ…ሩ
የእራሴ ዋግምት፤ ቶሎ ናለት
በፈሰሰዉ ደም - ʻንዲተካበት
ጫጫታ፣ ሁካታን - ይዘህለት
እራሱን ከራሱ - ይደበቅበት››
እሹሩ…ሩ…ሩ…ሩ
ተዉ ተወኝ እራሴ፡፡”

Read 2304 times